ሀገርን መሀል አድርገን፤ለሕዝብ ቅድሚያ ሰጥተን እንመካከር

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሰላምና አንድነት ግድ የሚላት ጊዜ ላይ ነን:: በተለያዩ ጊዜ የተነሱ ፖለቲካዊና ብሄር ተኮር እሳቤዎች የመከራ ገጽ አላብሰዋት ሰንብታለች:: ከጦርነት ወደጦርነት በሆነ የፉክክርና የይዋጣልን እልህ ለማንም በማይበጅ የብኩርና ግፊያ ውስጥ እልፍ ዓመታትን በሞትና በጉስቁልና ውስጥ ከርመናል:: በሰላም ስለሰላም መነጋገርና መግባባት አቅቶን ጠመንጃ ስንወለውልና ካራ ስንስል ከዛሬ ማለዳ ላይ ደርሰናል::

የሚያግባቡን ብዙ እያሉ እንደመዳፍ በጠበበ የልዩነት አውድ ላይ ተጠምደን ጣት ስንቀሳሰር፣ የታባክ ምናባክ ስንባባል ከሀገር ያገዘፉንን፣ በታሪክ ያደመቁንን ጸዐዳ መልኮቻችንን ከልለናል:: ከፊታችን ወዳለና በጋራ ወደተበጀ እውነት ከማየት ይልቅ አንሰውና ቀንጭረው አልታይ ወዳሉ የልዩነት መስኮች እያስተዋልን ኢትዮጵያዊነትን ሽረንዋል:: ወንድማማችነትን ዘርቶ ባበቀለ ሩህሩህ ልብ ላይ፣ ኢትዮጵያዊነትን ባጸደቀ ለም አእምሮ ላይ የዘረኝነት መርዝ ረጭተን ከተሲያት የከለሉንን፣ ከውርደት የታደጉንን ዋርካዎቻችንን አጠውልገናል::

ባልነበረ ተረት ተረት፣ በነጣጣይ እኩይ ትርክት ትውልዱ እንዲሰጋጋ እና እንዲፈራራ ጥላቻን አጋብተንበት ሆደ ባሻ እንዲሆን አድርገነዋል:: በጥላቻ ተቧድነን፣ ለጦርነት ተዛዝተን የነጻነቷን ምድር አስጊ፣ የምህረት እጆችን ገዳይ አድርገን ቀይረናቸዋል:: ስለሌላው ግድ የሚለው ሀበሻነት፣ የጣሊያንን ምርኮኞች አቅፎና ደግፎ በክብር ወደቀያቸው የሰደደ ኢትዮጵያዊነት በወንድሞቹ ላይ እንዲጨክን በዘረኝነት መርዝ አስክረንዋል:: ሀ ሲል ፊደል የቆጠረው ትውልድ፣ አቦጊዳ ሲል ግዕዝ ያጠናው ብላቴና በዝሆኖች ግፊያ ያለስራው አበሳ ቆጣሪ ከሆነ ሰንብቷል:: መካሪና ገሳጭ፣ አስታራቂና ዘካሪ ሽበታም ጠፍቶ በትዕቢተኞች በለው በለው ፍቅር የከሰመበትን አዲስ ማንነት ወርሰናል::

ሰላምና ፍቅር አብበው ያፈሩባት፣ ነጻነትና ሉአላዊነት አፍ የፈቱባት ምድር፣ ክብርን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን ለዓለም ያስተዋወቀች ጦብያ ምንም እንደሌለው በሰላም ርሀብ፣ በፍቅር ድርቀት ስትሰቃይ እንደማየት የሚያም የለም:: ለአብነት እነዚህን ጠቀስኩ እንጂ ጉዶቻችን ብዙ ናቸው:: ከትላንት ወደዛሬ የመጡ፣ ዛሬ ላይ ወልደን ያሳደግናቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የብሔር፣ የወሰን ትርክቶች ብዙ ናቸው:: ያለን ሳይበቃን አዲስ መከራ እየፈጠርን እንደ ጃርት ገላ በመላ ሰውነታችን ላይ የመከራ ቀስትን ታጥቀናል::

መፍትሄው ምንድ ነው? መልካሙ ነገር ሁሉም ችግር መፍትሄ ያለው መሆኑ ነው:: መፍትሄ ካለው እኛ ለምን መፍትሄ አጣን? መከራዎቻችንን ወደጦርነት እና ወደሞት ሲወስዱን ስለምን ዝም አልን? ዘረኝነት ከኢትዮጵያዊነት በልጦ ዋጋ ሲያስከፍለንና ታሪካችንን ሲቀማን እንደምን አስቻለን? በጋራ ሀገር እና ታሪክ ላይ እኔነት አብቦ እኛነትን ሲያጠወልግብን ምን ከጀልን? የሚሉ እና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች መነሳታቸው ግድ ነው:: እኛና ችግራችን ለምን እንዳልተግባባን፣ ችግር እኛን እኛም ችግርን አፍቅረን ለምን እንደኖርን አሁን እነግራችኋለው:: በእርግጥ አዲስ ነገር አልነግራችሁም የምታውቁትን ግን ደግሞ ችላ ያላችሁትን እውነታ ነው የማስታውሳችሁ::

