የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹ኅብር ሕይወቴ›› መጽሐፍ ላይ ያነበብኩት አንድ ገጠመኛቸው ትዝ አለኝ:: ደርግ ንጉሣዊ ሥርዓቱን አስወግዶ ይሁን ኢህአዴግ ደርግን አስወግዶ በየትኛው እንደሆነ ዘነጋሁት፤ ብቻ ግን ፕሮፌሰር ባህሩና ባልደረቦቻቸው ባለፈው ሥርዓት ዘመን የነበሩ ሰነዶችን እየሰበሰቡ ነው:: የመንግሥት ተቋማት የወረቀት ሰነዶችን በማስወገድ ስም አውጥተው እየጣሉ ነው:: ከሚጣሉ ወረቀቶች ውስጥ ግለሰቦች ይጠቅመናል ያሉትን እየመረጡ ይወስዳሉ::
ይህን ያወቀ አንድ የእነ ፕሮፌሰር ባህሩ ባልደረባ አንድ ሃሳብ መጣለት:: ይሄውም ያልተገኙ ወረቀቶችን በየግለሰቦች ቤት እየዞሩ መፈለግና መግዛት:: የተጣሉ ወረቀቶችን እያነሱ መልቀም የጀመሩት እነ ፕሮፌሰር ባህሩ፤ ከግለሰቦች ቤትም ‹‹እባካችሁ ከመንገድ ላይ የለቀማችሁትን ወረቀት ሽጡልን›› ማለት ጀመሩ:: ይህን ሲያደርጉ ማንም የገንዘብ ድጋፍ አያደርግላቸውም፤ ከኪሳቸው እያወጡ ነበር የሚገዙት:: ለምን? የወረቀቶችን ዋጋ (ጥቅም) ያውቃሉ!
ይህን ያስታወሰኝ የበጀት መዝጊያ የሆነው የሰኔ ወር በመጣ ቁጥር፣ ተቋማት ቦታ በቀየሩ ቁጥር፣ ተቋማት እድሳት ባደረጉ ቁጥር፣ እያወጡ የሚጥሉትን የወረቀት ክምር ሳስተውል ነው:: በተለይም በዚህ ዓመት በኮሪደር ልማቱ ምክንያት በብዙ አካባቢዎች ከተቋማት አቅራቢያ የሚጣሉ ወረቀቶችና ሌሎች ዕቃዎች ብዙ ነበሩ:: ችግሩ ግን በግንባታ እና በእድሳት ምክንያት የመጣ አይደለም፤ በየጊዜው በተቋማት ጊቢ ውስጥ የወረቀት ክምር ማየት የተለመደ ነው::
ይህን የሚያደርጉ አካላት ‹‹ለምን አደረጋችሁ?›› ቢባሉ የሚኖሯቸው መልሶች ግልጽ ናቸው:: የመጀመሪያው ‹‹ቆሻሻ እያስወግድን ነው›› የሚል ነው:: ቆሻሻ የሚሉበት ምክንያት ደግሞ ወረቀቶቹ ያገለገሉ ስለሆኑ፣ ለወደፊት ለምንም ነገር ስለማያስፈልጉ፣ በአጭሩ አገልግሎታቸው ያለፈ ስለሆነ አይጠቅሙም ብለን ነው ይላሉ::
ለእነዚህ ሰዎች የወረቀቶች አገልግሎት ለዕለቱና ለወቅቱ ብቻ ነው:: ለምሳሌ፤ የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የተመለከቱ ሥራዎችን የያዙ ሰነዶች ከሰኔ 30 በኋላ የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ስለሆነ ከዚህ በኋላ አያስፈልጉም ብለው ያምናሉ ማለት ነው:: ወይም ከአሥር ዓመት በላይ የቆዩ ወረቀቶች ‹‹ከዚህ በኋላ ምን ይሠራሉ?