በዩክሬን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ለማድረግ ሲያሴሩ ነበር የተባሉ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በዩክሬን መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ እና አመፅ ለማስነሳት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰምቷል፡፡

ቪቼ በሚል መጠሪያ የተሰየመው ቡድን አባላት በዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ ብጥብጥ እና አመፅ ለመቀስቀስ እንዲሁም ፓርላማውን ለመቆጣጠር አቅደው እንደነበር ተደርሶበታል ነው የተባለው፡፡

የዩክሬን ብሔራዊ ደኅንነት አገልግሎት ባወጣው መረጃ ቡድኑ ፓርላማውን ከመቆጣጠር ባለፈ ቁልፍ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮችን ከኃላፊነት ለማንሳት አሲሮ እንደነበር ገልጿል፡፡

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ለማድረግ አቅደው የነበረው ባሳለፍነው ዓርብ በአደባባይ በተከበረው የሕገ መንግሥት ቀን ሕዝባዊ አመፅ ካስነሱ በኋላ እሁድ እለት መፈንቅለ መንግሥቱን ለማድረግ እቅድ ይዘው እንደነበር ነው የተነገረው፡፡

በስም ያልተገለጹ የዩክሬን እና የውጭ መገናኛ ብዙኃን መፈንቅለ መንግሥቱን ለመዘገብ ዝግጅት ስለማድረጋቸው እንደተደረሰበት በደኅንነት ተቋሙ ሪፖርት ላይ ይፋ ተደርጓል፡፡

በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤት ውስጥ በርካታ ተቀጣጣይ ፈንጆች፣ የተለያየ አይነት የጦር መሣሪያዎች፣ ኮምፒውተሮች እና የመገናኛ መሣሪያዎች ተይዘዋል፡፡

የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ነው የተባለ ግለሰብ ቁጥራቸው እስከ ሁለት ሺህ የሚጠጉ የታጠቁ ቅጥር ወታደሮችን መልምሎ የዩክሬን ፓርላማን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ዝግጅቶችን አጠናቆ እንደነበር ነው የተነገረው፡፡

የዩክሬን ብሔራዊ ደኅንነት አገልግሎት ግለሰቦቹ ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዳለው የገለጸ ሲሆን፤ በይፋ ሩሲያን ለመወንጀል የሚያስችል ሁነኛ መረጃ ግን በእጁ ላይ እንደማይገኝ ገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሕገ መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ ሙከራ ክስ የቀረበባቸው ተጠርጣሪዎቹ ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ እስከ 10 ዓመት ጽኑ እሥራት የሚጠብቃቸው ይሆናል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You