ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ – ኢትዮጵያን በማገልገል

በኢትዮጵያ በአመሠራረታቸው ቀደምት ከሆኑና ለኢትዮጵያውያን ጉልህ አገልግሎት ከሰጡ የሕዝብ ተቋማት መካከል የብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው።

በድሮው ፓስተር_ኢንስቲትዩት በከብት ሕክምና /Imperial Veterinary Laboratory/ ክፍል ስር ሲሰራ የነበረው የአሁኑ ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት የተቋቋመው በ1956 ዓ.ም ነው። በወቅቱ የተመሰረተው ይህ ተቋም፣ በንጉሰ ነገስቱ መልካም ፈቃድ ወደ ቢሾፍቱ ተዘዋውሮ የከብት ሕክምና ኢንስቲትዩት /Imperial Veterinary Institute/ በሚል ነበር።

ኢንስቲትዩቱ በጅማሮው በግብርና ሚኒስቴር እንስሳት ጤና ጥበቃ መምሪያ ስር ተዋቅሮ ለአስተዳርና ለመስክ ሥራ እንቅስቃሴ ከሚኒስትሩ ጽ/ቤት ሲረዳ ነበር። በመቀጠልም ከፈረንሳይ መንግሥት (FRENCH VETERINARY MIS- SION) የቴክኒክ ተራድዖ በመፈቀዱ የነበረውን ውስን የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅም አጠናክሮ ግልጋሎቱን በተሻለ መንገድ ለተጠቃሚው ሲሰጥ ቆየ።

የተለያዩ የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባቶችን እንዲያመርት በቢሾፍቱ ከተማ የተመሰረተ የመንግስት ተቋም ሲሆን፣ እንደገና በመንግስት ልማት ድርጅትነት በአዋጅ ቁጥር 25/84 እንዲሁም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 52/1991 በኢትዮጵያ ጥራት ያላቸው የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባቶችን፣ መድኃኒቶችን እና ባዮሎጂካሎችን እንዲያመርት በተፈቀደ ካፒታል 45 ነጥብ 74 ሚሊዮን ብር ከዚህ ውስጥ ደግሞ በዓይነት እና በጥሬ ገንዘብ 40 ነጥብ 19 ሚሊዮን ብር በመክፈል በ 1991 ዓ.ም ተቋቋመ።

በ2015 ዓ.ም የመቋቋሚያ ደንቡ ተሻሽሎ በመንግስት ልማት ድርጅትነት በአዋጅ ቁጥር 25/84 እንዲሁም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 536/2015 ጥራት ያላቸው የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባቶችን፣ መድኃኒቶችን እና ባዮሎጂካሎችን እንዲያመርት በተፈቀደ ካፒታል 2.6 ቢሊዮን ብር ከዚህ ውስጥ በዓይነት እና በጥሬ ገንዘብ 640 ሚልዮን ብር በመክፈል የተቋቋመ ተቋም ነው።

ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 52/91 የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እየተጋ ያለ ተቋም ነው። እየጨመረ የመጣውን ከተገልጋዮችን ፍላጎት ጋር የተጣጣመ አገልግሎት ለመስጠት ስትራቴጂካዊ የትኩረት መስኮች ለይቶ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። ያለውን ካፒታል ኢንቨስት እያደረገ ተግባሩን ለማሳደግ፣ የእንስሳት መድኃኒት ለማምረትና ለማቅረብ፣ የደንበኞችን ዕርካታን ለማሳደግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል።

የማምረት አቅም፦

ተቋሙ ሲመሰረት ከነበረው ከአራት ዓይነት ክትባቶች ተነስቶ በአሁኑ ጊዜ 23 የተለያዩ የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባቶች አሳድጓል። ማለትም ዘጠኝ በባክቴሪያ እና 14 በቫይረስ ለሚከሰቱ በሽታዎች መከላከያ ክትባቶችን በማምረት ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ደንበኞች እያቀረበም ነው። የተቋሙ ክትባት የማምረት አቅም ጣሪያ ወደ 450 ሚሊዮን መጠን (ዶዝ) የሚጠጋ (448,245,067) ሲሆን፣ ሲመሰረት ከነበረው በዓመት አምስት ሺህ መጠን (ዶዝ) አሁን ወደ 340 ሚሊዮን ዶዝ ያህል (336,605,708) ክፍ ማለት የቻለ ነው።

