የሚያዋጣን ከሰላም ጎን መቆም ነው

ወቅቱ የክረምት መግቢያ የሰኔ ወር ቢሆንም የበጋዋ ጸሃይ ቦታዋን ለመልቀቅ የተናነቃት ይመስል ከዝናቡ ጋር ግብግብ ገጥማለች:: በየሰዓቱ ብልጭ እያለ ልብ የሚያቀልጠው የደመና ግላጭ የአላፊ አግዳሚውን አናት ያነደው ይዟል::

ወደ ማምሻ ግሮ ሰሪ እያዘገመ የነበረው ተሰማ አናቱ በጸሃይ ግሎ ብስጭት ብስጭት ብሎታል:: ቀዝቀዝ ማለት በመፈለጉ ብቻ ሳይሆን ወዳጆቹንም ፈልጎ ማምሻ ግሮ ሰሪ ተሰየመ::

ተሰማ ተቀምጦ እግሩ መሬት ነክቶ በደንብ ካረፈ በኋላ፤ የሚጠጣውንም አጣጥሞ የእጅ ስልኩን መነካካት ጀመረ:: ጊዜው ባለመምሸቱ ጓደኞቹ ተሰማ መንግስቴ እና ገብረየስ ገብረማሪያም ገና ወደ ማምሻ ቤት አልመጡም ነበር:: እስከዛው አይኑን ወደ ቴሌቪዥኑ ሲወረውር በአማራ ክልል ሰላም ለማውረድ ጥረቶች መጀመራቸውን እና የሰላም ካውንስል መቋቋሙን አዳመጠ:: ደስ አለው::

ብዙም ሳይቆዩ ዘውዴ እና ገብረየስ እንደልማዳቸው አምሽተው ሳይሆን በጊዜ ወደ ማምሻ ግሮሰሪ ብቅ አሉ:: ዘውዴ በፈገግታ ተቀበላቸው:: ዘውዴ ለተሰማ ‹‹የተፈፀመውን ሰማህ አለው?›› ገብረየስ ቀደም ብሎ ‹‹ አልሰማም፤›› ሲል ምላሽ ሰጠ:: ተሰማ ግራ ገባው ‹‹ የተፈፀመው ምንድን ነው? መቼም ይሔ በየማህበራዊ ድረገፁ የሚለጠፈውን ውሸት ይዛችሁ እንዳይሆን፤ የሆነው ምንድን ነው ምላሽ ስጡኝ::›› አለ::

ተሰማ ‹‹ አማራ ክልል ሰላም ሊወርድ ነው:: የሰላም ካውንስል ሊቋቋም መሆኑን በሚዲያ ሰማሁ ብሎ ››ደስታውን አበሰራቸው:: እነሱም ደስታው ተጋባባቸው:: በተለይም ተሰማ አማራ ክልል በነበረው ግጭት ምክንያት ከዘመዶቹ ጋር ከተገናኘ ረጅም ጊዜው ነበር:: የደህንነታቸው ጉዳይ አብዝቶ ያሳስበው ስለነበር እነሱም ሁልጊዜ አብረው ይጨነቁ ነበር:: እናም በሁሉም ፊት ላይ የተስፋ ብርሃን ይነበብ ነበር::

ተሰማ የጓደኞቹን መደሰት ካየ በኋላ ወጉን ቀጠለ:: ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገሩ ዳር ድንበር የሚዋደቅ፤ ከራሱ በፊት ሀገሩን የሚያስቀድም፤ ቀኝ ገዢዎችንና ሌሎች ወራሪ ኃይላትን አሳፍሮ የሚመልስ ጀግና ሕዝብ ነው:: ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሀገራት ነጻነትና እኩልነት የሚታገሉ፤ በአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የሆኑ ኩሩ ሕዝቦች ናቸው:: ይህም ጀግንነትና አይበገሬነት በተባበሩት መንግስታት ጭምር እውቅና አግኝቶ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን በሩዋንዳ፤ በቡርንዲ፤ በላይቤሪያና በሶማሊያ ተሰማርቶ ጀግንነቱን አስምስክሯል::

