ምክክር- አማራጭ የሌለው መፍትሄ

አለመግባባትና ግጭቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ምክክር /ውይይት/ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው። ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና ጥናቶችም ይህንኑ ነው የሚጠቁሙት:: ይሁን እንጂ በሳይንሳዊ መንገድ የሚተገበረው የምክክር መድረክ የየአገራቱ ባህል እና የማህበረሰብ ስነ ልቦና ውቅር ያገናዘበ ሊሆን አይችልም። በዚህ ምክንያት ተግባር ላይ ሲውል ነባራዊው የማህበረሰብ ስሪትን ካላገናዘበ በስተቀር ውጤታማ የማይሆንበት እድል ሰፊ ነው። ለዚህ ነው አንድ ወጥ የሆነ ሳይንሳዊ ቀመር ያለው የምክክር አጀንዳ ማዘጋጀት እንደማይቻል የዘርፉ ምሁራን የሚናገሩት::

በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን እንደሚገልፁት ‹‹ሀገራዊ ምክክር›› እንደ አንድ የማህበረሰብ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሶች መፍቻ ዘዴ በማህበረሰብ ሳይንስ ጠቢባን የተጠና አንድ ወጥ ትርጉም የተሰጠው ባለመሆኑ ለሁሉም የሚስማማ ሞዴል አይደለም:: ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግልፅ የትግበራ፤ እቅድና የአሰራር ደንቦችን ከተከተለ እንዲሁም ሀገራዊ ጉዳዮች በጥልቀት ከተመረመሩና በዛው መሰረት ላይ ከቆሙ የስኬት እድሉ ከፍ ያለ እንደሚሆን ይገመታል::

ምክክር ዋልታ ረገጥ የሆኑ የልዩነትና የግጭት ምክንያቶችን ለማርገብና ለማቀራረብ አቅም ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል:: እንዲህ አይነት ምክክሮችን በርካታ ሀገራት ሞክረውታል:: ተሳክቶላቸው ሀገራቸውን ወደ ሌላ ምዕራፍ ያሻገሩ እንዳሉ ሁሉ ለስኬት ያልበቁ ምክክሮችን ያካሄዱ ሀገራትም አሉ::

ሀገራት የውስጥ ችግሮች ሲገጥሟቸው ሕዝብን መሰረት ያደረጉ መድረኮችንና ሌሎች የውይይት መርሀ ግብሮችን ሲዘረጉ እንመለከታለን:: ከቦስኒያ የእርስ በርስ ፍጅት በኋላ የተዘረጉ ሀገራዊ ምክክሮች አብዛኞቹ ለውጥ ማምጣታቸውን ተመልክተናል:: ኢሲያዊቷ ካምቦዲያ ሀገራዊ ምክክርን ተግብራ ውጤት ካመጡ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ነች::

በአፍሪካም በሀገራዊ ምክክር ያለፉ ችግሮቻቸውን በእርቅና በምክክር አሉ:: በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት አንዷ ቱኒዚያ ናት:: የአረብ አመፅ የሚባለው አብዮት ተስፋፍቶ በአገሪቱ አመፅ ተነስቶ ቀውስ ተፈጠረ:: የነበረውን ቀውስ ለመፍታት ቱኒዚያ የምክክር ኮሚሽን አቋቁማ ምክክር በማድረግ ስኬታማ ውጤት አግኝታበታለች::

የቱኒዚያ ምክክር ለስኬት የበቃበት ምክንያት የመፍትሄ ጠንሳሾች በሆኑት ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አማካኝነት መሆኑ ይነገራል:: የዚህ ውይይት አመቻቾች ከታችኛው ማህበረሰብ ሀሳብ አምጥተው በብዙ ከመከሩ በኋላ አደጋ ውስጥ የነበረችን ሀገር ከነበረችበት ቀውስ እንድትወጣና እንድትረጋጋ አድርገዋል:: የምክክሩ አመቻቾች ከየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ነፃ የሆኑ፣ ከማንኛውም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ አትራፊነት ጉዳይ የሌላቸው፣ሀገሪቱ የገጠማትን ችግር ብቻ መፍታት ዓላማ ይዘው የተነሱ ሰዎች ስለነበሩ ተሳክቶላቸዋል::

ደቡብ አፍሪካም ከአፓርታይድ ስርዓት መጠናቀቅ በኋላ ‹‹ያለፈውን እንርሳና የወደፊቱን ብቻ እናስብ›› በሚለው መርሀቸው መሰረት ደም አፋሳሽ የነበረውን የታሪክ ክፍላቸውን በዕርቅ ቆልፈውበታል። የእርቅና እውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ‹‹Truth and Reconciliation Commission›› አቋቁመው ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ፈትተዋል::