ዓለም ከዘመነበት የስልጣኔ መነሻዎች መሀል ‹ሁሉም ችግር መፍትሄ አለው፣ ችግሩን በፈጠረው አእምሮ መፍትሄ ማምጣት አይቻልም› የሚሉት ምክረ ሀሳቦች በወርቅ ሚዛን የሚመዘኑ እጅግ ትርፋማዎቹ ናቸው:: ሁሉም ችግር መፍትሄ አለው ስንል መነጋገርንና መደማመጥን ላስቀደመ አእምሮ ነው:: ልዩነቱ ላይ ሳይሆን አንድነቱ ላይ ላተኮረ ማኅበረሰብ ነው:: ከጦርነት በፊት ሰላምን ለማምጣት ፖለቲካቸውን አስፍተው፣ ልባቸውን አግዝፈው ስለሀገርና ሕዝብ ሰላም ለማውረድ ለተስማሙት ነው:: ሁሉም ችግር መፍትሄ አለው ሲባል.. ልዩነትን ለውበት አንድነትን ለኃይል በመጠቀም መርህ ውስጥ ስላለው ልማትና እድገት፣ ዘመናዊነትና ስልጣኔ እያወራን ነው:: ኢትዮጵያዊነትን ባስቀደመ ሀገር ማለት ሰው፣ ሰው ማለት ሀገር ነው በሚለው ሊቀ ሀሳብ ለተመራ ነው::

ችግሩን በፈጠረው አእምሮ መፍትሄ ማምጣት አይቻልም ሲባል ደግሞ ችግርና ሰላም አብረው የሚሄዱ እንዳይደሉና ስለ ሰላም በሰላም መወያየትና በመደማመጥ ግድ እንደሚል እያስረዳን ነው:: የእኛ ሀገር የችግር አፈታት ዘዴ ከችግር ወደችግር ነው:: አባባሽ ነገሮችን ከመፍጠር ባለፈ መፍትሄ ተኮር መሆኑ እምብዛም ነው:: ችግሩን በፈጠረው አእምሮ ሰላም መፍጠር አይቻልም:: ስለጦርነት እያወራን፣ ስለዘረኝነት እየሰበክን እንዴት ነው አብሮነትን የምናጸናው? ገዳይና ሟች ያሉበትን የብቻ ትርክቶችን እየፈጠርን እንዴት ነው ተከባብረንና ተቻችለን የምንኖረው?

ሁሉም ችግር መፍትሄ አለው ስንል ሀገርን መሀል አድርገን ስንወያይና ለሕዝብ ቅድሚያ ሰጥተን ስለአብሮነት ስንመካከር ነው:: ላሉብን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ከነውጥ ፈጣሪነት ወጥተን ወደለውጥ ፈጣሪነት መሸጋገር አለብን:: ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላም ትፈልጋለች:: ሕዝባችን፣ ትውልዱ ፍቅር ይሻል:: ልማቱ፣ እንስሳቱ፣ አየሩ፣ ቀዬው ሞት ሰልችቶታል:: እውነቱ ቃታ በመሳብ ዝለናል:: እጆቻችን በመግደልና በመሞት ሻክረዋል:: እስኪ ደግሞ ጊዜውን ለሰላም እንልቀቅ:: እስኪ ደግሞ በሰላም ስለሰላም የሞት ደመናችንን ገፈን የተስፋ ጣይ እንፈንጥቅ::

የምድር ውበት ሰላም ናት:: የሰው ልጅ ዓርማው ፍቅር ነው:: ሰላምና ፍቅር በአንድ ሀገር ላይ እንደሉአላዊ ሰንደቅ ዓላማ የክብር ደፎች ናቸው:: ሰንደቅ ለአንድ ሀገር መጠሪያ ከዚያም ሲገዝፍ የክብርና የአይነኬ ወሰን ነው:: ሰላምና ፍቅርም በሕይወት ላይ እንዲሁ ናቸው:: ሰላም ከሌለን ምንም ነገር እንዳይኖረን ሆነን የተበጀን ነን:: ፍቅር ከራቀን እንደሚንሿሿ ናስ በማይሰማና በማይማርክ ሰውነት ውስጥ ለመኖር እንገደዳለን:: መታወሻችን ሞትና ጉስቁልና፣ ጥላቻና ዘረኝነት ሆኖ ትውልዱን ይሻገራል:: መታሰቢያችን ከምድር እንዳይጠፋ በክፋት ቀድሞ ተጠቃሾች እንድንሆን የክብር ቀርቶ የነውር ሀውልት ይቆምልናል:: እስኪ ስለፍቅር እንሙት:: እስኪ ስለሰላምና ስለወንድማማችነት እንድከም::

