የ2017 ዓ.ም የፌዴራል መንግሥት በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ሆኖ ፀደቀ

አዲስ አበባ፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2017 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት በጀትን 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንዲሆን በሙሉ ድምጽ አፀደቀ።

የ2017 ዓ.ም የፌዴራል መንግሥት በጀት የመንግሥትን ዕቅድ ለማሳካት ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ስለመሆኑ ምክር ቤቱ ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበትና 36ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ተገልጿል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በቋሚ ኮሚቴው የተዘጋጀውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል።

የ2017 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ሲዘጋጅ የመካከለኛ ዘመን የልማትና የኢንቨስትመንት እቅድን እንዲሁም የሁለተኛውን የሀገር በቀል እኮኖሚ ማሻሻያ የፊስካል ፖሊሲ ዓላማን መሠረት እንዳደረገ ጠቅሰዋል።

የ2016 በጀት ዓመት የወጪ አፈጻጸም ሂደትን በመገምገም እና በቀጣይ ዓመት ለሚተገበሩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገቶችን ለማፋጠን በሚያስችል መልኩ እንዲሁም ሊኖሩ የሚችሉ የፋይናንስ አቅሞችን በማገናዘብ መዘጋጀቱን አመላክተዋል።

በበጀት አሸፋፈን ራስን የመቻል አቅጣጫን የተከተለ እንዲሁም የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ድህነት ተኮር ለሆኑ ተግባራት ትኩረት የሰጠ የፕሮግራም በጀት አሠራርን መከተሉንም አቶ ደሳለኝ አብራርተዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት ላይ እንደተመላከተው የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር ሕግና ደንብን አክብሮ በመሥራት በኩል በባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በተደጋጋሚ ጉድለት እንዳለ መገለጹን በማስታወስም፤ በቀጣይ እንዳይደገምና ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የተመደበላቸውን በጀት ለታለመለት ዓላማ በውጤታማነት ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸው ተጠቁሟል።

የሚፀድቀውን በጀት የመንግሥትን የፋይናንስ የግዥና የንብረት አስተዳደር ሕጐችን እና ሥርዓቶችን ተክትለው ሥራ ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል። ይህንንም ለማረጋገጥ የክትትልና የቁጥር ሥራውን በማጠናከር ከሥርዓት ውጭ ለሚደረግ የበጀት አጠቃቀም ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ማሳሰቢያ ተሠጥቷል።

የሀገር ትልቁ የገቢ ምንጭ ታክስ መሆኑን ያመለከተው የውሳኔ ሃሳቡ፤ ታክስ በመሰብሰብ ያጋጠሙ ችግርችንና በታክስ ከፋዩ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

የታክስ አስተዳደሩን በማዘመንና ቀልጣፋ በማድረግ እንዲሁም ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ታክስ መሰወርና ግብር አለመክፈል ተገቢ አለመሆኑን በመገንዘብ ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ለ2017 ዓ.ም የተያዘውን የታክስ ገቢ እቅድ 612 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ወጪን ለመሸፈን ከፍተኛ ሥራ እንደሚሠራም አመላክቷል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You