አንድ ሰው አንድ ነገር ካለው ያንን ነገር ማን ሊጠቀምበት እንደሚገባ የመወሰን መብት አለው። ለምሳሌ ያህል፣ ከሌሎች ልጆች ጋር ለመጫወት ቤታቸው ልትሄዱ ትችሉ ይሆናል። ወደ ቤታችሁ ስትመለሱ ግን ከእነሱ ቤት አንድ ነገር ወስዳችሁ ብትመጡ ተገቢ አይደለም። የልጆቹ አባት ወይም እናት ካልፈቀዱ በቀር ምንም ነገር መውሰድ የለባችሁም። እነሱን ሳትጠይቁ ምንም ነገር ወስዳችሁ ብትገኙ ግን ይህ ተግባር ሌብነት ነው። አንድን ነገር ለመስረቅ የምትፈተኑት ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? የእናንተ ያልሆነውን ነገር ስትመኙ ነው። ስትሰርቁ ሌላ ሰው ባያይችሁ እንኳ አምላክ ያያለ ብሎ መቆጠብ የግድ ነው። አምላክ ደግሞ ስርቆትን እንደሚጠላ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ለአምላክና ለሰው ፍቅር ካለችሁ ፈጽሞ ሌባ እንዳትሆን ይረዳችኋል። በማለት በልጅነታችን ወላጆቻችን የሀይማኖት አባቶች የመከሩንን ምክር እንዳነሳ ያደረገኝ በቀላል ሌብነት ተነስተው ዘራፊ ሰለሆኑ ወጣቶች ታሪክ ላካፈላቹ ስለወደድኩ ነው።
በቅድሚያ ይህን ታሪክ ለማስተማሪያ ይሁን ብለው ጋዜጣችን ላይ እንድጠቀም የፈቀዱልንን የአዲስ አበባ ፖሊስ መዘገብ ቤት አባላት ከልብ እያመሰገነኩ ታሪኩን ላካፍላቸሁ።
ልማደኞቹ ዘራፊዎች
ጓደኝነታቸው የሚያስቀና ሲወጡም ሲገቡም የማይለያዩ ልጆች ነበሩ። መሽቶ ተለያይቶ ነግቶ እስኪገናኙ የሚነፋፈቁት ጓደኛሞች እድሜያቸው ተቀራራቢ ከመሆኑም በላይ አንድ ሰፈር ተወልደው እዛው አድገው አብረው ነበር የአስኳላን ደጅ የረገጡት።
በልጅነታቸው ጨዋታ የሚያበዙ ዘዋሪ ልጆች ቢሆንም የሰው ምክር የሚቀበሉ ታዛዥ ልጆች ነበሩ። ከፍ ከፍ እያሉ ሲሄዱ ግን ሳንቲም አየሰረቁ ጣፋጦችን መብላት የተለያዩ ነገሮችን መግዛት ተለማመዱ። ወላጆቻቸውም ልብ ሳይሉ ቀርተው ይሆን ቸል ብለው ሳይቀጧቸው ይቀራሉ።
እድሜያቸው ከፍ እያለ ሲሄድ ግን በከረሜላና በብስኩት የጀመሩትን ግዢ ወደ አደንዛዥ ሱስ አሳደገው ያገኙትን በሙሉ የሚመነትፉ ዋልጌ ልጆች ሆኑ። በልጅነታቸው አብረው ትምህርት ቤት እንደገቡት ሁሉ አንድ ላይ ትምህርታቸውን አቋረጡ።
ከዛም በየሰፈሩ ማውደለደል፤ ታክሲ ተራ እየቆሙ የተሳፈሪን ኪስ ማውለቅ ዋና ተግባራቸው ሆነ። ቀድመው ቸል ያሏቸው ወላጆቾቻቸውም ዘግይተውም ቢሆን የልጆቻቸውን መበላሸት እንደተረዱ ቢመክሩም ቢያስመክሩመ ሰሚ ጆሮ አላገኙም ።
በቀላል መነሻ ብዙ የለመዱት ልጆች እድሜያቸው ከፍ እያለ ሲሄድ ከበድ ከበድ ያሉ እቃዎችን በመስረቅ ከልጅነት ጀምሮ በሚያወቁት የዘረፋ ተግባር አጠናክረው ቀጠሉበት። ወጣቶቹም ለዚህ እኩይ ተግባራቸው ይመቻቸው ዘንድ ለብቻቸው ተከራይተው ዘርፎ አዳሪ ሆኑ።
ባለራይዱ
ለፍቶ አዳሪ ወጣት ነው ባለራይዱ። ከትንሽ ነገር ተነሰቶ ትልቅ የመሆን ህልም የሰነቀ ወጣት። ገና ከልጅነቱ ጀመሮ ያገኘውን ስራ በመሰራት ትምህርቱን ይከታተል ነበር። ባለው ትርፍ ሰአት በሙሉ ከመላላከ አንሰቶ እስከ ወያላነት፤ ከወያለነት በተጨማሪ ሊሰትሮውንም ጀብሎውንም እየሞከረ ያገኘውን ገንዘብ እቁብ ይጥልበት ነበር። በጣላት እቁብ አጠራቅሞ ትንሽዬ ሻይ ቤት ከፈቶ እየሰራ በትምህርቱ የገፋ ነበር። በትምህርቱም ውጤታማ ስለነበር ዩኒቨርስቲ ገብቶ በሆቴል ማኔጅመንት የመጀመሪያ ድግሪውን ይዟል።