እኤአ በ1994 የተከሰተው የሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ የተረጋጋውና ሰላም የሰፈነበት ሀገር መገንባት የተቻለው ተመሳሳይ ምክክር ከተደረገ በኋላ ነው:: ከሁሉም የከፋ የዘር ፍጅትን ያስተናገደችው ሩዋንዳ ሀገራዊ ምክክርን የብሄራዊ እርቅ ማሳለጫዋ አድርጋ በመጠቀሟ ከታላቁ ቁስል በፍጥነት በማገገም ለሌሎች አርአያ መሆን ችላለች::

ከላይ በምሳሌነት የጠቀስናቸው ሀገራት አሻጋሪ የሆነና ከነበሩበት ችግር ሊያወጣቸው የሚችል ምክክር ማድረግ ችለዋል:: ቱኒዚያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ ባካሄዱት ሀገራዊ ምክክር ላይ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ አካላት በሙሉ መካተታቸውንና ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል መወከሉን አስቀድመው አረጋግጠዋል:: ይህ ነው ለሌሎችም ምሳሌ እንዲሆኑ ያስቻላቸው:: ሀገራቱ ምክክሩን የጀመሩት ሁሉም እንደሚሳተፍ አረጋግጠው ነበር:: በዚህ ምክንያት የተሳካ ምክክር አድርገዋል::

ዛሬ ደግሞ ተራው የኢትዮጵያ መሆኑን እየተመለከትን ነው። ስኬታማ አፈፃፀም ያላቸው አገራትን ተሞክሮ በመቀመርና ከራሷ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በመቃኘት ለምክክሩ ቅድመ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀች ትገኛለች:: ለዚህ ነው መጪው መድረክ የሀሳብ ልዕልና የሚንፀባረቅበት እንደሚሆን የተገመተው:: በውጤቱም አዲስ የችግር አፈታት ባህል የሚዳብርበት እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል:: የሀሳብ ልዩነቶችን በማስተናገድ ችግሮችን ለመፍታት ምክክር ወሳኙ መሆኑን እንደሚያመላክትም ይጠበቃል::

እንደሚታወቀው ሀገራዊ ምክክር ለግጭትና አለመግባባቶች ምክንያት የሆኑ ሀሰተኛ ትርክቶችን በማስቀረት አንድነትን የሚያመጡ የጋራ ትርክቶችን በመገንባት በኩል ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል:: እስከ ዛሬ ድረስ በሀገራችን ሰፍኖ የኖረው የባላንጣነት ፖለቲካ በተሳሳተ ትርክቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑ ይታወቃል:: ይህንን ለማረቅ መፍትሄው በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ በስክነት መወያየት ነው። ትርክቶቹ በአጀንዳነት ለውይይት ቀረቡ ማለት ንፋስ መታቸው ወይም ተጋለጡ ማለት ነው:: ስለዚህ በመሰል ትርክቶች ላይ ቁጭ ብለን ጥቅምና ጉዳታቸውን ስንወያይ በምትካቸው ሊተካ የሚችለውን ሌላ እውነተኛ የጋራ ትርክት መፍጠር ያስችላል::

የመልካም ነገሮች ሁሉ መጀመሪያ ምክክር በመሆኑ ለሀገርም ሆነ ለሕዝብ ይዞት የሚመጣው አወንታዊ ጎን ቀላል ነገር አይደለም:: ማንኛውም ነገር ፀንቶ እንዲቆይ ከተፈለገ ምክክር ያስፈልጋል:: ኢትዮጵያን ለማሳደግና አሁን ካለችበት የበለጠ ከፍ ለማድረግ፣ አሁን ካሉብን ችግሮች ነፃ ለመውጣት ምክክር አስፈላጊና ወሳኝ ነው::

ምክክሩ አዲስ ተስፋን ይዞ እንደሚመጣ የብዙ ኢትዮጵያዊያን ምኞትና ፍላጎትም ጭምር ነው:: በእርግጥም በኢትዮጵያ ምክክር አዲስ ልደት ነው ማለት ይቻላል:: አዲስ ልደት ደግሞ አዲስ ተስፋ ሰንቆ የሚመጣ ነው:: እናም የኢትዮጵያችንን ችግሮች ነቅሰን የምናወጣበት፣ መፍትሄውንም የምንጠቁምበት፣ ለልጆቻችን የተደላደለ ኑሮ የሚኖሩበትን ሀገር ለመፍጠር የምናመቻችበት መድረክ ነው::

