” በአሁኑ ወቅት በክልሉ ምንም አይነት የፀጥታ ችግር የለም “አቶ አሰም የሱፍ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሠላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ፣ የፀጥታ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ

እንደ ሌሎች ክልሎች ሁሉ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ችግር ገጥሞት ነበር። እንደ ማንኛውም አካባቢ በዚህ አካባቢም ሠላም ርቆ፣ ጠብ ነግሶ ቆይቷል። እንደ አገራችን ሌላኛው ስፍራ ደም ፈሷል፤ ውድ የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ጠፍቷል። በስሩ ሰባት ወረዳዎች ያሉት መተከል ዞን በፌደራል ማዘዣ ማዕከል ትዕዛዝ ሥር እንዲተዳደር እስከ መወሰን ድረስ የዘለቀ ችግር የተፈጠረበት ክልል እንደ ነበር የሚረሳ አይደለም።

በወቅቱ፣ በተለይም በ2012 ዓ•ም አካባቢ ወልቂጤ፣ ሐዋሳ፣ አሶሳ እና ሌሎችም ቦታዎች ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ዜጎች በሌሎች ዜጎች ላይ ሰንዝረዋል። በጉጂ እና ጌዲኦ ዞኖች፣ በቄለም ወለጋ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ኢትዮ-ሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል፤ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ ውድ ሕይወታቸውንም አጥተዋል። እነዚህም ግጭቶች በተመለከተ በርካታ ዜናዎችና መረጃዎች በስፋት ይተላለፉ ነበር፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መሀመድ ሀምደኒል፣ በቀን 05/2012 ዓ/ም ከቀኑ 5፡00 አካባቢ ከአሶሳ ወደ ካማሼ በመሄድ ላያ ያለ የግል መኪና ማንነታቸው ያልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች ከካማሺ መገንጠያ፣ ማቃ ቢላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መኪናውን በማስቆም በከፈቱት ተኩስ የአንድ የፖሊስ አመራር ሕይወት ማለፉን አስመልክተው አስተላልፈውት በነበረው የውግዘት መልእክት “በአካባቢዉው የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኃይሎች ሕዝቡ በአሁኑ ሰዓት መረጋጋቱን በማየትና ሠላሙን ለማደፍረስ ታስቦና ሆን ተብሎ የተደረገ እንጂ ተግባሩ ከካማሺ ሕዝብ ጋር ምንም የሚያገናኘው” ነገር እንደ ሌለ፤ ተግባሩ የፀረሠላም ኃይሎች እንጂ ሕዝቡን እንደማይወክል የገለፁትን መለስ ብሎ በማስታወስ፤ እንዲሁም በክልሉ (ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል) በመንቀሳቀስና ሕዝቡን በመረዳት የክልሉን ሕዝብ ሲረብሹትና ሰላሙን ሲነሱት የነበሩት ከጉያው የወጡ ኃይሎች መሆናቸውን ያለ ማመንታት መናገር ይቻላል።

በጉባና በዳንጉር ወረዳዎች ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር፤ የማኅበረሰቡን አብሮ የመኖር እሴት ለመሸርሸርና እርስ በርሱ ለማጫረስ ወዘተረፈ የተሄደበትን ርቀት ላስታወሰ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራርና ሕዝብ ምን ምን አይነት ችግሮችን ፈንቅሎ እዚህ እንደ ደረሰ መገንዘብ አያዳግትም።

ዛሬ እንደምናየው ከመሆኑ በፊት በቤኒሻንጉል ክልል ፀጥታ እንደ ሰማይ ርቆ፤ ሰላም እንደ ንፋስ ብን ብሎ ጠፍቶ ዜጎች ላልጠበቁት ሁለንተናዊ ቀውስ ተዳርገው ነበር። ለልማት የታጨው በጀት ለሰላም ማስከበር፤ ለምርትና ምርታማነት የታሰበው ጊዜ የአካባቢ ሰላምና ፀጥታ፤ እንዲሁም ደህንነትን ማስከበር ላይ ይውል ዘንድ ግድ ብሎ ነበር። ይህ ብቻም አይደለም፣ መስከረም 2013 ዓ•ም አካባቢ የክልሉ መረበሽ ጫፍ ከመድረሱ የተነሳ የአጎራባች ክልሎች (ከአማራ ክልል በተጨማሪ የጋምቤላ፣ የሲዳማ እንዲሁም የደቡብ ክልል ልዩ ኃይሎች) ወደ አካባቢው በማቅናትና በክልሉ ተቋቁሞ በነበረው ኮማንድ ፖስት ስር በመሆን ሠላም ማስከበር ሥራ ሲሰሩ መቆየታቸው የሚዘነጋ አይደለም።

