ኢፕድ ተልዕኮውን ከመወጣት ጎን ለጎን ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትጋት እየተሳተፈ ይገኛል

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ ከመወጣት ጎን ለጎን ሀገራዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በትጋት እየተሳተፈ ይገኛል ሲሉ የድርጅቱ የይዘት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ከተማ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አመራሮችና ሠራተኞች በእንጦጦ ፓርክ በመገኘት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ትናንት አካሂደዋል፡፡ የዘንድሮ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር “የሚተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ከተማ በዕለቱ እንደገለጹት ድርጅቱ ተልዕኮውን ከመወጣት ጎን ለጎን ሀገራዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በትጋት እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከተጣለበት ሀገራዊ ኃላፊነት ወጪ እንደ ትልቅ ተልዕኮ ይዞ ከሚሠራባቸው አጀንዳዎች ውስጥ ቀዳሚ ነው ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ እንደሀገር ከተጀመረ አንስቶ እንደ ተቋም ዘገባ በመሥራት ኃላፊነቱን እየተወጣ እያንዳንዱ ሠራተኛና አመራር ደግሞ እንደ ዜጋ ዐሻራውን እያሳረፈ ይገኛል ብለዋል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ባሕል እንዲያደርገው በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ የማስተማርና የማስተዋወቅ ሥራ በትኩረት ሲሠራ መቆየቱንም ሲሉ ነው አቶ ፍቃዱ ያብራሩት፡፡

እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ ድርጅቱ በደም ልገሳ፣ የተለያዩ ድጋፍና የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ሠራተኛው በወርሐዊ ደመወዙ ለመቄዶኒያ ድጋፍ እንዲያደርግ በማድረግ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥ መቀነስና በየዘርፉ ላይ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሀገሪቱ የደን ሽፋን ከነበረበት ሦስት በመቶ ወደ ከ27 በመቶ በላይ መድረሱ ተስፋ ሰጪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የአረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥ ከመቀነሱም በላይ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ፣ የሥራና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ውጤት እያስገኘ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድም ተክሉ በበኩላቸው ድርጅቱ የአረንጓዴ ዐሻራ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በቂሊንጦና በእንጦጦ ፓርኮች ላይ የተለያዩ ችግኞች በመትከል በንቃት ሲሳተፍ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

የተተከሉ ችግኞች ከመንከባብ አኳያ ሥራዎች ቢሠሩም አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች መሥራት ይጠይቃል ያሉት አቶ ወንድም፤ በቀጣይ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ እንዲቻል ሠራተኛው በራሱ ተነሳሽነት መዋጮ አዋጥቶ እንክብካቤ ለሚያደርግ አካል እንዲሰጥ እንዲሁም በዓመት ሦስት ጊዜ በቦታው በመገኘት ክትትል እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባለፉት ዓመታት የተከላቸው ችግኞች 80 በመቶ ፀድቀዋል ያሉት ደግሞ የእንጦጦ ፓርክ የችግኝ ባለሙያ አቶ አስቻለ ደሳለኝ ናቸው፡፡

አቶ አስቻለ አክለውም፤ ድርጅቱ ያለማቋረጥ በፓርኩ ውስጥ ችግኝ እየተከለ እንዲሁም እየተከታተለ ይገኛል ያሉ ሲሆን ሌሎች ተቋማትም ከዚህ ልምድ በመውሰድ አንድ የራሳቸው ቦታ ወስደው ዐሻራቸውን ማኖር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You