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀግንነቱን ያህል ሰላም ወዳድም ነው:: በየትም ሥፍራ ቢኖር፣ የትኛውንም እምነት ቢከተል፣ በተለያዩ ቋንቋዎች ቢገለገል፣ ባህሎቹና ልማዶቹ ቢለያዩም ለሰላምና አብሮነት ሰፊ ቦታን ይሰጣል:: ሰላም የእሴቶቹ አንዱ መገለጫ ነው::

ሆኖም ከዚህ የኢትዮጵያውያን ባህል ባፈነገጠ መልኩ ፍላጎታቸውን በነፍጥ ማሳካት የሚፈልጉ ቡድኖች እየተበራከቱ መጥተዋል:: ከውይይት ይልቅ ነፍጥ ማንሳት የሚቀናቸውና ሰላም ወዳዱን ሕዝብ የሚረብሹ፤ አብሮነቱን የሚያውኩ፤ የኢትዮጵያን መረጋጋትና ሉአላዊነት የሚገዳደሩ ቡድኖች እዚህም እዚያም አቆጥቁጠዋል::

እነዚህ ወገኖች በሚፈጥሩት ሁከትና ብጥብጥም ልማት ተደናቅፏል፤ የሰዎች ወጥቶ መግባት ተስተጓጉሏል፤ አለፍ ሲልም የሀገር ህልውናንም አደጋ ላይ ወድቋል:: እኛም ባለፉት ግዝያት የተጎዳነው እና ለብዙ ሃሳብ የተዳረግነው በእነዚህ ቡድኖች የተነሳ ነው::›› በማለት ሃሳቡን አሳረገ::

ዘውዴ ቀበል አደረገና ጨዋታውን ቀጠለ:: ‹‹ዘውዴ ልክ ነህ:: ባለፉት ግዚያት ምን ያህል እንደተጨነቅክ እናውቃለን:: ከአንተ አልፎ እኛም ስንጨነቅ ቆይተናል:: አየህ ኢትዮጵያ ውስጥ የአንዱ ሰላም ደፍርሶ የሌላው ሰላም ሊረጋገጥ አይችልም:: አንዱ ጥይት እየጮኸበት አንዱ የሰላም አየር ሊተነፍስ አይችልም:: እጣችን የተሳሰረ ነው:: ስለዚህም አብረን ችግሮቻችንን መፍታትና በሰላም መኖር አለብን::

አሁን እኛ የተቸገርነው ሕዝብ ሳይሾማቸው ለሕዝብ ቆመናል በሚሉ ቡድኖች ነው:: እነዚህ ቡድኖች ሕዝብ ሳይሾማቸው የሕዝብ ወኪል ነን ከማለታቸው በሻገር አሉ የሚሏቸውን ችግሮች እንኳን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አይፈልጉም::

እነዚህ ቡድኖች ችግርን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ነውጠኛ ደጋፊዎችን የማሰባሰብ ሴራ ውስጥ ስለሚገቡ፣ በኢትዮጵያ እዚህም እዚያም ግጭቶች በርክተው ይታያሉ:: እነዚሁ ኃይላት ኃላፊነት የጎደላቸው ስለሆኑም ግጭትና መገዳደልን ጨምሮ የአገርን ተስፋ የሚያጨልሙ ድርጊቶች እንዲበራከቱ በማድረግ ላይ ይገኛሉ::

ለአገርና ለሕዝብ ከማሰብ ይልቅ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ስለተጠናወታቸውም ቆመንለታል ያሉትን ሕዝብ ሳይቀር በቁሙ ሲዘርፉ ተስተውለዋል::

