በሀገር ፍቅር… ወደ ሀገር ፍቅር ሲያሰኝ፣ ትዝ ሲል ስሜቱ…ያ! የጥንቱ ሙናዬን እያስታወሰ ሙናዬን ያስናፍቃል። እሷማ እዚያ የጥበብ እሳት፣ የትወናው ወላፈን፣ የመድረኩ ትኩሳት…ትኩስ የስሜት እሳት ነበረች። ከሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ደጃፍ ሳትጠፋ፣ ቲያትሩን ከሙዚቃው አጣምራ ስታበጃጅ ብዙ ዓመታትን አሳልፋለች። ከምንም በላይ በትወናው መድረክ ላይ ስትንበለበል ለተመለከታት “ኧረ እንዴትስ ያለችው ታምር ናት” የምታስብል ነበረች። ወደዚያ ብቅ ብሎ እሷን ያየ ሁሉ ዘመናትን ተሻግሮ፣ በዘመናት ሁዳዴ ዛሬም ድረስ ያስታውሳታል። እርሷን ማስታወስ ወደውና ፈቅደው ብቻ አይደለም፤ አንዴ አይመልከቷት እንጂ ከተመለከቷትማ በግድ ትዝ እንድትል የሚያደርጉ አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። ካያት ሁሉ የማያስታውሳት ማንስ አለና… ብዙዎችም ለምሳሌ ብለው አንድ ሰው ሲጠሩ “ልክ እንደ ሙናዬ” ነበር አብነታቸው ሁሉ። ፈርጠም ያለው ትዝታ በትወናዋ ይሁን እንጂ ሙናዬ ተዋናይት ብቻ አልነበረችም። ከትወናው ባሻገር በሙዚቃውም እሳት የላሰች ድምጻዊት ነበረች። በጣፋጭ ሙዚቃዎቿም ግሩም ትውስታን ለማኖር የበቃች ናት። በአድማጩ ዘንድ ተወዳጅነትን ካተረፉላት ሙዚቃዎቿ መሀከልም “ብርቱካኔ”፣ ትዝታዬ” እና “ጉብልዬ” የተሰኙት ተጠቃሾች ናቸው። ምናልባትም በኢትዮጵያ ሬዲዮ “የባህል ሙዚቃ ዝግጅት” የሚለውን መሰናዶ ዘወትር አርብ ምሽት ሲከታተል የነበረ ማንኛውም ሰው በተለይ እኚህን ሙዚቃዎች ለመርሳት አይችልም።
ሙናዬ መንበሩ ተወልዳ ያደገችው ከዚህቹ አዲስ አበባ ከናይጄሪያ ኤምባሲ ከፈረንሳይ ሰፈር ቁርጭምጭሚት ነበር። በልጅነት መንደሯ ውስጥ የጥበብ አድባር አልራቃትም። ከትወናው አስቀድሞም ወደ ጥበብ ቤት እንድትገባ መንገድ የሆናት ነገር ሙዚቃው ነበር። በልጅነቷ ሙዚቃን እንደ ነገሩ ለስሜቷ ያህል ብታንጎራጉርም ወደፊት ሙዚቀኛ ስለመሆን ተጨንቃበት የምታውቅ ግን አይመስልም። መረዋው ድምጽዋ ጎልቶ የሚወጣው በአበባየሆሽ ሰሞን ላይ ነበር። በበዓሉ ዕለት ትንንሾቹ የሰፈር ልጃገረዶች ተሰባስበው ከበሮውን እየደለቁና እየተምነሸነሹ “ኮለል በይ” ሲሉበት፣ የቡድኑ የአዝማች መሪ ሙናዬ መንበሩ ነበረች። አንደኛው የእንቁጣጣሽ ጭፈራ ግን ያላሰበችውን የእድሜ ልክ ሎተሪ ይዞላት ወጣ።