ኢትዮጵያ በሀገረ መንግስት ግንባታ ከዓለም ሀገራት ቀደምቷ እንደሆነች ሁሉ በሀገራዊ ምክክር በሀሳብ ልዕልና የተመሰረተ ምክክር ማሳያም መሆን ይጠበቅባታል:: ይህ እንዲሆን የአጀንዳ ልየታው ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዲሁም ተሳታፊ አካላት ሁሉ መካተታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል::

ውይይታችን በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ፣ የማንም ሀሳብ የማይናቅበት፣ የማንም ጥያቄ የማይረገጥበት፣ሁሉም ሰው የሚሰማውን ስህተት እንኳ ቢሆን አቅርቦ በውይይቱ ሂደት እየታረመ እንዲሄድ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት ሊሆን ይገባል:: አጀንዳዎች በትክክል ተለይተው ከወጡ የምክክሩን ሂደት 50 በመቶ እንዳለቀ ሊቆጠር ይገባል:: በመሆኑም አጀንዳ በማፍለቅ የሚሳተፉ አካላት በከፍተኛ ጥንቃቄና ኃላፊነት በተሞላው መንገድ ሊሰሩት ይገባል::

በእርግጥ ተሳታፊዎች የመለየት ስራውን አሳታፊ እና አካታች በሆነ መልኩ ለማከናወን አስፈላጊ የሆኑትን ተግባራት ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ሲከናወን ተመልክተናል:: የተለዩት ተወካዮች ትርጉም ያለው ተሳትፎ ከሚያደርጉባቸው የምክክር ምዕራፎች መካከል በምክክር አጀንዳዎችን የመለየት አንዱ ነው። በተጨማሪ ምክክር የሚደረግባቸውን እጅግ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን አሳታፊና አካታች በሆነ ሂደት የመለየቱ ስራ በራሱ ምክክር የሚፈልግ ነው። ከሁሉ በላይ ጉዳዩ ቅንነትና መግባባትን የሚጠይቅ በመሆኑ ሂደቱ በቀጣይ ለሚከናወነው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ስኬታማነት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል:: በመሆኑም መምህራን፣ ምሁራን፣ በተለያየ ደረጃ የተውጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች በአጀንደ ልየታው በመሳተፍ ለችግሮቻችን መፍትሄ ሀሳብን ማምጣት ይጠበቅባቸዋል::

በተለያየ ግዜ ከሚወጡ መረጃዎች መረዳት እንደምንችለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራውን ወደፊት ማምጣት ችሏል:: በአዲስ አበባ ከተማ የአጀንዳ ልይታ አከናውኗል:: በአጀንዳ ልየታው የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል:: ህብረተሰቡን ያማከለ ውክልናም ተንፀባርቆበታል:: የተካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ ግልፅና አሳታፊ መሆኑን ተሳታፊዎች ተናግረዋል:: አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደቱ መሰረታዊ የሚባሉ ችግሮችን የመለየት ስራ ተከናውኗል:: ህብረተሰቡ የሚያነሳው ማንኛውም ጥያቄዎች ቀርበዋል:: በኢትዮጵያ መንግስት አወቃቀር ውስጥ ህብረተሰቡ የማይፈልጋቸው ጉዳዮችንና መንግስት ያላሟላቸው ነገሮችን በዝርዝር ቀርበውበታል:: ከመንግስት የሚፈልጋቸው፣ ከሀገሪቱ መንግስት መዋቅር መከናወን የሚገባቸው ነገሮች በውይይቱ ቀርበው ተለይተዋል::

ይሁን እንጂ አንድ ጉዳይ ግን አሁንም በትኩረት ሊታይ ይገባል። እርሱም ኢትዮጵያ የተሟላ ምክክር እንድታደርግ ሁሉም አካል ተሳታፊ መሆን እንደሚጠበቅበት ማወቅ ነው:: የምክክሩ አንዱና ትልቁ ተግዳሮት የትጥቅ ትግል ለማድረግ ጫካ የገቡ እንዲሁም የሰላማዊ ፖለቲካ አቀንቃኝ ነን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ‹‹በኮሚሽኑ ላይ እምነት የለንም፣ ምክክሩ ላይ አንሳተፍም›› የሚል አይነት ይዘት ያላቸው መግለጫዎችን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያወጡ መመልከታችን ነው:: እነዚህ አካላት ኮሚሽኑ እንዲመሰረት የተለያዩ ሀሳቦችን እንዳዋጡ ሁሉ ምክክሩ እንዲደረግም በራቸውን ክፍት ማድረግ አለባቸው::

