ሰሜን ኮሪያ የቴሌቪዥን ስርጭቷን ወደ ሩሲያ ሳተላይት ቀየረች

ሰሜን ኮሪያ የቴሌቪዥን ስርጭቷን ወደ ሩሲያ ሳተላይት ቀየረች

ሰሜን ኮሪያ የመንግሥት ቴሌቪዥን ስርጭቶች የሚተላለፉበትን ከቻይና ወደ ሩሲያ ሳተላይት መቀየሯን የደቡብ ኮሪያ ዩኒፊኬሽን ሚኒስቴር ገልጿል።

ይህ ክትትል ለሚያደርጉ የደቡብ ኮሪያ የመንግሥት ኤጀንሲዎች እና ሚዲያዎች አስቸጋሪ ያደርገዋል ተብሏል።

የሰሜን ኮሪያ ሴንትራል ቴሌቪዥን ስርጭት ቀደም ሲል ይተላለፍ የነበረበትን ቻይናሳት12 ሳተላይት በመተው በሩሲያው ኤክፕረስ103 ሲተላለፍ መታየቱን ሮይተርስ የደቡብ ኮሪያውን የዲሽ አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል።

የሳተላይት ቅየራው የተካሄደው፣ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፒዮንግያንግ ጉብኝት ካደረጉ እና ከመሪው ኪም ጆንግ ኡን ጋር ወታራዊ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ነው።

የሰሜን ኮሪያን ቴሌቪዥን አሁንም በኦንላይን ማየት ቢቻልም፣ ጥራቱ አነስተኛ ነው።

የሚተላለፉት ይዘቶች በእቅድ የተዘጋጁ እና ፖለቲካዊ ቢሆኑም ዝግ ከሆነችው ሀገር የሚገኘው መረጃ ውስን ስለሆነ የደቡብ ኮሪያ መንግሥት እና ሚዲያዎች የሰሜን ኮሪያን ሚዲያዎች ይከታተላሉ።

ሰሜን ኮሪያ የቴሌቪዥን ስርጭቷን ወደ ሩሲያ ሳተላይት ካዛወረች በኋላ የሳተላይት ስርጭቱ በተወሰኑ የደቡብ ኮሪያ ቦታዎች እንደማይሠራ የገለጸው የዩኒፊኬሽን ሚኒስቴሩ የቴክኒክ ችግሩን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን አክሎ ገልጿል።

በደቡብ ኮሪያ የተፈቀደላቸው አካላት የሰሜን ኮሪያን ሚዲያዎች ይመለከታሉ፤ የደቡብ ኮሪያ ሕዝብ ግን እንዲያይ አይፈቀድለትም።

ሩሲያ በአሜሪካ የሚመራውን የምዕራባውያን ጥምረት ለመገዳደር ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ስታሳድግ፣ ቻይና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ሊያወሳስብ የሚችል ስምምነት ከማድረግ ታቅባለች።

ፑቲን እና ኪም በቅርብ በፒዮንግያንግ በፈረሙት የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት፣ ጥቃት በሚሰነዘርባቸው ወቅት አንዳቸው ለሌላኛቸው ሁሉንም አይነት ወታደራዊ ድጋፍ ይሰጣል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You