የዓለም የጀግንነት ኒሻን ያለው ሞቶ በመግደል ውስጥ ሳይሆን ለሰው ልጅ ሁሉ ሰላም በማወጅ ውስጥ ነው:: ጀግና ልብ ኖሮ ማኖርን እንጂ ገሎ መሞትን አያውቀውም::፡ ዘመናዊነትና ስልጣኔ ጥሎ መውደቅን አያውቁትም:: ከእኛ ለእኛ በሆኑ ገዳይ ነውሮቻችን ውስጥ ነን:: በየትም በሌሉ በእርስ በርስ ሽኩቻ ስር ከወደቅን ቆይተናል:: እስኪ ማን አጠቃን? ጣሊያን ቻለን? እንግሊዝና ዝያድባሬ ቻሉን? ግብጽና ጉርድፎች አሸነፉን? እርስ በርስ ነው እየተበላላን ያለነው:: እርስ በርሳችን ነው እየተናናቅን ያለነው:: ለዛም ነው ሞታችን ያላባራው:: ለዛም ነው መከራችን መጨረሻ ያጣው::

ትርፍ በሌለው በአንድ አይነት ሰጣ ገባ ውስጥ እስከመቼ እንደምንዘልቅ አላውቅም:: በእርቅና በምክክር ለዛውም በጊዜ የለበስነው የጥላቻ ካባ እስካላወለቅን ድረስ ራሳችንን በኢትዮጵያዊነት ለዛ ለማየት ዋጋ መክፈላችን የማይቀር ነው:: ይሄ ሁሉ ከመሆኑ በፊት አስታራቂና መካሪ ሆነው በመጡ እንደ ብሄራዊ ምክክር ባሉ ሕዝባዊ መድረኮች ላይ መወያየትና መነጋገር ያስፈልጋል:: በፍቅርና በይቅርታ፣ በአብሮነትና በኢትዮጵያዊነት ካልሆነ በእልህና በጥላቻ፣ በበቀልና በቂም እድፎቻችን አይጠሩም:: ካባዎቻችን አይወልቁም:: ዘረኝነት ከልሏት እንጂ፣ ተረት ተረት ሸፍኗት እንጂ በሁላችንም ልብ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት አለ:: እውነታችን እንዲታይ ጭንብላችንን እናውልቅ::

በሰከነ ልቦና ስላላየናቸው እንጂ ችግሮቻችን ቀሊሎች ናቸው:: በመነጋገር ስላልሄድንባቸው እንጂ ልዩነቶቻችን ለመገፋፋት የሚያበቁን አልነበሩም:: በሰላም ለሰላም ከበረታን ከአቅማችን በላይ የሚሆን ምንም የለም:: የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ከዓመታት እንቅስቃሴው በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያውን የአጀንዳ ልየታ መርሀ ግብሩን እያከናወነ ይገኛል:: ሳምንት በሚቆየው እና ከ2500 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት ይሄ መድረክ ተስፋ ሰጪ የሆኑ፣ የሀገራችንን መጻኢ እድል የሚወስኑ የሰላምና የአብሮነት ሀሳቦች እንደሚንሸራሸሩበት ይታመናል::

በሂደቱ አዲስ አበባን ወክለው የሚሳተፉ ተወካዮች ይመረጣሉ፣ የከተማው የምክክር ጉባኤ ይሰየማል:: ሌሎች በመርሀ ግብሩ የተቀመጡ እንደቅደም ተከተላቸው የሚሄዱበት መድረክ ነው:: ሰባቱንም ቀናት አዋጭና አትራፊ በሆኑ ክንውኖች በኩል እንደሚሻገር የተገለጸ ሲሆን ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ በማድረግ ሀገር በማዳን ስራው ላይ መሳተፍ ውዴታችን ሳይሆን ግዴታችን ይሆናል::

ሀገራችንን ለመታደግ ውይይት እንደቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ መስፈርት ነው:: በውይይት የማይፈታ ምንም ነገር የለም:: ሀሳብ ላለው ልብ ሁሉም ችግር ሀገር ለመቀየር መልካም አጋጣሚው ነው:: ሀሳብ ለሌለውና በእልህ ለሚኖር አእምሮ ግን ሁሉም ልዩነት ወደጦርነት የሚወስዱ ናቸው:: በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ችግር ፈጣሪነት እንጂ ችግር ፈቺነት ጎልቶ አይስተዋልም:: የምንቧደነው ለጠብ ነው:: ጎራ የምንፈጥረው ለግጭት ነው:: ለሰላምና ስለሰላም ጎራ ፈጥረን አናውቅም:: እኚህ ልምምዶቻችን ከትላንት ዛሬ ላይ አርፈው ነገንም ሊቀሙን እያኮበኮቡ ነው..በቃ ልንል ይገባል::