በተጨማሪም ክትባት ላልተመረተላቸው የእንስሳት በሽታዎች የክትባት ማበልፀግ ሥራና ኢንስቲትዩቱ ከሚያመርታቸው ክትባቶች ውስጥ መሻሻል የሚያስፈልጋቸውን በመለየት የማሻሻል ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል። እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ አዲስ የእንስሳት መድኃኒት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ገንብቶ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፣ ፋብሪካው በአሁኑ ጊዜ ሶስት ዓይነት የተለያዩ የእንስሳት መድኃኒቶችን የሚያመርትና በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ በዓመት በአንድ ፈረቃ (ሽፍት) 12 ነጥብ 12 ሚሊዮን ቦለስ የማምረት አቅም አለው።

የክትባት ማምረት ስራውን የጀመረው ኋላቀር በሚባል የማምረቻ መሳሪያና የአመራረት ዘዴ ሲሆን፣ ቁጥሩ ከ40 በማይበልጥ የሰው ኃይል፣ በዓመት ከሁለት እስከ አራት ሚሊዮን መጠን (ዶዝ) ክትባት ምርት፣ ከአራት እስከ ስድስት የማይበልጡ የክትባት አይነቶችና በ92 ሺህ ብር በጀት ነበር። አቅሙን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ በመምጣት በሰው ኃይል፣ ምቹ የስራ አካባቢ በመፍጠር፣ በመስሪያና ምርት አቅርቦት፤ የጥራት ስራ አመራርን ተግባራዊ በማድረግ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን አጎልብቶ የክትባት ምርቶቹን ለሀገር ውስጥና ለውጪ ደንበኞች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል።

ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት፤ በኢትዮጵያ በእንስሳት ጤና ዙሪያ ከሚሰሩ ተቋማት መካከል ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረና ለሀገሪቱ በዋናነት የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባት በማምረት ታሪክ በግንባር ቀደምትነት የሚነሳ ተቋም ነው። ኢንስቲትዩቱ ከምስረታው ዓመት ከ1956 ዓ.ም እስከ ዛሬ 2016 ዓ.ም ድረስ በእንስሳት ክትባት ምርት፣ የምርምር ሥራዎች በማካሄድ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

የእንስሳት በሽታን በተለይም የደስታ በሽታን ለመከላከልና ለማጥፋት በተደረገው አህጉራዊ ዘመቻ ክትባቶችን በማምረትና በማቅረብ ያበረከተው አስተዋጽኦ በሀገርና በአፍሪካ ደረጃ ምንጊዜም የሚታወሱና እውቅና ካገኘባቸው ሰስኬቶች መካካል የሚጠቀስ ነው።

ተቋሙ፣ በ1982 እ.ኤ.አ የዓለም አቀፍ የወርቅ ሜርኩሪ ተሸላሚ ብቸኛ ኢንስቲትዩት ለመሆን የበቃ ነው። በተለይ በቀንድ ከብት ገዳይነቱ ቀዳሚ ነበር የተባለለትን የሚሊዮኖች አርሶና አርብቶ አደርን ለጉዳት የዳረገውን የደስታ በሽታን ከሀገሪቱ ለማጥፋትና ለመቆጣጠር በተደረገ ዘመቻ የኢንስቲትዩቱ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ይታወቃል። ለዚህም በቅርቡ በኬንያ በተካሄደው የደስታ በሽታ ከዓለም እንዲሁም ከአፍሪካ የጠፋበትን 10ኛ ዓመት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ የደስታ በሽታን ከአፍሪካ ለማጥፋት ተቋሙ ላበረከተው አስተዋጽኦ ከአፍሪካ ሕብረት እውቅና አግኝቷል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ አባይነህ እንደሚናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ሀብት ዘርፉን ከመደገፍና የውስጥ ቴክኖሎጂ አቅምን ከመገንባት ባሻገር የሀገር ኢኮኖሚን ከመገንባት አንፃር ትልቅ እምቅ አቅም አለው።

ባለፉት 60 ዓመታት የእንሰሳት አርቢውን ሕብረተሰብ ዋነኛ ችግሮች የሆኑትን ተላላፊ የእንሰሳት በሽታዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል ከተቋቋመበት ከ1956 ዓ.ም ጀምሮ በክትባት ምርት እንዲሁም በበሽታ ምርምርና ምርመራ ላይ በትጋት ሲሰራ ቆይቷል፤ ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ ደግሞ በእንስሳት መድሃኒት ማቀነባበር ከመንግስት የተሰጠውን ተልእኮ በስኬት እየተወጣ ይገኛል።

እንደ ዶክተር ታከለ ገለፃ፤ ተቋሙ ሲመሰረት ከ10 በማይበልጡ ኢትዮጵያውያን ሰራኞችና በውጭ አገራት የባለሙያዎች ድጋፍ ስራ የጀመረ ነው። በአሁኑ ጊዜ 350 ቋሚ ሠራተኞችን የያዘ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውን ባለሙያዎች የሚሰራ ለመሆን በቅቷል፤ በአሁኑ ወቅት በሀገር ደረጃ ብቸኛ በምርምር የተደገፈ የክትባትና ባዮሎጂካልስ አምራች ተቋም ነው።

ኢንስቲትዩቱ፣ በኢትዮጵያ ጥራት ያላቸው የተለያዩ የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባቶችን፣ መድኃኒቶችን እና ባዮሎጂካሎችን በማምረት ለአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ 85 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የተሰማራበትን የግብርናውን ዘርፍ እየደገፈ የሚገኝ በመሆኑ እያበረከተ ያለው ሀገራዊ አስተዋጽዎ እጅግ ከፍተኛ ነው።

ከዚህም ባሻገር እነዚህ ምርቶች በተቋሙ ባይመረቱ ከውጭ ሀገር ቢገዙ ሊወጣ የሚችለውን የውጭ ምንዛሪ ከማስቀረት አንጻር ሚናው የጎላ ነው።

በተጨማሪም በ60 ዓመት ጉዞ ውስጥ ሀገሪቱ የደስታ በሽታን ለመቆጣጠር እንዲሁም ለማጥፋት ያወጣቸውን መርሃ ግብር ኢንስቲትዩቱ ክትባት በማምረት ሚናውን መወጣቱ ዛሬ ላይ ከዚህ አስከፊና የአርብቶ አደሩን ኢኮኖሚ ካወረደ ገዳይ በሽታ ነጻ ለማውጣት በተደረገው ርብርብ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከስኬት ታሪኮቹ መካከል ተጠቃሽ ነው።

ኢንስቲትዩቱ እስከ ዛሬ ባካበተው ልምድና የአሰራር ሂደትን እንዲሁም ትርፋማነቱን በመገንዘብ አቅሙን መገንባት እንዲያስችለው በሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢንስቲትዩቱ የተፈቀደ ካፒታል ወደ ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር እንዲያድግ መፈቀዱ ታውቋል። እንዲሁም የሰው ክትባት እንዲያመርት የተጠቀመው ሺልድ ክስ ኢንተርፕራይስ ጋር በኢትዮ ባዮፋርማ ግሩፕ በአንድ ጥላ ስር መደራጀቱ የማምረት አቅሙንና የአመራረት ቴክኖሎጂውን ለማዘመን መልካም አጋጣሚ የሚፈጥርለት ይሆናል ሲሉም ዶክተሩ ገልጸዋል።

