እስራኤል በካን ዮኒስ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች

እስራኤል በጋዛ ሁለተኛ ግዙፍ ከተማ በሆነችው ካን ዮኒስ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጠች፡፡

ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በከተማዋ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን የአየር ላይ ጥቃት ቀዝቀዝ ወዳለባት ራፋ ለመጓዝ ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል፡፡

በደቡባዊ የጋዛ ክፍል በአዲስ መልክ የተጀመረውን አዲስ ጥቃት ተከትሎ እስካሁን ስምንት ሰዎች ሲሞቱ ከ30 የሚልቁት ደግሞ መቁሰላቸው ተሰምቷል፡፡

የምድር ላይ ዘመቻው የተጀመረው በካን ዮኒስ አካባቢ ከሃማስ ጋር በትብብር ይዋጋል የሚባለው ኢስላሚክ ጃሐድ የተሰኘው ታጣቂ ሮኬት ወደ እሥራኤል መተኮሱን ተከትሎ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የእሥራኤል ጦር 20 ሮኬቶች ከካን ዮኒስ መተኮሳቸውን እና አብዛኞቹን ማክሸፍ መቻሉን ነው ያስታወቀው፡፡

የካን ዮኒስ ነዋሪዎች በእጅ ስልኮቻቸው ላይ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የድምፅ መልዕክት እንደደረሳቸው የተናገሩ ሲሆን፤ አልማዋሲ ወደ ተሰኘው በእሥራኤል ጦር ቁጥጥር ስር ወደሚገኝው ስፍራ እንዲያቀኑ እንደተነገራቸውም ነው የገለጹት፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እሥራኤል አዲስ የጀመረችው የምድር ላይ ዘመቻ በጋዛ ለንጹሐን ደህንነት ዋስትና የሚሆን ምንም ስፍራ እንዳይኖር የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

በሃማስ እና እስራኤል መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እስካልተደረሰ ድረስ ይህ ደም አፋሳሽ ጦርነት የንጹሐንን ሕይወት መቅጠፉን አያቆሙም ያሉት ዋና ጸሐፊው ፍልስጤማውያን ከጥቃት የሚደበቁበት ምንም አይነት ስፍራ በጋዛ የለም ብለዋል፡፡

የእሥራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦሩ ሀማስን ለማጥፋት መቃረቡን በገለጹበት በትላንትናው ንግግራቸው ጥቃቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተፈናቀሉ ሲሆን በአካባቢው በቂ እርዳታ አለመድረስ ከፍተኛ ረሀብን ሊያስከትል እንደሚችል የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በማስጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን የዘገበው አል ዓይን ነው፡፡

ከ8 ወራት በላይ በዘለቀው የጋዛ ጦርነት እስካሁን 37 ሺህ 900 ንጹሐን ሕይወታቸውን ሲያጡ ከ80 ሺህ የሚልቁት ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

አሜሪካ እና የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም መሪዎች በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም ተደርጎ ጦርነቱ እንዲቋጭ ጥሪ ቢያቀርቡም ሁነኛ መፍትሔን ገቢራዊ ማድረግ ተስኗቸው ጦርነቱ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You