የተሻለ የፈተና ውጤት የሚመዘገበው፣  ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓት ሲኖር ነው!

የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ብሔራዊ ፈተና ከትግራይ ክልል ውጭ ባሉ አካባቢዎች ከሐምሌ ሦስት እስከ ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲሁም በትግራይ ክልል ደግሞ ከሐምሌ ሁለት እስከ ሐምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ይፋ አድርጓል:: የዘንድሮው ፈተና እንደቀድሞው በወረቀት ብቻ ሳይሆን በኦንላይንም እንደሚሰጥም ተገልጿል::

ባለፉት ጥቂት ዓመታት፣ በተለይም በ2014 ዓ.ም እና በ2015 ዓ.ም፣ የተመዘገበው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ውጤት እጅግ አስደንጋጭ እንደነበር ይታወሳል:: የትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው የፈተናው ውጤት መረጃ መሠረት፣ በ2014 ዓ.ም ፈተናውን ከወሰዱ 899ሺ 520 ተማሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ ውጤት (ከ350 በላይ) ማስመዝገብ የቻሉት 29ሺ 909 (3.3%) እንዲሁም በ2015 ዓ.ም ደግሞ 845 ሺህ ተማሪዎች ፈተናውን ወስደው ከግማሽ በላይ ውጤት ያመጡት ተማሪዎች 27 ሺ 267 (3.2%) ብቻ መሆናቸው ይታወሳል::

ውጤቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ብዙ ዓይነት አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ነበር:: ከአስተያየቶቹ መካከል አንዱ ከግማሽ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ የትምህርት ጥራት አለመኖሩን የሚያመለክት እንደሆነ የሚገልፀው ሃሳብ ነበር:: ለትምህርት ጥራት መጓደሉም መንስዔዎች ናቸው የተባሉ ብዙ ምክንያቶችም ተጠቅሰዋል:: የሆነው ሆኖ፣ የፈተናው ውጤት አስደንጋጭና አስገራሚ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም:: ከአጠቃላይ ተፈታኞች መካከል አራት በመቶ ያህሉ እንኳ ከግማሽ በላይ ውጤት አለማስመዝገባቸው ‹‹ሀገር ተረካቢ ነው›› ስለሚባለው ትውልድ በእጅጉ እንድንጨነቅ ያስገድደናል::

የፈተናው ውጤት በምን ዓይነት የትምህርት ሁኔታ ውስጥ እያለፍን እንደምንገኝ በግልፅ አሳይቷል:: አራት ከመቶ ተፈታኞች እንኳ ከግማሽ በላይ ውጤት አለማስመዝገባቸው ትምህርትን እንዴት እየቀለድንበት እንደሆነ ጥሩ ማሳያ ነው:: ይህ ደግሞ የሀገር ግንባታ ዋነኛ መሠረት የሆነው ዓምድና የሀገሪቱ ሕልውና እጅግ አስደንጋጭ አደጋ ውስጥ እንደገባ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው:: ታዲያ ይህ የሆነው በእርግማን ወይም በክፉ ምኞት ሳይሆን በትምህርት ጥራት ጉድለት ምክንያት ነው:: ጥራት በጎደለው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለፈ ተማሪ ጥሩ ውጤት ሊያስመዘግብ አይችልም::

የዘንድሮ ፈተና ምን ዓይነት ውጤት እንደሚመዘገብበት ወደፊት የምናየው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ቢያንስ ካለፉት ሁለት ዓመታት የባሰ ውጤት እንዳይመዘገብ መስጋት ሞኝ ወይም ሟርተኛ አያስብልም:: ዘንድሮ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ በመንግሥትና በሌሎች ባለድርሻ አካላት የተከናወኑ ተግባራትን በሐቀኝነት መገምገም ይገባል::

ተፈታኞች ወደ ፈተና ማዕከላት ከሚገቡበት ቀን ጀምሮ የሚደረግላቸው ጥበቃና ድጋፍ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ግብዓት ነው:: የዘንድሮው ፈተና እንደቀድሞው በወረቀት ብቻ ሳይሆን በኦንላይንም ጭምር የሚሰጥ በመሆኑ፣ ተፈታኞች ከቴክኖሎጂው ጋር ያላቸው ትውውቅና ያዳበሩት ቅርበት ከፈተናው ውጤት ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት አለው::

የኢትዮጵያ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓት ለትምህርት ዘርፍ መሻሻልና የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት አዎንታዊ አስተዋፅዖዎችን እንዳበረከተ ባይካድም፣ ዓይነተ ብዙና ውስብስብ ችግሮችም አሉበት:: የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱ በንድፈ ሀሳብ እንጂ የተግባር ክህሎትና ፈጠራ ላይ ያተኮረ አይደለም።

የምዘና ሥርዓቱም ለተግባራዊ እውቀት ትኩረት አልሰጠም። ሥራ ፈላጊ እንጂ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ እየተፈጠረ አይደለም። የምርምርና የቴክኖሎጂ ሥራው ጎልብቶ ኢኮኖሚውን በሚፈልገው መጠን ሲያግዝም አይስተዋልም። ከትምህርትና ሥልጠናው እውቀት፣ ክህሎትና የሥራ ፈጣሪነት አመለካከት በበቂ ሁኔታ ይዞ ከመገኘት ይልቅ ትውልዱ ዲግሪና ዲፕሎማ (ወረቀት) አምላኪ ሆኗል። ይህም የትምህርት ዘርፉን ጉዞ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል::