ዶክተር ታከለ እንደሚሉት፤ አዳዲስ ምርቶችን ወደ ገበያ ሲያስገባ ከሌሎች የቴክኖሎጂ ድጋፍና ሽግግር አድርጎ ሳይሆን በራሱ ምርምር በማድረግና ምርቶችን በማበልጸግ መሆኑ ተቋሙ ምርምርና ስርጸት አዲስ ቴክኖሎጂን የማፍለቅ ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን ያሳያል።

ከዚህ ባሻገር ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ ዓለም አቀፍና ሀገር በቀል ተቋማት ለምርምር የሚደረጉ የፋይናንስ ድጋፍ ውድድሮች ላይ በመሳተፍና በማሸነፍ የኢንስቲትዩቱን የክትባት ምርምር ስራ፤ የላቦራቶሪና የሰው ኃይል አቅም በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ስኬት አስመዝግቧል ይላሉ።

ተቋሙ እንደ ሀገር ለእንስሳት ጤና ዘርፍ ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ በማበርከት የተለያዩ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ እውቅናዎችን አግኝቷል። ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል ለአገር ልማት ባበረከተው አስተዋፅኦ በ1975 ዓ.ም 22ኛው የሰላምና የትብብር ኮንፍረንስ ላይ ዓለም አቀፍ የወርቅ ሜርኩሪና 7ኛው አገር አቀፍ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ላይ በ2008 ዓ.ም ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የወርቅ ሜዳሊያ በመሸለም ሀገራዊ እውቅናዎችን ሁለት ጊዜ አግኝቷል።

በምርታማነቱና በጥራት ሥራ አመራሩ ተወዳዳሪ በመሆኑ የISO 9001:2000፣ 2008፣ 2015 እንዲሁም በምርምር ላብራቶሪዎች የISO 17025፤ 2005፣ 2017 እንዲሁም በመልካም አመራረት ትግበራ እውቅና ማግኘትና ማስቀጠል ችሏል።

በአሁኑ ወቅት ኢንስቲትዩቱ የክትባት ምርቶቹን የመልካም አመራረት ዘዴንና ዘመኑ የደረሰበትን የክትባት አመራረት ቴክኖሎጂ በመተግበር አቅሙን በመገንባት ላይ ይገኛል። የምርቶቹን ተደራሽነትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ እንዲያስችለው አዲስ የክትባት ማምረቻ ላቦራቶሪ ግንባታ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አቅዶ እንቅስቃሴ እንደጀመረ ዋና ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በቀንድ ከብት ሀብት ቀዳሚ ብትሆንም ከዘርፉ መጠቀም ያልቻለችው ዘመናዊ የእንስሳት ሕክምና እና እርባታ ባለመኖሩ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፤ በዚህም ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሀብቷ እንድትጠቀም በዘርፉ ያሉ ተቋማትና የምርምር ስራዎች ሚና ከፍተኛ ነው።

ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሃብቷ ተገቢውን ጥቅም እንዳታገኝ እንቅፋት ከሆኑ ተግዳሮቶች አንዱ የእንስሳት በሽታ ነው። በተለይም ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎች በግና ፍየሎችን የሚያጠቃው ደስታ መሰል በሽታ ሲሆን፣ በዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት እኤአ በ2030 በሽታውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ከስምምነት ላይ መደረሱን እና ኢትዮጵያም እኤአ በ2027 በሽታውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ፕሮግራም ቀርፃ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች፤ በዚህ ረገድ ኢንስቲትዩት እየተወጣው ያለው ሚና ጉልህ ነው።

እኛም በዚህ የባለውለታዎቻችን አምድ ከተመሠረተ ስድስት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረውንና ነገን አርቆ ማሰብ በሚችሉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ተመሥርቶ ዛሬ ላይ በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት ተደራሽ የሆነ የእንስሳት ሕክምና በመስጠት አለኝታ ሆኖ ያገለገለውን አንጋፋ ተቋም እንዲህ አመሰገንን። ሰላም!

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You