ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አነሳ

የዋንጫውን አሸናፊ ለመለየት እስከ መጨረሻው 30ኛ ሳምንት የውድድር መርሀ ግብር ድረስ አጓጊ ሆኖ የዘለቀው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2016 የውድድር ዘመን በመጨረሻም አዲስ ቻምፒዮን አግኝቷል።

በአሰልጣኝ በፀሎት ልኡልሰገድ እየተመራ 61 ነጥብ ይዞ የመጨረሻውን ወሳኝ ጨዋታ ያደረገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ኢትዮጵያ መድህንን በሱሌይማን ሀሚድና አዲስ ግደይ የመጀመሪያ አጋማሽ ግቦች ታግዞ በማሸነፍ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ አንስቷል።

በአሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚሰለጥነው መቻል በበኩሉ የ80ኛ ዓመት ክብረ-በዓሉን በዋንጫ ለማጣጣም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ የንግድ ባንክን መሸነፍ ወይም ነጥብ መጣል እየጠበቀ በተመሳሳይ ሰአት እዚያው ሀዋሳ ላይ በአርቴፊሻል ሜዳ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያደረገውን ፍልሚያ በምንይሉ ወንድሙ ብቸኛ ግብ መርታት ቢችልም በአንድ ነጥብ ልዩነት ዋንጫውን ሳያነሳ ቀርቷል። መቻል ለመጨረሻ ጊዜ 1980 ነበር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ያሸነፈው።

በዚህም በ2014 ዳግም የተቋቋመው እና ከፕሪሚየር ሊጉ ለዓመታት እርቆ የቆየው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ሊጉ ባደገበት ዓመት ዋንጫውን ለማንሳት ችሏል። ይህም ከሀዋሳ ከነማ እና ጅማ አባ ጅፋር ቀጥሎ ፕሪሚየር ሊጉን በተቀላቀለ የመጀመሪያው ዓመት ዋንጫ ያነሳ ሶስተኛው ቡድን አድርጎታል።

በ1990 ዓ.ም በአዲስ መልክ መካሄድ በጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከዚህ በፊት ስምንት ክለቦች ዋንጫውን አንስተዋል፡፡ ባለፉት 26 ዓመታት ቻምፒዮን በመሆን የአዲስ አበባ ክለቦች ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋንጫውን ያነሳ ዘጠነኛው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን ክለብ ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይህን ታሪካዊ ድሉን ተከትሎ የሊጉን ዋንጫ አንድ ጊዜ ማንሳት የቻሉትን ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት፣ ጅማ አባጅፋር፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ፋሲል ከነማን ታሪክ መጋራት ችሏል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በወንዶቹም በሴቶቹም ተመሳሳይ ክለብ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲያሸንፍ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ። በዚህም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀጣዩ ዓመት በሁለቱም ፆታ ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ የሚሳተፍ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ንግድ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራን ጨምሮ በበርካታ ደጋፊዎችና የክብር እንግዶች በስቴድየም ተገኝተዋል።

ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ሻሸመኔ ከተማ በመጡበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዳቸው ይታወቃል፡፡

በሊጉ 20 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለው የሀዋሳ ከተማው አሊ ሱሌማን የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ፉክክር በቀዳሚነት አጠናቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2017 ዓ.ም በፕሪምየር ሊጉ 19 ክለቦች እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማሳወቁ የሚታወስ ነው፡፡

በወረዱት ምትክ ሁለት ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ የሚሳተፉ ሲሆን፤ እንዲሁም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከውድድር ርቀው የቆዩት ሦስቱ የትግራይ ክለቦች ወደ ነበሩበት ሊግ እንዲመለሱ በመወሰኑ ቁጥሩ 19 መድረስ ችሏል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ የውድድር ዓመት ከ19ኙ ክለቦች አምስት ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚወርዱ ሲሆን፤ እንደተለመደው ሁለት ክለቦች ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ በማደግ የ2018 ዓ.ም ውድድር ወደ ነበረበት ተመልሶ በ16 ክለቦች መካከል የሚደረግ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባደገበት ዓመት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በማንሳት ሦስተኛው ክለብ ሆኗል፤

አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You