ለውጥ ከተስፋ ውስጥ የሚወለድ፤ በብዙ ተግዳሮት የሚፈተን፤ ስለተስፋ በፈቃደኝነት እና በቁርጠኝነት ብዙ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁነት እና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ማኅበረሰባዊ ንቅናቄ ነው ። ስኬታማነቱ የሚሰላውም ይህንኑ መሠረታዊ አውነታ ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ይታመናል።
የብዙ ገፊ ፍላጎቶች ድምር ውጤት ከመሆኑ አንጻርም ፤ ፍላጎቶችን አቻችሎ እና አጣጥሞ ከመሄድ ባለፈ፤ በፈተናዎች ውስጥ ያሉ ዕድሎችን ፈልቅቆ በማውጣት በለውጥ እሳቤ፤ በተለወጠ ማንነት ወደሚጨበጥ ተስፋ መለወጥ ያስፈልጋል።
በተለይም አሁን ባለንበት ዓለም አቀፋዊ እውነታ፤ ሀገራት በየራሳቸው የውስጥ ጉዳይ በፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ በተገደዱባቸው ሁኔታዎች ውስጥ የማኅበረሰብን የለውጥ ፍላጎቶች ለማሳካት የሚደረግ ጥረት በተለመደው መንገድ ውጤታማ ማድረግ የሚቻል አይደለም ።
ከተለመደው የአስተሳሰብ መስመር ወጥቶ ማሰብ የሚያስችል የአመራር ዝግጁነት መፍጠር ፤ ከተለመደው መስመር መውጣት ሊያስከትል የሚችለውን ተቃውሞ ፣ ውግዘት እና ጫና መሸከም የሚያስችል ቁርጠኝነት፤ ከሁሉም በላይ ሕዝባዊነትን መገንባት ያስፈልጋል።
በተለይም ከኋላቀርነት እና እሱ ከሚፈጥረው ድህነት እና ጠባቂነት ለመውጣት የሚደረግ የማኅበረሰብ ንቅናቄ፤ በየትኛውም መመዘኛ በተለመደው መንገድ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፤ እስካሁን ያለውም ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮ/ ትርክት ይህንኑ እውነታ የሚሸከም ነው ።
የተለመዱ መንገዶች በየትኛውም መመዘኛ የማኅበረሰብ የለውጥ መሻት ተጨባጭ ማድረግ አይቻልም። ይችላል በሎ ማሰብ እና ለመጓዝ መንቀሳቀስ፤ ለውጥ እና የለውጥ መሻቶችን በአግባቡ ካለመረዳት የሚመነጭ ብዙ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ነው።
ቀደም ባሉት ጊዜያት በእኛም ሀገር የተካሄዱ የለውጥ ንቅናቄዎች ፤ የተጓዙበት መንገድ በዘመነ መሳፍንቱ የአስተሳሰብ መሠረት ላይ የተገነባ በመሆኑ፤ ሕዝባችን ከእያንዳንዱ ለውጥ የፈለገውን ማግኘት ሳይችል ቀርቷል።
የለውጥ ዋዜማ ተስፋዎቹ የቅዠት ያህል ሆነውበት ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል ተገድዷል። በለውጥ ስም በሄድንባቸው የታሪክ ምዕራፎች፤ ሕዝባችን የሚሻትን የተለወጠች ሀገር ከመፍጠር ይልቅ፤ ለዘመናት ጸንታ የቆመችባቸው ምሰሶዎች የተናጉባቸው ናቸው።
ማኅበረሰባዊ ማንነታችን፤ የቀደመ ታሪካችንን እና የመሆን መሻችንን በአግባቡ ታሳቢ ያላደረጉ የለውጥ ታሪኮቻችን፤ በየምዕራፋቸው፤ አብሮነታችንን ፤ ብሔራዊ ማንነታችንን ከዚያም በለፈ ሀገረ መንግሥቱን ፈተና ላይ በሚጥሉ ክስተቶች የተሞሉ ነበሩ።
ይህን አውነታ ለመለወጥ፤ ከአምስት ዓመት በፊት እንደሀገር የጀመርነው ለውጥ፤ በብዙ ተስፋ ቢጀመርን፤ ለውጡ ከውስጥም ከውጭም ካጋጠሙት ተግዳሮቶች የተነሳ በብዙ መጎረባበጦች ውስጥ ለማለፍ ተገድዷል። በዚህም የለውጥ ሃይሉ በብዙ ተፈትኗል ።