ትምህርቱን አጠናቆ በአንድ ሆቴል አስተደዳሪ የመሆን እድል ሲያገኝ ከዚህ ቀደም ያጠራቀመውን ገንዘብና፤ የምግብ ቤቱን እቃ በመሸጥ የጎደለውን በመበደር ቪትዝ መኪና ገዛ። በሆቴሉ ውስጥ በፈረቃ ከመስራቱ የተነሳ ከእንቅልፍ የተረፈውን ጊዜ በሙሉ ራይድ በመስራት የተሻለ ህይወት ለመኖረ ይታትር ነበር።
ዘመኑን በሙሉ በስራና በትምህርት በማሳለፉ የተነሳ የፍቅር ጓደኛ እንኳን የኖረው ዘግይቶ ነበር። የወላጆቹ ለምን አታጋባም ጥያቄንና ውትወታን ለማስቀረት ብሎ ጓደኛ ቢይዝም ከልጅቷ ጋር በጣም በመግባባታቸው የተነሳ ደስ የሚል የፍቅር ጊዜ እያሳለፉ ነበር።
ከእሁድ በስተቀር ሁሉንም ቀንና ሌሊት በስራ የሚያሳልፈው ወጣት እዳውን ከፈሎ መኖሪያ ቤት እንደገዛ የወደዳትን ልጅ አግብቶ ተረጋገቶ ለመኖር አቅዶ በተለመደው ትጋት ስራውን ይሰራ ነበር። በአዲሱ ፍቅር ልቡ ቢጠፋም ህልሙ ከፍ ያለ ነበርና ጊዜውን አቻችሎ በመያዘ እሁድ እሁድ ከፍቅሩ ጋር እያሳለፈ በተቀረው ቀን በሙሉ ይሰራ ነበር።
ያልታሰበችው ምሽት
እለቱ ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 7ሰዓት 20 ደቂቃ ከሶስቱ ዘራፊዎች መካከል ሲሳይ በኋይሉ የተባለው ተከሳሽ ካልተያዙ ሁለት ግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ በዝናባማው የሰኔ ለሊት ነበር የተለመደ ስራቸውን ለመስራት ከቤት የወጡት።
ቦታው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጀሞ ኪሩ ሆቴል ተብሎ ከሚጠራው አከባቢ በእለቱ ባለራይዱ የተለመደ አገልግሎቱን ለመስጠት ቆሞ ተሳፋሪ ይጠባበቅ ነበር። ወጣቱ የራይድ አገልገሎት የሚሰጥበትን 1 ሚሊዮን 400 ሺ ብር የሚገመተውን ቪትዝ መኪና ይዞ ቆሞ እያለ ሌቦቹ ጓደኛሞች ወደ እርሱ በመምጣት ፒያሳ እንዲያደርሳቸው በመጠየቅ 600 ብር ይስማማሉ፡፡
በዚሁ መሰረትም ተከሳሽ ከመኪናው የኋላ ወንበር በሾፌሩ በኩል፣ አንደኛው ሌባ፣ ሁለተኛው ሌባ ደግሞ በተሳፋሪ በኩል ከኋላ ወንበር በመቀመጥ መጓዝ ጀመሩ። በመጓዝ ላይ እንዳሉ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 አለም ሰላም ድልድይ አካባቢ ሲደርሱ ጋቢና የተቀመጠው ሌባ ታማሚ በመምሰል ሊያስታውከኝ ነው መኪናውን አቁምልኝ ሲል ባለራይዱን ይጠይቀዋል። ባለራይዱም ዳገቱን ጨርሼ ላቁምልህ በማለት በፍጥነት ሲያሽከረክር አነደኛው ሌባ ባለራይዱን በእጁ አንገቱን አንቆ በመያዝ እና በሁለት በኩል ስለት ያለውን ጩቤ አንገቱ ላይ አድርጎበት በማስፈራራትና ሁለቱንም እጆቹን በስለት በመውጋት ጉዳት እንዲደርስበት ያደረጋል፡፡
ሌላኛው ሌባ ደግሞ ራሱን እንዳይከላከል ከኋላ ተበዳይን በመጎተት የመኪናውን የእጅ ፍሬን ስቦ ተሽከርካሪው እንዲቆም በማድረግ የግል ተበዳይን በጋራ በመተባበር ከተሽከርካሪው ውስጥ አውጥተው ጥለው መኪናውን ወሰዱ። መረጃው የደረሰው ፖሊስም ክትትል በማደረግ ሲሳይ በኋይሉ የተባለውን ሌባ ከነሰረቀው ተሽከርካሪው ይያዛል፡፡