›› ብለው ያስባሉ ማለት ነው:: ለሚያስወግዱት አካላት ወይም እንዲወገድ ትዕዛዝ ለሠጡት አመራሮች የወረቀቶች አገልግሎት ማለት ከእነርሱ ኃላፊነት ጋር የተያያዘ ብቻ ይመስላቸዋል፤ ምናልባትም ኃላፊነቱን ሲለቁት አይመለከተኝምና ይወገድ ይሉ ይሆናል:: ወረቀቶቹ የያዙት መረጃ የተጠያቂነት ጊዜ ገደቡ ካለፈ ከዚህ በኋላ ስለማልጠየቅበት ቢወገድም ችግር የለውም ብለው ያስቡ ይሆናል::
ነገሩ ግን ወዲህ ነው:: እያንዳንዱ የተጻፈ የተቋማት ሰነድ የሀገሪቱ ታሪክ ነው:: ቀላል ምሳሌ እንውሰድ:: ከ50 ዓመታት በፊት የተጻፉ ሰነዶች ስናገኝ በመገረም ስሜት ውስጥ ነው የምናነባቸው:: እነዚህ ሰነዶች ያን ያህል ከባድ እና የሀገር ዳር ድንበር ጉዳይ ሆነው አይደለም፤ ምናልባትም በመማሪያ ደብተር ሽፋን ላይ የሚሞላ ቅጽ ሊሆን ይችላል:: ዳሩ ግን የዚያን ዘመን ቅርጽ ያሳያሉ:: የዚያን ዘመን ሁኔታዎች ይገልጻሉ:: እንኳን የትልልቅ ተቋምት ሰነድ ይቅርና የአንድ አነስተኛ ምግብ ቤት የምግብ ዝርዝር (ሜኑ) ከዛሬ 30 እና 50 ዓመታት በኋላ ዋጋ አለው:: ጠረጴዛ ላይ የተነጠፈ የምግብ ዋጋ ዝርዝር ለዛሬው ያሉትን ምግቦች ከማየት ያለፈ ምንም ስሜት አይሰጠንም:: ለወደፊቱ ትውልድ ግን የሚነግረው ነገር አለው:: በተቋማት ውስጥ የፋይናንስ ክፍል ትንንሽ ደረሰኞች ዋጋ አላቸው፤ የስብሰባ ቃለ ጉባዔዎች ዋጋ አላቸው:: 25ኛ ዓመት፣ 50ኛ ዓመት… ምናምን እየተባለ በሚከበረው የተቋማት ማስተዋወቂያ ከበራሪ ወረቀቶች እስከ መጽሔት ይታተማል፤ እነዚህ ወረቀቶች ዋጋ አላቸው:: ያለምንም ምክንያት የሚታተም ወረቀት አይኖርም:: ስለዚህ እነዚህን ሰነዶች የሚያጠፏቸው ለምን ይሆን?
‹‹ለምን ታጠፏቸዋላችሁ?›› ብለን ብንጠይቅ ሁለተኛው መልስ የሚሆነው ወደ ዲጂታል ቀይረነዋል የሚል ሊሆን ይችላል:: እዚህ ላይ ሁለት ነገር መጠራጠር አለብን:: አንደኛው፤ የምር እነዚያ ሁሉ ወደ ውጭ የተጣሉ ወረቀቶች ወደ ዲጂታል ተቀይረዋል ወይ? የሚለው ነው:: አስፈላጊ አይደሉም ብለው የጣሏቸውን ወረቀቶች ወደ ዲጂታል ይቀይሯቸዋል ብሎ ማመን አስቸጋሪ ነው:: መጽሔቶችንና ሌሎች በራሪ ወረቀቶችን፣ ሰነዶችን የሚጥሏቸው አገልግሎታቸው አልፏል፣ ምንም የሚያስፈልጉበት ጉዳይ አይኖርም በሚል እንጂ ቦታ አጠበቡ በሚል ብቻ አይደለም:: የተጣሉትን ሁሉ ወደ ዲጂታል ቀይረውት ከሆነ ግን እሰየው ነበር!