በ1952 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ዕለት ሙናዬና ጓደኞቿ ሰፈር ውስጥ እየዞሩ አበባየሆሽ ሲጨፍሩ ከአንድ ትልቅ ሰው ቤት ደጅ ደረሱ። እኚህ ሰውም ብዙዎቻችን ለዘመናት ሠርጎቻችንን ያደመቅንበትን “ሙሽራዬ” የተሰኘውን ሙዚቃ የደረሱት አቶ በሻህ ተ/ ማሪያም ነበሩ። እነ ሙናዬም እንደተለመደው “አበባዮሽ” ብለው ጨፍረውና ሳንቲሟን ተቀብለው “ከብረው ይቆዩ ከብረው፤ ባመት ወንድ ልጅ ወልደው፤ ሠላሳ ጥጆች አሥረው…” በማለት መርቀው ለከርሞው መልካሙን እየተመኙ ሊሄዱ ሲሉ፤ አባወራው በአትኩሮት ሲከታቷላቸው ነበርና ሙናዬን ጠሯት።
ጠርተውም ድምጽዋን እንደወደዱት በመናገር በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ውስጥ ሊያስቀጥሯት እንደሚችሉና ለሷም መልካም አጋጣሚ መሆኑን አስረዷት። በጊዜው ሙናዬ ገና የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ብትሆንም፤ ነገር ግን የቤተሰቦቿ የኢኮኖሚ ሁኔታ የተዳከመና እሷንም ገና በልጅነት ያሳስባት የነበረ ጉዳይ ነው። ስለዚህም እነርሱን ለመደገፍ ስትል ብቻ ሳታቅማማ በሃሳባቸው ተስማምታ ሀገርን ፍቅርን ለመቀላቀል ወሰነች። ትምህርቷንም ከዚያው ከሦስተኛ ክፍል ላይ አቋርጣ የ15 ብር ደሞዝተኛ ሆነች። ከዚያ በኋላ በትወናው መድረክ ላይ ብቻ ከአንድ መቶ በላይ በሆኑ ሥራዎች ውስጥ ለመተወን በቃች።
ትንሽዋ ሙናዬ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ውስጥ ሁለገብ የመድረክ ፈርጥ ለመሆን እምብዛም ጊዜ አልፈጀባትም። ትወናን አሀዱ ብላ ስትጀምርም “ምቀኛው ዕድሌ አደረገኝ ሎሌ” በሚለው በአርቲስት ቀለመወርቅ ደበበ ሥራ ነበር። የብዙ ዝነኞችን የኋላ ታሪክ ለማሰስ ስንሞክር አብዛኛዎቹን ሊያመሳስላቸው የሚችል አንድ ነገር እናገኛለን፤ አሊያም እንረዳለን። ይኼውም አብዛኛዎቹ ወደ ዝና መንበር እስከሚመጡበት ጊዜ ድረስ በርከት ያሉ ሥራዎችን ሠርተው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን የመጨረሻውን የዝና እርካብ ያስረገጣቸው አንድ የተለየ ሥራ የሚኖራቸው መሆኑ ነው። ለአንዳንዶቹም ተቀጽላ የስማቸው መጠሪያ እስከመሆን ይደርሳል። የሙናዬ መንበሩ ችሎታም እንደ መስከረም አበባ ፈንድቶ የወጣው “የቀለጠው መንደር” በተሰኘው የቲያትር ትወናዋ ነበር። ያን የመድረክ ብቃቷን ያሳየችበትን በእያንዳንዱ ገቢር ውስጥ የነበረውን እንቅስቃሴ ከረዥም ዓመታት በኋላ እንኳን ዛሬም ድረስ ከአይነ ህሊናቸው ሳይጠፋ የሚያስታውሱ በርካታ ተመልካቾች ናቸው።