በሀሳብ የዳበረ ፖለቲካ፣ ለመነጋገርና ለመግባባት ደጃፉን የከፈተ የለም:: ለዛም ነው ኮሽ ባለ ቁጥር ጠመንጃ የምናነሳው:: ለዛም ነው ትንሽዋ የሀሳብ ጥበት ግዙፍ ልዩነትን ፈጥራ እልቂትና ውድመት የምታደፈርሰው:: ኢትዮጵያዊነትና ግብረገብነት በሌለበት፣ ሰላምና ወንድማማችነት ባልተረጋገጠበት ሀገር ላይ ሀገርና ሕዝብ ትውልድና ታሪክ ምንድነው? ጨዋነትና መከባበር፣ መቻቻልና መተቃቀፍ በሌሉበት ፖለቲካ ስር ምን የተስፋ ጣይ ይፈነጥቃል? በፍቅር ስም በወንድሞቼ እቅፍ ካልተሸሸኩ፣ በወገኖቼ ክንድ ካልተደገፍኩ፣ በትውልዱ ካልተኩራራሁ ኢትዮጵያዊነት ምን ሊፈይድ? እናም እንመለስ..ወደራሳችንና ወደቀልባችን እናዝግም::

በዘረኝነት በኩል ትውልድ ሀገር የለውም:: በእኔነት በኩል ሀገር ሰው አይኖራትም:: ሀገር እያጣን ያለነው ከኢትዮጵያዊነት ባስቀደምናቸው ምናምንቴዎቻችን ነው:: ወንድማማችነትን የተነፈግነው መሀከላችን በተበተኑ የጥላቻ ዘሮች ሳቢያ ነው:: ኢትዮጵያ ብለን ጀምረን እኛ ብለን ካላበቃን ትርፋችን እንደዚህ ቀደሙ ሞትና ጉስቁልና ነው:: እናም ስለሰላም በሰላም አብሮነታችንን እንመልስ::

ኢትዮጵያን የማዳን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ነን:: የምንድነውም ሆነ የምናድነው ደግሞ በሀሳብ ነው:: ጠመንጃ ሀገር አያድንም:: ጦርነት ሰላም አያመጣም:: ቂም በቀል የፍቅርን ደመና ይጋርዳሉ እንጂ ፍቅር አያዘንቡም:: ጥላቻ ታሪክ ይሸነቁራል እንጂ አብሮነትን አይጥፍም:: በጦርነት ሰላም የሚመጣ ቢሆን ኖሮ በዓለም ላይ በሰላሟ ቀዳሚዋን ሀገር በፈጠርን ነበር:: ጥላቻ፣ ቂም፣ በቀል፣ ዘረኝነት፣ የታሪክ ዝንፈት፣ የትርክት ጥመት የስልጣኔ መብቀያ ቢሆኑ ኖሮ ማን በደረሰብን:: ሁሉም ግን አክሳሪዎች ናቸው..እንሆ ከስረንም ባዷችንን ነን::

እንደ ሰላም ያሉ አንዳንድ ነገሮች ያለ አጋዥና ያለደጋፊ ብቻቸውን የተፈጠሩ ናቸው:: ብቻቸውን ይፈጠሩ እንጂ ሰው የሚለውን ታላቅ ፍጡር በክብርና በልዕልና ለማኖር ከማንም የተሻሉ የመኖር ዋስትና መሆን የሚችሉ ናቸው:: በሰላም ስለ ሰላም ጽንሰ ሀሳብም የአብሮነት ምሰሶ ሆኖ ሀገር የሚያቆም ነው:: ሰላም መር በሆነ የውይይት ማዕቀፍ ውስጥ ማለፍ የነበሩትን ከመሻርና ያሉትን ሰላማዊ ከማድረግ ረገድ ይሄ ነው የማይባል ሚና አለው::

ሀገር የእኔ የአንተ የሁላችን ቀለም ናት:: የደመቀችው ተሰባጥረን፣ ተዋህደን ስለተቀየጥን ነው:: ብዙ አስተሳሰቦች፣ ብዙ አመለካከቶች፣ ብዙ ባህሎች፣ ብዙ ስርዐቶች እንዲሁም ብዙ ልማዶች ለአንድ ማህበረሰብ የቅያሜ ሳይሆኑ የትቅቅፍ አንቀልባዎች ናቸው:: ውበታችን ከእኛ እንደተፈጠረ ሁሉ የችግሮቻችን መፍትሄም ከእኛው የሚመነጩ ናቸው:: ስለሆነም በሰላም ስለሰላም እንትጋ::

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You