ምክክር ሁሉን አቀፍ ጥቅም ስላለው መሳሪያ ይዘው ጫካ የገቡ አካላት የሕዝብ ጥያቄን አንግበው ከሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊከታተለው በሚችለው የምክክር መድርክ የሕዝብ ጥያቄዎቻቸውን የሚያቀርቡበት መንገድ መቀበልና መሳተፍ አትራፊ ያደርጋቸዋል:: ይህን እንዲሳካ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት አለ:: ኢትዮጵያ ከፓርቲም በላይ በመሆኗ ለራስ ብቻ ከማሰብ ወጣ ብለው ውጤታማ ምክክር እንዲደረግና ሀገር ተጠቃሚ እንድትሆን ተሳትፏቸው በርትቶ የበኩላቸውን አስተዋፆ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል:: ትጥቅን እንደ መፍትሄ አማራጭ የወሰዱ ኃይሎች ወደ ጠረጴዛው እንዲመጡ ግፊት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በእርግጥ የእያንዳንዱ የኢትዮጵያዊ ችግር ሙሉ በሙሉ አሁኑኑ በሀገራዊ ምክክሩ ሊፈታ አይችልም:: ነገር ግን በጥንቃቄ የተመራ ምክክር ቢያንስ የተቀራረበ ሀሳብ ይዞ ለመውጣትና የችግሮቻችንን መነሻ ለማወቅ ያስችለናል:: ጫፍና ጫፍ የወጣን ሀሳብ ወደ መሀል ማቀራረብ አንዱና ትልቁ ተግዳሮት ቢሆንም በጋራ ሆነን የምንፈታው ሊሆን ይገባል::

የማንግባባቸው ጉዳዮች ብዙ ናቸው:: በምልክቶቻችን እና በጀግኖቻችን ጭምር አንግባባም:: የእኛ ሀገር ከሌሎች ሀገራት አውድ በመጠንም ቢሆን ልዩነት እንዳለው ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል:: ዋናው ነገር ሁሉም የፖለቲካ ተሳታፊዎች ምክክሩን ለሚያመቻቸው አካል እምነት በመስጠት አይሆንም ከሚለው ሀሳብ ወጥተው ወደ ጠረጴዛ ውይይት መምጣት አለባቸው::

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባትም ሆነ የፖለቲካ ባህላችንን ለማዳበር ብዙ መትጋትና መልፋት ይጠበቅባቸዋል:: ልዩነቶችን በውይይት መፍታት መለማመድ መጀመር አለባቸው:: ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ በምክክር ሂደቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በንቃት መሳተፍ የውዴታ ግዴታው መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል::

የተጀመረው ምክክር ስኬታማ እንዲሆን መገናኛ ብዙሀን ዜጎች ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሊሰሩ ይገባል:: ይህ ምክክር ሀገርን የማዳን፣ ኢትዮጵያውያንን የማቀራረብ፣ ሰላምን የመፍጠር ተልዕኮ እንዳለው በመተረክ አስቻይ ሁኔታን መፍጠር አለባቸው:: አለፍም ብለው ‹‹ኢትዮጵያውያን እንመክራለን መክረን ከችግሮቻችን መውጣት እንችላለን፣ ችግሮቻችንን በአንቀልባ አዝለን ቁጭ ማለት የለብንም፣ ዛሬ ላይ ቁጭ ብለን እውነትን በጋራ እንፈልግ›› የሚሉ መሰል መልእክቶችን በማስተላለፍ ማህበረሰቡን ማበረታታት ይጠበቅባቸዋል::

ምሁራን አሻጋሪ የመፍትሄ ሀሳቦችን ማፍለቅ ተቀዳሚና ቋሚ ስራቸው ሊሆን ይገባል:: መገናኛ ብዙሀን ያሉንን ጥንካሬ እሴቶች ለትውልድ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል:: የትምህርትና የሀይማኖት ተቋማት ግብረገብ ያለውና ሀገር ወዳድ ትውልድ የመፍጥር ሚናቸውን መወጣት አለባቸው::

በድንቁርና ተባብሮ ከመጥፋት ይልቅ ተጋግዞ ክፉ ዘመንን ማሸነፍ ይገባልና ሁላችንም ሰላም፣ ዴሞክራሲና ፍትህ የሰፈነባት የጋራ ሀገር እንድትኖረን ተግተን እንስራ! ሰላም ከሰፈነባቸውና በእድገት ጎዳና ሽቅብ ከደረሱ ሀገራት እንደተማርነው በስክነት፣ በመረጋጋትና በከበሬታ መመካከር ሀገራዊ መፍትሄ መሆኑን ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል። ሰላም !!

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You