እነዚህ ቡድኖች ከመተማመን ይልቅ ጥርጣሬ፣ ከትብብር ይልቅ መገፋፋት፣ በግልጽ ከመነጋገር ይልቅ መተማማት ስለሚቀናቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ሕዝቡን አላስፈላጊ ወደ ሆነ ጥርጣሬ ውስጥ በመክተት አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት እየከፋፈሉ የዘመናት አብሮነቱን ሊነጥቁት ሲሯሯጡ ይታያሉ:: በእነዚህ ስግብግቦች የተነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ ጊዜን ለማሳለፍ ተገዷል:: ጓደኛችን ተሰማም የነዚሁ ቡድኖች አንዱ ሰለባ ነው:: ከእሱም አልፎ እኛም ተጎጂዎች ሆነናል::››ሲል ሃሳቡን አሳረገ::

የሁለቱንም ሃሳብ በአንክሮ ሲያዳምጥ የቆየው ገብረየስ ድመጹን ስሎ ወደ ውይይቱ ተቀላቀለ:: ‹‹ያላችሁት ምንም የሚወድቅ ነገር የለውም:: እንደውም እስካሁን ዝምታን መምረጣችን ለችግሩ መባባስ አጋዥ ሆነን ቆይተናል የሚል እምነት አለኝ::

እነዚህ ቡድኖችና ደጋፊዎቻቸው በሚለቋቸው መረጃዎች ጭምር ተወናብደን በተዘዋዋሪ ከሰላም ጎን መቆም አቅቶን ቆይተናል:: እነዚህን ቡድኖች ድርጊታቸው የሚያስቆማቸው የጸጥታ ኃይል ሲመጣ ደግሞ ግበረ አበሮቻቸውን ሰብስበው በሰፊው ስም የማጥፋት ዘመቻ ውስጥ ይገባሉ::

የኢትዮጵያን ሰንደቅ ለብሶ ታላላቅ ድሎችን የተጎናፀፈውን ጀግና የመከላከያ ሰራዊታችንንም በማጠልሸትም ኢትዮጵያን ለማሳነስም በቀቢጸ ተስፋ ሲሯሯጡ ታይተዋል:: ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡ እጅግ በጣም ሰላማዊና ለሕግ ትልቅ ትኩረት ስለሚሰጥ ለአመፅና ለብጥብጥ ሥፍራ የለውም እንጂ የእነዚህ አካላት ድርጊት ሀገርን የማፍረስ ዓላማ ጭምር ያለው ነው::

ስለዚህም አሁን ሁላችንም የሚያዋጣን ከሰላም ጎን መቆም ነው:: መወቃቀስና አንዱ አንዱ ላይ ጣት መጠቆሙ ያመጣልን ፋይዳ የለም:: የሰላም ሃሳብ የሚያነሳን ወገን ሁሉ መደገፍ አለብን:: ተሰማ እንዳለው በአማራ ክልል ያለው ግጭት ማብቃት አለበት:: ሰዎች በሰላም ወጥተው የመግባት ሕገ መንግስታዊ መብታቸው ሊከበር ይገባል:: እንደተባለውም የሰላም ካውንስል መቋቋሙ አንድ እርምጃ ነው ብዬ አምናለሁ ››ብሎ ሃሳቡን ቋጨ::

ተሰማ ሃሳቡን መደገፋቸው አበረታታውና ቀጣይ ሃሳብ ለማንሳት ተዘጋጀ:: ‹‹ እንደ አንድ ዜጋ ሁላችንም በየአቅማችን ኢትዮጵያን ማትረፍ ግዴታችን ነው፤ የሚል እምነት አለኝ:: ኢትዮጵያን ለማትረፍ በሚሠራው ሥራ ሰዎች ሊጎዱ ይችላሉ:: ያንን ተከትሎ ቅሬታ፣ አለፍ ሲል ቁጣ አልፎ ተርፎ ተቃውሞ እና አመፅ ሊያጋጥም ይችላል:: ይህ የሚጠበቅ ነው::