ስትተውን ለተመለከትናት፤ እየተመለከትን ያለነው ትወና ስለመሆኑ እስክንጠራጠር ድረስ ደህና አድርጋ ታሳምነናለች። ገጸ ባህሪያቶቿ በብዛት እሳት ለበስ ናቸው። በእናቶች ወግ ከላይ ሻሽውና ጥምጥም አስራ፣ ነጠላዋን ከወገቧ ላይ ሸብ አድርጋ፣ ሹራቧን ከእጀታው ሰብሰብ በማድረግ ላይ ታች ስትወረገረግማ እንኳንስ ተጋጣሚዋን ተመልካቹንም የማርበድበድ ሃይል አላት። ብዙዎች ከማይረሱላት የትወና ችሎታዋ አንዱ ያ አደገኛ አሽሟጣች ፊቷ ነበር። አንድን ነገር ለማመልከት ዛሬም በየማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ይህን ቅጽበታዊ ምስሏን በተለያየ መንገድ ሲጠቀሙበት እንመለከታለን። በእንደዚያ ዓይነቱ ቅጽበት ውስጥ ያለምንም ቃላት፣ እንደወረደ የልብን ስሜት ፊት ላይ የማሳየቱን ጥበብ የተቀበለችው እርሷ ብቻ እስክትመስለን ድረስ አስደምማናለች። ቅሉ በትወናው እንጂ በእውነተኛው ሕይወቷ ግን እጅግ ሰው አክባሪ የፍቅር እመቤት ነበረች። አንዳንድ ጊዜም እንዲህ ያለውን ነገር እሰማለሁ…በቀለድ በጨዋታውም ይሁን በቁም ነገሩ መሀል፣ እስከናካቴውም ይሁን በአጋጣሚ፣ አንዳንዶች ከእውነተኛው ማንነታቸው ፍጹም እርቀው የእውነት ባልሆነ የማስመሰል ዓለም ውስጥ ያሉ መስለው ሲታዩ “ሙናዬ መንበሩማ አልሞተችም ኤገሌ ውጧት ነው እንጂ፤ ኤገሊት ውጣት ነው እንጂ…” ብለው ሲያፌዙ እመለከታለሁ። እዚህ ጋር የሚታይ አንድ እውነታ ቢኖር የሙናዬ ብቃት የመጨረሻው የትወና ልክ ተደርጎ መቆጠሩን ነው።
ጊዜው 1950ዎቹ አጋማሽ ላይ ነበር። ሙናዬ ደግሞ በወቅቱ ገና ከአፍላነት ያለፈች ትኩስ ወጣት ነበረች። በወቅቱም የሀገር ፍቅር ቲያትር አባላት “የእድሜ ልክ እስራት” የሚለውን የማቲያስ በቀለን ቲያትር በጅማ ከተማ ለማሳየት ጓዛቸውን ሸክፈው ወደዚያው አቀኑ። ቲያትሩ የሚታየው በአቅራቢያው ባሉ አካባቢዎች ሁሉ በመዘዋወር ነበርና ሙናዬ የምትተውንበት ይኼው ቲያትርም በመጀመሪያዎቹ ቀናት እጅግ በተሳካ ሁኔታ በደማቅ ድባብ ታጅቦ ታየ። ቲያትሩ ላይ ስታሳይ በነበረው ብቃቷም ሙናዬ የብዙ ተመልካቾችን ልብ እስከመሰወር ደርሳ ነበር። ሁለት ያህል መድረኮች ሲቀሩ ግን የመድረኳ እሳት ድንገት በከፍተኛ ህመም ውስጥ ወደቀች። አባላቱ ሁሉ ተደናግጠው ሰዓታት እስኪቀሩ ድረስ ቢታገሉም ከህመሟ አገግማ መድረክ ላይ ለመቆም የሚያስችላት ተስፋና ጉልበት ተሟጠጠ። በአጋጣሚ ገጸ ባህሪዋን ያጠናች ሌላ ሴትም ነበረችና አማራጩ እሷን መተካት ብቻ ሆነ። በሰዓቱ ከህመሟ ጋር ስትታገል የነበረችውን ሙናዬን አበርትተው ለብቻዋ ከአንድ ቤት ውስጥ ትተዋት ቀጣዩን ዝግጅት ለማቅረብ ወደስፍራው አመሩ። ሙናዬ ተኝታ የነበረችው ከአንድ ቅንጡ ሆቴል ውስጥ አሊያም ከሰው ጋር ከተመቻቸ ሥፍራ አነበረም። በጊዜው ወደ ክፍለ ሀገሮች ሥራዎቻቸውን ይዘው የሚሄዱ የሁሉም የጥበብ ባለሙያዎች አማራጭ የነበረው ማኅበረሰቡን እያስቸገሩ በጭቃና በደሳሳ ቤቶች ውስጥ ማደር ብቻ ነበር። ከዚያ ቤት ውስጥ ሆና ብቻዋን በሰቀቀን ሦስት ያህል ሰዓታትን ካሳለፈች ኋላ ግን አንድ አስደንጋጭ ነገር ገጠማት። በአራቱም አቅጣጫ የጅብ መንጋ ቤቱን ወሮ ማነፍነፍ ጀመረ። ሁኔታው ለሙናዬ እጅግ አስፈሪና ብርክ የሚያሲዝ ነበር። የከበባት የጅብ መንጋ አካሄዱ አደገኛ እንደሆነ ስትረዳ ግን እንደምንም ብላ የይድረሱልኝ ጥሪዋን አቀለጠችው። የርዳታ ጩኸቷን ሳይሰሙ ጥቂት ዘግይተው ቢሆን ኖሮ ሕይወቷ አደጋ ላይ በወደቀ ነበር፤ ግን የአካባቢው ሰዎች ተሯሩጠው ከዚህ ጉድ አወጧት።
እርሷን በቅርበት የሚያውቃት ሰው፤ ካሏት ብዙ ነገሮች መካከል ሊናገርላት የሚችለው አንደኛው ነገር ቢኖር ለጥበብ ሙያዋ ስላትን ትልቅ ክብር ይሆናል። ከልጅነት እስከ ዕውቀት እድሜዋን ሁሉ ሰጥታ የኖረችለትና የኖረችበት እንደመሆኑ ከሙያዋ አስበልጣ የምታየው ነገር የላትም። አሳቻ የሕይወት ጣጣና ፈተናው ብዙ ነውና በአንድ ወቅትም እጅግ ከባድ የሆነ የመከራ አጋሰስ ከፊቷ ድቅን አለባት። አንድ አዲስ ቲያትር ልምምድ ጨርሳ ለመድረክ ሊበቃ የቀረው በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ነበሩ። ለማሳየት በዝግጅት ላይ ሳሉ ግን ሙናዬ ድንገት የልጇን መሞት ሰማች። ሞት አንድ አስቀያሚ ነገር ሆኖ ሳለ ሌላ ተጨማሪ ፈተና መዞ ሲመጣ ደግሞ ለክፋቱ የሚሆን ስሜት አይኖርም። የተፈጠረው ሁኔታ የቲያትር ቡድን አባላቱንም ትልቅ ጭንቀት ውስጥ የከተተ ነገር ነበር። ሙናዬ መንበሩ በዚያ መከራ ውስጥ አልፋ ከዚያ የቲያትር መድረክ ላይ ቆማ ትታያለች ብሎ ተስፋ ያደረገ አልነበረም። እርሷ ግን የሥራው መበላሸት ብቻም ሳይሆን ቲያትሩን ለመመልከት አሰፍስፎ የሚጠብቀውን ተመልካች ስሜት ላለመንካት ብላ ታዳሚውን በማክበር ሥራውን ለመሥራት ወሰነች። ልቧን ኀዘን እየደቆሰውም ኀዘኗን ዋጥ አድርጋ መድረኩ ላይ ወጣች። ውስጧ እያለቀሰም ጥርሷ ግን ስቆ በድንቅ ብቃት ሠርታ ጨረሰችው። ብዙ ተመልካቾች በፍቅር ዓይን፣ በስስት እንዲመለከቷት ያስገደዳቸው አንደኛው አጋጣሚም ይኼው ነበር። እስከዛሬ ድረስም ለተመልካች ክብር በተምሳሌትነት እንደ ባንዲራ ተደርጎ የሚውለበለበው የእርሷ ስም ነው።
ሙናዬ በትወናው መድረክ ላይ ጀምራ በትወናው ብቻ አልጨረሰችም። ሙና የሙዚቃ ካሴትም አሳትማ ነበር። የአልበም ሥራዋን የሠራላትም በ1950ዎቹና 60ዎቹ ተወዳጅ የነበረው ሳባ ሙዚቃ ቤት ነበር። ባለክሩ ካሴቷም አምስት ከፊት 6 ከጀርባ በድምሩ 11 ሙዚቃዎቹን የያዘ ሥራ ነበር። “ጉብልዬ” የተሰኘው ምርጡ ሥራዋም ከእነዚህ አንደኛው ነበር። “ገና ለገና”፣ “የመውደድ ትርጉሙ”፣ “ቤቴ ብለህ ማረኝ”፣ “አንዱ ዓለም ትዳር ነው”፣ “ለወሬኛ ዝግ ነው”፣ “ሐሜት ምግብ አይሆንም” እና ሌሎችም ከአልበሙ ውስጥ የተካተቱ ናቸው።
ፈተና ታቅፎ የሚመጣ የሕይወት ድንግዝግዝ አንዳንዴም ቁልቁል እየወረደ ማለቂያው እንደ ዓባይ ወንዝ ይሆናል። እጅግ በርካታ የሆኑ መጥፎ አጋጣሚዎቿ ተወርተው የማያልቁ ናቸው። ደግሞም መልካም ነው ብላ ከጀመረቻቸው መንገዶች ላይ ሁሉ መጥፎ የትግል ሳንካ ሳይጋረጥባት አያልፍም። በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ውስጥ በትንሽ ደሞዝ ትልቁን ሥራ እየሠሩ ከነበሩት አንዷ ሙናዬ መንበሩ ብትሆንም በውስጡ የምትስተናገድበት ሁኔታ ግን ጥሩ የሚባል አነበረም ለማለት ይቻላል። በየጊዜው ከኃላፊዎቹ ደብዳቤዎች ይጎርፉላታል። በጊዜው የነበረው መመሪያና ደንብ እናትነትን በደንብ ያላማከለ በመሆኑ አንደኛው ፈተናም ልጅ በመውለጃ ሰዓቷ ነበር። መጋቢት 2 ቀን 1965ዓ.ም ከመሥሪያ ቤቷ ደብዳቤ ተጻፈላት። ይህን ደብዳቤ ለማንበብ ስንጀምር ያስቀን ይሆናል ስንጨርስ ግን እንዲያ አይደለም። “…እርስዎ በየጊዜው እያረገዙ የድርጅትዎን ሥራ በማጓደል ከስራ ከመነጠልዎ ሌላ 40 ቀን ሙሉ ከሥራ ቀሪ በመሆን ሥራ በድለዋል…” የሚል ነበር። እንዳነሳነው የሙናዬ ወርሃዊ ደሞዝ እጅግ አነስተኛ ስለነበር በዚያ ብቻ ቤተሰቧን ለማስተዳደር አትችልም ነበር።
እናም ኑሮዋን ለመደገፍ ስትል እንደ አብዛኛዎቹ የጥበብ ሰዎችም ከቲያትር ቤቱ ሥራ ጎን ለጎን መዝናኛ ቤት ከፍታ መሥራት ጀመረች። ብዙም ሳትቆይ ግን ሌላ ደብዳቤ ደረሳት። የማስጠንቀቂያ ደብዳቤው የተጻፈላት በ1967ዓ.ም ሲሆን እንዲህ የሚል ነበር፤ “…እርስዎ በመድረክ የሚነቅፉትን ተግባር ተደራቢ ሥራ በማድረግ የመጠጥ ቤት ንግድ አቋቁመዋል። ከአንደበት ልፈፋ ይልቅ ቅንጣት ድርጊት ይበልጣል እንደሚባለው በመድረክ የሚያስተላልፉትን መልእክት በመጠጥ ቤት ሥራዎ ሽረዋል…” እያለ ማስጠንቀቂያውን አስከትሎ ይቀጥላል። ሕይወትም እንዲሁ ይቀጥላል…ሙያዋን ከምንምና ከማንም ጋር ለንጽጽር እንኳን አታቀርበውምና የምሽት ቤቷን ክርችም አድርጋ ዘግታ በሙሉ ልብ ወደመድረኳ ገባች። “የቀለጠው መንደር” ድንቅ ማስታወሻዋን ያስቀመጠችውም እንዲህ እየሆነች ነበር።
ጅግራ ጅግራውን እንደሚያበቅል ሁሉ የወይን ፍሬም የሚሰጠው ወይኑን ነው። አርቲስት ሙናዬ መንበሩ የራሷን አምሳል ለጥበብ ሰጥታለች። ከልጆቿ መካከልም ሀረገወይን በቀለ የምትባለው ልጇ በትወናው ቀኙን መንገዷን ተከትላለች። እድሉ ተሰጥቷት ይህች ልጅ በሰፊው መድረክ ብትቆም ሙናዬን ዳግም እንደምንመለከታት ጥርጥር የለውም ሲሉ ጠቆም የሚያደርጉ ሰዎችም እንዲሁ አሉ። በቅጡ ሳያበስሉት ያለፉትን የእናቷን ውለታም ምናልባት በልጅ እያስታወስን እንክሳት ይሆናል።
ዘመን በዘመን እየተሻረ፣ ሙናዬም በችሎታዋ ላይ ችሎታን፣ በዝናዋ ላይም ዝናን እየጨመረች ስትሄድ፤ ሞት ግን ከእድሜዋ ላይ እድሜን እየቀነሰ ወደ እርሷ ሲገስግስ ነበር። ዳናዋን ሲከተል ከርሞ በነሐሴ 10 ቀን 1995ዓ.ም ሌሊት ደርሶ ከሕይወቷ ፊት ተደነቀረ። ሞት እንግዲህ ሞት ነው። ተመልሰህ ና ተብሎ ቀጠሮ የማይሰጠው፣ ያልፈጸምኳት ቀሪ ግብር አለኝ ተብሎ ስለአቦ አይሉት ነገር…በዚያ አስቀያሚ አጋሰሱ ላይ ጭኖ ይዟት ሄደ። ከወሰዳት ድፍን 21 ዓመታት ሊቆጠሩ የቀራት አንዲት ነጠላ ወር ብቻ ናት። እኚህ ሁሉ የዘመን አጎዛዎች ቢነጠፉም ሙናዬ ግን የምትታየው ልክ እንደትናት ማታ ነው። የምስሏ ቀለማት ዛሬም ድረስ ሳይፋቁና ሳይደበዝዙ ደማቅ ሆነው ይታያሉ። የእርሷ ደምግባት ከሙያዋ መልክ ላይ ነው። የትወናዋ ጥግ የደረሰበት የብቃቷ መጨረሻ፤ ከመጨረሻው እስትንፋሷ ጋር አብሮ አልተቋረጠም። አፈሩን ገለባ ያድርግላትና ከአፈር በታች ሆናም “ልክ እንደ ሙናዬ… እንደሙናዬ” ነበሩ ቃላቱም። ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ደጃፍ ጎራ ስንል፤ ሙናዬን ከተቀረጸው የድንጋይ ሐውልቷ ላይ እንመለከታታለን። በ1996ዓ.ም ከቆመላት ከዚህ ሐውልት ላይም ከሀገር ፍቅር እና ከሙያ ቤተሰቦቿ የተጻፈላት እንዲህ የሚል ጽሁፍ አለ፤
“ሙና ዓለም
ጥበብ ዕጹብ
ዕጹብ ጥበብ
ሞት በሥራ ሲገደብ
ስም ህያው ሆኖ
ለዘለዓለም ሊያረብብ”
በማለት ውዱን የብዕር ማስታወሻቸውን አኖሩላት። ሙና..ሙናዬ…እሳቷ የጥበብ ነበልባል… ትውልድ አልፋ በትውልድ ትቀጥላለች።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም