እንቦጭ በጣና ጤና (ውበት) እና ህልውና ላይ አደጋ የጋረጠ በጥባጭ አረም ነው። አረሙን ለማጥፋት በሰው ሀይል ሙከራ ቢደረግም በማግስቱ የበለጠ ተስፋፍቶ ይገኛል፡፡ በዚህ የተነሳም በቀላሉ ለማስወገድ አልተቻለም።
እንቦጭን ለማጥፋት ግለሰቦች፣ ባለሀብቶችና በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች ፣ባንኮች፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር እና ክልሎች የጣና ሀይቅ ለሚገኝበት የአማራ ክልል መንግሥት የገንዘብ እርዳታ አድርገዋል። ዜጎች በመተባበርና በመረባረብ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ ።
የጣና ሀይቅ የባህር ዳር ከተማ እና የክልሉ ውበት ብቻ አይደለም፤የኢትዮጵያም ህልውና ነው። እንቦጭ በእንጭጩ ካልተቀጨ የአካባቢው ሥነ ምህዳር ይዛባል። በሀይቁ ላይ ሕይወታቸው የተመሰረተ አሳ አስጋሪዎች፣ የአሳ ምግብ አዘጋጆች፣ የጀልባ ትራንስፖርት ባለቤቶች፣ በሐይቁ ውስጥ የሚገኙ ጥንታዊ ገዳማትን ጨምሮ አስጎብኝዎች ተጎጂዎች ናቸው ።
ችግሩ በጊዜ ካልተፈታ ተፅዕኖው ወደ ሱዳንና ግብፅ ሊደርስ እንደሚችልም ይታመናል ። ጣና ቀስ በቀስ እንደ ሀሮማያ ሀይቅ ጠፍ መሬት ወይም ምድረበዳ እንዳይሆን ርብርቡ መጠናከር አለበት ።
ዘመናችን እንቦጭና በጥባጭ ለሤራ በጋራ የዘመቱበት ነው ማለት ይቻላል። እንቦጭ የሚያስከ ትለውን ችግር የምናየው በጣና ሐይቅ ተወስኖ ቢሆንም፣ ችግሩ ግን ሀገር አቀፍም ነው።
ባለፈው አመት በሀገሪቱ በህዝብ ተጋድሎ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች የመለሱ ተግባሮች እየተካናወኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ ለውጥ ያልጣማቸው አንዳንድ ወገኖች ታዲያ ለውጡን ወደሁዋላ ለመመለስ እየሞከሩ ናቸው፡፡ እነዚህ በጥባጮች በጠነሰሱት ሴራም የዜጎች ህይወት አልፏል፤ በርካታ የሚሆኑትም ለመፈናቀል ተዳርገዋል፡፡
በመሠረቱ በለውጡ ሰዎች ቢከፉና ቢያኮርፉ አይደንቅም፡፡ መንቀፍም ሆነ መደገፍ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ነው። ከለውጡ ጀርባ ሆነው ነውጥ መቀስቀስም ሆነ ህዝብን በህዝብ ላይ ብሔርን በብሔር ላይ ማነሳሳት ግን ወንጀል ነው። ስለዚህ በለውጡ የተከፉ ሰዎች እንደ እንቦጭ ህዝብና ሀገርን መጉዳት የለባቸውም፡፡ በጥባጮች የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ እያወኩ እንዲቀጥሉ እድል መስጠትም አይገባም። እንቦጭና በጥባጭ በእንጭጩ ካልተቀጩ ሰላም የለም ፤ የሀገርና የዜጎች እድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው።
የሀገርን ሰላም ጤናና ህልውና የሚያውኩ በጥባጮች እንደ እንቦጭ መነቀል አለባቸው። በእነዚህ በጥባጮች እኩይ ድርጊት በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ፣በአዲሰ አበባ ከተማ አቅራቢያ በቡራዩ አካባቢ፣ በድሬዳዋና ሐዋሳ ከተሞች በተፈጠረው ነውጥ ዜጎች ህይወታውን አጥተዋል ፣ቆስለዋል፤ ተፈናቅለዋል፡፡ መንግስትና ህዝብ በወሰዱት እርምጃም በእነዚህ አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋትን መልሶ መምጣት ተችሏል፡፡
በምእራብ ወለጋ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሼ ዞንና በደቡብ ክልል ካፋና ሸካ ዞኖች የለውጥ ሂደቱን ለመቀልበስ፤ ኢፍትሐዊነትን እና ሥርዓተ አልበኝነትን ለማንገሥ የሚፍጨረጨሩ ሀይሎችን ለመቆጣጠር መከላከያና ሌሎች የፀጥታ አካላት በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል።