በተጨማሪ የሰው ፍፁም የለውም፤ በዚህ ሂደት ውስጥ መፈፀም የሌለባቸው ድርጊቶች ተፈፅመው ሊሆኑ ይችላሉ:: ነገር ግን ምንም ሆነ ምን ከማንም ሰው በላይ ኢትዮጵያ ትልቃለች:: ኢትዮጵያ የብዙዎች ደም የፈሰሰላት፤ ብዙዎች የተሰውላት አገር ናት:: ስለአገራችን ስናስብ እና ስንጨነቅ አገራችንን ለማትረፍ የምንሰራውን ሥራ ተከትሎ ጉዳዩን ባለመረዳት ወይም ከግል ጥቅም ጋር በማገናኘት የሚቃወም ሰው ቁጥር እያደገ ሊመጣ ይችላል፤ ሆኖም ዋነኛው ጉዳያችን ኢትዮጵያ ናትና በቅድሚያ ሀገራችንን ልናተርፍ ይገባል::

በዋነኝነት ደግሞ ኢትዮጵያን ማትረፍ የምንችለው ሰላሟን በማስጠበቅ ነው:: በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሁላችንም ወደ ብሄራችን ወይንም ወደ ኃይማኖታችን በማድላት ኢትዮጵያን ጎድተናት ይሆናል:: ሆኖም የምንከስበት አሁን ነው ብዬ አስባለሁ:: ስለዚህም ሁላችንም ኢትዮጵያን ለመካስ ምን ያህል ተዘጋጅተናል::

እስኪ ወደ እራሳችን እንመልከት እኔ፤ አንተ፤ እናንተ አገራችሁን ኢትዮጵያን ብላችሁ አስባችሁ ትሠራላችሁ?›› ሲል ዘውዴን ጠየቀው:: ዘውዴ በበኩሉ ‹‹ ችግሩ አገራችንን አስበን ቀንና ለሊት ተግተን ብንሠራም፤ ከውስጥም ከውጪም ጠላት በዛብን:: ውጪ ያለው ጠላት ኢትዮጵያን ብሎ ስለ ኢትዮጵያ የሚሠራውን ማጥፋት ይፈልጋል:: ምክንያቱም ኢትዮጵያን የማፍረስ እና ታሪኳን የማጥፋት ፍላጎት አለው:: ስለዚህ ኢትዮጵያ ላይ በተለያየ መንገድ ዘመቻ ላይ ነው:: ይህ ስውር የውጪ የጠላት ኃይል ጠላትን የሚቃወመውን ሁሉ መደገፍ እንዳለበት አምኖ የውጪ ጠላት ከአገር ውስጥ ጠላት ጋር በመተባበር እየሠራ ነው:: የውስጥ ጠላት እንዴት ተፈጠረ? ካላችሁ በአሠራር ስህተት የተፈጠሩ ጥቃቅን ጉዳዮችን በማጉላት እና ያንንም በማስተጋባት ሰዎች ስለአገር የሚያስቡትን፣ ስለአገር የሚሰሩትን የሚጠሉበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነው:: በሌላም በኩል ለውጭ ጠላቶች የሚላላኩና ምንዳ የሚጣልላቸውም ቀላል አይደሉም::

በየጊዜው በሚፈጠሩ ወቅታዊ ሁኔታዎች በመሳብ ዋናውን ሀገር ጉዳይ የሚረሱ ቀላል ቁጥር የላቸውም:: ሀገር ግንባታ ደግሞ አልጋ በአልጋ አይደለም፤ በአንድ ጀንበር ተጀምሮ በአንድ ጀንበር የሚያበቃም አይደለም:: ብዙዎች የተማሩ የተባሉ ሰዎች ሳይቀሩ አይተው መረዳት ተስኗቸዋል:: መደገፍ ያለባቸውን ከመደገፍ ይልቅ ዘላለማቸውን የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም አሁንም አገር ለማጥፋት እየተባበሩ ነው::