ዛሬ የምንመለከተው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ትናንት ነገሮችን ልብ ማለት ባልቻሉ ልጆቹ፤ ለሶስተኛ ወገን ሀሳብ በተገዙ የራሱ ወገኖች ሲተራመስ ነበር። ምስኪኑ የክልሉ ሕዝብ በማያውቀው ጉዳይ ከመጎዳቱም ባለፈ እንደ ጎጂ ተደርጎ እዚህ መሀል ከተማ፣ መዲናዋ ድረስ ሲወራበት ነበር። ሕዝቡን የማይወክሉ ሕዝቡን የማይወክል ስራን በመስራታቸው ምክንያት የክልሉ ሕዝብ በሌላው ላይ ጦር እንደ መዘዘ ተደርጎ እስኪወራ ድረስ በክልሉ ሠላም አልነበረም።

ዛሬስ ምን ለውጥ አለ ስንል ከክልሉ ሠላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ የፀጥታ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰም የሱፍ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ።

 

 አዲስ ዘመን :- በቅድሚያ እርሶ የሚመሩትን ዘርፍ ዐቢይ ተግባር ቢገልፁልን።

አቶ አሰም የሱፍ:- እኔ የምመራው ዘርፍ የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ነው፡፡ ዘርፉ እንደ ተቋምም ሆነ ሠላምና ፀጥታ ዘርፍ ተልእኮው በክልሉ ዘላቂ ሠላም መገንባትና የማኅበረሰቡን ደህንነተ በተሟላ መልኩ ማስጠበቅ ነው።

አዲስ ዘመን:- ተልእኮው ይህ ከሆነ ይህንን ተልእኮውን በአግባቡ ሲወጣ ቆይቷል ይላሉ?

አቶ አሰም የሱፍ:- አዎ፣ ሲወጣ ቆይቷል፤ እየተወጣም ነው። ይሁን እንጂ መሰናክሎች የሉም ማለት አይደለም፤ እንደ ማንኛውም የአገራችን ክፍሎች እኛም ጋ የጸጥታ ችግሮች ተከስተው ነበር። በተለይ ያለፉት አራት ዓመታት ብዙ የተፈተንበት፤ ወደ ድርድርም የገባንበትና ውጤትም ያስመዘገብንበት ነው።

በተለይ ይህ ክልል ራሱ የለውጡ አካል ስለነበር፤ ለውጡን ተከትሎ ያኮረፉ ኃይሎች ጠመንጃ ወደ መተኮስ ነው የገቡት። ለማደናቀፍ ጥረት መደረጉ ስለማይቀር፣ ይህ ይጠበቅ ነበር። እንደ ሌሎች አካባቢዎች ሁሉ እዚህ እኛ ክልልም የሆነው ይኸው ነው። በተለይ በሶስት ዞኖችና በአንድ ልዩ ወረዳ ውስጥ ችግሮች ተከስተው ነበር። በሁለት ዞኖች ከፍተኛ ውድመትና ሰብአዊ ቀውስ ደርሷል። መፈናቀልም ነበር።

ይህ ያኮረፈ ኃይል፣ ለውጡን ለማደናቀፍ በማሰብ በተነሱ ኃይሎች በተቆሰቆሰ እሳት ምክንያት በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል። ንብረቶች ወድመዋል። የሰው ልጅ ሕይወት ጠፍቷል። ባለፉት ስድስት የለውጥ (በተለይም ከወደዚህ ያሉት አራት) ዓመታት ከፍተኛ ቀውስ ነበር። ከአሶሳ ዞን ውጪ በሁሉም ዞኖች ማለት ይቻላል ያኮረፈው ቡድን፤ የለውጡ ተቃዋሚ ኃይል የፈጠራቸው የፀጥታ ችግሮች ነበሩ።

ከላይ እንዳልኩህ፣ ያኮረፈው ቡድን፣ ጥቅሜ ቀረብኝ ያለው ክፍል፣ ፅንፈኛው በፈጠራቸው ግጭቶች በሚያሳዝን ሁኔታ የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት መውደም ተከስቷል። መተከልና ካማሺ ብቻ ከ400ሺህ በላይ (ከአጠቃላይ ነዋሪው ሕዝብ ከ70% በላይ) ሕዝብ የተፈናቀለ ሲሆን፣ ወደ ሱዳን እስከ መሰደድ ድረስ የሄዱ አሉ። በማኦ-ኮሞ፣ አሶሳ ዙሪያም እንደዛው የሕዝብ መፈናቀል ነበር። ማክሸፍ ተቻለ እንጂ፣ ከሶስተኛ ወገን ተልእኮ ወስደው በነበሩ አካላት የተደራጀ ስራን በመስራት ክልሉን የማፍረስ ስራ ነበር ሲሰራ የነበረው። በተለይ በቤኒን ሲንቀሳቀስ የነበረው ቡድን ከሸኔና ፅንፈኛው የአማራ ኃይል ድጋፍ ይደረግለት ነበር። አሁን እነዚህን  ሁሉ፤ ሳያውቁት ወደ ወገናቸው ሲተኩሱ የነበሩትን ሁሉ ወደየ አካባቢያቸው መመለስ፤ ወደ ልማት ስራዎች ማሰማራት ተችሏል። የከፍተኛ አመራሮች ቡድንና የፀጥታ አካላት ባደረጓቸው የማወያየት ተግባራትም በሕብረተሰቡ መካከል መተማመን ተፈጥሯል።

ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉም ነበሩ። እነሱም ወደ እዚህ የመጡበት ሁኔታ ነበር። ባንባሲ ወረዳ ላይ መጠለያ ተደርጎ ሰፍረው ነበር። በከፊል እየተመለሱ ነው። ከሱዳን፣ ከቡሩንዲ – – – ሁሉ ተፈናቅለው ወደዚህ በመምጣት ከ6 ዓመት በላይ የኖሩ ነበሩ። አሁን ሄደዋል። አሁንም ያሉ ሱዳናውያን አሉ። ይህ በራሱ ለክልላችን ድርብ ችግር ሆኖ ነው የቆየው። ቢሆንም ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን እንደ አገርም፣ እንደ ክልል አመራርም ኃላፊነታችንንና የሚጠበቅብንን እየተወጣን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን :- በእናንተ ግምገማ፣ ይህ ቡድን አሁን በምን አይነት ደረጃ ላይ ነው ያለው?

አቶ አሰም የሱፍ:- በቅድሚያ ያኮረፈ ቡድን፣ ከዚህ ክልልም፣ ከዚህ ክልል ውጪም ተደራጅቶ ይህንን ክልል ሊያፈርስ እንደ ፈለገ ተደረሰበት። ይህ የተደራጀ፣ አኩራፊ ቡድንም ከሁለተኛና ሶስተኛ ወገን ክልሉን የማፍረስ ተልእኮ የተሰጠው፤ ትእዛዝ የተቀበለ መሆኑም ተደረሰበት። በጉዳዩ ላይ ሙሉ ግንዛቤ ተያዘ። በተደረሰበት ግንዛቤ ልክም ክልሉ መፍረስ እንደ ሌለበት፤ ያኮረፈው ኃይልም ያልተገነዘበው ነገር እንዳለ መረዳት እንዳለበት፤ ወደ ወገኑ ለመተኮስ ጫካ የገባው ቡድንም በማያውቀው ጉዳይ ወገኑ ላይ እየተኮሰ፤ ወንድሙን እየገደለ እንደሆነ እንዲያውቀው ማድረግ አስፈላጊ ስለ መሆኑ መግባበት ላይ ተደረሰ። በዚሁ መሰረትም ወደ መነጋገሩ ስራ ተገባ። በአራቱም አቅጣጫ ድርድሩ ተጀመረ። ከክልሉ ውጪ፤ ውጭ አገር (ሱዳን) ከሄዱት ጋር ሳይቀር ለውይይት ተጋበዙ። ከአጎራባች ክልሎች ጋር በጋራ መስራቱም ተጠናክሮ ቀጠለ።

በአመራሩ በኩል፣ ከፌደራል ጀምሮ ለሰላም ሲባል ከፍተኛ መስዋእትነት ተከፍሎ በድርድር ወደ ስምምነት በመምጣት ወደ ሰላም ተመልሰዋል። ፕሬዚዳንቱ ሳይቀሩ፣ አመራሩ ኃላፊነት ወስዶ፣ ጫካ ድረስ በመሄድና በመነጋገር፤ በማመንና በማሳመን፤ የመተማመን ስራዎች ተሰርተው ሰላም ወርዷል። ከነ መሳሪያቸው ነው የተመለሱት። በሰላምም መሳሪያቸውን አስረክበዋል፤ ተረክበናቸዋል።

አሁን ወደ ልማት ገብተዋል። በተለያዩ ዘርፎችም ተሰማርተው፤ ተደራጅተው ወደ ስራ በመግባት ውጤታማ እየሆኑ ነው። እርሻ፣ ወርቅ፣ ሸቀጣሸቀጥ ንግድ ወዘተ ከተሰማሩባቸው መስኮች መካከል ናቸው። እስከ ባለፈው ሚያዝያ ወር ብቻ በክልሉ የሰላም ጥሪን ተቀብለው የገቡ ከስምንት ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች በተለያዩ ሥራዎች ተሰማርተው ይገኛሉ።

ወደ ስራ የተሰማሩት ዝም ብለው አይደለም። ክልሉ ባመቻቸው፣ ባዘጋጀውና በፈጠረው እድል ወደ መጠቀም ከመሄዳቸው አስቀድሞ ተሀድሶ እንዲወስዱ ተደርገዋል። በተሀድሶው መሰረትም ወደ ነበሩበት የስነልቦና ሁኔታ እንዲመለሱ፤ ከማህበረሰቡም ጋር በቀላሉ እንዲዋሀዱና እንዲደራጁ ተደርጓል።

እነዚህን ወገኖች ለመጥቀም ሲባል እንደ ክልልና ሕዝብ ብዙ ዋጋ ተከፍሏል። ከሌሎች ልማቶች በመቀነስ 46 ትራክተሮች፣ 26 የወርቅ ማሽኖች፣ ባጃጅና ሌሎችም ተገዝቶላቸው ነው ወደ ስራ የገቡት። ይህ ሁሉ የተደረገው በእቅድ ከተያዙት የልማት ስራዎች ተቀንሶ ነው። በአጠቃላይ ከልማት ላይ ተቀንሶ ከ288 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል።

አዲስ ዘመን :- አሁን ክልሉ ሠላም ነው ማለት ይቻላል?

አቶ አሰም የሱፍ:– አዎ፣ አንፃራዊ ሠላም አለ። በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ በክልላችን በሠላም ወጥቶ በሠላም መግባት የተቻለባቸው ዓመታት ናቸው። በአሁኑ ወቅት በክልሉ ምንም አይነት የፀጥታ ችግር የለም።

አዲስ ዘመን :- አንፃራዊ ሠላም የሚለው እንዴት ይገለፃል?

አቶ አሰም የሱፍ:- አንፃራዊ ሠላም አለ ሲባል ሙሉ ለሙሉ ስጋት የለም ማለት አይደለም። ሁኔታዎችን በቅርብ መከታተል ያስፈልጋል። አንፃራዊ ሠላም አለ ሲባል ሙሉ ለሙሉ ወደ ድሮው፣ ወደ ነበረበት ተመልሷል ማለትም አይደለም። ክልሉና የክልሉ ሕዝብ ከነበረበት ሁከት፣ ረብሻና የፀጥታ ስጋት ወጥቶ ወደ ልማት የተመለሰበት ሁኔታ ነው ያለው ለማለት ነው። ሁኔታዎችን ወደ ሠላም ለማምጣት ሲጀመርም ቅድሚያ ተሰጥቶ የነበረው ሠላሙን ላጣው፤ ለተፈናቀለው ማኅበረሰብ ቅድሚያ በመስጠት፤ የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው በመመለስ ነበር። ከአጎራባች (ለምሳሌ ከኦሮሚያ) የመጡ ተፈናቃዮችንም ወደ መጠለያ በማስገባትና አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንዲያገኙ በማድረግ ነው። እነዚህ ወገኖች ወደ ክልልና አካባቢያቸው እንዲመለሱም እየተደረገ ይገኛል።

አሁን በክልሉ የትም ቦታ መንቀሳቀስ ይቻላል። ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውና የፀጥታ ስጋት የነበረባቸው አካባቢዎች ሳይቀሩ ወደ ስራ ገብተዋል፤ አካባቢዎቹ ፀጥታ ሰፍኖባቸዋል። የመንቀሳቀስ ችግር የለም። የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማስፈርና በአካባቢው የተሰማሩ ባለሃብቶችን ዘላቂ ደህንነት በማስጠበቅ አካባቢውን የልማት ኮሪደር የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው። ያ ማለት ግን አሁን ምንም ችግር የለም ማለት አይደለም። ችግሮች አሉ።

አዲስ ዘመን:- ችግሮች ካሉ ምን ምን እንደ ሆኑ መግለፅ ከተቻለ ቢገልፁልን?

አቶ አሰም የሱፍ:- እንደሚታወቀው እንደ አገርም ሆነ እንደ ክልል ሠላም ለማስፈን የአንድ አካባቢ ሠላም መሆን ብቻውን በቂ አይደለም። የአንድ አገር ሠላም መሆን የሚረጋገጠው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ሠላም ሲሰፍን ነው። ጉዳዩን ወደ ክልሎችም ስናመጣው ያው ነው። ማለትም ሁሉም ክልሎች ሠላም ካልሆኑ አንድ ክልል ብቻውን ሠላም መሆን አይችልም። ምን ማለት ነው፣ የእኛ ክልል የውስጥ ሠላም መኖር ብቻ ክልላችንን ሠላም አያደርገውም። ለእኛ የተሟላ ሠላም የአጎራባች ክልሎች ሁሉ ሠላም መሆን ያስፈልጋል። አጎራባቻችን አማራ ክልል ሠላም ከሌለ እኛ ጋ ሠላም አለ ማለት አይቻልም። አዋሳኛችን ኦሮሚያ ክልል ሠላም ከሌለ የእኛ ሠላም መሆን ብቻ የተሟላ ሠላም እንዲኖረን ሊያደርገን አይችልም። ለዚህ ነው ችግር አለ የምንለው። እንደ ልብ ወደ አጎራባች፣ አዋሳኝ ክልሎች ገብተን መውጣት አልቻልንም፤ አንችልም። ዳንጉር አካባቢ ችግር አለ፤ ፅንፈኛው እየገባ ይወጣል። በመተከልም እንዲሁ እየገባ የሚወጣበት ሁኔታ አለ።

ወደ አማራ፤ ወደ ኦሮሚያ ክልል እንደ ፈለጉ መሄድ አይቻልም። ይህ፣ የክልላችንን ሕዝብ እንቅስቃሴ የሚገድብ ፀረ-ሠላም ተግባር ደግሞ ከሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ ሸቀጦችን ከማምጣት ጀምሮ ምን ያህል ችግር እንደፈጠረና ሕዝቡን ለኑሮ ውድነት እየዳረገ መሆኑ እየታየ ነው።

አንድ ሕዝብ የገበያ መረጋጋት፣ ሸቀጦችን የመገብየት፣ የማስገባት፣ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በነፃነት የመንቀሳቀስ ወዘተ መብቱ ከተገደበ ያ ማሕበረሰብ የተሟላ ነፃነት፤ የተሟላ ሠላም አለው ማለት አይቻልም። የተሟላ ነፃነት፤ የተሟላ ሠላም አለ ማለት የሚቻለው ከነጎረቤቶቻችን ሠላም ስናገኝ፤ ሠላም ሲኖር፤ በሠላም ወደ ጎረቤት ክልሎች ሄደን ስንመጣ ነው። ያ ከሌለ እንደ ሰላም እጦት ነው የሚቆጠረው። ያ ሕዝብ የሚበላው ካጣ አሁንም ችግር ነው ማለት ነው።

አዲስ ዘመን:- ከችግሮች አኳያ አሁን ያለውን ሁኔታ ባጭሩ መግለፅ ይቻላል?

አቶ አሰም የሱፍ:- ይቻላል። እንዳልኩህ፣ አሁን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ችግሮች አሉ። አጎራባች ክልሎች አካባቢ ችግሮች አሉ። በኦሮሚያ ሸኔ እየተንቀሳቀሰ ነው። እየገባ የመውጣት ሁኔታ አለ። አማራ አካባቢም ችግርች አሉ። ፅንፈኛው ይንቀሳቀሳል። ሕብረተሰቡን እያጠቁ የሚመስሉ ሁኔታዎች አሉ። አሁንም ኢመደበኛ አደረጃጀቶች አሉ። እርግጥ ነው ቅድመ መከላከል ስራ እየተሰራ ነው። ግን በቂ አይደለም። ቤንኒሻንጉል ጉሙዝ እንደ ክልል ነፃና ሠላማዊ ይሁን እንጂ ወደ አጎራባች ክልልች በነፃነት መመላለስ አይችልም። ወደ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች መንቀሳቀስ ከባድ ብቻ ሳይሆን አይቻልም። በጋራ መስራትን የሚጠይቁ ስራዎች አሉ። እንደ አገር የፌደራል መንግሥትን ስራዎች የሚፈልጉ ስራዎች አሉ። የመከላከያን ስራ የሚፈልጉ ስራዎች አሉ። የኃይል ርምጃ የሚፈልጉ ስራዎች አሉ። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚፈልጉ ስራዎች አሉ።

አዲስ ዘመን :- ከክልሎች፣ በተለይም ከአጎራባች ክልሎች ጋር በሠላም ዙሪያ አብራችሁ ከመስራት አኳያ ያላችሁን ግንኙነት ቢገልፁልን ?

አቶ አሰም የሱፍ:– ከአማራ፣ ከኦሮሚያ ጋር ግንኙነቶች አሉን። ያም አንፃራዊው ሠላም እንዲመጣ አግዟል። ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በሠላም ሚኒስቴር የሚመራ፣ በየሶስት ወሩ የሚካሄድ ፎረም አለን። የጋራ ስብሰባዎችን፤ ውይይቶችን እናደርጋለን። በዛ ፎረም ላይ እየተገናኘን እንመክራለን። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ስራዎችን የመስራት ነገርም አለ። ይህ ሁሉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል።

አዲስ ዘመን :- እንደ አጠቃላይ ምን ቢደረግ ጥተሩ ነው ይላሉ?

አቶ አሰም የሱፍ:– አሁን ከዛ ብንወጣም ለአራት ዓመት በከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው የቆየነው። ሰላም ማጣት ማለት ምን ማለት እንደሆነ እናውቀዋለን። ብዙ ነገሮች ሊደረጉ ይችላሉ። አንዱ ጋ ሠላም ከሌለ ሌላው ጋ ሠላም ሊኖር እንደማይችል በመገንዘብ አጎራባች ክልሎች አብረው፤ በጋራ ሊሰሩ ይገባል። የአንዱ ክልል ሠላም አለመሆን ለሌላው ክልልም ሠላም አለመሆን ምክንያት ነውና በአንዱ ክልል ችግር ሲፈጠር ያንን ችግር ለመፍታት ተናቦ፣ ተግባብቶ፣ ተባብሮ፣ መረጃ ተለዋውጦ በጋራ መስራት ይገባል። እኔ ጋ ችግር የለም ብሎ መቀመጥ ምንም ፋይዳ የለውም። አያስኬድም። እንደ ብልፅግናም ያለው አቋም ይሄ ነው፤ የጋራ ሠላም ላይ መስራት ነው የሚገባው።

አዲስ ዘመን :- የፌዴራል መንግስት የነበረውን እገዛ እንዴት ይገልጹታል ?

አቶ አሰም የሱፍ:- እርግጥ ነው። በክልላችን ሰላም ማስፈን የቻልነው በአገር መከላከያ ኃይል ነው። ከመከላከያ ጋር እጅና ጓንት ሆነን በመስራት ነው። የፌደራል መንግስትን አቅጣጫ ተከትለን በመስራታችን ነው ለውጤት የበቃነው። ነገር ግን፣ አጎራባች ክልሎች ጋ ችግር ሲኖር ቤኒሻንጉል አማራ ክልል ሄዶ ስርዓት ማስያዝ አይችልም። ኦሮሚያ ክልል ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገብቶ ሠላም ሊያመጣ አይችልም። በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ውስጥ ችግሮችን ሊፈታ የሚችለው፤ ጣልቃ ሊገባ የሚችሉት ፌደራል ፖሊስና እና መከላከያ ሰራዊት ናቸው። ይህ ሊሆን፣ ሊደረግ ይገባል። በአጎራባች ክልሎች አካባቢ አሁንም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አሉ።

እነዚህን በኃይል ማስቆም ይገባል። ኃይል ያስፈልጋል። የኃይል ስራ የሚፈልጉ ጉዳዮች አሉ። የኃይል ርምጃን የግድ የሚሉ እንቅስቃሴዎች አሉ። ይህንን ማድረግ የሚችለው፤ ሕገመንግሥታዊ መብትም ያለው ደግሞ መከላከያ ነው።

አዲስ ዘመን :- በመጨረሻም ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ አሰም የሱፍ:- የተገኘውን አንፃራዊ ሠላም ለማስቀጠልም ሆነ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ተቋማዊ ስራዎች በሚገባ መሰራት አለባቸው። ፖሊስ፣ መከላከያ እና ሌሎች የሚመለከታቸው ሁሉ ተቋማዊ በሆነ መልኩ መስራት አለባቸው። የሕዝብ አደረጃጀቶችን (ሴቶች፣ ወጣቶች ወዘተ) ማጠናከር ያስፈልጋል። ማሕበረሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ ማድረግ ያስፈልጋል (ኮሚዩኒቲ ፖሊሲንግ ሊጠናከር ይገባል)።

የተገኘውን አንፃራዊ ሠላም ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ የአካባቢው ማሕበረሰብ ከዚህ በፊት ሲያደርግ የነበረውን ትብብር የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል። ባለፉት አራት ዓመታት በፀጥታ ችግር ውስጥ የቆየው የክልላችን ሕዝብ በጋራ ባደረገው ጥረት ወደ አሁኑ አንፃራዊ ሠላም መምጣት ችሏል። ይህ አሁንም የበለጠ ተጠናክሮና ሕዝባዊ መሰረት ይዞ መቀጠል አለበት።

ለሁሉም ጦርነት አክሳሪ እንጂ አትራፊ አለመሆኑ፤ ለማንም እንደማይጠቅም፤ ሁሉንም ወገን እንደሚጎዳ፤ አገርና ሕዝብን ወደ ኋላ እንደሚያስቀር መንገር፤ ትምህርት መስጠት አለበት። ሁሉም ይህንን እንዲረዳ መሰራት ያለበት ሁሉ መሰራት አለበት። ትምህርት ያስፈልጋል። ውይይት ያስፈልጋል። የወጣቶች ክበባት መጠናከር አለባቸው። የሠላም እናቶችን ማሳተፍ ያስፈልጋል። የሠላም እሴቶችን መገንባት ያስፈልጋል። በክልሎች የአመራር ለአመራር ግንኙነቶች መጠናከር አለባቸው። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ መስራት ያስፈልጋል። መከላከያና የፀጥታ ኃይሉ በጋራ እየሰሩት ያለው የሠላም ማስከበር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። እነዚህና ሌሎችም በሚገባ ከተሰራባቸው ዘላቂ ሠላም ይኖራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

አዲስ ዘመን፡- ስለ ሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።

አቶ አሰም የሱፍ፡- እኔም እዚህ ድረስ መጥታችሁ ለአስተያየት ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You