አሁንም በምሥራቅ ወለጋ ቤንሻንጉል ጉሙዝ በቴፒ በሸካና ከማሼ አካባቢዎች ለውጡ ያስፈራቸው አኩራፊዎች ለውጡን ለማጨናገፍ እየተፍጨረጨሩ ናቸው። ችግሩ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎችም እየታየ ነው፡፡
ወላጆች ተማሪዎቻቸውን ልጆቻቸውን ለትምህርት ሲልኩ መንግሥትም እንደ ወላጅና መምህር ሆኖ ተማሪዎችን ተረክቦ ያስተምራል። ተማሪዎችም ዩኒቨርሲቲን ሲቀላቀሉ ለነገይቱ ኢትዮጵያ የሚበጅ ዕውቀት እንዲሸምቱ እንጂ በብሄርና በብሔር እየተከፋፈሉ እንዲፋጁ እና እንዲሻኮቱ አይደለም።
ዩኒቨርሲቲዎች ዕውቀት የሚገበይባቸው እንጂ ሁከት የሚሸመትባቸው እንዳልሆኑ ተማሪዎች መገንዘብ አለባቸው። የአፍራሽ ሀይሎች ሴራ ማራመጃ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት ለመፍታት መንቀሳቀስ እንጂ ለውጡን ወደሁዋላ ለመመለስ ለሚያስቡ ሀይሎች መሳሪያ መሆን የለባቸውም።
በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በተፈጠረ ግጭት የሰላምና ፀጥታ አስከባሪዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲው አመራሮች ድክመት ጎልቶ ታይቷል። ግጭት የሚያባብሱ ነገሮችን ተማሪዎች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች ማራቅ ይገባል፡፡”ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው” እንደሚ ባለው ግጭት የሚያባብሱ ነገሮች ካሉ ለሚመለከተው አካል ማስረዳት ይገባል፤ ይህም ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለዜጎች ሁሉ የተመረጠ ነው። የሰለጠነ ሽንጡን ገትሮ ሲከራከር ያልሰለጠነ ደግሞ ሽጉጡን ደግኖ ወይም ወድሮ ሊደራደር ይሞክራል። ችግራችን መፍታት ያለብን በጉልበት ሳይሆን በውይይት ነው ።
በዩኒቨርሲቲ ግቢዎች እና አካባቢዎች ፀጥታ አስከባሪዎች እንዲሰማሩ ይደረጋል፤ በአካባቢው የሚሰማሩት ለሰላምና ፀጥታ ዘብ መቆም እንጂ ግጭት ሲከሰት ለመታዘብ አይደለም። አካባቢውን እየዞሩ በመቃኘት ችግሮችን መገመት ሥራቸው ነው፤ በአሶሳ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ገላግለው የፈቱ ፖሊሶች በአካባቢው ቆመው ሁኔታውን መቃኘት ነበረባቸው። በሥፍራው ቢቆዩ ኖሮ ችግሮች አይከሰቱም ነበር።
በመንግሥትም በኩል ችግሩን ለመፍታት እየሠራን ነው የሚለው መግለጫ ብቻውን መፍትሔ አያመጣም። በርግጥም ችግሩን ከሥር መሠረቱ መንጥሮ መጣል ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡ እስከ መቼ ድረስ ነው እንዲህ ዓይነት ችግሮች በየቦታው ሲከሰቱ የሚሰማው። የመንግሥት ትልቁ ላፊነት የሕግ የበላይነትን ማስከበር ነው።
የተለያዩ ነፃ አውጪ ድርጅቶች በተለያየ መልኩ ሲንቀሳቀሱ ቆይተው ለውጡን ዐይተው ጦራቸውን ፈተው ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል። ሰሞኑን ወደ ሀገር የገባው የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር አንዱ ነው። ይህም ፓርቲው በሀገር ውስጥ ሰላማዊ በሆነ መልኩ የፖለቲካ አላማውን ለማራመድ ዝግጁ መሆኑን ያሳያል።
በዚህ ዘመን የሚያዋጣውም ይህ ነው፡፡ ሀሳብን በነጻነት ማራመድ በሚቻልበት በዚህ ዘመን ለመበጥበጥ መንቀሳቀስ ብዙም የዜጎችን ሕይወት ከማመሳቀል ውጪ የሚፈይደው የለም፡፡ በመሆኑም በጥባጮች ራሳቸውን ማስተካከል ካልቻሉ መንግስት ሊያስተካክላቸውይገባል፡፡ ህዝቡም መሳራያቸው ከመሆን መቆጠብ ይኖርበታል፤ የሚወስደውን እያንዳንዱን እርምጃ ቆም ብሎ ማሰብ ይኖርበታል፡፡
በርግጥ ለውጥ በአንድ ጀምበር ያማረና የሰመረ ሊሆን አይችልም፤ የአልጋ በአልጋ ጉዞም አይደለም ፤ብዙ ውጣ ውረዶች ማለፍን ይጠይቃል። ነገር ግን መንግሥት ለዜጎቹ ደህንነት ዋስትና መስጠት አለበት። የሕግ የበላይነትን ማስከበሩ ጉዳይ እሹሩሩ እየተባለ መቀጠል የለበትም። ነውጠኞችን ለህግ በማቅረብ ለዜጎች ሰላምና ፀጥታን ማስከበር ዋና ኃላፊነቱ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ጥቅምት በአውሮፓ ጉብኝታቸው ወቅት የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ‟ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብርታት የሚጠይቀውን ጎዳና መምረጣቸውን ጠቅሰው፣ ‹‹እኛም ከጎናቸው እንቆማለን” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልፀው ነበር። በኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብት፣ ማህበራዊና የባህል ዘርፎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጥ እንዲመጣ ያሳዩት ቁርጠኝነትና ያደረጉት ማሻሻያ በሀገሪቷ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
ዶክተር ዐብይ ከፈረንሳይ ጉብኝት በኋላ ወደ ጀርመን በርሊን በማምራትም ከጀርመን መራሂተ- መንግሥት አንጌላ መርከል ጋር የሁለቱን ሀገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮዎች ዙሪያ ተወያይተዋል። በጉብኝቱም የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርክል በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፤ ጀርመን በቀጥታም ይሁን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅት ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርክል ገልፀዋል።
ቀደም ሲልም በአሜሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ያደረጓቸው ጉብኝቶች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመሳሳይ አድናቆት የተቸረባቸው ናቸው፡፡ ተመድ የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምም ዋስትና ያለው መሆኑን በመጠቆም ለውጡን አድንቀዋል።
ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲናፍቁት የኖሩትንና እጃቸው ውስጥ ያስገቡትን፣ እንዲሁም ሀገሮችና አለም አቀፍ ተቋማት አድናቆት የቸሩትንና ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉ ማረጋገጫ የሰጡትን ይህን ለውጥ መጠበቅ ይገባል፡፡ በለውጡ ተስፋ የቆረጡ አካላት ሁከትን እየመረጡ መቀጠል የለባቸውም፤ መንግሥት በእነዚህ አካላት ላይ አስተማሪ ርምጃ በመውሰድ ለህግ ማቅረብ ግዴታው ነው።
ቀደምሲል እንደገለፅነው በአሁኑ ወቅት ችግሮች ጎልተው ከሚታይባቸው አካባቢዎች መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ይጠቀሳሉ። በቅርቡም በምስራቅ ወለጋ ዞን ተመሳሳይ ችግር ተከስቷል፡፡
ይህን ተከትሎም ከሐሙስ ኅዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. አመሻሽ ጀምሮ ከምዕራብ ወለጋ ዞን ጋር በሚዋሰኑ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዞኖች የፌዴራል ፖሊስን ጨምሮ፣ በርካታ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መሰማራታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ የመንግስት እርምጃ የአካባቢውን ሰላም፣ ደህንነትና መረጋጋት ለመመለስ ተገቢ መፍትሔ እንደሚሆን ይታመናል። ይህን መሰል ርምጃ እንዲወሰድ በሚልም ነው እንቦጭና በጥባጭ በእንጭጩ ይቀጭ ያልነው።