የአንድ ሀገር የትምህርት ሥርዓት መበላሸት የሀገሪቱ ሕልውና አደጋ ውስጥ እንደገባ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል:: ሠላም የሰፈነባት፣ ማኅበራዊ መረጋጋት ያለባት፣ ምጣኔ ሀብቷ ያደገና ፖለቲካዋ የሰከነ ሀገር እውን ማድረግ የሚቻለው ጥራት ባለው የትምህርት ሥርዓት የተገነባ ትውልድ ማፍራት ሲቻል ነው::

ጥራት በሌለውና በወደቀ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለፈ ትውልድ ለሀገር ሕልውና ትልቅ አደጋ ይሆናል:: ለዚህም ነው ‹‹አንድን ሀገር ለማፍረስ ጦር ማዝመት ሳያስፈልግ፣ የሀገሪቱን የትምህርት ሥርዓት ማበላሸት በቂ ነው›› የሚባለውን ሃሳብ በተደጋጋሚ የምንሰማው::

በራሳቸው የሚተማመኑ፣ በምክንያታዊ ትንተና የሚያምኑ፣ በሙያቸው ብቃት ያላቸው፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ አዳዲስ ግኝቶችን አፍላቂዎች፣ ጠንካራ የሥነ ምግባርና ግብረገባዊ እሴቶችን የተላበሱ፣ ለሕግ ዘብ የቆሙ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ ሆነው አጠቃላይ ሰብዕናቸው የተገነባ ዜጎችን ማፍራት የሚቻለው ጥራት ባለው የትምህርት ሥርዓት ነው።

አንዲት ሀገር ሁለንተናዊ እድገትን በማምጣት የሕዝቦቿን ኑሮ ማሳደግ የምትችለው በሚኖራት የሰው ኃይል እምቅ አቅም ነው:: የሰው ኃይል መገንቢያው ዋነኛው መሣሪያ ደግሞ ትምህርት ነው:: አስተማማኝና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ብቸኛው መንገድ ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓትን መዘርጋት ነው:: ‹‹ዋናው ሽፋን/ብዛት ነው፤ የጥራቱ ጉዳይ ቀስ ብሎ ይታሰብበታል›› የተባለው አካሄድ ለኢትዮጵያ ምን እንዳተረፈላት አይተናል:: የትምህርት ሥርዓቱ ብልሽት ሀገሪቱን ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፤ እያስከፈላትም ይገኛል::

የትምህርት ጥራትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ተማሪዎችን ያማከለ ዘመናዊና አሳታፊ የመማር ማስተማር ሂደት መከተል፤ የመምህራን ጥራትና ተነሳሽነት ማጎልበት፤ ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደትን መከተል፤ ተማሪዎችን ማነቃቃት፤ ጠንካራ የትምህርት ቤት አመራርን ማብቃት፤ ምቹና ጤናማ የትምህርት አካባቢ መፍጠር፤ የማስተማሪያ ግብዓቶች ማሟላት እንዲሁም የተማሪዎች ሥነ ምግባርን ማሳደግ ይገባል።

የተማሪዎች ትምህርታቸውን በሚገባ የመከታተል፤ የመምህራን በጥራት የማስተማር፤ የትምህርት አመራር ስትራቴጂካዊ አመራር የመስጠት እንዲሁም የወላጆች ልጆቻቸውን በንቃት የመከታተልና የመደገፍ ተግባራት በቅንጅት ሊከናወኑ ይገባል። በትምህርትና ሥልጠና በቂ የሰው ኃይል ለማፍራት ባለፉት ዓመታት የትምህርትን ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነት፣ አግባብነትና ጥራትን ለማጎልበት የተሠሩ ሥራዎች ያስገኙትን ውጤት መገምገምም ይገባል::

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ በሥነ ምግባር፣ በመልካም እሴትና በብቃት የታነጸ ዜጋን ለማፍራት በሚያስችል መንገድ የተቀረፀ፣ የሀገሪቱን ዕድገትና አንድነት የሚያስቀጥል እንዲሁ ስራ ጠባቂ ከመሆን ይልቅ ለሥራ ፈጣሪነትና ለሀገር በቀል እውቀቶች ተገቢውን ትኩረት የሰጠ መሆኑን በሚገባ መፈተሽና ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የተሻለ የፈተና ውጤት የሚመዘገበው፣ ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓት ሲኖር ነው!

የትምህርት ሥርዓቱን/የመማር ማስተማር ሥራ በተግባር ተኮር እውቀት በመደገፍ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት መጣር ያስፈልጋል:: አዲሱ የትምህርት ሥርዓት ይህን ጥረት እውን ለማድረግ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል:: ስለሆነም በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ሥራ ፈጣሪነትን ባሕሉ ያደረገ ትውልድ እንዲፈጠር የትምህርት ሥርዓቱን ትግበራ በከፍተኛ ጥንቃቄና ትጋት መምራት ይገባል!

ወንድይራድ ሰይፈሚካኤል

አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You