ከእስር ቤት ሽጉጥ ነጥቀው ያመለጡት የፓኪስታን እስረኞች

ፓኪስታን ከምታስተዳድረው የካሽሚር ግዛት 18 እስረኞች ማምለጣቸው ተነገረ፡፡

እስረኞቹ የማረሚያ ቤት ጠባቂ ሽጉጥ በመቀማት አስፈራርተው ከእስር ቤት ማመለጣቸው ነው የተሰማው። ራዋላኮት ከተሰኘው እስር ቤት ካመለጡት እስረኞች መካከል ስድስቱ የሞት ፍርደኞች ሲሆኑ ሦስቱ ደግሞ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት የተፈረደባቸው እንደሆኑ ታውቋል፡፡

የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ ሪያዝ ሙግሀል ከእስረኞቹ መካከል አንደኛው ከፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ ማለፉን የተናገሩ ሲሆን ቀሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከፍተኛ አሰሳ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መሰል የእስረኞች ማምለጥ በፓኪስታን ያልተለመደ በመሆኑ ጉዳዩ አጋጣሚ ወይስ ታስቦበት የተደረገ ነው በሚል ምርመራ እየተከናወነ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

እስረኞቹ በወቅቱ በጥበቃ ላይ የነበረ የማረሚያ ቤት ፖሊስ እጅ ላይ ሽጉጥ በመንጠቅ ከእስር ቤት ማምለጣቸው ሲነገር ሁኔታው አጋጣሚ ስለ መሆኑ ከፍተኛ ጥርጣሬን አጭሯል፡፡

በአሁኑ ወቅት የእስር ቤቱን ዋና ኃላፊ ጨምሮ በቀኑ ተረኛ የነበሩ ጠባቂዎች ከሥራ የታገዱ ሲሆን ምርመራው በነዚህ አካላት ላይ ያተኩራል ነው የተባለው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን እስረኞች ሲኖሩ አሜሪካ በቁጥር ቀዳሚዋ ናት በሀገሪቱ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ እስረኞች የሚገኙባት ሲሆን ቻይና በ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን እስረኞች ትከተላለች፡፡

ብራዚል፣ ሕንድ፣ ቱርክ፣ ሩሲያ እና ሜክሲኮ በርካታ እስረኞች ከሚገኙባቸው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ። በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ከተለያዩ እስር ቤቶች ያመልጣሉ፡፡

ጠንካራ የእስር ቤት ጥበቃ እና ሥርዓት እንዳላት የሚነገርላት አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ እስረኞች ከሚያመልጡባቸው ሀገራት መካከል በአንደኛ ደረጃ ትገኛለች። እ.አ.አ. በ2019 ከአሜሪካ የተለያዩ እስር ቤቶች 2231 እስረኞች ማምለጥ ችለው ነበር፡፡

ጤናማ የእስረኞች ምጣኔ ከመቶ ሺህ ሰዎች መካከል 140 ሰዎች ብቻ ሊሆኑ እንደሚገባ የሚነገረው የመንግሥታቱ ድርጅት፤

ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር እንዲሁም ሰዎች ሕግን በራሳቸው እጅ ለማስከበር የሚወስዱት እርምጃ መጨመር ወንጀሎች እንዲበራከቱ እና የእስረኞች ቁጥርም በዛው ልክ እንዲያሻቅብ ምክንያት መሆኑን ድርጅቱ በስጋት መልክ ያነሳዋል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You