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ጥቆማ እንደደረስው ክትትል በመጀመሩ የተነሳ የተሰረቀው ተሽከርካሪ ከዘራፊዎቹ እጅ ሳይወጣ ከአንደኛው ሌባ ጋር በቁጥጥር ስር ሊያውለው ቻሉ ፤ ግብረ አበሮቹን እንዲጠቁም የተጠየቀው ተጠርጣሪ አሉ የተባለ ቦታን በሙሉ ቢያመላክትም ለጊዜው ሊደረስባቸው ሳይችል ቀረ። በዚህም የተነሳ የተበዳይን ንብረት ይዞ እጅ ከፍንጅ የተያዘውን ሌባ ከሶ ሊያስፈርድበት ወሰነ።
በዚህም የተገኘውን መረጃ በሙሉ አጠናቅሩ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ አቀረበ።
በመሆኑም በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 671/1/ለ/ መሰረት ተከሳሽ በፈፀመው የከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
የዐቃቤ ሕግ ክስ ዝርዝር
ዐቃቤ ሕግም ሲሳይ በኃይሉ የተባለው ተከሳሽ ካልተያዙ ሁለት ግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ 20 ደቂቃ ሲሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጀሞ ኪሩ ሆቴል ተብሎ ከሚጠራው ቦታ የግል ተበዳይ የራይድ አገልግሎት የሚሰጥበትን 1 ሚሊዮን 400 ሺ ብር የሚገመት ዋጋ ያላትን ቪትዝ መኪና ይዞ ቆሞ እያለ ተከሳሽ ወደ እርሱ በመምጣት ፒያሳ እንዲያደርሳቸው በመጠየቅ 600 ብር ይስማማሉ፡፡
በዚሁ መሰረትም ተከሳሽ ከመኪናው የኋላ ወንበር በሾፌሩ በኩል፣ አንደኛው ያልተያዘው ግብረ-አበር ጋቢና፣ 2ኛና ያልተያዘው ግብረ-አበር ደግሞ በተሳፋሪ በኩል ከኋላ ወንበር በመቀመጥ በመጓዝ ላይ እንዳሉ ልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 08 አለም ሰላም ድልድይ አካባቢ ሲደርሱ ጋቢና የተቀመጠው ታማሚ በመምሰል ሊያስመልሰኝ ነው መኪናውን አቁምልኝ ሲል የግል ተበዳይን ሲጠይቅ ዳገቱን ጨርሼ ላቁምልህ በማለት በፍጥነት ሲያሽከረክር ተከሳሽ የግል ተበዳይን በእጁ አንገቱን አንቆ በመያዝ እና በሁለት በኩል ስለት ያለውን ጩቤ አንገቱ ላይ አድርጎበት በማስፈራራትና ሁለቱንም እጆቹን በስለት በመውጋት ጉዳት እንዲደርስበት ያደረጋል፡፡
2ኛው ያልተያዘው ግብረ-አበር ደግሞ የግል ተበዳይን እንዳይከላከል ከኋላ ተበዳይን በመጎተት የመኪናውን የእጅ ፍሬን ስቦ ተሽከርካሪው እንዲቆም በማድረግ የግል ተበዳይን በጋራ በመተባበር ከተሽከርካሪው ውስጥ አውጥተው ጥለው መኪናውን የወሰዱ ሲሆን ተከሳሽ በፖሊስ ክትትል ከነተሽከርካሪው ይያዛል፡፡
በመሆኑም በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 671/1/ለ/ መሰረት ተከሳሽ በፈፀመው የከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ውሳኔ
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰሙ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር የለኝም በማለት የቀረበበትን ክስ መከላከል አልቻለም ነበር። ተከሳሽ የቀረበበትን ወንጀል ማስተባበል ባለመቻሉ ምክንያት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠትና የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ13 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም