ከ80 ዓመታት በላይ የዘለቀው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እንግሊዝኛ ጋዜጣ

እነሆ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ በውጭ ሀገር ቋንቋ የሚታተም የራሷ ጋዜጣ አልነበራትም። በ1933 ዓ.ም በኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎ እና በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የዲፕሎማሲ ትግል የጣሊያን ፋሽስት ወራሪ ኢትዮጵያን ለቆ ሲወጣ ንጉሡ ከተሰደዱበት እንግሊዝ ሀገር ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። የጣሊያን ፋሽስት ወራሪ ተሸንፎ ሲወጣ እና የፋሽስቱ የጨለማ ዘመን አልፎ ንጉሡ ከተሰደዱበት ሲመለሱ፣ ኢትዮጵያም ክብሯን ስታስጠብቅ ዘመኑን እንደ አዲስ በመጀመር ‹‹አዲስ ዘመን›› የሚባል በአማርኛ ቋንቋ የሚታተም ጋዜጣ ተጀመረ።

በአማርኛ ቋንቋ የሚታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ግን ለኢትዮጵያውያን እንጂ የኢትዮጵያን ምንነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርስ አልነበረም። በተለይም በዓለም አቀፉ ቋንቋ በእንግሊዝኛ የኢትዮጵያን ሁነቶችና የኢትዮጵያን ምንነት የሚያሳውቅ ጋዜጣ ያስፈልግ ነበር። በዚህም ምክንያት ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ›› የተሰኘው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ተመሠረተ። እነሆ ዛሬ ድረስ የሀገሪቱ ብቸኛ ዕለታዊ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ሆኖ ቀጥሏል።

በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ81 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 27 ቀን 1935 ዓ.ም የተመሠረተውን ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ›› ጋዜጣ እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት የታሪክ ክስተቶችን እናስታውስ።

ከ105 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 24 ቀን 1911 ዓ.ም ደራሲ፣ ሀኪምና የምጣኔ ሀብት ጥናት ባለሙያ የነበሩት ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ አረፉ። ‹‹አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ›› እና ‹‹መንግሥትና ሕዝብ አስተዳደር›› የሚሉ መጻሕፍት ያሏቸው ሲሆን በተለይም በምጣኔ ሀብት ሊቅነታቸው በሰፊው ይነገርላቸዋል።

ከ80 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 24 ቀን 1936 ዓ.ም የቅኔ፣ የትርጓሜና የቋንቋ ሊቅ የነበሩት አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ አረፉ። ‹‹መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› የተባለውን የግዕዝና የአማርኛ መዝገበ ቃላት የጻፉ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ፊደል አመጣጡንና ባህሉን በውል አስተባብረው በማቅረባቸውም በጊዜው ተቋቁመው ለነበሩት ትምህርት ቤቶች መመሪያና መማሪያ ለመሆን በቅተዋል። ቀጥለውም ትንሽ አማርኛ ፊደል ከአረብና ከዕብራይስጥ አቆራኝተው አሳትመዋል። አለቃ ኪዳነወልድ ከግዕዝና ከአማርኛ በተጨማሪ አረብኛ፣ ዕብራይስጥ እና የላቲን ቋንቋዎችን ጠንቅቀው ያውቁ ነበር።

ከ248 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 27 ቀን 1768 ዓ.ም፤ ወይም በራሳቸው የዘመን ቀመር ጁላይ 4 ቀን 1776 በዛሬዋ ልዕለ ኃያል አሜሪካ እንዲህ ሆነ። እነሆ ዛሬ የዓለም አድራጊ ፈጣሪ ነኝ የምትል ይቺ ሀገር ከ248 ዓመታት በፊት ቅኝ ተገዢ ነበረች። ለዘመናት በቅኝ ግዛት የቆየችው አሜሪካ ከ248 ዓመታት በፊት ሰኔ 27 ቀን 1768 ዓ.ም 13 ግዛቶችን ይዛ ከእንግሊዝ ነፃ ወጥታ ሉዓላዊት ሀገር መሆኗን አወጀች። እነሆ ዛሬ ግን የዓለም ልዕለ ኃያል ሀገር ሆነች። በዚያን ዘመን የነበረውን የኢትዮጵያ ታሪክ ስናስታውስ፤ የዘመነ መሳፍንት ወቅት ነበር።

ከ77 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም ባለቅኔ፣ ደራሲና ገጣሚ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ አረፉ። ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ‹‹ወላድ ኢትዮጵያ››፣ ‹‹የኛማ ሀገር›› እና ‹‹ድንግል ሀገሬ ሆይ›› የተሰኙ የድርሰት ሥራዎች ያሏቸው ሲሆን በዋናነት ግን በዚህ ግጥማቸው ይታወቃሉ።

ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ

የሞተልሽ ሳለ የገደለሽ በላ

የዚህ ግጥማቸው መልዕክት፤ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በነበረው የፋሽት ጣሊያን ወረራ ጊዜ የተጋደሉ አርበኞች ተገቢውን ክብር ሳያገኙ፤ ይባስ ብሎም አንዳንዶቹ በስቅላት ተገድለው (ለምሳሌ በላይ ዘለቀ) ለጠላት ያደሩ ባንዳዎች ግን ሥልጣን ሲሰጣቸው የነበረውን አሠራር ለመቃወም ነው ይባላል። እነሆ ዛሬ ድረስ ብዙዎች የግጥሙን መልዕክት ለየሚፈልጉት ዓውድ ይጠቀሙታል።

የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ዝርዝር ታሪክ ሐምሌ 3 ቀን 2014 ዓ.ም የታተመ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹ሳምንቱን በታሪክ›› ዓምድ ላይ ያገኙታል።

አሁን በዝርዝር ወደምናየው የመጀመሪያውና አንጋፋው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ›› ታሪክ እንለፍ።

‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ›› ጋዜጣ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሰኔ 27 ቀን 1935 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር 1943) ተመሠረተ። ጋዜጣው ሲጀመር በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ የሚታተም ሲሆን በዕለተ ቅዳሜ ለአንባቢ ይደርስ ነበር።

ጋዜጣው ለህትመት ሲበቃ የአርበ ጠባብ (tabloid) ቅርጽ የነበረው ሲሆን፤ በ25 ሳንቲም ይሸጥ ነበር። በወቅቱ ጋዜጣውን በቋሚ ደንበኝነት የሚወስዱ ግለሰቦችና ተቋማት በዓመት የፖስታን ዋጋ ሳይጨምር 13 ሽልንግ (ስድስት ብር ከ50 ሳንቲም መሆኑ ነው) ይከፍሉ ነበር።

የጋዜጣው የመጀመሪያ አዘጋጅ ኢያን ኤ. ሲምሰን የተባለ እንግሊዛዊ ነበር። እርሱም በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ከሐምሌ 3 ቀን 1943 እስከ የካቲት 12 ቀን 1944 የመጀመሪያው የ ‹‹ዘ ኢትዮጵያን›› ሄራልድ ጋዜጣ አርታኢ ሆኖ አገልግሏል። በወቅቱ ይህ ሰው የጋዜጣው ርዕሰ አንቀጽ አጻጸፍ ደረጃ ከፍ እንዲልና አልፎ አልፎም በሁለተኛ ገፅ ላይ የሚታተሙ አስተያየቶች እንዲኖሩ አድርጓል።

ኢያን ኤ. ሲምሰን በጣሊያን ወረራ ጊዜ እንግሊዝ ኢትዮጵያን ስታግዝ የእንግሊዝ የመረጃ ሠራተኛ እንደነበር የኢትዮጵያን ሄራል የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ ያዕቆብ ወልማርያም ተናግረዋል።

በዚህ እንግሊዛዊ በሚዘጋጅበት ጊዜ የነበረው የጋዜጣው ይዘት፤ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ሕዝባቸው የሚበለጽግበትን መንገድ ለማሳየትና ለመርዳት ብዙ የሚለፉና የሚደክሙ፣ እረፍት የሌላቸው ሰው፣ ተወዳጅ ንጉሥ፣ የሚወዱትን ሥራ ለመሥራት ዝግጁና ቆራጥ፣ ሌላው ዓለም ምስቅልቅል ውስጥ ባለበት በዚያን ወቅት ነገሮችን በአዲስ ለመጀመር ወደፊት የሚራመዱ… የመሳሰሉትን የሚገልጽ ነበር። እነሆ አንድ እንግሊዛዊ በዚህ ልክ የኢትዮጵያን መሪ ያደንቅ ነበር ማለት ነው።

ከዚህ እንግሊዛዊ በኋላ የጋዜጣው አዘጋጅ የሆነው ደግሞ አሜሪካዊ ነው፤ ዊሊያም ኤም ስቲን የተባለው ይህ አሜሪካዊ በእነርሱ የዘመን ዘመር (ጋዜጣውም እንግሊዘኛ መሆኑን ልብ ይሏል) ከየካቲት 1944 እስከ 1945 የጋዜጣው አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል። እንዲህ እንዲህ እያለ ጋዜጣው በውጭ ሀገራት ዜጎች ሲዘጋጅ ቆይቷል።

ለ15 ዓመታት ያህል ሳምንታዊ ሆኖ የቆየው ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ›› በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1958 በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢ ሲ ኤ) በአዲስ አበባ መመሥረትን ምክንያት በማድረግ ዕለታዊ እንዲሆን ተደረገ።

ጋዜጣው ዕለታዊ መሆን በጀመረ በዓመቱ በ1959 ኢትዮጵያዊው ያዕቆብ ወልደማርያም በምክትል አዘጋጅነት የ‹‹ዘ ኢትዮጵያ ሄራልድ›› ጋዜጣ ተቀላቀሉ። ከ1960 ጀምሮ አፍሮ አሜሪካዊውን ታልቦት ተክተው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ተጠባባቂ አዘጋጅ ሆነው መሥራት ጀመሩ። በወቅቱ አቶ ያዕቆብ ዜና፣ የዜና አርትዖት ሥራ በመሥራት፣ መጣጥፍና ሌሎች ሥራዎችን መተርጎም ዋና ሥራቸው ነበር። በወቅቱ ዋና አዘጋጅ የሚለው ስም ተጽፎ ባይገኝም ከዚያን ጊዜ በኋላ ግን የጋዜጣው ዋና አዘጋጆች ኢትዮጵያውያን ሆነው ቀጥለዋል። አቶ ያዕቆብ ወልደማርያም የመጀመሪያው የ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ›› ዋና አዘጋጅ ተደርገው ይወሰዳሉ።

‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ›› ጋዜጣ ይዘጋጅ የነበረው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ መረጃ ለመስጠት እና ለውጭ ቱሪስቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚካሄደው ሁነት መረጃ ለመስጠት የተቋቋመ እንደነበር ‹‹The quest for press freedom: one hundred history of the Media in Ethiopia›› የተሰኘው በአቶ መሠረት ቸኮል የተዘጋጀው መጽሐፍ ይገልጻል። በወቅቱ ጋዜጣው ቋሚ ዘጋቢና የተሟላ ሥርዓት እንዳልነበረው በዚሁ መጽሐፍ ተጠቅሷል። በሌላ በኩል እንደ ሌሎች ጋዜጦች ጋዜጣው ሕግና የዲዛይን አሠራር እንዳልነበረው በዚሁም መጽሐፍ ተጠቅሷል። የሀገር ውስጥ ዜናዎችንም ከጋዜጣው ላይ ማግኘት ከባድ በመሆኑ ጋዜጣው በውጭ ዜና ምንጮች ላይ የተንጠለጠለ እንደነበር የጋዜጣው ሰነዶች ያሳያሉ።

‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ›› ጋዜጣ ሐምሌ 23 ቀን 1958 ዓ.ም (እ.አ.አ 1966) የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን የ74ኛ ዓመት ልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ 16 የገፅ ብዛት ያለው ልዩ ዕትም ታትሞ ለአንባቢ ቀርቧል። የጋዜጣው የገጽ ቁጥር ቢጨምርም ይዘቱ ግን ትኩረት አድርጎ የሚያወሳው የንጉሠ ነገሥቱን ከውልደት እስከ ሹመት ያለውን ታሪክ ነበር።

በ1967 ዓ.ም (እ.አ.አ 1974) በኢትዮጵያ የተካሄደውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ የጋዜጣው ርዕሰ አንቀጽ (ኤዲቶሪያል) ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› በሚል ጽሑፍ ተተክቶ የወታደራዊ አስተዳደር ደርግን አቋም ማንፀባረቅ ጀመረ። ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ተወግዶ ኢህአዴግ ሀገር ማስተዳደር ሲጀምርም እንደዚሁ የሥርዓቱ ባህሪያት ይንፀባረቁበት ነበር።

‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ›› ጋዜጣ በዓለም አቀፉ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተም የኢትዮጵያን አቋም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያንፀባርቅ ጋዜጣ ነው። ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝብ የነፃነት አርዓያ ናትና የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ ይህ የኢትዮጵያ ጋዜጣ ከፍተኛ ትግል አድርጓል፤ የኢትዮጵያን አቋም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አንፀባርቋል። ከጋዜጣው በተገኙ ሰነዶች ጥቂቶችን እናስታውስ።

የአፍሪካ ነፃ ሀገራት ጉባዔ መካሄዱን የገለፀ ሲሆን፤ ‹‹የአፍሪካ ቤተሰብ ጉባዔ›› በሚል ርዕስ ተሳታፊዎች ‹‹የአፍሪካ ነፃነት አሁን›› የሚል አቋም ማንጸባረቃቸውን ዘግቧል። ጉባዔው አፍሪካውያን በጠቅላላ ነፃ እንዲወጡ እንጂ ጥያቄው የተወሰኑ ሀገራትን ብቻ እንደማይመለከትም በአፅንዖት አቋም እንደተያዘ ዘግቧል። ‹‹ሁላችንም ነፃነትን እንሻለን፤ ቅኝ ግዛት በቅቶናል፤ ቅኝ ግዛትና ኢምፔሪያሊዝም ይውደሙ! ከአፍሪካ እጃችሁን አንሱ፣ አፍሪካ ነፃ ትውጣ!›› የሚለውን ጠንካራ አቋም በራሳቸው በኢምፔሪያሊስቶች ቋንቋ (እንግሊዝኛ) አንጸባርቋል።

በ1959 ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እያበረከተችው ያለው ሚና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ሲል ዘግቧል። ኢትዮጵያ ቀደምት፣ ቅኝ ያልተገዛች እና ነፃ ሀገር መሆኗን እና በተለያዩ ተቋማት የምታደርጋቸው ተሳትፎዎች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት እየሆነች ነው ሲል ይዘግባል። ይህ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን ተጠቅማ አፍሪካ ሙሉ ለሙሉ ነፃ እንድትወጣ ቀዳሚ ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ የሚገልፀው ዜናው፤ ብዙ ሀገራት ኢትዮጵያን እንደ ተምሳሌት ወስደው ለነፃነት እየተነሳሱ መሆኑን ዘግቦ አሳይቷል።

በዚያው ልክ ግን የተለያዩ መሰናክሎች ኢትዮጵያ በበቂ ሁኔታ ለአህጉሪቱ ነፃነት እንዳትታገል እንቅፋት እየሆኑባት እንደሚገኙም አስረድቷል። በተለይም በአህጉሪቱ የጋራ መድረክ አለመኖር እንቅፋት እንደነበር እና የአፍሪካ ነፃ ሀገራት ጉባዔ መመሥረት ግን በተወሰነ መልኩ ጥሩ ዕድል ይዞ እንደመጣ በወቅቱ የትግሉ ልሳን ሆኖ ተናግሯል።

በዚያው ዓመት በጋዜጣው በወጣ ርዕሰ አንቀፅ ስለደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ሥርዓት ያትታል። ‹‹በደቡብ አፍሪካ ከሳሹ ተከሰሰ››( South Africa: the accuser stands accused›› የሚል ርዕስ በሰጠው ርዕሰ አንቀፅ ስለደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ አቋም የያዘበት ሐተታ አስነብቧል።

በዚያው ወቅት ስለጎረቤት ሀገር ሶማሊያ የፊት ገፁ ላይ ይዞት በወጣ ርዕሰ አንቀፅ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛትን እንጂ ነፃነትን አትቃወምም›› በሚል ርዕስ፤ ከሶማሊያ ነፃነት ጋር የተሳሳቱ ዘገባዎች እና ፕሮፓጋንዳዎች እየተሠሩ መሆኑን በመግለጽ፤ ኢትዮጵያ ለሶማሊያም ይሁን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ነፃነት እኩል እየታገለች መሆኗን በግልጽ ተናግሯል።

‹‹ኢትዮጵያ የሶማሊያን መዋሃድ ትቃወማለችን?›› የሚል ጥያቄያዊ ርዕስ ባለው ሌላ ርዕሰ አንቀፅ፤ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ከሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላሂ ኢሳ ጋር በቴሌግራም ማውራታቸውን እና ኢትዮጵያ የሶማሊያ አንድነትን እንደምትደግፍ እና ፈረንሳይ ፈጥራው የሄደችውን የድንበር ጉዳይ በስምምነት የሚያልቅ እንደሆነ እንደተነጋገሩ ያትታል። በወቅቱ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ስለነበር ጋዜጣው የኢትዮጵያን አቋም በዓለም አቀፉ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ያሳውቅ ነበር።

በአፍሪካ ጉዳይ ላይ በሰፊው ይሠራ የነበረው ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ በጥር 1960 (እ.አ.አ) ኮንጎ የመጀመሪያ የነፃነት ቀኗን እንዳከበረች ገልጾ፤ የ75 ዓመታት የኮንጎ የቅኝ ግዛት ዘመን ማብቃቱን ዘግቧል። ኮንጎ አዲሷ እና ትልቋ ነፃ የወጣች ሀገር ሆናለች ሲልም ይገልጻል። በርዕሰ አንቀፅ አቋሙ ‹‹ኮንጎ ነፃነቷን አገኘች›› ሲል ሰንዶ እናገኘዋለን። ቀጥሎም አፍሪካ በ1960 አዲስ ለውጥ እያስተናገደች መሆኑን በአጽንዖት ይናገራል። እነዚህ የጋዜጣው ሐተታዎችና ዜናዎች የኢትዮጵያን የነፃነት አስጀማሪነትና ቀስቃሽነት ይመሰክራሉ።

ጋዜጣው በ1960 ይዞት በወጣ ዜና የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በሶማሊያ የአባልነት ጉዳይ መወያየቱን እና ኢትዮጵያ የሶማሊያ ነፃነት እንዲፋጠን፣ ቀኑ በግልፅ ተለይቶ እንዲወሰን በመጎትጎት ለሶማሊያ ነፃነት ትልቅ ሚና እንደነበራት ሰንዷል።

በአጠቃላይ ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ›› ጋዜጣ ከ80 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያን ምንነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲያስተዋውቅ የኖረ እና አሁንም በማስተዋወቅ ላይ የሚገኝ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጋዜጣ ነው።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You