የአተያይ እና የአመለካከት ልዩነት የተለመደ ነው:: ስለአገራችን ስናስብ የችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ ሁከትና ብጥብጥ ነው ብሎ ማሰብ አይገባም:: በመነጋገር እንጂ በኃይል እርምጃ የትም መድረስ አይቻልም:: ተነጋግሮ ችግሩን ከስር መሰረቱ መፍታት ካልተቻለ በሁከትና ብጥብጥ የሰው ሕይወት ይጠፋል፤ የሀገር ሃብት ይወድማል::

ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹ ታዲያ የኃይል እርምጃ እንዳይወሰድ አንዱ የገዛ ሌላኛውን ወንድሙን እንዳይወጋ ከተፈለገ ሰላም እና ሥርዓት መስፈን አለበት:: ዋነኛው ማንም ስለኢትዮጵያ ቀን እና ለሊት የሚያስበው ሰው መነሻ እና መድረሻው የኢትዮጵያ ሰላም እና ዕድገት ብቻ ነው:: ያለሰላም ዕድገት ዘላቂ መሆን አይችልም::›› ሲል ተናገረ::

ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር እጅግ በጣም የተወሳሰበ ነው:: ብዙዎቻችን አንዳንዴም የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ሳይቀሩ ስላለው ችግር ለሕዝቡ የማሳወቅ ክፍተት አለባቸው:: መረጃ በወቅቱ ለሕዝብ ከማድረስ አንጻር ክፍተት አለ:: ሕዝቡ በአግባቡ መረጃ ቢደርሰው መንግስትን በአግባቡ መረዳት ይችላል፤ ከመንግስት ጋር ሆኖም የተጀመረውን ሀገርን የማቅናት ዘመቻ ከግቡ ማድረስ አይሳነውም::›› ሲል ያለውን እምነት ገለፀ::

ተሰማ በበኩሉ ‹‹ ዋነኛው ችግር አብዛኞቻችን የሩቅ ተመልካችና ተቺ ሆነን መገኘታችን ነው:: አለፍ ሲልም በሽርፍራፊ ሳንቲም ሀገራችንን የመንቀይር መብዛታችን ነው:: ያለንን ገንዘብ እንኳን መብላት የምንችለው ሀገር ስትኖር መሆኑን ዘንግተናል:: ማንም የማይክደው ብዙ ሰው ስለአገር ይጨነቃል:: ምክንያቱም ሕይወቱ ከአገሩ ጋር የተቆራኘ ነው:: ነገር ግን ጥቂቶች በሚፈጥሩት ውዥንብርና ትርምስ የብዙሃኑ ሕይወት መታመሱ የሚያሳዝን ነው::

ሰውን ከምንም በላይ ተግባር ያሳምነዋል፤ ማየት ማመን ነው:: ሰው መልካም ነገር ሲያይ ይደሰታል፤ ያመሰግናል:: ስህተቶች ሲኖሩም አግባብ በሆነ መልኩ ማስረዳት ይገባል:: እጸጽ እየፈገሉ ሰዎችን ለአመጽ መጥራት እና አላስፈጊ ሁከት መፍጠር ትርፉ ኪሳራ ብቻ ነው:: በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች ከአመጽ ትርፍን፤ ከሀገር ኪሳራ ሃብትን የሚጋብሱ አሉ:: እነዚህ ሰዎችን መምከር በክንቱ መድከም ነው:: ምክንቱም እነዚህ ሰዎች ገቢ በሁከትና ብጥብጥ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ሰላም ወረደ ማለት እነዚህ ሰዎች ሃብት ነጠፈ እንደማለት ነው:: ስለዚህም ሁላችንም ልንነቃ ይገባል:: ለጥቂቶች ብለን እራሳችንን መስዋዕት ማድረግ የለብንም:: ሁላችንም በደስታ መኖር የምንችለው ሀገር በሰላም ውላ ስታድር መሆኑን መገንዘብ አለብን:: ›› ብሎ በረጅሙ ተንፍሶ ሃሳቡን አሳረገ::

ፍሬው ማንችሎት

 አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You