የቡና አምራች፣ አቅራቢና ላኪን እያገናኘ ያለው የቀጥታ የግብይት ሥርዓት የውጪ ንግድ ገቢን እያሳደገ ነው

ጅማ፡- በቡና አምራች፣ አቅራቢና ላኪ መካከል የተፈጠረው የቀጥታ የገበያ ትስስር ከውጪ የቡና ንግድ የሚገኘውን ገቢ እያሳደገ ነው ሲል የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ። ሀገራዊ የቡናና ቅመማ ቅመም ኤግዚቢሽን በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ኤግዚቢሽኑ በቡና፣ በቅመማ ቅመም ዘርፍ ላይ ለተሠማሩ አምራቾች፣ አቅራቢዎችና በላኪዎች መካከል የተዘረጋውን የቀጥታ የግብይት ሥርዓት በማጠናከር ተጠቃሚነታቸውን ለማስፋትና ሀገሪቱ የምታገኘውን የውጪ ገቢ ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው ተብሏል።

የኤግዚቢሽኑን መከፈት አስመልክተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)፤ በቡና አምራች፣ በአቅራቢና በላኪ መካከል የተፈጠረው ቀጥታ የገበያ ትስስር ሀገሪቱ ከቡና የውጪ ንግድ እያገኘች ያለውን ገቢ በማሳደግ ትልቅ ለውጥ እያስገኘ ነው።

በቡና አምራች፣ አቅራቢና ላኪ መካከል የተፈጠረው ቀጥታ የገበያ ትስስር ሀገሪቱ የምታገኘውን የቡና የውጪ ገቢ ከማሳደግ ባለፈ በዘርፉ የተሠማሩ አምራቾች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎችን የገቢ አቅም እያሳደገ ነው ብለዋል።

የቡናን ምርት በጥራት አምርቶ ለውጪ ገበያ በማቅረብ የሀገሪቱ የውጪ ገቢ እያደገ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሀገሪቱ ከቡና የወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ ከሚሊዮን ዶላር ወደ ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል።

ቡናን በጥራት አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ እየተገኘ ያለው ገቢ እያደገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በ2014 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር፣ በ2015 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን አብራርተዋል፡፡ በተያዘው ዓመት ከፍተኛ የውጪ ዶላር ተገኝቷል ብለዋል።

እንደ አዱኛ (ዶ/ር) ገለጻ፤ በአምራቾች፣ በአቅራቢዎችና በላኪዎች መካከል የቀጥታ የግብይት ሥርዓት ባልነበረበት ወቅት አቅራቢና ላኪ በአካል አይተዋወቁም ነበር። ሁለቱም በወኪሎቻቸው ነበረ የሚገናኙት፡፡ ወኪሎቻቸው በቆረጡላቸው ዋጋ እንዲገበያዩ ይገደዳሉ፤ ይህም አቅራቢዎች ከላኪዎች የተቆረጠው ገንዘብ እንዳይደርሳቸው አድርጎ ቆይቷል።

አሁን የተጀመረው በዘርፉ የተሠማሩትን አካላት በቀጥታ የገበያ ትስስር የማገበያየት ሥራ ደላላዎችን ከመካከል በማውጣት ችግሩ እየተፈታ ነው ብለዋል።

ደላላው ከገበያ ሥርዓቱ እንዲወጣ መደረጉ አምራች፣ አቅራቢና ላኪውን በገቢ እያሳደገ ነው። ሀገሪቱም በቡና የውጪ ንግድ ገቢ አቅሟ እያደገ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በዘርፋ እየተሠራ ያለው አምራችን፣ አቅራቢንና ላኪን በቀጥታ የማገናኘት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ መሠረት አሰፋ በበኩላቸው፤ የአምራች፣ የአቅራቢና የላኪዎች ቀጥታ የገበያ ትስስር የሀገሪቱን የውጪ የቡና ንግድ ገቢ እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።

አምራቾችን፣ ከአቅራቢዎች፣ አቅራቢዎችን ከላኪዎች ጋር በቀጥታ ተገናኝተው ግብይት እንዲያደርጉ መደረጉ በገበያ ሥርዓቱ የነበረውን ችግር እየፈታ ነው ብለዋል።

የቀጥታ የንግድ ትስስር በገበያ ደላላዎች ከመሐል እንዲወጡ ስላደረገ በአምራች፣ በአቅራቢና በላኪ መካከል ያለው ችግር እየተፈታ መሆኑን ጠቁመው፤ የቀጥታ ገበያ ትሰስር የመፍጠሩ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አመላክተዋል።

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You