ከተለመደው አስተሳሰብ ወጣ ብሎ ለውጡን ለመምራት የተደረገው ሙከራ አንድም፤ በአሮጌ /ሙት አስተሳሰብ ሁለንተናው በተያዘ ቡድን እና ግለሰብ፤ ከዛም በላይ አስተሳሰቡ በፈጠረው እብሪት እና ጽንፈኝነት በፈጠረው አደጋ ፈተና ውስጥ ወድቋል ።
ይህ ሆኖ ግን የለውጥ ሃይሉ በፈተና ውስጥ ያሉ እድሎችን ነቅሶ በማውጣት፤ በተለወጠ ማንነት እና በአዲስ የለውጥ መንገድ የሕዝቡን የለውጥ መሻት ተጨባጭ ሊያደርጉ የሚችሉ ተስፋ ሰጪ ጅማሬዎችን ተግባራዊ አድርጓል፤ እያደረገም ነው።
የሀገሪቱን የፖለቲካ ባህል ከአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት በማውጣት፤ ሀገር እና ሕዝብ አሸናፊ የሚሆኑበትን አዲስ አቃፊ እና አካታች፤ ከጠበንጃ ወደ ጠረጴዛ የሚወስድ የፖለቲካ ባህል እውን ለማድረግ በሃላፊነት እየተንቀሳቀሰ ነው።
አለመግባባቶችን በኃይል ከመፍታት ይልቅ ባሉ አማራጮች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተንቀሳቅሷል። ከሕወሓት፤ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር የነበረውን እና ያለውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ረጅም ርቀት በመጓዝ አስመስክሯል ።
በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ባልታየ መንገድ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን የካቢኔ አባላት እስከ ማድረግ የዘለቀ ተጨባጭ ርምጃዎችን ወስዶ ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሀገር ግንባታ ያላቸውን አቅም ተግባራዊ የሚያደርጉበትን መልካም ዕድል ፈጥሯል።
ሀገሪቱ በብዙ ፈተናዎች ባለፈችበት ሁኔታ ውስጥ፤ ፈተናዎች የሚፈጥሯቸውን ዕድሎች ነቅሶ በማውጣት ፤ ዕድሎቹን በአዲስ ዕይታ እና በተለወጠ ማንነት ወደ ልማት በመለወጥ፤ በሀገሪቱ ላይ የተነገሩ ብዙ ሟርቶችን መቀልበስ ችሏል።
ፈተናዎችን ተሸክሞ ማሻገር የሚያስችል ኢኮኖሚ ከመገንባት ጀምሮ፤ በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚደረጉ ጥረቶች ከተስፋ አልፈው ተጨባጭ የለውጥ ትሩፋት የሆኑበት ሀገራዊ ትርክት ተፈጥሯል።
ሀገረ መንግሥቱን በተሻለ መሠረት ላይ ማጽናት የሚያስችሉ የተቋማት ግንባታዎችን በስኬት አከናውኗል ። ሀገሪቱን ከትናንት በተሻለ መልኩ ከየትኛውም ስጋት መታደግ የሚያስችል የመከላከያ እና የጸጥታ አቅም መገንባት ተችለዋል።
የለውጥ ኃይሉ በፈተና ውስጥ ያሉ ዕድሎችን ነቅሶ በማውጣት፤ በተለወጠ ማንነት እና በአዲስ የለውጥ መንገድ የሕዝቡን የለውጥ መሻት ተጨባጭ ለማድረግ እስካሁን የሄደበት መንገድ ካስገኘው ውጤት ይልቅ ወደፊት ይዞት የሚመጣው ሀገራዊ የለውጥ ትሩፋት የበለጠ እንደሚሆን ይታመናል።
በተለይም መላው ሕዝብ የለውጡን ኃይል የተለወጠ አዲስ አተያይ በአግባቡ ከተረዳ እና፤ለለውጥ ሃይሉ ሁለንተናዊ አቅም መሆን ከቻለ፤ የተለወጠች ሀገር የማየት እና ለትውልዶች የማሸጋገር መሻቱ፤ ከምኞት ወደሚጨበጥ የታሪክ ትርክት የሚለወጥበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2016 ዓ.ም