ወደ ዲጂታል ቀይረውታል የሚለውን በየዋህነት አምነን ተቀበልን እንበልና ሁለተኛውን ችግር እንመልከት:: በሠለጠኑት ሀገራት መረጃዎች ወደ ዲጂታል ሲቀየሩ ወረቀት ላይ የነበሩትን በማጥፋት አይደለም፤ የወረቀቶቹ ራሳቸውን ችለው ሌላ ታሪክ ናቸው:: ለብቻቸው ይቀመጣሉ:: ‹‹ከወረቀት ነፃ አገልግሎት›› ሲባል ቢያንስ ከዚህ በኋላ የሚሠሩ ሥራዎችን በዲጂታል ማድረግ እንጂ የነበሩትን ማጥፋት ማለት አይደለም:: የቴክኖሎጂው ፈጣሪ በሆኑት ሀገራት እንኳን የወረቀት አገልግሎት አልቀረም:: በዋናነት ደግሞ ከዚህ በፊት የነበሩ የወረቀት ሰነዶችን በማጥፋት አይደለም::
የመጀመሪያው ችግር ሁሉም ወደ ዲጂታል የተቀየሩ ላይሆኑ ይችላሉ የሚለው ከሆነ፤ ሁለተኛው ችግር ደግሞ ዲጂታል ራሱ አስተማማኝ አይደለም:: የዲጂታሉ ዓለም ምን ምን ደካማ ጎኖች አሉት? የሚሉ መረጃዎችን ስንበረብር የምናገኘው የመጀመሪያው ችግር የሳይበር ጥቃት ነው:: ምንም እንኳን ጥቃቱ የሚደረገው ሀገራዊ ምሥጢር ለሆኑት መረጃዎች ቢሆንም እግረ መንገዱን ግን ብዙ መረጃዎችም ይጠፋሉ:: በሌላ በኩል የዲጂታሉ ዓለም ስንት ዘመን እንደሚኖር አይታወቅም:: ለአሠራር ቀልጣፋና ምቹ የሆነውን ያህል የሚያጋጥሙት ችግሮች ደግሞ በታዳጊ ሀገራት አቅም የማይጠገን ሊሆን ይችላል:: ለምሳሌ፤ ኢሜይል ለብዙ ዓመታት የቆዩ መረጃዎችን አጠፋለሁ ብሎ ነበር:: ልክ እንደዚህ ሁሉ ሌሎች የዲጂታል አማራጮችም ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል ማለት ነው::
ምንም እንኳን በዚህ ዘመን የወረቀት አገልግሎት እንጠቀም ማለት ቢያስቸግርም ቢያንስ ግን የተገለገልንባቸውን ማጥፋት አይገባም::
‹‹ለምን ያጠፏቸዋል?›› ብለን ብንጠይቅ አንድ አደገኛ ብልሹ አሠራር ሊኖር ይችላል:: ለምሳሌ፤ ብልሹ አሠራሮች እንዳይታዩባቸው የሚፈልጉ፣ ከሕዝብ በጀት ላይ አለግባብ ሥራ የሠሩ ሰነዱ እንዳይገኝ ሊያጠፉት ይችላሉ:: በተለይም አንዳንድ ሰነዶች የተጠያቂነት ጊዜ ገደብ ያላቸው ናቸው:: ያ ጊዜ ገደብ ካለፈ ቢያንስ ለጊዜው ተጠያቂ አልሆንም በሚል የታሪክ ተጠያቂ ላለመሆን ያጠፉት ይሆናል:: በግደለሽነት ከሚጣሉት ሰነዶች ይልቅ ተጠያቂነትን ለመሸሽ ታስቦበት የሚጠፉ ሰነዶች የበለጠ ጎጂ ናቸው::
ያም ሆነ ይህ ተቋማት በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ሊኖራቸው ይገባል:: በግደለሽነት ሰነዶችን የሚያጠፉ ሠራተኞችና አመራሮችም የዛሬ ሥራ የነገ ታሪክ ነውና አውጥቶ ከመጣል ይልቅ በአግባቡ ማስቀመጥ ይለመድ! የሀገር ታሪክ ሲባል የግድ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወይም የምርጫ ክርክር ሂደት ብቻ አይደለም:: የሥራ ሰነዶችም ለታሪክ የሚቀመጡ እንጂ በቆሻሻ ስም የሚወገዱ አይደሉም!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም