“24 ሰዓት የሕዝብን ሕይወት ለመለወጥ የሚተጋን መንግሥት ሕዝቡ ካላመነ ማንን ያምናል?” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው እለት በፓርላማ በመገኘት ከአባላቱ ለተነሱ የሠላም፣ የኢኮኖሚያ፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የዲፕሎማሲያዊ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። እኛም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽ እና ማብራሪያ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቅርበነዋል ።

የተከበሩ አፈ ጉባኤ፣ የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት ዓመቱን በሙሉ እጅግ ሰፋፊ ሥራዎች ስትሠሩ ቆይታችሁ የዚህን ዓመት ሥራ የምታገባድዱበትና ለሚቀጥለው ዓመት ሥራ ዝግጅት ለማድረግ ወደየአካባቢያችሁ ሄዳችሁ የቁጥጥር፣ የክትትል፣ የሥልጠና ሥራ ለመሥራት በምትዘጋጁበት ጊዜ ላይ እንኳን በሠላም አደረሳችሁ ማለት እወዳለሁ።

ለተነሱት ጥያቄዎች በተቻለ መጠን መረጃ መስጠት በሚያስችል መልኩ ምላሽ ለመስጠት ሙከራ አደርጋለሁ። ሙከራዬን የምጀምረው በኢኮኖሚ ጉዳዮች ይሆናል ።

በመጀመሪያ የተከበረው ምክር ቤት በውል እንደሚገነዘበው በዚህ ዓመት፣ ባለፈው ዓመት፣ ከዛም ቀድሞ በነበረው ዓመት አጠቃላይ ዓላማችን ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ በተከታታይ አንዱ ያመጣውን ጦስ ማብረድ ሳንችል፣ ሌላ ጦስ፣ ሌላ አደጋ፣ ሌላ ችግር እያስከተለ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ነው ያለነው። ወረርሽኝ፣ ጦርነቶች፣ በቅርቡ በእኛ ቀጣና የገጠመው የቀይ ባሕር ወይም ደግሞ የኤደን ባሕረ ሰላጤን /ገልፍ ኦፍ ኤደን/ አካባቢን ያጋጠመውን ችግር ጨምሮ የዓለም ኢኮኖሚን፣ የዓለምን የንግድ እንቅስቃሴን በከፍተኛ ደረጃ ያወከ ያም ሁከት በተሟላ መንገድ ያልረገበ፣ የዓለምን ኢኮኖሚ እየየፈተነ ያለ ሁኔታ ይታያል።

እነዚህን በቅርብና በሩቅ ያሉ አደጋዎችና ጦሶች ወደእኛ ሲመጡ፣ በሙሉ አቅማቸው የእኛን ኢኮኖሚና ጉዞ ሊገዳደሩ በሚያስችላቸው ሁኔታ አደጋ ገጥሞን ነበር። በወረርሽኝ፣ የውጪ ጦርነት ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥ ያጋጠመን የእርስ በርስ ግጭት እነዚህ ሁሉ ተደማምረው የኢኮኖሚ ጉዞው በጣም ፈታኝ፣ በጣም አታካች፣ ያለሙትን፣ የፈለጉትን ለመጨበጥ በእጅጉ መትጋት የሚጠይቅ ዘመን ሆኗል።

ይሄን ችግር እኛ ከዓለም ጋር በጋራ የምንቋደሰው፣ የምንወርሰው፣ የምንጋራው ቢሆንም፣ እኛ በተለይ የለውጡ መንግሥት በተለየ ደግሞ የገጠሙን ተግዳሮቶች ነበሩ። አንደኛው የወረስንው ዕዳ ነው። እንደሀገር ከፍተኛ የዕዳ ቀንበር ትከሻዋን ያጎበጣትን ሀገር ነው የተረከብነው። የውጪ ዕዳ፣ የሀገር ውስጥ ዕዳ። በርካታ ፕሮጀክቶች በእናንተም ሲገለጡ የነበሩ ብዙ ቃል የተገቡ ግን ፈቀቅ ማለት ያልቻሉ ሰፋፊ ሥራዎች የቆሙበት ሁኔታ ነበር።

ዓለም ላይ ከገጠመው ፈተና በተጨማሪ እኛ የተረከብነው ዕዳ ተጨምሮ መሮጥ በሚገባን ልክ ለመሮጥ የራሱ የሆነ ፈተና የተጋረጠብን ቢሆንም፣ ከፈተናዎች መካከል፣ ከፈተናዎች ውስጥ ዕድልን ፡(ኦፖርቹኒቲን) ፈልቅቆ የማውጣት እና የመጠቀም አካሄድ፣ በተቀየረ አመለካከት፣ በተቀየረ የአሠራር ሥርዓት፣ በተቀየረ አሠራርና የሥራ ባሕል መከተል በመቻላችን እጅግ እጅግ አስደማሚ በሆነ መንገድ ስኬታማ ዓመት ነው ያሳለፍነው።

በዚህ ዓመት እጅግ አስደማሚ ውጤቶች ያመጣንበት በእያንዳንዱ ሴክተር በድል በኩራት ሊገለጹ የሚችሉ ውጤቶች የተገኙበት ነው። ይሄ ቦግ እልም እንዳይል በሚቀጥለው ዓመት በዚሁ መንገድ ማስቀጠል ከቻልን ያለምንም ጥርጥር ከችግሮቻችን ተገላግለን ብልጽግናችንን ለማረጋገጥ በሚያስችል ጉዞ ላይ እንዳለን በሁሉም አመላካች በሚታይ እጅግ አስደማሚ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ይታያሉ።

የተከበረው ምክር ቤት እንደሚገነዘበው የአንድ መንግሥት የልማት፣ የማኅበራዊ ጉዳዮች ትልሞቹን የማሳኪያ የሀብት ምንጮች በቅድሚያ /ፕራይፐሊ/ ሁለት ናቸው። አንደኛው ግብር ነው። ሁለተኛው ዜጎች የሚቆጥቡትን ገንዘብ ተበድሮ ልማታዊ በሆኑ መስኮች ኢንቨስት ማድረግ ነው።

ከግብርና በቁጠባ ከተገኘ ሀብት ውጪ ያሉ የመንግሥታት የሀብት ምንጮች እንደ እርዳታና ብድር ያሉት ቋሚ የሀብት ምንጮች ተደርገው አይወሰዱም፤ ከሁኔታ ጋር የሚቀያየሩ ናቸው። የመንግሥታትን የልማት ትልም ለማሳካት ቋሚ የልማት ምንጭ የሚሆነው ግብርና የዜጎች ቁጠባ ነው። ያንን ሀብት ወደ ልማት ሳይክል በማስገባት ሀገራት ሊለወጡ ሊቀየሩ ይችላሉ።

የእኛን ሥራዎች መመዘን ያለብን እነዚህ ሁለት የሀብት ምንጮች ለመንግሥት ምን አስገኙ፣ መንግሥት እነሱን ተጠቅሞ ምን ሠራ የሚለውን ስናይ ስኬቶቻችንን፣ ሌብነት ላይ ያለውን ፈተና በሚዛን ለመገንዘብ ያግዛል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ የፌዴራል መንግሥት ከስልሳ አራት ሺህ ግለሰቦችና ቡድኖች ወይም ኩባንያዎች ግብር ይሰበስባል። ስልሳ አራት ሺ ሰዎች ከፍለውት መቶ ሃያ ሚሊዮኖች ሰዎች ይጠይቁታል። ስልሳ አራት ሺ ሰዎች የሚከፍሉት ግብር ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ሀብት ጋር በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ በምንፈልገው ልክ፣ በምናስበው ልክ በሁሉም መስክ ልማት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመምራት ለማምጣት እንቸገራለን።

ምናልባት ግብር በበቂ ደረጃ እስኪሰበሰብ እንደዚህ ቀደሙ በብድር ይሠራ እንዳይባል ዕዳ ያጎበጠው ኢኮኖሚ ስለሆነ ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ ምንም አይነት

ኮሜርሻል ብድር አንበደርም ብለን አንድ ዶላር ኮሜርሻል ብድር ላለፉት ስድስት ዓመታት አልወሰድንም። በአንጻሩ ኢትዮጵያ የነበረባት ዕዳ ወደ ልጆቻችን መሸጋገር የለበትም በሚል ጽኑ እምነት ዛሬ ኢትዮጵያ ያለባት የውጭ ዕዳ ወደ 17 ነጥብ አምስት በመቶ ከጂዲፒ ዝቅ ብሏል። ይሄ ትልቅ ድልና ትልቅ ዜና ነው።

ይሄ የምነግራችሁ ቁጥር ከሰሐራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገሮች በአማካይ የጂዲፒአቸው ስልሳ በመቶ ዕዳ ነው። ከዛም በላይ ዕዳ ያለባቸው ሀገራት አሉ። ወደ 17 በመቶ ማውረድ መቻል በጣም በጣም ተስፋ ሰጪ ቢሆንም በሚቀጥሉት ዓመታት በሚደረጉ ርብርቦች ከ10 በመቶ በታች መውረድ አለበት።

ከፍተኛ ዕዳ ያለባቸው ሀገራት ዕዳው ማቹር ሲያደርግ /እየበዛ ሲሄድ/ የሚያገኙትን ገቢ በሙሉ ዕዳ ለመክፈል ስለሚያውሉ አዳዲስ የልማት እቅድ ለመያዝ ይቸገራሉ። አፍሪካውያን ወንድሞቻችን በአማካይ ስልሳ በመቶ ከጂዲፒያቸው ዕዳ ባለበት ጊዜ ኢትዮጵያ 17ነጥብ አምስት በመቶ ደርሳለች የሚለውን አስደማሚ ዜና አቅልለን አናየውም። ይሄን ውጤት ለማምጣት የከፈልንውን ዋጋ ስለምናውቅ።

ሳንበደር ባለፉት ዓመታት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከዚህ ቀደም ተበድራችሁታል የተባለን ሀብት ስንከፍል ቆይተናል። በዚህ ምክንያት ወደልጆቻችን ዕዳ እንዳይሻገር አንድ ርምጃ ወደፊት መጓዝ ችለናል። ተጨማሪ ርምጃዎች ግን ይጠበቅብናል።

የዓለምን አጠቃላይ ሁኔታ፣ የእኛን ሁኔታ፣ ገቢያችንን፣ የዕዳ ጫናዎችን ከተገነዘብን በኋላ በእያንዳንዱ ማክሮ አመላካች ደግሞ ምን ነበር የሠራነው የሚለውን ማየት ለተነሳው ጥያቄ በቂ ምላሽ ለመስጠት ያግዛል።

የመጀመሪያው ማየት የሚገባን ገቢና ወጪያችንን ነው። በዚህ ዓመት መንግሥት 529 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ባለፉት አስራ አንድ ወራት /የዚህ ወር አልተጠቃለለም/ 466 ቢሊዮን ብር ወይም 96 በመቶ ገቢ ሰብስቧል። ይሄን በደረቁ ከአምናው ጋር ስናወዳድረው ከፍተኛ መሻሻል ያለው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ምክንያቱም እቅዱን እናንተም እንደምታውቁት የተለጠጠ /በጣም አምቢሽየስ/ ስለነበረ ከዚህ አንጻር ስኬቱ በቀላሉ አይታይም።

በወጪ ደግሞ ስንመለከት 730 ቢሊዮን ብር ለማውጣት አቅደን 716 ቢሊዮን ብር ወጪ ወይም 98 በመቶ አውጥተናል። በወጪያችንና ገቢያችን መካከል ያለው የበጀት ጉድለት /በጀት ደፊሲት/ አሳሳቢ በሆነ መንገድ መታየት ያለበት የበጀት ጉድለት የሚያመጣው ጫና /ኮንሲኮዮንስ/ ስላለው ነው።

ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ የበጀት ጉድለት እናንተም እንደምታውቁት ከጂዲፒያችን አራት በመቶ ነበር። ይህን ዘንድሮ ወደ ሁለት ነጥብ አምስት በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል። ይህ በራሱ ትልቅ ውጤት ነው፤፤ ነገር ግን ሁለት ነጥብ አምስት በመቶ የበጀት ጉድለት ከምን ምንጭ ነው የምንሞላው የሚለውን ካልመለስን ደግሞ ገቢ ቅድም እንዳነሳሁት የራሱ ውስንነት ስላለበት የገንዘብ ምንጩ ሌሎች የማክሮ አመላካቾችን /ኢንዲኬተሮችን/ ሊያናጋ ይችላል። ለምሳሌ ኢንፍሌሽንን። ለዚህም ጤነኛ የሆነ የበጀት ጉድለት አጠቃቀምን ለመከተል በፖሊሲያችን በግልጽ አመላክተን በሪፎርሙ ውስጥ እንዲታይ ለማድረግ ተችሏል።

በኛ ገቢ ውስጥ ያሉት አንኳር አንኳር ችግሮች ምንድን ናቸው ያላችሁ እንደሆነ አንደኛው ኮንትሮባንድ ነው። ኮንትሮባንድ አሁንም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጋሬጣ ነው። ወርቅን ጨምሮ በርካታ ሸቀጦች ሕገወጥ በሆነ መንገድ ወደ ተለያየ ሀገሮች ይወጣሉ። ሁለተኛው ገቢ ስወራ ነው። የኛን ድርሻ ወስደን የመንግሥትን ድርሻ መስጠት ሲገባን በተለያየ መንገድ ገቢ የመሰወር ልምምድ ይታያል፤ ይህም በበቂ ደረጃ ገቢ ለመሰብሰብ ያለንን ፍላጎት እንዳናሟላ ጋሬጣ ሆኖብናል።

ሦስተኛው የንግድ ማጭበርበር ነው። በተለይ በገቢና ወጪ ንግዶች ላይ የሚታየው የንግድ ማጭበርበር ኢትዮጵያ በቀላሉ ሰብስባ ልማቷን ለመመገብ የሚያስችላት ሀብት ማመንጨት እየቻለች እነዚህ ዋና ዋና ምክንያቶች ከመንግሥት የማስፈፀም አቅም ውስንነት ጋር ተዳምረው በበቂ ደረጃ ገቢ ለመሰብሰብ ጋሬጣ ሆነውብናል።

የተከበረው ምክር ቤት ከገቢ ጋር ተያይዞ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ ያለበት አፍሪካን ጨምሮ በብዙ ሀገራት ዜጎች ዘንድ የሚነሳው ከፍተኛ የግብር ጫና አለብን የሚል ነው። የኛ ግን በተቃራኒው ከፍተኛ የታክስ ስወራ አለብን ነው የሚል ነው።

ይህንንም በቀላል መንገድ ለማመላከት በአፍሪካ ውስጥ ሞሮኮ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርቷ /ጂዲፒዋ/ 32 በመቶ ግብር በዓመት ትሰበስባለች። ደቡብ አፍሪካ 24 በመቶ፣ ኬኒያም 15 ነጥብ 9 በመቶ ይሰበስባሉ፤ ኬኒያ ይህን ለመጨመር ባደረገችው ጥረት ነው ሰሞኑን ችግር የገጠማት።

እኛ የምንሰበስበው ገቢ ከኬኒያ በግማሽ ያንሳል፤ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርታችን /ጂዲፒያችን/ ሰባት በመቶ ገደማ ነው ግብር የምንሰበስበው። ሰባት በመቶ የምንሰበስበውን 10 በመቶ እንኳ ማድረስ ቢቻል ቅድም ሲነሱ የነበሩ የልማት ጥያቄዎችን በስፋት ለመመለስ ያግዛል። ይህንን ግብር የመሰወር ልምምድ ብንቀንስ ቢያንስ ከሰሐራ በታች የአፍሪካ ሀገራት እኩል እንኳ ባንሆን የተቀራረበ ግብር መሰብሰብ ብንችል ውጤታማ ልንሆን እንደምንችል ያመላክታል።

በገቢ አሰባሰቡ ላይ ያለው ዋንኛው ችግር እያንዳንዱ ዜጋ እርሱ ብቻ በመሰወሩ ሀገር ላይ ጉዳት አያስከትልም፤ ሌሎች ይከፍላሉ የሚል እምነት በሚከተሉ ብዙ የዚህ አይነት አመለካከት ተጋሪዎች ሀገር ትጎዳለች።

በአንድ ወቅት የአንድ አካባቢ አስተዳዳሪ እያንዳንዱ ሰው አንድ አንድ ኩባያ ወተት ይዞ መጥቶ በተዘጋጀለት በርሜል እንዲገለብጥ ያዛል። ሁሉም ሰዎች ውስጡ ምን እንዳለ ከውጪ በማያሳይ ኩባያ ፈሳሽ ነገር ይዘው ወደ በርሜሉ እየወሰዱ ይገለብጣሉ። ከእነዚያ ሰዎች መካከል አንደኛው ሁሉም ጎረቤት ወተት ወስዶ ከገለበጠ እኔ አንድ ብርጭቆ ውሀ በአንድ በርሜል ውስጥ ብጨምር ወተቱን እምብዛም ስለማያቀጥነው ችግር የለውም ብሎ ውሀ ይዞ ይሄዳል።

ያንን ውሀም ወደ በርሜል ገልብጦ ጉዞ ከጀመረ በኋላ እንዲያው ምን ያህል አደጋ እንደገጠመ ለማየት ዞር ብሎ ከፍቶ በርሜሉን ሲመለከት በርሜል ውስጥ አንድ ኩባያ ወተት የለም። ሁሉም ለካ እኔ ብቻ ነኝ እያለ የሚገለብጠው ውሀ ነው። እኔ ብቻ ነኝ እያልን የምንገለብጠው ውሀ ሲሰናሰል ወይም ሲደመር የታሰበው ነገር ከግብ እንዳይመታ እንዳይሳካ ያደርጋል።

ግብር ላይ ቅድም በአጀንዳ የተያዘውን አዋጅ ጨምሮ በርካታ ማሻሻያዎች የምናደርገው ዜጎች የሚገባቸውን አግኝተው፤ ለመንግሥት የሚገባውን በታማኝነት የመክፈል ባሕል ፣አሠራር፣ ሕግ እንዲዳብር ለማድረግ ነው።

ከተቋሙ አንፃር በርካታ ሪፎርሞች ተጀምረዋል። ተቋሙን የማዘመን /አውቶሜት የማድረግ/ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ። በትብብር መንፈስ በዚህ ዓመት የተሻለ ገቢ ለማስገባት ጥረት ይደረጋል።

ሁለተኛው አመላካች መታየት ያለበት ገቢና ወጪ /ኢምፖርትና ኤክስፖርት/ ነው። የለውጡን በፊት ዓመታት መለስ ብላችሁ ተመልከቱ። በአማካይ 19 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ ከሁሉም መስኮች ይገኝ ነበር። ከለውጡ በኋላ በአማካይ ብንመለከት 23 ቢሊዮን ዶላር ማመንጨት ችለናል። በትክክለኛው /አክችዋል/ አኃዝ ሲታይ መሻሻሎች አሉ። ይሁንና ካለው ፍላጎት አንፃር ሲታይ ግን አሁንም በጣም በጣም አናሳ ነው።

ዘንድሮ ወደ ውጪ በተላኩ ሸቀጦችና አገልግሎቶች /በኤክስፖርት ኦፍ ጉድስ እና ሰርቪስስ/ በሁለቱም መስክ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት ተችሏል። በተለይ በቅባት እህል፣ በጥራ ጥሬ፣ በወርቅ፣ /ወርቅ አምና ከነበረው ከፍተኛ መሻሻል አምጥቷል፣ ቡናና አበባ እንደተጠበቀ ሆኖ/ አዳዲስ መሻሻሎች ታይተዋል።

ዘንድሮ የዛሬ አምስት ስድስት ወር ገደማ የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ መንፈቅ አፈጸጸም ግምገማ በማክሮ ደረጃ ስናደርግ ዘንድሮ የወጪ ምርት /ኤክስፖርት/ አቅማችን ከአምናው ያንሳል፤ የአምናውን ልናሳካ አንችልም የሚል ግምገማ ነበረን። ምክንያቱ ቀይ ባሕር ላይ የተከሰተው ችግር ነው። በዚህ ችግር ሳቢያ የምናስወጣቸውም የምናስገባቸውም እቃዎች በከፍተኛ ደረጃ ችግር ገጥሟቸዋል። ሸቀጦቹ አልመጡም ብቻ ሳይሆን ጅቡቲ መምጣት ሲገባቸው ወደ ኤዢያ ተመልሰው የሄዱበት ሁኔታ ታይቷል፤ በጣም በርካታ መርከቦች ይህ ችግር ገጥሟቸዋል።

ያንን ገምግመን አፈጻጸሙ ባጠረ ጊዜ አይሻሻልም፤ የወጪ ንግዳችን /ኤክስፖርታችን/ ይጎዳል የሚል ግምገማ ይዘን ነበር። ይሁንና ዘንድሮ ከአምናው ከአራት በመቶ በላይ እድገት ያለው የወጪ ንግድ /ኤክስፖርት/ አፈጻጸም ማረጋገጥ ተችሏል። ከነበረው ችግር አንፃር ሲታይ ይህ በጣም ትልቅ ድል ነው ።

ሬሜታንስ ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል። ይህም ከአምናው መሻሻል አለው። በአፍሪካ ካሉ መሰል ሀገራት አንፃር ሲታይ ግን በጣም በጣም አናሳ ነው።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በተመለከተም በተለያዩ የዜና ምንጮች እንደሰማችሁት ኢትዮጵያ አሁንም በምሥራቅ አፍሪካ ትልቋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የምትስብ ሀገር ናት፤ ዘንድሮ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ መሳብ ተችሏል። ሌሎች መስኮችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ23 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማመንጨት ተችሏል።

ከውጊያው፣ ከእርዳታ ማነስ፣ ከብድር መጥፋት፣ በቀይ ባሕር ከገጠመን ችግር አንፃር ሲታይ ዘንድሮ የተሳካ ነው ብለን ገምግመናል። ከዚያ በላይ መሄድ ግን እንፈልጋለን። የነበረው ውጫዊ ችግር፣ በዚያ ላይ በበቂ ደረጃ ለመጓዝ ለመሮጥ ያለንን ፍላጎት በተወሰነ መልኩ ገትቶታል።

ከወጪ ንግዱ /ኤክስፖርቱ/ ቀጥሎ የሚታየው አንዱ ቁልፍ ነገር የገቢ ንግዱ/ኢምፖርት/ ነው። በገቢ ንግዱ ውስጥ ግን በወጪ ንግድ /ኤክስፖርት/ ፍላጎታችን ተደምሮ የሚታየው የተኪ ምርት ጉዳይ ነው። ግብርናን ጨምሮ በኢንዱስትሪ በአንዳንድ ምርቶች ባደረግነው

የገቢ ምርት መተካት /ኢምፖርት ሰብስቲትውሽን/ ሥራ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከዚህ ቀደም ከውጪ የምናስገባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ ማምረት ችለናል።

ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ስንዴ ነው። በስንዴ ላይ በተከናወነው ተግባር ብዙ ብር አስቀርተናል። የፋብሪካ ምርቶች 40 በመቶ ደርሰናል። የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ምርቶችን መጠቀም ጀምረናል። ይሄ በጣም በጣም ተስፋ ሰጪ ነገር ነው። ወደ 50፣ 60፣ 70 እያደገ ከሄደ ገቢ ምርትን ከተካን፣ የወጪ ምርትን /ኤክስፖርት/ ካሳደግን በገቢና ወጪ ንግድ መካከል ያለው የንግድ ክፍተት /ትሬድ ዴፊሴት/ እየቀነሰ ከሄደ ጤናማ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት በእጅጉ ያግዛል።

ከገቢ ምርት /ኢምፖርት/ አንፃር ሦስት ዋና ዋና ነገሮችን /አይተሞችን/ ብቻ ወስደን እንመልከት። እነሱም ነዳጅ፣ ማዳበሪያና እዳ ክፍያ ናቸው። ለነዳጅ አራት ቢሊዮን ዶላር ገደማ በዓመት እናወጣለን፤ ለማዳበሪያ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ለዕዳ ክፍያ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገደማ እናወጣለን። በድምሩ እነዚህ ሦስት አይተሞች በዓመት 7 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይበላሉ።

ኤክስፖርት ኦፍ ሰርቪስን ትተን የወጪ ሸቀጦችን /ኤክስፖርት ኦፍ ጉድስ/ ለጥጠን ብናይና በዚህም ከፍተኛ ብለነው /ማክሲመም/ አራት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የምናስገባ ከሆነና፣ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የምናወጣ ከሆነ ከፍተኛ ክፍተት አለ ማለት ነው። መድኃኒትና ሌሎች ሸቀጦችን ሳንጨምር በነዚህ ሦስት ኮሞዲቲዎች ብቻ ያለው የውጪ ምንዛሪ ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነው።

በተለይ ነዳጅን በሚመለከት ሰፋ ያሉ ጥናቶች ለማድረግ ሞክረናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ገደማ መኪናዎች አሉ። ለውጡ እንደመጣ ከነበረው አኅዝ እጥፍ ሆናል ማለት ነው። ያኔ የዚህ ግማሽ ገደማ መኪናዎች ነበሩ፤ አሁን የመኪናዎቹ ቁጥር በእጥፍ አድጓል።

የነዳጅ ፍላጎታችንም አድጓል። ነገር ግን አሳሳቢው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ መኪኖች ከ355ሺህ በላይ የሚሆኑት አውቶሞቢሎች ናቸው። እንደሚታወቀው፤ ባለ ሁለት ቁጥር ሰሌዳዎቹ መኪኖች የግለሰብ መኪኖች ናቸው። ለብዙኃን ትራንስፖርት ከሚውለው፣ ለንግድ ሥርዓት ከሚውለው ቁጥር በላይ አንደኛ ቁጥር የያዘው አውቶሞቢል ነው።

የኢትዮጵያ አውቶሞቢል ባለቤቶች በዚሁ አጋጣሚ እንዲገነዘቡ የሚያስፈልገው ከሌለን ሀብት ላይ በከፍተኛ መጨናነቅ የምናመጣው ነዳጅ መጥቶ ግለሰቦችን ከመደጎም አልፎ አብዛኛውን ሕዝብ ማገልገል ወደ የሚችልበት ደረጃ መድረስ አልቻለም።

አዲስ አበባ ላይ ምግብ፣ ቤትና ትራንስፖርት በጣም በጣም ከፍተኛ ችግር ነው ያለው። ምግብን በሚመለከት በተማሪ ምገባ፣ በማዕድ ማጋራት እና በጓሮ አትክልት እያለን በዓመት በዓል ወቅቶች ደሃው እንዳይሰቃይ በመንግሥት ደረጃ ኮሚቴዎች አቋቁመን እህል እየገዛን በየእሁድና ቅዳሜ ገበያው እያሰራጨን ዋጋን ለመቆጣጠር ጥረት አድርገናል፤ አልጨረስንም፤ ተሞክሯል።

ቤትን በሚመለከት ሁለት ዓመት ሦስት ዓመት የሚፈጀውን ባሕላችንን ቀይረን በሁለት ወር በሦስት ወር ለደሃ ቤት በመሥራት እና በመጠገን፤ ኮንዶሚኒየም በመጨረስ፣ የግሉ ሴክተር የጀመረውን አፋጥኖ እንዲጨርስ በማድረግ እየተሠራ ነው፤ በዚህም የቤት ችግር ተፈታ እንኳን ባይባል ከፍተኛ መሻሻሎች አሉ። ችግሩን የመፍታቱ ጥረት ገና ሰፊ ሥራ ይፈልጋል።

ትራንስፖርት ግን የተቀናጀ ኢንተርቬሽን ካላደረግን በስተቀር 11 ሰዓት 12 ሰዓት መንገድ ላይ ወጥታችሁ ማየት ከቻላችሁ በጣም ነው የሚያሳዝነው። ሕዝቡ ሥራ ውሎ በጣም ረጃጅም ሰልፎች አሉ። እዚያው ጎን ብዙ አውቶሞቢሎች አንድ ሰው ሁለት ሰው ጭነው ሲንቀሳቀሱ ሊታዩ ይችላሉ። እንደሀገር ሀብት እንዴት ነው በራይድ የጀመርነውን ሥርዓት አጠናክረን በሠራተኛ መግቢያና መውጫ ሁሉም መኪኖች የመንግሥት የግልም ሕዝቡን ማገልገል የሚችልበትን መንገድ ካልተከተልን በስተቀር ነዳጁን ድጎማ እያደረግን ያ ገንዘብ ለሀገር የማይደርስ ከሆነ የሕዝቡን እንቅስቃሴ የማያግዝ ከሆነ እንደሀገር ለምናስበው እድገት ፀር ነው።

ግለሰቦች ባለመኪና መሆናቸው በጣም ጥሩ ነገር ነው፤ እንፈልገዋለን። ነገር ግን ግለሰቦች አንድ ሰው ሁለት ሰው በመኪና እየሄዱ፤ ሦስት አራት ሰው የሚጫን ቦታ እያላቸው ሰዎች አለአግባብ ለሰዓታት የሚሰለፉ ከሆነ ያ ጉልበት ያ ጊዜ እንደሀገር ባከነ ማለት ነው። ይሄን በተለየ መንገድ መፍታት የምንችልበት ሥራ ካልሠራን በከተማችን የትራንስፖርት ጉዳይ ምንም እንኳን ለነዳጅ ከፍተኛ ሀብት ቢናወጣም አሁንም መከራ ነው፤ ሰዎች ይቸገራሉ።

በቅርቡ በካቢኔ ገምግመን የመንግሥት መኪኖች በሥራ መውጫ ሰዓት ሕዝቡን እንዲያገለግሉ ተብሎ ሙከራዎች ተጀምረዋል፤ በቂ አይደለም። የተከበረው ምክር ቤት ከዚህ አንጻር ማገዝ ይኖርበታል። ሕዝባችንን ለማገልገል በምንችለው አቅም ሁሉ በተለይ ደሃውን ለመርዳት የቀደመ ተግባር መፈጸም ስላለብን ይህንን እንደክፍተት ወስደን የምንሠራበት ይሆናል።

በገቢና ወጪ በኩል /ኢንፖርትና ኤክስፖርት/ ይህንን ካልኩ በመጀመርነው መንገድ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ልብስ ላይ ኢትዮጵያ ታምርት ባልነው በግብርናው በኢንዱስትሪው አስፋፋተን ከሄድን አብዛኛው የገቢ ፍላጎታችን በእነዚህ በኩል ሊሸፈን ይችላል። በዚህም የሚበላ፣ የለበሰ፤ ከታከመ ደግሞ መድኃኒት የሚያገዛ ዜጋ ካለን አንዳንድ ትርፍ ጉዳዮችን ልንተው ስለምንችል እንደ ሀገር ያሉብንን ችግሮች ለመቀነስ በከፍተኛ ደረጃ የሚያግዝ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል።

ከገቢና ወጪ ምርት /ኢንፖርትና ኤክስፖርት/ ቀጥሎ ማየት የሚገባን አመላካች የፋይናንስ ዘርፍ ነው። የፋይናንስ ዘርፉ የተረጋጋ /ስቴብል/ ነው አይደለም የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፤ ይህም አጠቃላይ የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚን ለመገምገም ለሚፈልጉ ሚዛናዊ ለሆኑ ሰዎች ዕድል ይሰጣል።

በነገራችንን ላይ የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚው በብዙ አጥኚዎች ችግር አለበት እንደተባለው እርግጥ ነው ኢኮኖሚያችን ብዙ ሥራ ይፈልጋል። ለዚያ ሰፋፊ ሪፎርም እየሠራ ነው። ግን በብዙ አጥኚዎች ያለው በዓለም ላይ ፈጣን እድገት እያመጣች ያለች ሀገር የዛሬ አርባ ዓመት በ2075 ከዓለም 16 .. 17ኛ ኢኮኖሚ የምትገነባ አገር፣ በ2100 የዛሬ 75 ዓመት በዓለም ሰባተኛው ኢኮኖሚ የምትገነባ ሀገር ናት ኢትዮጵያ የሚል ነው በርካታ ጥናቶች የሚያሳዩት። ከፍተኛ ተስፋ ከፍተኛ ሕልም ነው የሚታየው። ያን ሕልም ልጆቻችን መኖር እንዲችሉ ግን እኛ መሠረት መጣል ይጠበቅብናል።

የፋይናንሻል ሴክተርን ብንወሰድ ባንኮች 17 ገደማ ነበሩ፤ ዛሬ 32 ደርሰዋል። ቁጥራቸው አድጓል። ቅርንጫፎታቸው 5ሺ400 ገደማ ነበሩ፤ ዛሬ ከእጥፍ በላይ አድገው ከ12ሺ 800 በላይ ቅርንጫፎች ተከፍተዋል። ተደራሽነታቸው አድጓል ማለት ነው።

የቁጠባ ሂሳብ ደብተር 38 ሚሊዮን የነበረ ዛሬ ከ100 ሚሊዮን በልጧል፤ በርካታ ሰዎች ወደ ባንክ ኢንዱስትሪው እየገቡ ነው። መግባታቸው ብቻ ግን አይደለም በብዙ አመላካች በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ አመላካች ሲታይ የፋይናንሻል ሴክተሩ ጤናማ እና መሸሻሎችን እያሳየ ያለ መሆኑን ያመላክታል። ለምሳሌ የማይመለሱ ብድሮች አሉ። የዓለም አማካኝ አምስት በመቶ ነው። የኢትዮጵያ አማካኝ 4ነጥብ 5 በመቶ ነው፤ ከዓለም አማካኝ ያነሰ ማለት ነው። ይህም ጤናማ መሆኑን ያመላክታል።

ከሚሰበሰበው ሀብት ቢያንስ 80 በመቶ ያህሉ ለግል ሴክተር የሚመደብ ነው። ይህም የግሉ ሴክተር እንዲነቃቃ በእጅጉ ያግዛል። የባንኮችን አጠቃላይ ትርፋማነት ስናይ ዘንድሮ እንኳ ከ24 በመቶ በላይ ነው። ትርፋማነታቸው፣ ተደራሽነታቸው እያደገ ነው። የማበደር አቅማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እየታየበት ነው ተብሎ አጠቃላይ ጤናማ ነው ሊባል ይችላል።

በዚሁ አጋጣሚ በቅርቡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገጠመ የቴክኒክ ችግር የተሰረቁ ወይም የተዘዋዋሩ ገንዘቦች እንደነበሩ ይታወሳል። በሕዝባችን ጨዋነት፣ በተቋሙ ጥንካሬ ዛሬ ከ99 ነጥብ 34 በመቶ በላይ ገንዘቡ ተመልሷል። ቀሪው በነጥብ አምስት ስድስት የሚገመት፣ ከአንድ በመቶ በታች የሆነ ነው እሱ በመሰብሰብ ላይ ያለ ሀብት ነው።

ገንዘቡ በሚዘዋወርበት ምሽት ገንዘቡን በቀላል መንገድ መውስድ ብዙ ለወሰዱ ሰዎች ቀላል ነበር። ለመመለስ ግን ብዙ ሰዎች ሰልፍ ይዘው ጊዜ አጥፍተው ብሩን መልሰዋል። ኢትዮጵያውያን እንደተባለው ሌብነት ችግር ቢሆንም፣ የማይናቅ ጨዋነትም ደግሞ አለ። እሱንም ማድነቅ ጠቃሚ ነው የሚሆነው። በብዙ ሀገራት ማጅራት እየተመታ የሚዘረፍበት፣ ባንኮች በታጠቁ ኃይሎች የሚዘረፉበት፣ ሀገር ውስጥ ዜጎች ሊያውም ወጣቶች የደረሳቸው ገንዘብ የኔ አይደለም አይገባኝም ብለው ለመመለስ የነበራቸውን ቁርጠኝነት ማድነቅ ተገቢ ይመስለኛል።

ይሄ እንዳለ ሆኖ ባለፉት አምስት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያ ባንኮች ለኢትዮጵያውያን ዝግ ሆነው መቆየታቸው ይቀራል፤ ተዘጋጁ፤ ራሳችሁን አዘጋጁ፤ የውጭ ባንኮችን እናስገባለን፤ ውድድር ያስፈልጋል ብለን ለባንክ ሴክተር በተደጋጋሚ ስንናገር መቆየታችን ይታወሳል።

ይህንን የውድድር መንፈስ የምንፈልግበት ዋና ምክንያት አንዱ ማሳያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። ኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድሮ ትርፋማነቱንና እድገቱን ጠብቆ መሄድ ከቻለ ለምንድነው ሌሎቹ ዋናዋና እድሜ ጠገብ ዘርፎች ለውድድር ዝግጁ የማይሆኑት የሚል ጥያቄ የቆየ ነው።

ለምሳሌ ቴሌኮም ለውድድር ይዘጋጅ ሲባል የነበረውን ተቃርኖ እና ፈተና ሁላችሁም ታስታውሳላችሁ፤ የማይታሰብ ነው፣ ቴሌኮምን ላብራይዝድ ማድረግ /ኮማንዲንግ ኃይል ስለሆነ/ ስህተት ነው የሚል ሰፊ ተቃውሞ ነበር።

ነገር ግን ቴሌኮም በለውጡ ማግስት 37 ሚሊዮን ተጠቃሚ ነበረው። ዛሬ 77 ሚሊዮን ተጠቃሚ አለው። የተኛ አንበሳ/ጃይንት/ ነው፤ የተኛውን አንበሳ የቀሰቀሰው ውድድር ነው። ተጠቃሚውን ተውትና ሞባይል ባንኪንግ ከጀመርን ሦስት ዓመት ገደማ ነው። ዛሬ 47 ሚሊዮን ሰዎች በሞባይል ባንኪንግ ይጠቀማሉ።

አስቡት 70 … 80 ዓመት የቆዩ ባንኮች 100 ሚሊዮን የሚጠጋ የባንክ ሂሳብ አላቸው እያለን ሦስት ዓመት ያልሞላ ሞባይል ባንኪንግ 47 ሚሊዮን ተጠቃሚ አለው ማለት በጣም ከፍተኛ እምርታ ነው። ትራንዛክሽን ሰፊ ነው። እንዴት መጣ ሳፋሪኮም ሊመጣ ነው፤ ሳፋሪኮም ሊጀምር ነው ሲባል ተኝቶ የነበረው ሪፎርም ተነቃቅቶ በጣም በጣም አስደማሚ ውጤት አምጥቷል ።

ይህንን በባንኮች መድገም እንፈልጋለን። 37 ባንክ ብዙ ነው። ሰብሰብ ብለው 10 ጠንካራ ባንክ አሁን 12 ሺ የደረሰው የባንክ ቅርንጫፍ 15 ሺ ቢያደርሱት ቴክኖሎጂ ቢጠቀሙ፣ አሠራራቸውን ቢያዘመኑ፣ ያው ሁሉም እንደምታዩት በጣም ቆንጆ ቆንጆ ፎቆች ሠርተዋል። በርካታ የሰው ኃይል አፍርተዋል። ተደራሽነት አስፍተዋል። ትርፋማነታቸው አድጓል። ሰብሰብ ብለው ቢወዳደሩ በእጅጉ ይጠቅመናል።

የሚጠቅሙት ደግሞ በሁለት መንገድ ነው። አንደኛ በሀገር ውስጥ ያልተለማመድናቸው አሠራሮች እንለማመዳለን፡፤ ለምሳሌ በውጭ ሀገር ባንክርስ አንድ አዋጭ ኩባንያ፣ ትርፋማ ኩባንያ እነርሱ ጋር እስኪመጣ አይጠብቁም። ወደ ኩባንያው ሄደው አጥንተው ከአንተ ጋር መሥራት እንፈልጋለን ብር ልናበደርህ እንፈልጋለን ብለው ጥያቄ ያቀርባሉ።

እኛ ዘንድ ኩባንያዎች ባንክ ሄደው ለመበደር ራሱ ተጨማሪ መስፈርት አለው፤ ተጨማሪ ሂደቶች አሉት። እንደዚህ አይነት አሠራር እንዲቀየር ውድድሩ በእጅጉ ያግዛል። በውስጥ ተደራሽነት ያሰፋል፤ በውጭ ደግሞ ሁላችሁም እንደምታውቁት የአፍሪካ ኮመን ፍሬም ወርክ ተፈርሟል፤ ምን ማለት ነው? በአፍሪካ ደረጃ የንግድ መሳለጥን ለመክፈት ስምምነት ፈፅመናል።

የኬኒያ ባንከርስ ከሌላ ጋር የሚወዳደሩ ከሆነ፣ የዩጋንዳ ባንከርስ ከሌላ ጋር የሚወዳደሩ ከሆነ፣ የሩዋንዳ ባንከርስ ከሌላ ጋር የሚወዳደሩ ከሆነ፣ የእኛ ከውድድር ውጭ አይደለም፤ በሃገር ውስጥም ዝግ ከሆኑ ነገ ባለው ዓለም ውስጥ ቦታ የለንም ማለት ነው።

ለረዥም ጊዜ ዘግተን አቆይተናቸዋል፤ አሁን ለውድድር ዝግጁ መሆን አለባቸው። ለዚያ አንዱ ማነቆ የብሔራዊ ባንክ አቅም መጠናከር ነበረበት፣ አዋጁ ፖሊሲው መመሪያዎችን በስፋት አሻሽለን ተቋሙን ለማጠናከር ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። ከዚህ አንፃር ባንክም ነገ እንደቴሌ ኮም፣ እንደአየር መንገድ ተወዳዳሪ ሆኖ አሁን ያሉብንን አንዳንድ ማነቆዎች በሚፈታ ቁመና ላይ ሥራቸውን እንደሚሠሩ ተስፋ ይደረጋል። ነገር ግን ጤናማ እንደሆኑ ያመላክታል።

አራተኛው በማክሮ ቢታይ ጠቃሚ የሚሆነው ኢንፍሌሽን (ግሽበት) ነው፤ የእኛን ኢኮኖሚ ለመገምገም አንዱ መታየት ያለበት ኢንፍሌሽን (ግሽበት) ነው። ኢንፊሌሽን ልክ እንደውጊያው ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የሁሉም ዓለም ሀገሮች ዋነኛ አጀንዳ ሆኗል።

ይህ ዓመት ታላቁ የምርጫ ዓመት ይባላል፤ በዓለም ላይ በርካታ ሃገሮች ምርጫ እያደረጉ ነበር፤ ወይም እያደረጉ ነው። ለምሳሌ አሜሪካ የሚደረገውን ምርጫ ብንወስድ አንደኛው የንግግር ቋጠሮ የኑሮ ውድነት /ኮስት ኦፊ ሊቪንግ ክራይስስ/ ነው። አሁን ብሪታኒያ ላይ ብንከታተል አንዱ ጉዳይ የኑሮ ውድነት ነው። በአውሮፓ ኅብረት፣ ሕንድ፣ ደቡብ አፍሪካ ላይ የነበረው ውድድር ተመሳሳይ አጀንዳ ነበረው።

በየትኛውም የዓለም ጫፍ ብትሄዱ የኑሮ ውድነት ዋናውና ቁልፉ የምርጫ ክርክር አንጓ ነጥብ ነው። እንደ ድሮው አፍሪካ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ትልልቅ ሃብት ያላቸውንም ሃገራት ጭምር በከፍተኛ ደረጃ እያናጋ ያለ ሁኔታ ነው።

ለምሳሌ በአሜሪካ ከለውጡ በፊት አንድ ጋሎን ነዳጅ ሁለት ዶላር የሚገዛ ከሆነ ዛሬ ቢያንስ ስድስት ዶላር ይገዛል። እንቁላል፣ ዳቦም ሆነ በፈለግነው አይነት ብንለካው በከፍተኛ ደረጃ ዋጋው ጨምሯል። በእርግጥ

ያ ዋጋ መጨመር መሸከም የሚችል ሲስተም፣ መሸከም የሚችል የማምረት አቅም፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ በዶላር ስለሆነ ግብይቱ የውጭ ምንዛሪ ስለማያቀርብ እንደኛ ጫናው ከፍተኛ ላይሆን ይችላል። በሁሉም ዓለም ግን በከፍተኛ ደረጃ አጀንዳ ሆኖ ይነገራል።

አንዳንድ ሃገራት ከ60 በመቶ እስከ 200 በመቶ ኢንፍሌሽን (ግሽበት) ጨምሮባቸዋል። አሁንም ከዚያ ለመውጣት ያለው ሁኔታ አስጊ እንደሆነ ይነገራል። የበርካታ ሃገራት ስብራት፣ የበርካታ ሃገራት ጭንቀት ፣ የበርካታ ሃገራት ውጥረት እንደሆነ መገንዘብ ጠቃሚ ነው። የተለየ ለኢትዮጵያ ብቻ የሆነ ችግር አይደለም፤ አጠቃላይ ዓለም ላይ ያለው ቀውስ (ክራይስስ) እየጎዳ ያለው አንዱ የማክሮ አመላካች ነው።

በእኛ ሁኔታ ሲታይ ባለፈው እንዳነሳሁላችሁ በርካታ ሃገራትን ሙያተኞችን፣ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የሚሠሩ ኢትዮጵያውያንን ለማነጋገር ሞክረን ነበር፤ ምን ብናደርግ ነው ይህንን ችግር የምንፈታው? ብለን። በተለይ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ልማትን የሚጋብዝ፣ ልማትን የሚያፋጥን መንግሥት እዛው ላይ እያለ የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር በጣም ፈታኝ ነበረ።

የኮሪደር ልማት፣ ህዳሴ ወዘተ እያልን እዛው ላይ እያለን የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር ያስቸግራል። ምክንያቱም በጣም በርካታ ሃብት ስለሚወጣ። ኢንፍሌሽኑን ለመቀነስ አንዱ መንገድ እየተፋጠነ ያለውን ልማት መግታት ነው የሚል ሀሳብ ተነስቶ ነበር፤ ልማቱን ብንገታው ደግሞ በሌላ መንገድ ከኑሮ ውድነት ያላነሰ የሥራ አጥነት ደግሞ ችግር ስላለ አንደኛውን ብንፈታ አንደኛው ቁስል መልሶ ጠልፎ ስለሚይዘን ይህንን አጣጥመን /ባላንስ አድርገን/ ልማትን ሳናቋርጥ ፣ ሥራ አጥነትን ለመፍታት እየሞከርን ኢንፍሌሽን መቀነስ ቀላል ጉዞ አልነበረም።

የብዙዎች አማካሪዎች፣ ሙያተኞች ምክር የነበረው ያለው መፍትሔ አንድ ብቻ ነው፤ በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ የሚል ነው። በፍላጎት እና በአቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ደግሞ ዋናው መንገድ ምርታማነትን ማሳደግ ነው። ተመልከቱ የኛን ኢንሼቲቮች። ኩታገጠም፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ፍራፍሬ የጓሮ አትክልት፣ ተማሪ ምገባ፣ የደሃ ቤት ማደስ፣ ማዕድ ማጋራት ከኢኒሼቲቮቹ መካከል ናቸው። እያንዳንዱ የመንግሥት ኢኒሺየቲቭ ኢንሼቲቭ ብቻ ሳይሆን እጅግ የተቀደሰ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች በተወሰነ ደረጃ ለማገዝ ሙከራ ያደረገ ኢንሽየቲቭ ስንከተል ቆይተናል።

ምን አመጣ ሲባልም፣ ስንዴ ቅድም አንስቻለሁ። ሰብል ምርት አምና እንደ ሀገር በዓመት 395 ሚሊዮን ኩንታል ነው ያመረትነው። ዘንድሮ 507 ሚሊዮን ኩንታል አምርተናል። 100 ሚሊዮን ኩንታል በአንድ ዓመት ተጨምሯል። ይሄ ትልቅ ድል ነው።

ምርት ተጨመረና የገበያ ትስስሩ ተፈታ ወይ? ሁሉም ቦታ ዋጋ እኩል ነው ወይ? አይደለም። ሌላ ፈተና ነው እሱ። 500 ሚሊዮን ኩንታል ለኢትዮጵያ በቂ ነው ወይ አይደለም፤ መጨመር አለበት፤ ግን ትልቅ እድገት ነው።

ይሄ እድገት ለምን መጣ? ኢትዮጵያ መሬት አላት፤ ውሃ አላት፤ ሰው አላት። ኩታገጠም አድርጋ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ብትጠቀም ከዚህ በላይ ምርቷን ማሳደግ የሚያስችል ዕድል አላት። አንዳንዱ ሀገር ወይ ውሃ የለውም፣ ወይ ሰው የለውም ወይም መሬት የለውም። እኛ ግን ስላለን ብናመርት ኑሮ ውድነት ታክል ማድረግ /መቆጣጠር/ እንችላለን።

የሌማት ትሩፋትን እንውሰድ። ከጀመረነው ገና ሁለት ዓመት በቅጡ አልሞላውም። የሌማት ትሩፋት ለኢትዮጵያ በጣም በጣም ጠቃሚ ነው። የሌማት ትሩፋትን ጀምረን ከፍተኛ አቅም አሟጠን መጠቀም የሚቻል ደረጃ ደርሰናል።

ይሄ የዶሮ የማባዛት ሥርዓት በጣም ውስብስብ ምስጢር በውስጡ አለው። ፓረንት የሚባለውን ጫጩት የሚያፈሩ ግራንድ ፓረንት የሚባል ደግሞ ከዚያ በላይ በጣም በርከት ያለ ጫጩት ለማራባት የሚያግዝ ሥርዓት አለ። ያ ግራንድ ፓረንት በአፍሪካ ውስጥ የለም። ኢትዮጵያ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት በጣም በጣም እልህ አስጨራሽ ነው እየሆነ ያለው።

ያም ሆኖ በየቀበሌው በየከተማው ክላስተር ብለን ዶሮ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት እንቁላል ላይ ያመጣውን ውጤት ተመልከቱ። ከጫፍ ጫፍ ሊባል አይችልም፤ ሁሉም ከተሞች ሊባል አይችልም። ነገር ግን የእንቁላል ዋጋ ከ15 ብር፣ 11፣ 10፣ ዘጠኝ፣ ስምንት አንዳንድ ቦታ ሰባት ብር የገባበት አለ። የሌማት ትሩፋት እንቁላል፣ የዶሮ ሥጋ፣ ዋጋ እንዲቀንስ አድርጎ ተስፋ እያመጣ ነው።

የማር ምርትን ብንመለከት ከለውጡ በኋላ የዛሬ ሁለት ሦስት ዓመት፣ በዓመት 30 ሺህ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ነበር እንደ ትልቅ ድል የሚነገረው፤ ዘንድሮ አንድ ሚሊየን ዘመናዊ የንብ ቀፎ ነው የደረሰው። ከሰባት እጥፍ በላይ የኢትዮጵያ የማር ምርት አድጓል። እጥፍ አይደለም ሰባት እጥፍ ነው ያደገው። እነዚህ ምርቶች እያደጉ ሲሄዱ በዚያው ደረጃ የንግድ ሥርዓቱ ሲስተካከል የዋጋ ቅነሳውም በዚያው መንገድ እየቀነሰ እየተስተካከለ እንደሚሄድ ይጠበቃል።

መንግሥት ከምርት በተጨማሪ ከፍተኛ ድጎማ አድርጓል። ቅድም መድኃኒት ብያለሁ፣ በማዳበሪያ ከፍተኛ ድጎማ አለ። ከውጭ የሚገቡ ምግብ ነክ አይነቶች ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የግብር እፎይታ አግኝተው መንግሥት ግብር አጥቶ እንዲገቡ ተደርጓል።

ይሄ ሁሉ ተደምሮ አምና በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት 30 በመቶ የነበረው ወደ 23 በመቶ ዝቅ ብሏል። ይሄንን ውጤት ብዙ ሀገራት እና የፋይናንስ ተቋማት ያደንቃሉ። አሁን ኢንፍሌሽን መቀነስ አጠቃላይ ባለው ሁኔታ በማይቻልበት ጊዜ ሰባት በመቶ መቀነሳችሁ ምርት እያደገ ከሄደ አሠራር ካሻሻላችሁ በሚቀጥለው ዓመትም ሰፊ ርቀት መሄድ ትችሉ ይሆናልና ጥሩ ጅምር ነው ይላሉ።

የኛ የማክሮ ቁጠባ የሚያሳየው ግን እንደዛ አይደለም፤ ሰባት በመቶ በቂ አይደለም። የዋጋ ንረት እንደሀገር ጉዳት ያለው ቢሆንም ዋነኛው ጉዳቱ ዱላው የሚያርፈው ደሃው ላይ ነው። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ይቸገራሉ። አሁን በጀመርነው ደረጃ በየዓመቱ ሰባት በመቶ እያደግን ከሄድን ብዙ ርቀት አንሄድም። ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል።

ኢንሼቲቮቻችን ላይ ምርታማነት እንዲያድግ ተጨማሪ ሥራዎች መሥራት ይገባናል። ምርታማነት እንዲያድግ ተጨማሪ ሀብት/ሪሶርስ/ ማስቀመጥ አለብን፤ ይህም መስኖ እንዲስፋፋ፣ ኩታገጠም እንዲስፋፋ በዘንድሮ በጀትም መመላከት አለበት ብለን ለማየት ሞክረናል።

የበጋ እርሻ አምና በጣም አስደማሚ ውጤት ነው ያመጣነው። ወደ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ ሄክታር መሬት በስንዴ ሸፈነናል።

ዘንድሮ ከሃያ አራት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለማረስ እቅድ ተይዟል። ለወጡ እንደመጣ 14 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር ነበር ኢትዮጵያ የምታርሰው። ዘንድሮ ከተሳካልን በዚህ ላይ 10 ሚሊየን ሄክታር መሬት እንጨምራለን።

ኢትዮጵያ 35፣ 40 ሚሊዮን ሄክታር ማረስ ትችላለች፤ በኖራ መሬቷን ማከም ከቻለች፣ ውሃ የሌለባቸውን ቦታዎች ውሃ ማግኘት ከቻለች፣ ገና ትልቅ አቅም አላት። ነገር ግን 24፣ 25 ሚሊዮን ሄክታር ማረስ ትልቅ እምርታ ስለሆነ የተከበረው ምክር ቤትም ሚናውን ከተጫወተ በኑሮ ውድነትም በኢኮኖሚ እድገት ላይም ከፍተኛ ለውጥ ልናመጣ እንችላለን።

በስንዴ በሩዝ የጀመርናቸውን እርምጃዎች ማጠናከር ያስፈልጋል። አሁን አፍሪካ ላይ ኢትዮጵያ በቡና ምርት አንደኛ ሆናለች። በስንዴ ምርት አንደኛ ነች። በእንስሳት አንደኛ ነች። በማር አንደኛ ነች፣ ፍራፍሬ እና ሩዝ፣ ሻይ፣ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በምንሠራቸው ሥራዎች ያንን ቦታ መያዝ ትችላለች የሚል ግምት አለ።

በተለይ ሻይ እና ሩዝ ቢበዛ በሁለት ዓመታት ውስጥ ምርታችንን ማሳደግ እንችላለን። ሩዝ አምና ዘጠኝ ሚሊዮን፣ በዚህ ዓመት 37 ሚሊዮን ኩንታል ነው ያመረትነው። በያዝነው ዓመትም የምናቅደው ይህን እጥፍ ለማድረግ ነው። ያ ተጠናክሮ ከቀጠለ በብዙ መንገድ በኑሮ ውድነት ያለው ጫና ይቀንሳል።

የቅዳሜና እሁድ ገበያ አምና 600 የነበረው ገበያ አሁን ከሺ አልፏል። ይህም ለእጅ አጠር ሰዎች በእጅጉ የሚያግዝ መንገድ ስለሆነ እንደዚህ አይነት መንገድ በመከተል የኑሮ ውድነትን ለማቃለልና የደሃውን ሕይወት ለማሻሻል፣ ድህነትን ለመቀነስ በሀገራችን ሰፊ ጥረት ተደርጓል። ውጤቱም አበረታች ነው።

ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ስንገባ ኢንዱስትሪን በሚመለከት የተነሳው ጥያቄ ዘንድሮ አንድ በጣም የተሳካልን መስክ ቢኖር ኢንዱስትሪ ነው። 10 ነጥብ 1 ከመቶ እድገት የሚጠበቀው በኢንዱስትሪ ሴክተር ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› በሚለው ንቅናቄ ከ390 በላይ ፋብሪካዎች ምርት በመጀመራቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ 217 ገደማ የሚሆኑ ፋብሪካዎች ምርት ጀምረዋል።

ይህ ለሠራተኛውም ትርጉም አለው፤ ለወጪ ንግድም ትርጉም አለው፣ የገቢ ምርትን ለመተካትም ትርጉም አለው። ለምሳሌ አምና ሲሚንቶ አጀንዳ ነበር። ግንባታ እያደገ ነው። የሲሚንቶ ምርት እያነሰ መጥቷል። ዘንድሮ በነባር የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ብቻ 30 ከመቶ የምርት እድገት መጥቷል። ነገር ግን ለሚ ሲሚንቶ የሚባለው በቅርቡ የሚመረቀውና ሥራ የሚጀምረው ሲሚንቶ ፋብሪካ በጠንካራ የግል ሴክተርና የመንግሥት ከፍተኛ ትብብርና ድጋፍ የተሠራ ነው።

ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ አሁን ኢትዮጵያ የምታመርተውን፤ እስከዛሬ የምታመርተውን 50 ከመቶ የማምረት አቅም አለው። ምን አልባትም በአፍሪካ ትልቁ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሳይሆን አይቀርም። ይህ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት በተሟላ ሁኔታ ሥራ የሚጀምር ነው። እንዲዚህ አይነት በመንግሥት ተመርጠው የሚወሰዱ ወሳኝ ጣልቃ ገብነቶች ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ደረጃ እምርታ እንዲያሳይ አግዟል። ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ ከምንሠራቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ ስማርት ላይት ነው።

ይህ ስማርት ላይት ብርሃንና ውበት ብቻ አይደለም ያለው። የካሜራ ሲ ሲ ቲቪ እዛው ላይ ይይዛል። ኔት ዎርክ ያሳልጣል። ወደፊት ትስስር ሲያድግ የትራፊክ መጨናነቅ መረጃ ይሰጣል። በጣም በርካታ ጠቃሚ ነገር በውስጡ የያዘ ነው። ከሸራተን ሆቴልና ሳይንስ ሙዚየም ጀርባ የነበረችውን ቦታ ስንሠራ መቶ ከመቶ ከውጪ አስመጥተን ነው የሠራነው።፡

አሁን ግን ፒያሳ፣ ቦሌ በየቦታው የሚታው ኢትዮጵያ ውስጥ አምርተን ነው እየሠራን ያለነው። ናሙና አመጣን፤ ለኢንዱስትሪዎች ሰጠን፤ ኢንዱስትሪዎች አምርተው ሥራ ጀምረዋል። በሌላ በኩል ለቱሪዝም ለሳፋሪ የሚሆኑ መኪናዎች በሌሎች ሀገራት አየን፤ ለአንድ ኩባንያ ናሙና ሰጠን፤ በጥቂት ግዜያት ውስጥ ሠርተው ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ችለዋል። ወደፊት ሌሎች ገበያዎች እናፈላልግላቸዋለን።

በኢትዮጵያ ውስጥ በኤሌክትሪክ ብስክሌት፣ ሞተር ሳይክል፣ አውቶሞቢሎች በርካታ ፋብሪካዎች ሥራ ጀምረዋል። የሚያነቃቁ ነገሮች ከብረት ጋር ተያይዞ የሶሱ፣ የአይረን ኦር ጉዳይ፣ ከባድ ኢንዱስትሪ ስለሆነ ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም ከዛ በመለስ ያሉት የብረት ሥራዎች በከፍተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ መሻሻል እያመጡ ነው። ይህ ውጤት የመጣበት ምክንያት በኢነርጂ፣ በመሬት፣ በፋይናንስ አቅርቦት፣ አንዳንድ የቢሮክራሲ ችግሮች በመቀነስ፣ ሲስተም አውቶሜት በማድረግ፣ ገበያ በማፈላለግ ድጋፍ ለማድረግ ሙከራ በመደረጉ ነው።

ዘንድሮ በኢንዱስትሪ ያመጣነውን 10 ነጥብ 1 ከመቶ እድገት በሚያስቀጥል መንገድ ጥቂት ዓመታት መሄድ ከቻልን በምናስበው ልክ ቀጣይነት ያለው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ ያግዛል። ያ ደግሞ እንዲሆን በኢንዱስትሪ ፓርኮች የጀመርነው ጉዞ በቂ ስላልሆነ ነፃ የንግድ ቀጣና ጀምረናል።

መሬትና ውሃ ማዘጋጀት፣ መሠረተ ልማት መገንባት፣ ባለሃብት መጥራት ከባለፈው ስህተታችን ተምረን ዕዳ በማያመጣ መልኩ ዝግጅት ጀምረን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶች እየታዩ ነው። እነዚህ ጉዳዮች በምናስበው መንገድ ከሄዱ በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ እንደሚያደርጉን ይጠበቃል። ስለዚህ ኢንዱስትሪው ዘንድሮ አመርቂ ውጤት ነው ያለው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

ከግብዓት አንፃር የተነሳው ማዳበሪያን በሚመለከት ኢትዮጵያ 15 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ነው የምታስገባው። ወደብ የሌላቸው የአፍሪካ ሀገራት 5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ማስገባታቸውን እጠራጠራለሁ። ወደብ ሳይኖራት 15 ሚሊዮን ኩንታል አፈር ማዳበሪያ ካለበት ጭና፣ አጓጉዛ፣ ወደብ ላይ አውርዳ ወደሀገር ውስጥ ማስገባት ሎጀስቲኩ ብቻ ምን ያህል አታካች ሥራ እንደሆነ በሥራው ውስጥ ያሉ ሰዎች ያውቁታል።

ገንዘቡን ተውትና ያ 15 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ከመጣ በኋላ ዝም ብሎ አዲስ አበባ የሚቀር ቢሆን ችግር የለውም። በመላ ሀገሪቱ ይሰራጫል። በቂ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት በሌለበት ማለት ነው። ለግዢ የምናወጣው የውጪ ምንዛሪ ብቻ ሳይሆን ከገዛንበት እስከምናደርስበት የትራንስፖርት ሰንሰለቱ የውጪ ምንዛሪ ነው። ከዚህ ነቀምትና አርባ ምንጭ ለመውሰድ

ነዳጅ ደጉመን ነው የምንወስደው። ብዙ ሀብት፣ ጉልበትና፣ ትጋት ይጠይቃል። ቀላል ሥራ አይደለም።

ያም ሆኖ አምና የነበረውን ችግር ታውቃላችሁ። የምርት እድገት ማረጋገጥ እንፈልጋለን። ወሳኝ ግብዓት ስለሆነ ገና ከፓርላማ እንደወጣን ኮሚቴ ተቋቁሞ ቀደም ብሎ አመርቂ ሥራ በመሠራቱ ዘንድሮ ከ13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ሀገር ውስጥ ገብቶ በስርጭት ላይ ይገኛል። 2 ሚሊዮን ገደማው ጅቡቲ እየገባ ነው ያለው።

በሁሉ መስክ ሲታይ የዘንድሮው የማዳበሪያ ስርጭት ከአምናው ጋር ለውድድር የማይበቃና የተሳካ ነው ማለት ይቻላል። ፍፁም እንከን የለሽ ነው ማለት ግን አይቻልም። ሌቦች አሉ። አደናቃፊዎች አሉ። ደላሎች አሉ። እኛ በዚህ ሁሉ መከራ ካመጣን በኋላ ወደሌላ ሀገር የሚያሸሹ አሉ። ችግሮች አሉ። ያም ሆኖ ግን አርሶ አደራችን አብዛኛው ቦታ ከሚደርሰው ቦታዎች ውጪ ያሉት ከአምናው በተሻለ እንዲያገኙ ለማድረግ ሰፊና የተሳካ ሥራ መሥራት ተችሏል።

ከግብዓት አንፃር የማዳበሪያ ተነሳ እንጂ የስንዴ ልማት ስንጀምር ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም አይነት የምርጥ ዘር የማቅረብ ብቃት አልነበረም። ማዳበሪያም አምጥተን፤ ምርጥ ዘርም አምጥተን ነበር የጀመርነው ሥራውን። ፍላጎታችን እያደገ ሲሄድ ለምድን ነው ምርጥ ዘር የጠፋው፤ ሀገረኛ ዘሮች ለምን ጠፉ ስንል ባለፉት አመታት በለሆሳስ እውቀት እየመሰለን፣ በለሆሳስ ቴክኖሎጂ እየመሰለን፣ በለሆሳስ መሻሻል እየመሰለን ሀገር በቀል ዘሮች አጥፍተን ጨርሰናል። ፈተናውን ያየነው ሥራውን ስንጀምር ነው። ምንም ማዳበሪያ ብናመርት፣ ፓምፕ ብንገዛ፣ ኩታ ገጠም ብንል ምርጥ ዘርን መጠበቅ ካልቻልን ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያ ጉሮሮ በሌሎች እጅ የተያዘ ነው ማለት ነው። ይህ አደገኛ ፈተና መሆኑን ተገንዝበን ሰፊ ሥራ ሠርተን ስንዴ ወደ 60 እና 70 ከመቶ ደርሰናል።

በሚቀጥሉት ዓመታት ኢትዮጵያ የምርጥ ዘር ጉዳይን ትሸፍናለች የሚል እምነት አለኝ። መስኖ ላይ፤ ዝርዝሩን አላነሳም በጣም ሰፊ ሥራዎች እየሠራን ነው። ፓምፕ ብቻ ብንወስድ በዚህ ዓመት ቢያንስ ቢያንስ 40 ሺህ ፓምፕ ነው የገባው፤ እና መስኖ ላይ የጀመርነውን ሥራ ማጠናከር ያስፈልጋል። ከሥራው ስፋት አንፃር የመስኖ ሥራዎች በባሕሪያቸው ከዋና ከተማ የራቁ በመሆናቸው የማስፈጸም ውስንነት አለ፤ ተቋሙ አዲስ ነው። አንድ ሳምንት ሶማሌ፣ አንድ ሳምንት ጋምቤላ፣ አንድ ሳምንት አፋር ምናምን ስለሆነ ቀላል አይደለም። ያንን ለማሻሻል የተወሰኑ ለውጦችን እንዳደረግን የተከበረው ምክር ቤት ይገነዘባል።

ዘንድሮ ያመረትነውን መቶ ሚሊዮን ኩንታል፣ በጥራት ነው፤ በዚህ ዓመት ቢያንስ 100 ሚሊዮን ኩንታል ከደገምን የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት በአስተማማኝ መሠረት ላይ ይቀመጣል። ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንዲትችል በርካታ ሀገራት ረድተውናል፤ አሜሪካ ላለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ በምግብ እንዳትቸገር በርካታ የስንዴ እርዳታ አድርገውልናል። የአውሮፓ ሀገራት በርካታ እርዳታ አድርገውልናል፤ እነዚህን ሀገራት እጅግ አድርገን እናመሰግናለን፤ ብድር ከፋይም ያድርገን እንላለን።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከእርዳታ ባንገላገልም፤ የምንፈልገው እርዳታ ግን ስንዴ ሳይሆን፣ ማሽን፣ ፓምፕ ዕውቀት ሊሆን ይችላል። ይሄንን ጉዳይ አሳካን ማለት ስሟ በድህነት የሚታወቅበትን የታሪክ እጥፋት ቀየርን፣ ብልጽግናችንን አረጋገጥን ማለት ነው። ደግሞም እናሳካዋለን። ይህን በምርት ላይ የጀመርነውን በሀገር በብቃት ለማሰራጨት፣ ውስንነቶችን እያሻሻልን፣ የሥራ ባህላችንን እያዘመንን ውጤታማ ለመሆን ጥረት ይደረጋል።

እስካሁን ያነሳኋቸውን ጉዳዮች ጠቅሎ የሚይዝ አንድ ኢንዲኬተር ነገር፤ በኢትዮጵያ የሥራ አጥ ቁጥር ነበር፤ አለ። በየዓመቱ ይጨምራል፣ ይሄ ነገር አደገኛ ነው ብለን ተቋም በሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ማቋቋማችን ለተከበረው ምክር ቤት ግልጽ ነው። ይህ ተቋም ከተቋቋመ ጥቂት ዓመታት የሆነው ሲሆን የመጣው ውጤት በተለይ በዚህ ዓመት እጅግ እጅግ አስደማሚ ነው።

ከሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሰው በላይ ሥራ ማስገኘት ተችሏል። ሦስት ነጥብ አራት ሰው ሥራ ያስያዝነው ቅድም ባነሳሁት ኢንዱስትሪ በሀገር ውስጥ ነው በሌማት፣ በመንገድ፣ በኮሪደሮች ልማት ፕሮጀክቶች ነው። ሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ያልነው ከመጣልን ሪፖርት 17 በመቶውን ቆርጠን በጣም ኮንሰርቫቲቭ ሆነ ፊገር ነው። ኢንፍሌትድ ቁጥር እንዳይመጣ ብለን ማለት ነው፤ አንድ በአንድ ያቀረብነው በውጭ ሀገር ያለውን ነው፤ በሀገር ውስጥ ያለውን 17 በመቶ ቆርጠን ነው።

በውጭ ሀገር ካቻምና 40 ሺህ ገደማ፣ አምና 100 ሺህ ገደማ በተቋሙ መላኩን ታስታውሳላችሁ። ዘንድሮ 332 ሺህ ሰው በህጋዊ መንገድ ሰልጥኖ፣ ማን ጋ እንደተቀጠረ፣ በስንት ብር እንደተቀጠረ፣ ማወቅ በሚቻል መልኩ ከአምናው በእጥፍ ያደገ መላክ ተችሏል። ይሄ ቁጥር አንዳንድ ማሻሻያዎችን ካደረግን ሊያድግ ይችላል። ይሄ ቁጥር በራሱ መንገድ የሚሄደውን፣ በደላላ የሚሄደውን አይጨምርም፤ ተቋሙ የሚሄደውን ብቻ ነው። በጣም አስደማሚውና ተስፋ ሰጪው አዲሱ ዘርፍ ደግሞ ቢ ፒ ዖ ነው።

ኢን ሪሞት ጆፕ የሚባል፤ አውት ሶርስ የማድረግ፤ ከዚህ በፊት በህንድ የሚታወቀውን፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች እዚህ ተቀምጠው አሜሪካ ላለ ኩባንያ ኮድ ማድረግ እንዲችሉ፤ የተለያየ አናሊሲስ ሥራ፣ የዳታ ትሪያንጉሌሽን ሥራ የሚሰሩ ወጣቶች ተፈጥረዋል። ይሄ ቁጥር በሚያስደንቅ ሁኔታ 60 ሺህ ሰው ደርሷል። እነዚህ ወደ ውጭ ከምንልካቸውም የሚሻለው፤ አንደኛ ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋይ ናቸው፣ ሀገራቸው፣ ቤተሰባቸው ላይ ሆነው የሚሰሩ ናቸው፤ ከዚያ በተረፈ በጣም አጓጊ የሥራ ዘርፍ ነው።

ይሄ ተቋም በሀገር ውስጥ፣ በውጭ እና በአውጭ ሶርሲንግ የጀመረውን አጠናክሮ በሚቀጥለው ዓመት የተሻለ ውጤት ልናገኝ እንደምንችል አመላካች ነገር አለው፤ ዘንድሮ ግን በሥራ ፈጠራ ሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በየትኛውም መመዘኛ እጅግ አስደማሚ ውጤት ነው። ከዚህ አንጻር ተቋሙን ማጠናከር ያስፈልጋል፤ በጣም ጥሩ ጅምር ነው።

ሌላው ትምህርት ነው። ትምህርት በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት፤ ኢትዮጵያ የወጣት ሀገር ነው፤ ታች ላይ በምንሰራው ሥራ ዛሬ ላይ ውጤቱን ባናይም ውሎ አድሮ ልጆቻችን ተስፋ ያላቸው፣ የማይለምኑ፣ በልካቸው የሚታዩ ይሆናሉ በሚል እሳቤ የተከበረው ምክር ቤት እንደሚያውቀው ፤ አንዳንዶቻችን በቂ መረጃ ከሌለን ስትሄዱ እንደምታዩት፣ በኬጂ እና ዜሮ ክፍል በሚባለው ባለፉት ዓመታት ከ30 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል ኢትዮጵያ ውስጥ ይሄንን ቁጥር በቀላሉ ሌላ ቦታ አናገኘውም። የኛ ድል ስለሆነ አይቀልብንም። ለምንድነው መዋዕለ ሕፃናት ላይ የምንሰራው ያላችሁ እንደሆነ እዚያ ካልሰራን ላይ ከወጣ በኋላ ችግር አለ። ኬጂ እየሰራን፣ አንደኛ ደረጃ እየገነባን፣ ሁለተኛ ደረጃ እየገነባን፤ ተማሪዎች እንዳይቀሩ በትምህርት ቤት ምገባ ምን ያህል እንዳስፋፋን ታውቃላችሁ። ይሄ አንዳንዶችን ወደኋላ የሚተው እንዳይሆን የዓይነ ሥውራን ትምህርት ቤት፣ ለሴተኛ አዳሪዎች ‹‹የነገዋ ኢትዮጵያ›› የሚባለው ተቋም፣ እንዳላችሁት አስደማሚ ነው።

የዓይነ ሥውራን አዳሪ ትምህርት ቤት የአሜሪካን ስኩል ጨምሮ አንድም ሃይስኩል በጥራቱ እሱን አያክልም። የአሜሪካን ስኬል፣ ሌሎች ፕራይቬት ስኩል ብቻ ሳይሆን አንድም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ የዓይነ ሥውራን አዳሪ ትምህርት ቤትን ያክል ጥራት የለውም። ጭንቀታችን እዚያ የተማሩ ልጆች ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ እንዴት ብለው ይኖራሉ የሚለው ነው።

ማደሪያቸው፣ መማሪያ ክፍላቸው እንዳያችሁት ነው፤ ለእነርሱ ስለሆነ ግዴለም በሚል የተሠራ ሥራ አይደለም፤ በሚገባቸው ልክ የተሠራ ሥራ ነው። ያስደስተኛል ይህን ስናገር። ለእነርሱ ብቻ አይደለም፤ ድሃ ተኮር መሆናችንን፣ ሰውኛ መሆናችንን መገንዘብ እንድትችሉ፣ እዚህ አቧሬ አካባቢ ቤት ስንገነባ እንደነበር ታውቃላችሁ፤ አሁን ፎቅ በፎቅ ሆነናል እንዳያችሁት፤ አቧሬ ብቻ በርካታ ፎቆችን ከሠራን በኋላ ጂ ፕላስ ኢለቨን፣ ጂ ፕላስ ትዌልቭ ሠርተናል፤ የሚሸጥ አይደለም፤ እጅ አጠር ለሆኑ ለድሃዎች ነው።

ለድሃዎች የሚሰጥ ቤት አልጋ ካለው፣ ሶፋ ካለው ይበቃል አላልንም፣ ፍሬንድሺፕ እንዳለው፣ ዓድዋ እንዳለው በየሰፈሩ ፓርክ እየሰራን ነው ያለነው፤ ድሃም ቢሆን ከልጆቹ ጋር የሚቀመጥበት የሚናፈስበት ቦታ እንዳያጣ፤ ለድሃ ይበቃሃል ብለን አይደለም የምንሠራው፤ በሚገባው ልክ ነው የምንሠራው።ለድሃ አንድ ብር ይበቃዋል ብለን ሳይሆን በሚገባውና በሚያስፈልገው ልክ ነው የምንሠራው። ይኼ መብዛት አለበት መበራከት አለበት ትክክል ነው።

የብላይንድ እስኩል የነገዋ ተቋም አንዳንዴ ምን ማለት ነው? ብዙ አካል ጉዳተኛ አለ። መብዛት አለበት ማለት ነው፤ ከጥራት ከስርጭት አንጻር አድጎ። ይኼንን በመሠረት ደረጃ እየሠራን መጽሐፍ ህትመት በሚመለከት ዘንድሮ 45 ሚሊዮን ዶላር አውጥተን በጣም በርካታ መጽሐፍቶችን አሳትመን አስገብተናል እንደምታውቁት። ተደራሽነቱም እየሰፋ ነው ያለው። የቀረውም አሁን በሂደት ላይ ነው ያለው። የተውነው ጉዳይ አይደለም።

ዩኒቨርሲቲን በሚመለከት ግን አንድ የተከበሩ የምክር ቤት አባል ላነሱት ሁለት ነገር ከግምት ብናስገባ፣ ለውጥ ከመጣ ጀምሮ በአንድም ቦታ አንድም ዩኒቨርሲቲ አልሠራንም። ለውጥ ከመጣ ጀምሮ ከዩኒቨርሲቲ ይልቅ ኬጂ ላይ ብንገነባ ይሻላል ነው ያልነው። ይህንን ስንል የሚስቱ ሰዎች አሉ። ከዩኒቨርሲቲ ገንዘብ ቀምተን ለ2ኛ ደረጃ ለ1ኛ ደረጃ ያዋልን የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፤ ግን እንደዛ አይደለም እውነቱ።

የተከበረው ምክር ቤት ከዚህ ሴሽን በኋላ ያለፉት ዓመታትን በጀት እንዲያገላብጥ አደራ እላለሁ። ከለውጡ በፊት ቢበዛ የዩኒቨርሲቲው በጀት የነበረው፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ 40 ቢሊዮን ብር ነው። ዛሬ የዩኒቨርሲቲ በጀት 60 ቢሊን ብር ነው። 50 በመቶ አድጓል። ከፈለግን ይኼን ገንዘብ እንደተለመደው ኮንደሚኒየም መጠፍጠፍ እንችላለን። የኛ ሀሳብ ግን አዳዲስ ኮንደሚኒየም መጠፍጠፍ ዋጋ የለውም።

በየተቋማቱ የጥራት ችግር አለ። ዩኒቨርሲቲ የሚለውን ስም ይዘው በዚያው ልክ ብቃት የላቸውም በሚል በርካታ ብር እያፈሰስን ነው። አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ከ10-15 ፕሮጀክቶች አላቸው። ስሙ ያኛው ዩኒቨርሲቲ ሆኖ፤ ባህርዳር ሆኖ ጅማ ሆኖ…ከእነርሱ ውስጥ እንደአጋጣሚ ሆኖ ክብርት ያነሱት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነው። የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምናልባት በኢትዮጵያ ደረጃ ትልቁን ሆስፒታል ከነገወዲያ ያስመርቃል። በኢትዮጵያ ደረጃ…ታዩታላችሁ መጠኑን። ለዩኒቨርሲቲ የሚሰጠውን ገንዘብ እንዲቀንሱ ሳይሆን ጥራት ያለው እንዳያንስና ስም እንዳይበዛ ነው።

ስም የበዛው ኮንሲኬውንስ አለው ቅድም በኦዲት የተነሳውም ችግር አንዱ ሚታየው ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ነው። ኦዲት ሁሉ ሌብነት ነው ብዬ ባልወስድም ከተባለ በኋላ ሲፈተሽ ማብዛት ላይ ብቻ ሳይሆን ጥራት ላይ ነው ማተኮር የሚሻለን። ከእነርሱ ይልቅ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋት፣ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ማስፋት ጠቃሚ ይሆናል፤ ለምን የምንፈልገው ዓይነት ትውልድ ለመፍጠር ስለሚያግዘን በዚያው መንፈስ ብንረዳው መልካም ይሆናል።

የመምህራን ደመወዝ ከአንዳንድ ክልሎች ጋር ተያይዞ የተነሳው የተከበረው ምክር ቤት እንዲረዳው የሚያስፈልገው፤ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ካደረጉ ወሳኝ ወሳኝ ምሰሶዎች መካከል ሦስቱን ብጠቅስ አርሶአደር፣ ወታደርና መምህር ነው። አርሶአደር አሁን በሚደረጉ ለውጦች ማዳበሪያም እየደጎምን፣ ኩታ ገጠመም እያልን ፓፕንም እያቀረብን ኑሮው ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያሳየ ነው ያለው። ወታደርና መምህር ግን ለኢትዮጵያ ደማቸውን ከመስጠት ውጭ እስካሁን ባለው ሁኔታ ከኢትዮጵያ ነገ በልጆቻችን እናየዋለን ከሚል ተስፋ ውጭ በቂ ነገር አግኝተው አያውቁም።

ከማንም በላይ እውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ህይወታቸውን የሚገብሩ የሥራ መስኮች ሆነው ሲያበቁ በቂ ክፍያ የማያገኙ ናቸው፤ ያልተከፈለው አይደለም ሁሉም። ይኼ መምህራንና ወታደሮች ምሰሶ ሆነው ተርበው ባያስተምሩ ኖሮ እንደ ሀገርስ መቀጠል እንችል ነበር ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በዚሁ አጋጣሚ የተከበረው ምክር ቤት ከይቅርታ ጋር ለኢትዮጵያ መምህራንና ወታደሮች ክብር እንዲሰጥልኝ በታላቅ ትህትና እጠይቃለሁ። …አመሰግናለሁ በዚህ የሚያበቃ አይደለም፤ ተጨማሪ እርምጃዎች መንግሥት ይወስዳል። ብዙ እየሰጡ ስለሆነ በሚገባቸው ልክም ባይሆን በመጠኑ ማሻሻል አስፈላጊ ስለሆነ ነው።

ነገር ግን በአንዳንድ ክልሎች እያጋጠመ ያለው ችግር፤ የተከበረው ምክር ቤት የደመወዝ ጥያቄ እኔን ሲጠይቀኝ ይገርመኛል። ምክንያቱም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባወጣው ቀመር እናንተ ምታጸድቁት በጀት ብቻ ነው ማስተዳደር የሚቻለው። ክልሎች ባልተገባ መንገድ ክልል ክልል ክልል የሚል ጥያቄ ያነሱና ክልሎች ደግሞ ዞን ዞን ዞን ይሉና ወረዳ ወረዳ ወረዳ ይሉና ኮብራ ኮብራ ኮብራ ይሉና ከዚያ ደመወዝ የለም ይላሉ።

ይህንን የክልል ምክር ቤት መፈተሽ አለበት። የሚገባቸው ይሰጣቸዋል። ማን ያጸደቀው? ፌዴሬሽን ያጸደቀው እናንተ ያጸደቃችሁት። ገበያቸውን ማሻሻልና ተቋማቸውን በአቅማቸው ልክ ሪፎርም ማድረግ የእነርሱ ሥራ ነው። ይኼ ለዚህ ምክር ቤት ግልጽ ይመስለኛል። ሁሉም በሚያስገባው ሳይዝ ልክ እንጂ ለምሳሌ ኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን መምህር ካላት ሲሸልስም አንድ ሚሊዮን መምህር አትልም ሀገር ስለሆነች። በሚያስፈልጋት ልክ ነው የምታደርገው በተለይ ዞን ወረዳ በሚለው ስትራክቸር ከጫፍ ጫፍ ወጥ መሆኑ ክልሎች መፈተሽ አለባቸው።

አንዳንድ ቦታ ወረዳ በቂ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አዲስ አበባ ቀበሌ እኮ የለውም። ብዙ ክልሎች ጋር የሚያስፈልገው ቀበሌ ነው። ቀበሌን ማጠናከር ነው። ቀበሌ ላይ ያሉ ሚሊሻዎች፣ ቀበሌ ላይ ያሉ የቀበሌ ሊቀመንበሮች በእግራቸው እየሄዱ በቅርበት ሲሠሩ፤ ከፍ ያለው ሄይራርኪ ግን ብዙ ነገር ስለሚያስፈልገው በሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ ክልሎች ያንን ነገር ማየት ይኖርባቸዋል።

ያም ሆኖ የፌዴራል መንግሥት ችግሩ እንዳይባባስ በብድር ለማገዝ ሙከራ አድርጓል። ይኼ ነገር ወደዚህ ሳይሆን መምጣት ያለበት የክልል ምክር ቤቶች በጀታቸውን ሲያጸድቁ እነዚህን ጉዳዮች አይተው ተቆጣጥረው መገምገም ያለባቸው ይመስለኛል። ሁሉም ክልል ምክር ቤት ስላለው፣ በዚህ መንፈስ ብትረዱት መልካም ይሆናል።

ጤናን በሚመለከት፤ ጤና ዛሬም ነገም በጣም ወሳኝ፣ ልናስብበት የሚገባ ሴክተር ነው። የኛ አካሄድ ጤናማ የሆነ የአኗኗር ዘዬ መፍጠር ነው። በከተማና በገጠር ከነበሩ የኑሮ ዘዬዎች ትንሽ ሻል ያለ ነው። የከባቢው

ግሪን የሚታይበት፣ ወክ የሚደረግበት፣ ከመኪና ይልቅ በእግር የሚኬድበት፣ ጥላ ይዘን ከምናደርገው መቀመጥ ይልቅ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተን ዛፍ ስር ለመቀመጥ የምንችልበትን ነገር አቅም በፈቀደ መጠን ለማምጣት ሙከራ እየተደረገ ነው። የሚሠሩ መንገዶች አብዛኛው ሰው የሚጠቀምባቸው፣ አብዛኛውን በሽታ ለመከላከል እየተጠቀመ ይመጣል።

ያ እንዳለ ሆኖ ኮሌራ እንደ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስከትለውን አደጋ ለመቀነስ አሥር ሚሊዮን አካባቢ ክትባቶች ተሰጥተዋል፤ በዚህ ዓመት። ኩፍኝ በ58 ወረዳዎች ክትባት ተሰጥቷል። ወባ በርካታ አጎበሮች ተሰራጭተዋል። ይኼ ብቻ በቂ ስላልሆነ ከውጭ መድኃኒት እያስገባን የኢትዮጵያን የመድኃኒት ፍላጎት ማቅረብ ስለማንችል እስካሁን በሀገር ውስጥ ተመርተው ፍላጎታችንን ይሸፍኑ የነበሩትን ከ8 በመቶ ወደ 38 በመቶ አሳድገናል።

በሀገር ውስጥ ያለው ምርት 36 በመቶ አድጓል ይኼ ትልቅ ዜና ነው። ባለፈው እንዳነሳሁት በተወሰኑ መድኃኒቶች ኤክስፖርት እናደርጋለን። ግን ውስን ናቸው መስፋት አለበት። ለዚህ ነው በቅርቡ የመጀመሪያውን አምራቾች በኤግዚቢሽን ያየነው። መደገፍ ማበረታት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ በትራዲሽን በጣም ሰፊ አቅም አላት። ከ6 ሺህ በላይ ኢንዲጅኒየስ ዛፍ አላት። ከዚያ ውስጥ በጣም ብዙ መድኃኒቶች ሊወጡ ይችላሉ። እነርሱን በመጠቀም የመድኃኒት አቅርቦታችንን ለማሻሻል ጥረት ይደረጋል።

ሆስፒታል ግንባታ ከጥቂት ወራት በፊት የመከላከያ ቢሾፍቱ ላይ ግንባታ መደረጉ ይታወሳል። አሁን እንዳነሳሁት በዚህ ዊኬንድ አርባ ምንጭ ይመረቃል። ትላልቅ ሆስፒታሎች ናቸው። በግልም አዲስ አበባ ውስጥ እየተሠሩ ያሉ ሆስፒታሎች ቀላል አይደሉም። በሲኤምሲ አካባቢ ብንሄድ ከጭንቅላት ስትሮክ ጋር ተያይዞ ችግር ቢገጥመን በየትኛውም የዓለም ክፍል ውስጥ ባለው ስታንዳርድ ለመፍታት የሚያስችል ብቃት ያለው ወንድም ከዲያስፖራ መጥቶ የሠራው በጣም የሚያስደንቅ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እኔ ራሴ ያየኋቸው የአካባቢው ሀገራት ይጠቀሙበታል።

ከልብ ጋር በተያያዘ በእዚያው አቅራቢያ ሌላ ወንድም የልብ ችግር ያጋጠማቸውን ሰዎች ማገዝ የሚችልበት ሆስፒታል በጥሩ ሁኔታ ይገኛል። ሌሎችም በጣም በርካታ ሆስፒታሎች አሉ። ምናልባት ጤና ሚኒስቴር እና የተከበረው ምክር ቤት ቢሰራበት ብዬ የማስበው ሰዎች ሰው ሲታመምባቸው የት መውሰድ እንዳለባቸው ይቸገራሉ።

አንዳንዴ ሆስፒታሉ እያለ ባለማወቅ ምክንያት ጊዜ እየወሰድን ሰዎች ይጎዳሉ። ሰው የት ጋር ምን አይነት በሽታ እንደሚወሰድ ማስተማር ያስፈልጋል። ለሁሉ ጉዳይ ጥቁር አንበሳ ለሁሉ ጉዳይ ኮሪያ ሆስፒታል ሳይሆን ለበሽታው ትክለለኛ ፍቱን መድኃኒት የሚገኝበት ቦታ ለይተን መገልገል የምንችልበትን እውቀት እየፈጠርን ብንሄድ የኢትዮጵያ የጤና ሴክተር መሻሻሎች እያመጣ እንደሚሄድ ተስፋ ይደረጋል።

በጥቅሉ ኢኮኖሚው ሲታይ ዘንድሮ 7ነጥብ 9 በመቶ እድገት ይጠበቃል። ተጠቃሎ የመጣው መስከረም አካባቢ ነው፣ ይሄ በግብርናው 6ነጥብ2 በመቶ ይጠበቃል። ቅድም እንዳነሳሁት በማር፣ በአሳ፣ በሰብል ምርት በቡናም ጭምር በሻይ አስደማሚ እምርታዎች አሉ። ይህ የግብርና እድገት ሙሉ ለሙሉ እንደሚሳካ ምንም ጥርጥር የለውም። ሁለተኛው ኢንዱስትሪ ነው፣ ቅድም በዝርዝር እንዳነሳሁት 10ነጥብ1 በመቶ እድገት ይጠበቃል።

ሶስተኛው አገልግሎት ነው፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በቴሌ ኮሙዩኒኬሽን፣ በፋይናንሻል ሴክተር ያነሳኋቸው እንደተጠበቁ ሆነው በቱሪዝም ብንወስድ ዘንድሮ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም 37 ሚሊዮን ገደማ ደርሷል። እንዳያችሁት እዚህም እዚያም ለሰው ለዓይን ማራኪ የሆኑ ነገሮች እየተሰሩ ሲሄዱ ሰው መዝናናት፣ መናፈስ፣ መውጣት ልማድ እያደረገ ነው። ይሄ ሰላማችን በተሟላ ሁኔታ ቢረጋገጥ በሀገር ውስጥም በውጪም ትልቅ ገበያ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።

ይህንን እድገት በሚቀጥለውም ዓመት ለማስቀጠል ወይ ለማሻሻል የያዝነው በጀት 971 ቢሊዮን ብር ነው። አብዛኛው በጀት ለድህነት ቅነሳ፣ ለልማት ስራዎቻችን፣ ለማህበራዊ ጉዳዮቻችን መፍትሄ እንዲሆኑ የተዘጋጀ ነው። ይህ በጀት እውነቱን ለመናገር በቂ አይደለም፤ ግን የበጀት ዴፊሲት አሁን ካስቀመጥነው በላይ እንዲሆን አልተፈለገም። ላለፉት አምስት ዓመት ገደማ ከአይኤምኤፍ፣ ከወርልድ ባንክ ጋር ሰፊ ንግግር፣ ውይይት፣ ድርድር ሲደረግ እንደቆየ ታውቃላችሁ።

እኛም አስቸጋሪዎች እነሱም አስቸጋሪዎች በመሆናቸው አምስት ዓመት ሙሉ የወሰደ የሪፎርም አጀንዳዎች ነበሩ። አሁን አንዳንድ ወዳጅ ሀገሮቻችን ባደረጉልን ድጋፍ አብዛኛው ሃሳቦቻችን ተቀባይነት እያገኙ ይመስላል። ይህ ጉዳይ ተሳክቶ ሪፎርሙን ካጸደቅን ተጨማሪ 10ነጥብ5 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመታት ታገኛለች። ይህንን ገንዘብ ስለምታገኝ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ማሻሻያዎች በበጀት ሊደረጉ ይችላሉ፤ ከጸደቀ። መጽደቁ ላይ ያለው ፈተና ምንድነው እኛ አሁን ባለንበት ሁኔታ ቢሻሻሉ ብለን የምናስባቸው ኤሪያዎች አሉ፤ ሌላው ለጊዜው ቢቆይልን የምንላቸው ጉዳዮች አሉ፤ እነዛ ጉዳዮች በሙሉ ተቀባይነት ካገኙና ከተስማማን እንደዚህ ዓይነት ዕድል ከፊታችን ስላለ ያኔ ያን እድል አይቶ መጠቀም በጀት ማሻሻል ይቻላል።

አሁን ግን ባለን ሀብት ልክ የቀረበው በጀት ቢያንስ ሚኒመም የምንፈልገውን ልናሳካበት እንችላለን ወደ ማክሲመም ለማሳደግ ደግሞ የሪፎርም አጀንዳውን ካሳካን ውጤታማ መሆን ይቻላል። ይህ የሪፎርም አጀንዳ ኢትዮጵያን ያሳሰራት በተለይም የዕዳ ቀምበሯን በመፍታት ረገድ አርቴፊሻል የሆኑ ቫሊዩስ በማስተካከል ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ከፍተኛ ጠቀሜታም ይኖረዋል።

ነገር ግን እኛም ተርም አለን እነሱም ተርም አላቸው እነዚህ ተርሞች ተመጣጥነው ወደትክክለኛ ቦታ እስኪመጡ ፋይናል ደረጃ እስኪደርሱ ድረስ አስቀድመን ያን ታሳቢ አድርገን መስራት ስለሌለብን ባለን ሪሶርስ ብቻ ነው ያቀረብነው። ይህ የቀረበው ሪሶርስ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአይሲቲ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም ባሰብነው ልክ ስራችንን ከሰራን ኢንፍሌሽን በዚህኛው ዓመት ያገኘነውን ድል በዚኛውም ከደገመን ሥራ በዚህ ዓመት ያገኘነውን በተለይ በውጪ በሚቀጥለው ዓመት እጥፍ ማድረግ ከቻልን በኤክስፖርት በአንዳንድ ምክንያት ያጋጠሙን የነበሩ ችግሮች በህግ ማሻሻያዎች ተፈተው ምርት አድጎ ኤክስፖርታችን ካደገ የፋይናንሻል ሴክተሩን እድገት ማስጠበቀው ከቻልን በተለይ ግብር ቤዝ አስፍተን የተሻለ ግብር ማግኘት ከቻልን የሚቀጥለው ዓመት እድገት ከዘንድሮው እድገት ሊሻል ይችላል።

እስካሁን ላለው ኢኮኖሚን በሚመለከት ግን ብዥታ ላለባቸው ሰዎች የእኛ መንግሥት የምዕራቡ ዓለም መንግሥት ቢሆን ኖሮ ቁጭ ብሎ ሳይሆን ቆሞ ሊናገር የሚያስችለው ትልልቅ ድሎች አሉት። አንደኛ በአምስት ዓመት የኢትዮጵያን ጂዲፒ እጥፍ አድርገናል። እኛ ቢሮም ገብተን የኢትዮጵያ ጂዲፒ 86 ቢሊዮን ዶላር፤ ዛሬ 205 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ሁለተኛ ከለውጡ ማግስት ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ሁለተኛው ትልቁ ኢኮኖሚ ነበር ከኬንያ ቀጥሎ። ዛሬ ስድስቱ ጎረቤቶቻችን ተደምረው የእኛን ጂዲፒ አያክሉም አንደኛ ብቻም ሳይሆን በአንደኛና በሁለተኛ መካከል በጣም ሰፊ ልዩነት አለ። እንደዚህ ዓይነት ድሎች፤ ድሎቻቸውን በጣም ሴሌብሬት በሚያደርጉ መንግሥታት አይን ቢታይ ብዙ አስደማሚ ውጤቶች አሉ።

እኛ ግን ከምናስበው አንጻር ገና ስለሆንን መጓዝ ከምናስበው አንጻር ጅምር ስለሆነ ሚዛኑን የሳተ ግርግር መፍጠር ባንፈልግም ማክሮ ኢኮኖሚያችን፤ የኢኮኖሚ … በጣም በጥሩ ደረጃ ነው ያለው። በሚቀጥሉት ዓመታት ዕዳችንን ቀንሰን እድገታችንን ካስቀጠልን ሁሌም እንደምለው ብልጽግናችን አይቀሬ ይሆናል። ይህንን ታሳቢ አድርጎ የተከበረው ምክር ቤት በጀታችንን በማጽደቅ ድጋፍ እንደሚያደርግልን ያለንን እምነት እየገለጽኩ በቀሩት ሃሳቦች ከተፈቀደልን ከጤና እረፍት በኋላ እንቀጥላለን።

….ቅድም ለመመለስ ከሞክርኳቸው ውጪ ለተነሱ ጥያቄዎች ፤ እንዲሁ ኢንፎርማቲፍ በሆነ መንገድ ጠቅለል አድርጌ ሃሳቦቼን ለማንሳት እሞክራለሁ። በመጀመሪያም፤ ለውጥ የለውጡ መንግሥት ፣ ከለውጡ በኋላ እያልን የምንነጋገረውን ንግግር መለስ ብለን ለውጥ ለምን አስፈለገ? ምን ለመለወጥ ነው ያስብነው? አመለካከት አይደለም ወይ? አሠራር አይደለም ወይ? የሥራ ባሕል አይደለም ወይ? ለውጥ እያልን ያለነው፤ ግለሰቦችን ሰዎችን ከስልጣን መቀያየር አልነበረም፤ ሰዎች የታገሉት፣ የሞቱት የተደረገው አጠቃላይ ጥረት በኢኮኖሚያችን ፣በማህበራዊ ጉዳይችን በነበሩ ችግሮች መፍትሔ ያስፈልጋል፤ አዲስ ሃሳብ፣አዲስ አካሄድ፣ አዲስ አሠራር ያስፈልጋል፤ በነበረው ሁኔታ መጓዝ አንችልም። በሚል መነሻ እና እሳቤ ነው። የለውጡ አንኳር ጥያቄዎች በሁለት ተከፍለው ሊታዩ ይችላሉ።

አንደኛው ነባር ችግሮች ናቸው፤ ያኔ በነበረው ሁኔታ የማይታዩ ነባር ችግሮች ፖለቲካዊ ችግሮች ነበሩ፤ ታሪካዊ ችግሮች ነበሩ ማህበራዊ ችግሮች ነበሩ፤ ከጥንት ጀምሮ ሲከማቹ ሲወርዱ ሲዋረዱ የመጡ ማለት ነው። ሁለተኛው ወቅታዊ ችግሮች ናቸው፤ ከወቅታዊ ችግሮች መካከል አንደኛው ኢኮኖሚ ስብራት ነው፤ እዳ እየበዛ ፕሮጀክቶች እየበዙ ያለው ሁኔታ በሚጠበቀው ልክ ውጤት እያመጣ አይደለም የሚል ነበር።

ለመጀመሪያው ነባር ችግር ለፖለቲካው ለማህበራዊ ለታሪኩ ችግር ለውጡ መፍትሔ ብሎ ይህም ፓርላማ አጽድቆት የቀረበው ነገር አንደኛው ሀገራዊ ምክክር ነው። ምክንያቱም ያኔ ችግር ያልነውን ጉዳይ እኛ ብቻ ተሰብስበን መፍትሔው ይሄ ነው ልንል አንችልም፤ ተመክሮ፣ተወያይቶ አንደኛው ሌላኛውን ሰምቶ፣ የጋራ የሆነ እሳቤ መያዝን ይጠይቃል፤ ይቻላል ብያችኋለሁ ብዙ ሀገራት ቀያይረዋል፤በእኛም ሀገር ተደርጓል ግን አያዋጣም፤ በምክክር፣ በውይይት ሲደረግ ይበልጥ ጠቃሚ ይሆናል።

ከምክክር ባሻገር ምክክሩ ነገንም የሚሰራ ስለሆነ የምክክሩ ውጤት ለነገ ስለሆነ የሚገለገለው ትናንትና የነበሩ ጉዳዮችስ እንዴት እልባት ያገኙ? ለሚለው ደግሞ ትራንዚሺናል ጀስቲስ እንፍጠር ፤ ያለፉ ጉዳዮችን የምንቋጭበት፣ የምንዘጋበት መንገድ እናብጅ የሚል ነው። ሶስተኛው ተቋማን፣ ሕጎችን፣ አሠራሮችን እናሻሽል፣ ምን ያህል ሕግ ነው 40 ዓመት 50 ዓመት 60 ዓመት የቆየ የቀየራችሁት፤ ያሁሉ እኮ የዚያ አካል ነው። የምርጫ ሕግን ጨምሮ በጣም በርካታ ሕጎችን ከዚህ ቀደም የምንማረርባቸውን ያሻሻልነው፤ በለውጡ ከተነሱ አንኳር ጉዳዮች ውስጥ ስለሆኑና ምላሽ እንዲያገኙ ነው።

በወቅታዊ ጉዳዮችስ የእዳ ቀንበር በዛብን መቀነስ አለብን በሚል ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ያደረግነው ለዚህ ነው። እዳውን ቀነስነው እኮ፤ ፕሮጀክቶች ቆመዋል፤ እነ ህዳሴው ግድብ ችግር ውስጥ ናቸው፤ ሊፈቱ ይገባል፤ ተፈቱ እኮ! ተፈተው አለቁ ። ያኔ የነበረ ችግር ከዚያ ወዲህ የታከለ ችግር ተፈቶ አለቀ ማለት ግን አይደለም። ችግር ስንፈጥረው እንጂ ስንፈታው ጊዜ ወሳጅ ነው። ግን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ-ግብርን ቀርጸን እየሠራን ያለነው የሚጨበጥ የሚታይ ውጤት አምጥተናል።

በእርዳታ የምትታወቅ ሀገር እንዴት አድርገን የተረጂ ቁጥር ጨምረን ስንዴ እርዳት እናብዛ ከሚል ወጥተን ለረዱን እንመሰግናለን፤ አሁን እራሳችንን እንመግባለን፤ በሚል በፓርላማ ደረጃ መነጋገር እኮ የለውጡ ውጤት ነው። ለዚያ ለውጥ የታገለ፣ ለዚያ ለውጥ የደከመ፣ በየትኛውም አንግል ያለ ሰው፤ ይህን ውጤት ሲይ የልፋቴ ዋጋ ነው ማለት ነው ያለበት።

የእኛ ነገር ግን የሆነው ጥያቄ እናነሳለን፤ ለጥያቄው መልስ ሲሰጥም ጥያቄ እናነሳለን። በማንኛውም ጉዳይ ብትመረምሩ ሙስናን ጨምሮ ጥያቄ እናነሳለን ለምላሹም ጥያቄ እናነሳለን። ታግለን ላገኘነው ውጤት ፤ ታግለን ላመጣነው ፍሬ ክብር የሚሰጥ ባህል የለንም። አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩ ይሄ የቀብር ጠባይ ነው ይላሉ።

የቀብር ጠባይ የተጸናወታቸው ሰዎች ወይም የአዱሬ ባህሪ የተጸናወታቸው ሰዎች አምጡ ነው፤ በቃ የለም ። ቀብር አስር ጊዜ ብትሰጠው ዋጥ አድርጎ ጨምር ነው እንጂ ትናንትና ቀብረሃልና በቃ አይልም። ቀብር ሞት ይበቃ አይልም የሰጠነውን ነው የሚወስደው፤ እና ያገኘነውን ፍሬ የምናከብር፣ የምናመሰግን፤ ለቀረው ደግሞ በጋራ የምንሠራ ከሆንን የምናስበው ለውጥ ይመጣል። እንዲያ ካልሆነ በስተቀር ለምሳሌ በባህል ለውጥ እናምጣ ማለት ትክክል አይለም፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲን ማግለል ትክክል አይደለም፤ በጋራ ሆነን ለሀገር አጀንዳ ልንሰራ እንችላለን፤ አቃፊ አካታች የሆነ የፖለቲካ ባህል እንፍጠር አልን።

በካቢኔያችን፣ በአዲስ አበባ ፣ በክልሎች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ተካተው መሥራት ለኢትዮጵያ እኮ አዲስ ታሪክ ነው፤ አልነበረም ለውጡ ነው ያመጣው። ግን ሰምታችሁ ከሆነ እስከ አሁን የገቡት በውጤት የተለኩ፣ ውጤታማ የሆኑት እየተሸለሙ እየተወደሱ ይሂዱ ሳይሆን፤ ሀገራቸውን የሚያገለግሉ ሰዎች ከመንግሥት ጋር ከሠሩ፤ ትናንትና አካታች ሥርዓት ይፈጠር ያለው ሰውዬ የመጀመሪያ ጠላት አድርጎ የሚታገለው እነርሱን ነው።

አሁን የሽግግር መንግሥት እንደሚባለው ማለት ነው፤ ምን ማለት ነው ከዚህም ከዚያም ይውጣጣ ማለት ነው። የተውጣጣ መንግሥት ለመፍጠር ቁጥሩ አነሰ እናስፋ ሳይሆን የገቡትን ጠላት፤ እኔነኝ ያንን ቦታ መያዝ ያለብኝ የሚል እሳቤ የለም እንጂ አካታች የፖለቲካ ባህል መፍጠር የለውጡ ውጤት ነው። ከጠመንጃ ወደ ጠረጴዛ እንሂድ ኤርትራም ያላችሁ፣ ኬንያም ያላችሁ፣ አሜሪካም ያላችሁ ኑ ብለን እኮ እዚሁ ቤት ነው ጥሪ ያቀረብነው።

በሰላም ሁሉ መጥቶ፤ አይ የመጣሁት፤ የተጋበዝኩ የመሰለኝ አራት ኪሎ ነው ያ ካልሆነማ ጫካ አሉ እንጂ፤ ለውጡ ጋብዟል። ዋልታ ረገጥ የሆነ እሳቤ ይቅር ፤ የእኛ ሰፈር፣ የእኛ መንደር የእኛ ብሔር የሚለውን እንተው በጋራ እንደመር ሶማሌውም የሀገር ባለቤት ነው፣ አፋሩም የሀገር ባለቤት ነው፣ ትግራዩም የሀገር ባለቤት ነው፣ በጋራ ከሆን በቂ ሀገር ነው ያለን ይበቃናል ሀገሩ፤ ስንል በብሄር በሽታ ተጠምቆ በየቀኑ ስለብሄር የሚያቀረሸው ሁሉ እኛን በብሄር ሊክስ ይፈልጋል። ምንድነው ፈተናው ያላችሁ እንደሆነ ትልቁ ፈተና አዲሱን ሃሳብና አመለካከት ሰዎች ላይ መጨመር አይደለም።

የነበራቸውን ቆሻሻ አመለካከት ከእነርሱ ውስጥ ማውጣት ነው።የነበረው እንደሞላ ብርጭቆ ውሃ ይዟል። አዲሱ በየት በኩል ይግባ። አዲስ እንዲገባ የነበረው መደፋት አለበት። ያ እሳቤ ብዙዎችን ያስቸግራል። እዛም እዚም የትም ቦታ ብትመለከቱ ትልቁ ችግር አዲስ እሳቤ ለመቀበል መቸገር ነው። በዚህ ምክንያት ቅድም በኢኮኖሚ እንዳነሳሁት ብዙ አስደማሚ ውጤት እያመጣች ያለች ሀገር በትናንሽ ጉዳይ ስሟ እንዲጎድፍ፣ ጉዞዋ እንዲደናቀፍ፣ የጀመረችው የዲሞክራሲ ግንባታ እንዲደናቀፍ የሚሰሩ ሰዎች አሉ።

ታላቁ መፅሐፍ ‹‹የሞተ ትንኝ የተቀመመ ሽቶ ያበላሻል›› ይላል። ሽቶ ለመቀመም ጣጣው ብዙ ነው።ግን አንድ ትንኝ ታበላሸዋለች።እኛም ጋር የሚሰሩ ሥራዎች ወንድም ወንድሙን የሚገድል ከሆነ፣ ሰላም ከሌለ፣ በብሄር የምንገፋፋ ከሆነ ምንም ብናመጣ ትርጉም የለውም። ለዚህ ነው መስከንና ወደ ቀልባችን መመለስ የሚያስፈልገው።ከዚህ አንፃር ሰላምን እንመለክት። ሰላም በሀገራች ውሎ ያደረ ስር የሰደደ በሽታ ነው። ኢትዮጵያ ከግጭት ታሪክ ነፃ ወጥታ አታውቅም። ጀግኖች ናችሁ ሀገራችሁን ትወዳላችሁ የልማት እሳቤያችሁ ደስ ይላል ግን በረባው ባልረባው ትገዳደላላችሁ ነው የሚሉን።

አያቶቻችን የተዋጉት ቅድመ አያቶቻችን ተጣልተው

ባቆዩላቸው ጠብ ነው። አባቶቻችን የተዋጉት የአያቶቻቸውን ጠብ ነው። እኛ አሁን የምንዋጋው የአባቶቻችንን ጠብ ነው። ይህ ነገር እንዳይሸጋገር ይቁም በምክክር እናቁመው. እርስትም ወርሰን፣ ጦርነትም ወርሰን እንዴት ይሆናል። አያዛልቅም እናቁመው፡ ብለን ጦርነት እንዳይጀመር ያልከፈልነው ዋጋ የለም።

ለምሳሌ ሸኔ ጋር አባገዳዎች የሀገር ሽማግሌዎች ጫካ ልከናል። ሕወሓት ጋር እዚህ ሀገር ያሉ ባለሀብቶች ሰብስበን እባካችሁ የጥይት ድምፅ ትግራይ አያስፈልግም አስቁሙ ብለናል። አማራ ክልልም ተመሳሳይ ነው። ስንለምን የደከምን ይመስላቸውና ያስቸግራሉ። አሁን ችግር የሆነው ሁለት ነገር ነው። ስትለምን ይቅር እንነጋገር አይ ደካማ ስለሆኑ ነው።ሶስት ክላሽ ይዘው ውር ውር ሲሉ አራት ኪሎ ይታያቸዋል። ትንሽ መንገድ ሲጓዙ ካለ እነርሱ ጀግና የለም። አርበኛ የለም። ትንሽ ሲቆነጠጡ ደግሞ ዘር ማጥፋት ነው። አንተ ስትገድል ዘር ማጥፋት ካልሆነ እኔ ስገድል ሊሆን አይችልም። መግደል መተው ነው መፍትሔው።

አንገዳደል ቁጭ ብለን እንነጋገር ሲባል ዝግጁ መሆን ካልቻልን አንድ ጊዜ ከገባንበት በኋላ ጦርነት ባለጌ ነው። መልክ የለውም። አስቀያሚ ነው። ጦርነት መጀመር በጣም ቀላል ነገር ነው። ከኪስ ውስጥ በሚወጣ ትንሽዬ ክብሪት ስንጥር እሳት እንደሚለኮሰው ሁሉ በተለኮሰው መጠን ልክ አይጠፋም። ማገዶ አንድዶ ቤት አውድሞ ለማጥፋት አድክሞ ነው የሚጠፋው። እሳት መለኮስና ማጥፋት እኩል አይደለም። ጦርነትም እንደዚሁ ነው። ስትጀምረው ቀላል ነው። ጫር ነው የምታደርገው።ስትጨርሰው ማቆም እንኳ ቢሳካልህ ብዙ ሰው በልቶ ነው። ጥቅም የለውም። ለዚህ ነው በተደጋጋሚ የጥይት ድምፅ ይብቃን የምንለው። እኛ ውጊያ አንፈልግም። ብዙ የልማት ህልሞች አሉ። ለእርሱ ጊዜ የለንም።

ጊዜ የለንም ማለት ውትድርና አይገባንም ማለትም አይደለም። እንደዚህ አይነት ጨዋታ ለመከላከል አይገቡንም ማለት አይደለም።በርካታ ሰዎች በነዋይ ፍቅር ሰክረዋል። ያ የነዋይ ጥማታቸውን ለመመለስ የመጨረሻው ግብ ስልጣን መያዝ ነው ብለው ያስባሉ።እኔ ካልሁንኩ ይላሉ።እንዲያውም እግረ መንገድ ለአባቶቼና ለታላላቅ ወንድሞቼ ምክር ቢጤ ልለግሳቸው። በቅርቡ አንዳንድ ቦታ ላይ መፈንቅለ መንግሥት እናካሂዳለን ብለው አንዳንድ አባቶቻችን ውይይት ያደርጋሉ። መፈንቅለ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ አይሳካም። እኛ ወታደሮች ነን መፈንቅለ መንግሥት እንዳይሳካ አድርገን ነው ተቋማትን የሠራነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት አንድ ጊዜ ተሳክቷል። የዛሬ ሃምሳ ዓመት።ከሃምሳ ዓመት በኋላ ብዙ የሚረቡና የማይረቡ ሙከራዎች ነበሩ።አልተሳኩም።አሁን ጭራሽ አይሳካም።እና ለወንድሞቼና ለታላላቆቼ ምክር መስጠት የምፈልገው ጊዜ አታባክኑ።የወዳጆቻችንን ሀገር ገንዘብ አታባክኑ።ገስት ሃውስ አታጣቡ። አይሳካም።

በግጭት፣ በጦርነት፣ በሽፍታነት፣ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ኢትዮጵያ ውስጥ መያዝ ማለት ብሎኑ እንደተበላበት ጥርስ ማለት ነው። የሚሽከረከር እንጂ የማይሻገር። ስፓናቶ የሆነ ብሎን ዝም ብሎ ነው የሚሽከረከረው አያስርም። አይሻገርም።እዛው መርገጥ እንጂ መሻገር አይችልም።በተደጋጋሚ እንደዚህ አይነት ምክር ስንለግስ ቀለል አድርገው የሄዱ ሰዎች በኃላ ዋጋ ይከፍላሉ።

ለተከበረው ምክር ቤት ማረጋገጥ የምፈልገው ዛሬ ሰላም እንዲሆን ነው እኛ የምንፈልገው። ለሰላም የሚከፈል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁዎች ነን። ለምን

ከሰላም ውጭ ያለው አማራጭ እንደ ሞተ አንበሳ ዋጋ የለውም። አንበሳ በሕይወት ሳለ በምንም መመዘኛ ከውሻ ጋር አይወዳደርም።አንበሳ አንበሳ ነው። ጠቢቡ ምን ይለዋል የሞተ አንበሳ ሕያው ከሆነ ውሻ ያንሳል። ሕያው የሆነ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላል ምክንያቱም ሕያው ስለሆነ። ህያው የሆነ አስተሳሰብና እሳቤ ከሞተው ከዛ እሳቤ ይሻላል። ምን የሚለው እንሰብሰብ።አንድ እንሁን የሁላችን ሀገር ነው። በጋራ እናልማ በንግግር በውይይት በምርጫ እንመን ይህ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው።

እንበልና ይህ የማይሳካው ነገር ተሳካ እንበል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ገድለን መፈንቅለ መንግሥት ብናደርግ ኢትዮጵያን ሌላ ሱዳን እናደርጋት ይሁን እንጂ ሀገር ሆኖ እኛም መንግሥት ሆነን አንቀጥልም መቼም። እንዴት ነው ሰዎች የሚያስቡት። የኦሮሚያው ሸኔ ተሳክቶለት አዲስ አበባ ቢመጣ ምንያደርጋል ኢትዮጵያን ያፈርሳል እንጂ ከወዲሁ ካለ እኔ ሌላው ሰው አይደለም የሚል እሳቤ ይዞ። አማራ ክልል ያለው ሸኔ ቢመጣ ምን ያደርጋል።የአባቶቼን እርስት እወርሳለሁ እያለ። ይሕ የሁላችን እርስት ነው።

የአባቶቼ አይደለም፤ የአባቶቻችን እርስት ነው። የጋራ እርስታችን ነው። በጋራ ልንወርሰው፣ ልናለማው የሚገባ ነው። ይሄን እሳቤ ይዘህ ቢሳካልህ ዋጋ የለውም። ይሄንን መተው እና አረንጓዴ ባህል፣ ንጽህና፣ እውነትን መከተል፣ የሥራ ባህል፣ ድሃን መርዳት፣ ከሌብነት መጠበቅ፣ ኢትዮጵያን ከልብ አብዝቶ መውደድ፣ በሥራና በውጤት ማመን ባህላችን ብናደርግ ልጆቻችን መልካም ፍሬ ይወርሳሉ።

ፕሮፖጋንዳ፣ ውሸት ከሆነ ግን ጥቅም የለውም። እሺ በሆነ ጊዜ፣ በሆነ ምክንያት ወንድሞቻችን እንደዛ አስበዋልና እናስብ፤ ሰው ሲበሳጭ፣ ሲናደድ፣ ተገቢ አስተሳሰብ መያዝ ወይም (logical) መሆን ያቅተዋል። ልክ የፈላ ውሃ ፊታችንን ማሳየት እንደማይችለው፤ በውሃ ውስጥ ፊታችንን ለማየት ውሃ እንኳን መስከን ስላለበት፤ አሁን ደግሞ ሰክነው ተረጋግተው፤ ይሄ ጉዞ ሰው ይበላል፤ አያዋጣም፤ እንምከር እንነጋገር ቢሉ በጣም ጠቃሚ ይመስለኛል።

ለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሌ እንደሚለው አሁንም በጣም ዝግጁ ነው። ውጊያውን በሚመለከት የሚነሱ ጉዳዮች፤ አንድ ድርስ ውሃ ደርሶ ግመል በዚያ ውሃ ውስጥ ትሻገራለች። ግመል እንደተሻገረች ቀበሮ ሩጣ መጥታ ከዚያኛው ጫፍ ሆና ግመሉን፤ “ግመል ሆይ፤ ውሃው እንዴት የደረሰ ውሃ ነው። ብገባ እሻገርበት ይሆን ወይ፤ የት ይደርሳል” ስትላት “አይ ብዙም አይደል ከጉልበቴ ትንሽ ከፍ ያለ ነው” አለቻት።

“እንደዛማ ከሆነ ልሞክረው” ብላ ቀበሮ ገብታ ልትሻገር ስትል ውሃው አንገዳገዳትና እንደምንም ተመልሳ “ምነው ግመል ዋሸሽኚ” አለቻት። “እረ አልዋሸሁሽም፤ ከጉልበቴ ከፍ ያለ አልሁሽ እንጂ፤ ከጉልበትሽ ከፍ ያለ አላልሁሽም”። ሦስት ክላሽ ከያዝህ፤ በሦስት ክላሽ መመዘን አስቸጋሪ ነው። መንግሥት ስለሆነ የበለጠ መሳሪያ ይኖረዋል ማለት ነው። ከገባህ መግጠም ነው። ዋናው አለመግባት ነው። ከገባህ በኋላ ቦክስ እኳ አይደለም፤ ኪሎው ስንት ነው? ተብሎ የሚለካካበት ቦታ አይደለም ጦርነት። እንደዚህ አይነት እሳቤ ኢትዮጵያን ወደኋላ ስለሚጎትት መተው በጣም በጣም ይሻላል።

በአማራ ክልል ለተነሳው ጉዳይ፤ እምነቱን ጨምሮ በአማራም፣ በኦሮሚያም ክልሎች ያለው ዋናው ችግር በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል። አንደኛው “ዱር ግባ፣ ዱር የገባ ጀግና ነው፣ ዱር የገባ ስልጣን ይይዛል፣ ዱር የገባ ይከናወንለታል” የሚል ኃይለኛ የራቀ ፕሮፓጋንዳ ነው። የዚህ ፕሮፓጋንዳ ባለቤቶች እሳቱ አይለበልባቸውም፤ ጢሱ አያጥናቸውም። ልጆቻቸው አይነኩም፤ በእርቀት ይፎክራሉ።

ሁለተኛው ሰለባ ደግሞ “ጥራኝ ዱሩ” የሚለው ነው። ያነን ሰምቶ፤ “ጥራኝ ዱሩ” ይላል። ዱር የአንበሳ፣ የጅብ፣… የዱር አራዊት ቦታ ነው። የፖለቲከኛ ቦታ ከተማ፣ ፓርላማ፣ ምርጫ ክርክር፣ ሚዲያ ነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን። “ጥራኝ ዱሩ” ብሎ ከገባ በኋላ በዛፕሮፓጋንዳ ተሰልቦ ከዛ በኋላ የሚፈጠረው ቀውስ ለመፍትሄ ያስቸግራል። ብዙ ሰው ግምገማው (assessment) የራቀ ነው። ገብቶት ኢትዮጵያ ያለችበትን አውቆ አይደለም። አሁን ኢትዮጵያ ልትፈርስ ስለሆነ ምንም ነገር ስላልቀረ ብሎ ይገመግማሉ። ምንም አያውቁም፤ እኛ እኮ ጠንክረን ጠንክረን ብረት በሆንንበት ዘመን፤ በዚህ ጊዜ አምናና ታች አምና፣ ከዛበፊት የሚያውቀውን ታሪክ የሚገመግመው። ምክንያቱም አያውቅም ምን እንዳለ።

በዚህ ምክንያት ሊሠሩ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ በጣም በርካታ ወጣቶች በመጥፎ ነገር፣ በመጥፎ ፕሮፓጋንዳ ተወስደዋል። ይሄ እንዲቀር በተደጋጋሚ ልመና አድርገናል። ነገር ግን ሕዝቡ እምነት ጎደለው ለተባለው፤ መቼም ሕዝቡን ከናንተ በላይ እኛ እናውቀዋለን፤ ከናንተ በላይ እኛ እንመራዋለን፤ ከናንተ በላይ እኛ እናወያየዋለን። እኛ እንደድሮ መንግሥታት የተደበቅን ሳንሆን ሕዝብ ውስጥ የምንኖር ነን፣ እናውቀዋለን። ስለሕዝብ ለኛ መንገር ሳይሆን “እኛ አናምናቹህም” ቢባል እኛ እና እናንተ እንደፓርቲ ለመተማመን፣ ልንነጋገር እንችላለን።

ሕዝቡ ግን የአማራ ሕዝብ ወይም የኦሮሞ ሕዝብ መንገድ የሚሠራለትን ሰው ሳያምን፤ በመንገድ ላይ ድንጋይ እየደረደረ የሚዘጋበትን ሰው እንዴት ሊያምን ይችላል። ትምህርት ቤት የሚገነባለትን ሰው ሳያምን፤ ልጆቹ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ የሚከለክልለትን ሰው እንዴት ሊያምን ይችላል። ምን ያክል ብንንቀው ነው ሕዝቡን፤ ይቺን ለማመዛዘን። ግብርና ይሳለጥ፣ የበጋ ስንዴ ይብዛ፣ ልመና ይቁም ብሎ የሚተጋውን ጠርጥሮ፤ እንዴት ማዳበሪያ እንዳይንቀሳቀስ የሚያደናቅፈውን አርሶ አደሩ ሊያምን ይችላል።

እንደዚህ አንታለል። እንደዛ አይደለም የሕዝቡ ፍላጎት። ሰላም ይፈልጋል፣ ሕዝቡ ለውጥ ይፈልጋል፣ ሕዝብ እድገት ይፈልጋል። ነገር ግን ጫካም የገቡት ልጆቹ ስለሆኑ፤ እንደውጭ ወራሪ ጠላት “በቃ ጨርሷቸው” ብሎ አሳልፎ አይሰጥም፤ የልጅ ነገር ነው። ይሄን መቀበል ያስፈልጋል። ኢትዮጵያዊያን ከማንም ሀገር ጋር ብንዋጋ ፈተናው እንደአሁኑ አይደለም። እርስ በርስ ትናንትም መከራ ነው፤ ነገም መከራ ነው። አባት ልጁን ጠላ ማለት እንዲገደል አሳልፎ ይሰጣል ማለት አይደለም። ተነጋገሩ የሚለን ሕዝቡ ለዛ ነው። ለዛ እኛ በጣም ዝግጁዎች ነን።

እስረኛ መፍታት አሁን እኛ እንታማለን። “እንዴት እስረኛ ትፈታለህ?” ተብለን ስንገመገም፣ ስንወቀስ እንዳልነበረ። ያልፈታነው ጉድ አለ እንዴ? እስርቤቱን እኮ በሩን ከፍተን ነው የለቀቅነው። በዚህ አንታማም። አብረን እንሥራ በማለት እኛ እንታማለን? እየለመን እያወያየን፤ ቢሯችነን ከፍተን እያስገባን፣ ሰዎች ቢሯችን ሲገቡ ቢሯችን እያማራቸው “እዛው እንቆይ” እያሉ ተቸገሩ እንጂ። ለድርድር ክፍት መሆን እኛ እንታማለን? ጦርነት እያለቀ እያለ፤ ሰላም ይበልጣል፣ ድርድር ይሻለናል በሚል አልተወያየንም እንዴ? እኛ ለድርድር ክፍት ነን። በሰለጠነ መንገድ ለሚደረግ ንግግር ምንም ችግር የለብንም።

ግን “ደካማ መንግሥት” ብላችሁ የምታስቡ ግለሰቦች እና ቡድኖች፤ መንግሥት ደካማ እንኳን መሆን ቢፈልግ እንዳትፈቅዱለት። ኢትዮጵያ ትፈርሳለች። ደካማ መንግሥት አያስፈልገንም፣ አፍራሽ ብዙ ነው ያለው። አታዩም እንዴ የሱዳን ወንድሞቻችን ምን እየሆኑ እንዳሉ። መፍረስ ለልጆቻችን አይጠቅምም።

የታሰሩ ግለሰቦችን በሚመለከት በሁለት መንገድ ማየት ጥሩ ነው። ለምሳሌ ከዚህ ፓርላማ የታሰሩት ወንድማችን፤ ሁሉም ተቃዋሚ የሚታሰር ከሆነ፤ ጠያቂየ ለምን አልታሰሩም? ጠያቂየ እኳ ተቀምጠው እየጠየቁኝ ነው፤ እዚህ። እርሶዎን የሚያስቀምጥ፤ እርሳቸውን የሚያሳስር ነገር ካለ ልዩነት (difference) አለ ማለት ነው። ልዩነቱን ግን እኔ ዳኛ አይደለሁም፤ ወንጀለኛ ናቸው፣ ጥፋተኛ ናቸው ልል አልችልም። የፍትህ ሥርዓቱ አይቶ፤ መርምሮ ፍርድ ይስጥ።

የግል ምኞትህ ያሉኝ እንደሆነ ግን እርስዎም እርሳቸውም ከእርሶ ጎን ተቀምጠው ባያቸው ደስታውን አልችለውም። በሰላማዊ መንገድ አራት ኪሎ ተቀምጦ ጉዞ ወደ አራት ኪሎ ከሚሉ አራት ኪሎ ተቀምጠው ጉዞ ወደ ፓርላማ እያሉ በሰላም ቢታገሉ ችግር የለብንም። የግል ጥላቻ የለኝም፤ የግል መግፋትም የለብኝም። ሕግ ከፈታቸውና ከእኛ መካከል ቢሆኑ ደስታውን አልችለውም። ግን ሁላችንም ማወቅ ያለብን የፓርላማ አባል መሆን፤ ጋዜጠኛ መሆን፤ ሚኒስትር መሆን ማዕከላዊ ኮሚቴ መሆን ከወንጀልና ከጥፋት አይታደገንም። አለማጥፋት ነው ፤ የእኔ ዋስትና አለማጥፋት ነው። ከአጠፋሁ እመጣለሁ ያለመከሰስ መብቴ ይነሳል እጠየቃለሁ።

እዚህ አካባቢ መቀመጥ ለማንኛውም ጥፋት ዋስትና አድርገው ጋዜጠኛ ዝም ብሎ መንገደኛ ይነሳና ዩቲዩብ ከፍቶ እኔ ጋዜጠኛ ነኝ እንደሚለው ያ ትክክል አይደለም። ጋዜጠኛ ህግ አለው፤ ወታደርም ህግ አለው መጠየቅ አለበት እንደተባለው ነው። ሚኒስትርም ህግ አለው በዚያ አግባብ ማየት ነው ጠቃሚ የሚሆነው። በዚያ አግባብ ማየት ካልቻልን ሳናስበው ስራችንን ቆርጠን እንጥልና በኋላ የማንጠግነው ነገር ይፈጠራል። በዚህ አግባብ ማየት ጥሩ ነው።

አማራ ሰላም ካላልሆነ፤ ኦሮምያ ሰላም ካልሆነ፣ ትግራይ ሰላም ካልሆነ የመጀመሪያ ተጎጂ እኛ ነን። ኢትዮጵያን ማበልጸግ ስለምንፈልግ አይሳካልንም ማለት ነው። ሰላሙን አብዝተን እንወዳለን። እዚህ ጫፍ ያለው አሀዳዊ መንግሥት ነው፤ የአማራ መንግሥት ነው፤ ብሎ ሲከስ ይውላል፤ እዚህ ጫፍ ያለው የኦሮሞ መንግሥት ነው ብሎ ሲከስ ይውላል። ይህ የኦሮሞ መንግሥት አይደለም፤ የአማራ መንግሥት አይደለም።

ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት ነው። ሁሉን ኢትዮጵያዊ በእኩል የሚወድ በእኩል የሚያገለግል ነው። በአንድ ጽሁፎቻችንን፣ በአንድ ስልጣናችን ፣ በአንድ ንግግራችን፣ በአንድ ተግባራችን አድሎ አይገኝም። ሁላችንም በዚያ መንፈስ እኩል እንሁን። እኔ ብቻ የሚለው ግን አይጠቅምምና በጋራ ሆነን ሀገራችንን ብናለማ ፤ ለልጆቻችን መልካም ነገር ብናስቀምጥ ይሻላል። በዚሁ መንፈስ መሄድ ነው እምነት ስጋት ባይሆንብኝም እምነትም ቢሆን የመጀመሪያው እምነትን መፍጠሪያ መንገድ ንግግር ነው።

ታዲያ በደብዳቤ አንተማመን። በሚዲያ ፕሮፓጋንዳ አንተማመን ፤ ተገናኝተን አምንሃለሁ አላምንህም እንዴት ዋሽተሃል ተሳስተሃል ተባብለን ተነጋግረን ጥፋት ካለ ይቅር ተባብለን ነው መተማመን የሚፈጠረው። እንነጋገር ያልነው እኮ መነጋገርን ሲለምኑ ኖረው አሁን ተነጋገሩ ስንል መነጋገር አያስፈልግም ።

 

 

ሌላው መታወቅ ያለበት ነገር በእንደዚህ አይነት መነጋገርና ምክክር በምርጫ የተመረጠ መንግሥት ብዙ የሚያገኘው ነገር የለም። እኛ እኮ ተመረጥን እኮ። በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመረጥን። ሁለት ዓመት አለን ማንም አይነካብንም። ንግግርና ውይይት እድል የሚሰጠው በምርጫ ላላሸነፉና ሀሳቦች አሉን፤ ሕዝብ ሀሳባችንን ቢያደምጥ፣ አውድ ቢፈጠር መድረክ ቢፈጠር ሀሳቦቻችንን ሊገዙ፣ ሊደመጡ ይችላሉ የሚሉ ሰዎች ተጠቃሚዎች ናቸው። እንቢ ባዮች ደግሞ እነርሱ ናቸው። ይህንን በደንብ አስተውሎ መነጋገር ያስፈልጋል። እስካሁን ያየሁት ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ነው አዲስ አበባ ላይ ያለው። አግዘን አብረን ብንሰራ ጥሩ ይመስለኛል።

በእኛ በኩል ባለፈውም እንዳነሳሁት በናሽናል ዲያሎጉ ጣልቃ መግባት አንፈልግም አምነን እንደማንኛውም ፓርቲ ተወያይተን ፤ ጠቃሚ ሀሳቦች ካሉ ወስደን ካላመንን ተከራክረን ሕዝብ ይዳኘን ለማለት ዝግጁዎች ነን። በህዝብ ዳኝነት የሚያምን ማንኛውም ሰው ከውይይት መሸሽ የለበትም። ህዝብ ዋጋ የለውም ካለ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም።

ፕሪቶሪያን በሚመለከት ፕሪቶሪያ የባህል ለውጥ አካል ነው። ነገን በዊጊያ ጀምሮ በዊጊያ መጨረስ አያስፈፈልግም የሚል አካል ነው። በጣም ጥሩ ድል ነው። በፕሩቶሪያ ምክንያት ተኩስ ቆሟል፤ የሚጠፉ ሕይወቶች ቆመዋል። የቆሰሉ ሰዎች ህክምና እያገኙ ነው። የተለያዩ ቤተሰቦች ተገናኝተዋል፤ መንቀሳቀስ የሚቸገሩ ሰዎች መንቀሳቀስ ጀምረዋል። የታሰሩ ተፈተዋል፤ ከስራ የታገዱ ስራ ይዘዋል። መብራት፣ ባንክ፣ አየር መንገድ፣ ቴሌኮሚኒኬሽን በጣም በርካታ ሰርቪሶች ሥራ ጀምረዋል። ይህ ሁሉ ድል ነው። የትግራይ ሕዝብ ያገኘው እፎይታ የእኛም እፎይታ ስለሆነ።

በባለፈው ከትግራይ ከተውጣጡ ሰዎች ጋር ስንወያይ ሁለት አንኳር ነገር አንስተውልናል። መንግስት መቋቋሙ ጥሩ ነገር ነው፤ ሰርቪስ መጀመሩ ጥሩ ነገር ነው። የተጀመረው ልማት ይጠናከር፤ ለምሳሌ ዩኒቨርስቲ እንኳን ብንወስድ ምን ያህል እንደተገነቡና ስራ እንደጀመሩ ሰሞኑን ሲያስመርቁ ኤታችሁ ሊሆን ይችላል። እንደማንኛውም ዩኒቨርሲቲ ጥያቄ አላቸው። በጀት ፤ ግንባታ ጥያቄ አላቸው። ከነአካቴው ከመቆም ስራ መጀራቸው ጥሩ ነገር ነው።

አንኳር ጉዳይ የነበረው መልሶ ማቋቋምና የተፈናቀሉ ሰዎችን በሚመለከት ነው። ልክ በኢኮኖሚ ቅድም እንዳነሳሁት በተፈናቀሉት ሰዎች በጣም ጥሩ እምርታ ነው ያለው። በራያና በጸለምት የተፈናቀሉ ሰዎች የመመለሱ ሥራ ጥሩ ጅማሮዎች አሉት። በራያ የነበረው አመላለስ ችግር አለበት። ከአስቀመጥነው አቅጣጫ፣ ከአስቀመጥነው መንገድ ወጣ ያለ ነው። እኛ ግን ወጣ ስላለ እንዋጋ አላልንም።

ቅድም እንዳልኩት ጠርተን ተወያይተን፣ ተመካክረን መታረም ያለበት እንዲታረም አድርገን ነገር ግን የተመለሰው ህዝብ ደግሞ እናንተ ስላጠፋችሁ ተመለሱ ተብሎ ከሚወጣ በአስቀመጥነው አቅጣጫ የሚቆበት መንገድ ይፈጠር ብለን ለማስተካከል ሙከራ እያደረግን ነው። በጸለምት ደግሞ ከራያ ተምረን የተሸለ ጅማሮዎች አሉ። ይህ ማለት አልጋ በአልጋ ማለት አይደለም። አንዴ ከዚህ አንዴ ከዚያ ሰዎች እንቅፋት ይፈጥራሉ።

እንወያያለን፣ እንስማማለን፣ እንዘጋጃለን የሆኑ ሰዎች ይነሱና እንቅፋት ይፈጥራሉ። በትግራይ ክልላዊ መንግስት የሽግግር መንግስቱ፤ በህውሃት ዋና ዋና ኃላፊዎች እኔ ያለኝ አሁን ያለኝ እምነት በሰላማዊ መንገድ ጉዳዩ እንዲፈታ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፤ በዚህ አግባብ እየሰሩ ነው። ከመንግስቱና ከህውሃት ኃላፊዎች ውጪ ግን ነገር ቢበላሽ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። አሁንም እለኸኝነታቸው ያልቀነሰ፣ አሁንም የበዛ ቁጣ ያላቸው ግለሰቦች አሉ።

ለእነርሱ ያለኝ ምክር እልኸኝነትና የበዛ ቁጣ መጀመሪያ እናንተን ይጎዳል፤ ወንድሞቻችሁን ይጎዳል ጥሩ አይደለም ተዉት። የትናንትናን ጥፋት በሚደግም መንገድ አትሂዱ፣ የክልሉን መንግስት አግዙ፤ ባለፈውም ብያለሁ አግዙ ማለት መልካም ሀሳቦች አብራችሁ ሁኑ። ችግር ካለ ደግሞ አርቁ አርሙ ማለት ነው። በዚህ አግባብ ከሄድን ትግራይ ያለው ቁስል በአንዴ ይሽራል ባይባልም በጣም በጣም ከፍተኛ እርምጃ ነው። እስኪ አስቡት ፕሪቶሪያ ላይ የነበረው ንግግር፣ ዋነኛ ንግግር ሰርቪስ ይመለስ ነው። መቶ ፐርሰንት ተመልሷል። በትግራይ የሽግግር መንግስት ይቋቋም ነው። መቶ ፐርሰንት ተመልሷል።

እዚያ ውስጥ ሀረግ ያስገባነው የተፈናቀለውን ሰዎችና አጨቃጫቂ ቦታዎች በህገመንግስቱ ይመለስ ነው ያልነው እንጂ አሁን በምንሄደው መንገድ ዝርዝር እቅዳችን እንጂ ፕሪቶሪያ ላይ የለም። ግን በዝርዝር እቅዳችን ህገመንግስቱን መሰረት አድርገን የተፈናቀሉ ሰዎች ከየትም ቦታ ቢሆን መመለስ አለበት ባልነው አቅጣጫ መሰረት ከትግራይ ተፈናቅለው የቆዩ ሰዎች በጥቂት ቁጥርም ቢሆን መመለስ ጀምረዋል።

ከአማራም ቢሆን ወደ ኦሮሚያ እንደዚሁ በመቶ ሺህዎች ተመልሰዋል። ይሄ መጠናከር አለበት። ዜጎች ተንቀሳቅሰው መስራት፣መኖር የሚችሉበት ነገር መስፋት አለበት። ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ውስጥ ኤርትራዊያን፣ሱዳናዊያን፣ሱማሊያዊያን በነፃ በሚንቀሳቀሱበት ሀገር ውስጥ፣በስደተኛ ካምፕ ውስጥ በማይቀመጡበት ሀገር ውስጥ ኢትዮጵያዊያን ከቦታቦታ መንቀሳቀስ መቸገር የለባቸውም። ይሄ ድካማችን ነው ማስተካከል አለብን። በዚህ አግባብ ነው እየተሄደ ያለው።

ነገር ግን ቻይናዎች አንድ አባባል አላቸው። አንዳንድ ሰዎች መቶ ፐርሰንት ጊዜያቸውን በመክሰስ፣ በመቆጣት፣ የሁሉ ነገር ጥፋት የላይኛውን ሰው በማድረግ ያጠፋሉ። እነዚህ ሰዎች ሞተዋል ይሏቸዋል፤ ሁልጊዜ ለጥፋቱም፣ ለልማቱም፣ ለውጊያውም ወቃሽ የሆነ ሰው የሞተ ሰው ነው። ግማሽ የሚኖር ሰው ደግሞ ሌላ መውቀስ ትቶ ራሱን ይወቅሳል። ሃላፊነት መውሰድ አይደለም መወቀስ፤ እሱም ግማሽ መኖር ነው፤ ትክክል አይደለም። ዋናው ከወቀሳ መፅዳት ነው። ትክክል የሆነውን ማድረግ ነው። ጥፋት ተፈፅሞ እንኳ ከሆነ ከዚያ ተምሮ ወደ መልካም ነገር መሄድ ነው። ትላንትናን እየጠቀሱ ነገን ማበላሸት ተገቢ አይመስለኝም።

እናም በዚያው መንፈስ ፕሪቶሪያ ወደኋላ እንዳይመለስና ዳግም እልቂት እንዳንሰማ፣ዳግም ሰው እንዳይሞት በተቻለ መጠን በከፍተኛ ትግስት ነገሩን መምራት ጠቃሚ ነው። በዚያው መንገድ ነው እየሄድን ያለነው። ብዙ ጊዜ ችግሮች ሲፈጠሩ ቶሎ ወደ ግጭት እንዲገባ የሚገፋፉ ሃይሎች ከግራም ከቀኝም አሉ። እኛ ግጭት አንፈልግም። በትግራይም፣ በአማራም፣ በኦሮሚያም በሌላም አካባቢ ግጭት አያስፈልገንም። ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን ሰብስበን ልማት ላይ ማዋል እንፈልጋለን። ሰላምን ግን በነፃ አናገኛትም። በብዙ ትዕግስት፣ በብዙ ድካም ነው የምናገኛት። ለዚያም መከፈል የሚገባውን ዋጋ ለመክፈል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

ሠብዓዊ መብትን በሚመለከት ሠብዓዊ መብት ደስ የሚል ቋንቋ ነው። ለሰዎች የሚደረግ መብት እንደው በግርድፉ ሲታይ ደስ የሚል ቋንቋ ነው። ነግር ግን ይሄ ቋንቋ ከዋናው የትርጉም ግንድ ወጥቶ የፖለቲካ መጠቀሚያ እየሆነ ነው። ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የሚታመሱት በዚህ ታርጋ ነው። ለሰው ልጆች መብት ማሰብ፣ የሰው ልጆችን ማክበር /ዝም በሎ በዩቲዩብ በመናገር ብቻ ሳይሆን የተሻለ ቤት እንዲኖራቸው፣ የተሻለ ቦታ እንዲማሩ፣ እንዲበሉ፣ የተከበረ ሕይወት እንዲኖራቸው ማድረግ ጭምር ነው መብቱ እንጂ ስለእነሱ ምግብ፣ ስለእነሱ ቤት ሳትጨነቅ በሚዲያ መናገር ብቻ መብት ሊሆን አይችልም።

አሁን የተከበረው ምክርቤት ብዙ ነገር ሳላበዛ የሠብዓዊ መብት የሚባል አዋጅ፣ ተቋም፣አሠራር መፈተሽ ያስፈልጋል። እኛ ደመወዝ የማንከፍለው፣ ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለእናንተ መተው ነው።

እኔ አሁን የማያቸው በየትም ቦታ ያሉ የሠብዓዊ መብት ሃሳቦችና ተቋማትን ልክ እንደመርፌ ነው። መርፌ የራሱን ቀዳዳ መስፋት አይችልም። የራሳቸውን ደካማ ጎን ማየት አይችሉም። ይሄ ጥሩ አይደለም። ሀገር ያፈርሳል፤ ጥቅም የለውም። ተቋሞቻችንን ፀዳ ማድረግ አለብን። እነዚህ ተቋማት ከሁለት ተፅእኖ ነፃ መሆን አለባቸው። ከኢትዮጵያ መንግሥት ተፅእኖ ነፃ መሆን አለባቸው። እኛ እየገባን እንደፈለግን የምናደርጋቸው መሆን የለባቸውም። ከሌላም ሀገራትና ፍላጎቶች ነፃ መሆን አለባቸው። አሁን ያሉት ከኛ ነፃ ሆኑና እንደሱ አይሠራም መስተካከል ያስፈልገዋል።

ያ ማለት ግን የሠብዓዊ መብት ኢትዮጵያ ውስጥ አይፈጸምም ማለት አይደለም። ስህተቶቻችንን በደንብ ማረም መገምገም ኃላፊነት መውሰድ ይጠበቅብናል ። ከዚህ አንፃር መከላከያና ፖሊስን በእጅጉ ማመስገን እፈልጋለሁ።

መከላከያ ዛሬ በሺህ የሚቆጠር አባላቱ በወታደራዊ ፍርድ ቤት እሥር ቤት ነው ያሉት። ከኮድ ኦፍ ኮንዳክት ውጪ በማይገባ መንገድ ኦፕሬሽን ሠርታችኋል ተብሎ። በጅምላ ግድያ ምናምን የሚባለው በጅምላ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥትና ወታደር አይገድልም። በጅምላ ለማሸነፍ ይነሳና ሲሞት ነው ፤ በጅምላ ሞቱ የሚለው እንጂ አይገድልም። ማንኛው ስህተት ደግሞ ከተፈጸመበት ኃላፊነት ወስደን እናርማለን ። እንዴት አድርገን ሕዝባችንን እንገድላለን? ከሕዝባችን ማንስ ይገድላል? ማነው ራሱን የሚገድለው ? የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ማለት እኮ ሁሉም ነው። ነገር ግን ለተፈጠሩ ስህተቶች በየቦታው ለሚያጋጥሙ ስህተቶች በጣም በጣም የተሻለ ሥነ ምግባር ያለው /ኤቲካል ሠራዊት ያለን ቢሆንም ግለሰብም ቢሆን ችግር ከፈጠረ መጠየቅ አለበት ።

በቅርቡ አንድ ሱዳናዊ ባለሀብት አግኝቼ ነበር። ይሄ ባለሀብት በካርቱም ብዙ ፋብሪካዎች አሉት። ኢትዮጵያ ውስጥ ትግራይ ፋብሪካዎች አሉት። እና እኛ ውጊያ ላይ በነበርንበት ጊዜ አልመጣም። አሁን ሱዳን ውጊያው ሲፈጠር መጣ። እዚያ ያለው ካርቱም ያለው ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ወድሟል። እና እዚህ ሲመጣ የትግራዩ በጣም ስለተጋነነ ወድሟል ብሎ አስቦ ነው የመጣው። ትግራይ ሲሄድ ግን ፋብሪካው አንድ ስንጥር አልተነካም። የት ተዋጋችሁ? መች ተዋጋችሁ? ነው ያለው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አንድም የትግራይ ከተሞች በሚወድሙበት አግባብ አልሠራም። ፕሮፓጋንዳውን ተዉት። ካላመናችሁ እስኪ ነገ ሂዱ። ነገ ሂዱና መቀለ ከተማ ውስጥ አዲግራት ከተማ ውስጥ ውጊያን ፈልጋችሁት ካገኛችሁት ጠይቁኝ ስትመጡ። አይታይም። በጥንቃቄ የተመራ ያ ማለት ግን ስህተት አልነበረም ሰው አልተጎዳም ማለት አልነበረም። ውጊያ ባለጌ ስለሆነ ይጎዳል። ያን እያረሙ እያረሙ መሔድ ያስፈልጋል ። በድምሩ እንደዛ የምናነሳ ከሆነ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።

የሕዝብ እምነት ቅንጣት ጥርጥር የለኝም። 24 ሰዓት የሕዝብን ሕይወት ለመለወጥ የሚተጋ መንግሥት ሕዝብ ካላመነ ማንን ያምናል? በደንብ ነው የሚያምነው ሕዝባችን። ይሄንንማ በምርጫ አረጋገጠልን። በሚቀጥለውስ? በደንብ ካልሠራን፤ የፓርላማ አባላት በሁለት ዓመት ውስጥ ቃል በገባነው ልክ ካልፈጸምን የኢትዮጵያ ሕዝብ አይመርጠንም። ለመታመን ከመረጥን እንሥራ። አሁን በጀመርነው መንገድ ሳናቋርጥ የእኛና የሕዝብ ኮንትራት የእኛና የሕዝብ መተማመኛ ተግባር ነው። ከተማ እንቀይራለን ብለን ከተማን አፍርሰን ስንሠራ እያየን ካለመነን በምን ያምናል? እምነት የሚገነባው በሥራ ነው። በዚህ አግባብ መቀጠል ጠቃሚ ይመስለኛል። በእኛ በኩል ያለውን ለማረም የሚጋነነውን ደግሞ በሚዛን ማየት መልካም ይሆናል።

ሙስናን በሚመለከት ሙስና ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የሆነ ምልከታ አለው። እኔ የፓርላማ አባል ሆኜ በቆየሁበት ጊዜ ልክ ቀደም ተብሎ እንደተነሳው በዚያው መንገድ ነበር ሙስናን አልታገልንም ፣መታገል አለብን እያልኩ የማነሳው፤ አሁን ባለሁበት የሥራ ቦታ ግን ትንሽ ነገሮች ለማየት ዕድል ስላገኘሁ በሚዛን ነው ነገር የማየው።

አንደኛው ሌብነት ነቀርሳ ነው። ሌባ ሰው ምንም ቢሆን ዋጋ የለውም። ለራሱም ለልጆቹም፤ ሌብነት መጠን የለውም ትንሹም ትልቁም መጥፎ ነው። መጥፋት አለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ እየተጀመረ ያለው የሌብነት አካሄድ የምናስበውን ጉዞ ያደናቅፋል፤ በሽታ ነው። ብንዋጋው ልናቆመው ይገባል። ይህ ሃሳብ ነው። ለዚህ ነው የሲቪል ሰርቪስ ርፎርም፣ የሕግ ማሻሸያ፣ የተቋማት ርፎርም፣ የምንለው መታረም መታረቅ የሚገባቸው ጉዳዮች ስላሉ ነው።

ግን ይህ ፓርላማ ሙስናን እንድንታገል ይፈልጋል ወይ? ትፈልጋላችሁ? የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙስናን እንድንታገል ይፈልጋል ወይ? አዎ፤ በአፍ አይደለም በተግባር ነው። ለምሳሌ በቀደም የንብረት ማስመለስ አዋጅ ወጥቶ ነበር። በትንሹ እሱን ብቻ ልመልከት ። ጥቅት ግለሰቦች ኢትዮጵያ ውስጥ በረከት ያሉ ቢሊዮኖች ቁጥራቸውን አልጠራም። በርከት ያሉ ቢሊዮኖች ዝም ብለው አየር ላይ የሚንቀሳቀሱ ብሮች አገኘን፤ ብዙ ናቸው ቢሊዮንስ ናቸው። እነዚህ ብሮች ምንጫቸው የት ነው ብለን ስንከተል የገንዘቡ ባለቤት ሆነው ያገኘናቸው አርሶ አደሮችና እንኳን ቢሊየን ሚሊየን ብር ያላዩ ሰዎች ናቸው።

ምንም በማያውቁ አክስቶች፤ ምንም በማያውቁ አያቶች የሚንቀሳቀሱ ትላልቅ ገንዘቦች አሉ፤ ይህንን ገንዘብ ከየት አመጣህ ብሎ መጠየቅ የኢትዮጵያ መንግሥት አይችልም ሕግ የለም፤ እኔ ለምሳሌ ሌባ ሆኜ ሰርቄ በአንድ አጎቴ አርሶ አደር ስም የሚነግድ ከሆነ በእኔ አካውንት ላይ ካልታየ በስተቀር ማንንም መጠየቅ አይቻልም።

ይሄ ትክክል አይደለም መመርመር አለበት፤ ከፍተኛ ሀብት የሚያንቀሳቅስ ሰው ከየት እንዳመጣው ማስረጃ ማቅረብ አለበት ብለን ተወያይተን ሕግ ስናወጣ፤ ከውጭ አስር ዶላር ለላከው ሬምታንስ ሃያ ብር ለላኩ ሰዎች እነርሱን ለመቅጣት ታስቦ ነው ተባለ፤ አይደለም። ሌቦች አሉ እነዛን ሌቦች በሕግ ለመጠየቅ ግን ድሮ የነበረው አካውንት ይታይ ነው። ፀረሙስና የሚመዘግበው እኮ አካውንት ነው። አሁን ቀረ እሱ ፋሽን፤ ያ ብር የሚንቀሳቀስበት ሰውዬ እራሱ ስለማወቁ እርግጠኛ አይደለሁም። እንፈትሽ ስንል አየር ላይ የነበረውን ጫጫታ አይታችሁታል። ቁርጠኛ ከሆናችሁ የሚወጡ ሕጎች ጤነኞችን ለመንካት አይደለም፤ ሌቦችን ለማረም ነው።

ርምጃ በሚመለከት እኮ እናንተ ውይይት ላይ አንስታችኋል፣ በሺህ የሚቆጠር ሰው ታስሯል፣ በርካታ ሀብት ተመልሷል ግን በቂ አይደለም። ከዚያ በላይ ሥራ ያስፈልጋል። እነዚህ ሰዎች ብር ስላላቸው ዩቲዩቤሩን፣ ፌስቡክሩን ይከፍሉትና ያንጫጩታል ገና ሕጉ ሳይወጣ ሰንሰለት ስለሆነ ይንጫጫል፤ እኛ ደግሞ ስናጣራ እሱን እናረግባለን አንዳንድ በትክክል ያልተናበብንባቸው አዋጆች ጥፋት ሊያመጡ ይችላሉ። በመንግሥት በኩል ያለ ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ አይገባም።

በሁለት መንገድ ግን የተከበረው ምክር ቤት (balance) እንዲያደርግ እፈልጋለሁ። አንደኛ የኢትዮጵያ መንግሥት መቶ በመቶ ከፈለጋችሁ አንድ ሚሊዮን

ፐርሰንት እርግጠኛ ሆኜ የማወራው መንግሥታዊ ሌብነት አያካሂድም። ውሸት ነው። የፈለገ የዓለም ተቋም የፈለገ የዓለም ሳይንቲስት መርምሮ መንግሥታዊ ሌብነት አንድ ብር ሊያገኝብን አይችልም። እኛ የኢትዮጵያን ሀብት አናሸሽም ለዚህ ነው ከተማችንን የምንሠራው። ሲሸሽማ እናውቃለን እኮ ሥራ እንዴት እንደነበረ፤ አንድ ብር መንግሥታዊ በሆነ መንገድ (re direct) አያደርግም ይሄ መንግሥት። ያገኛትን ስሙኒ ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያፈሳል።

በዚህም ምክንያት ተቃዋሚዎቻችን ሥራችንን መደበቅ ሲያቅታቸው ከየት አምጥተው ሠሩት ይላሉ። መንግሥታዊ ሌብነት የለም ፤ ይህ ማለት ግን ግለሰቦች፣ ሥራ ላይ ያሉ ሃላፊዎች አይሰርቁም ማለት አይደለም። ሰዎች ላይ ይወራል፤ እንገመግማለን፣ እንፈትሻለን፣ ምንም አይነት ነገር ለማግኘት ስንቸገር ክትትል እንቀጥላለን። ቅድም እንዳልኳችሁ ምናልባት በስም ለውጥ ተደርጎ ከሆነም በዚህ አዋጅ አማካኝነት ሊገኝ ይችላል።

አለበለዚያ እኛ ጠንቋይ አንቀልብም፤ ዝም ብለን እንዲሁ አይተን ሰው በምን እናውቃለን። እስቲ የፓርላማ አባል የተጨበጠ አቶ ከበደ አስር ብር ሰርቆ እዚህ ጋር አድርጎ አስቀምጧል ይበለንና ርምጃ ካልወሰድን ይጠይቀን፤ ጥቅል ንግግር ከሆነ ግን መንግሥት ይቸገራል። ክስ ሂደት አለው ፍርድ ቤት ሲሄድ፣ አቃቤ ሕግ ጋር ሲሄድ በምርመራ ሂደት ውስጥ ውድቅ ይደረጋል፤ ይህንን ፈተና መገንዘብ ጠቃሚ ነው።

ሁለተኛው የተከበረው ምክር ቤት ቢያስተውል ጥሩ የሚሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሙስና የትም አፍሪካ ሀገር ካለው ሙስና አይወዳደርም። በብዙ የአፍሪካ ሀገራት የአንድ ፓርላማ አባል የሚበላው ደሞዝ እዚህ ያላችሁን የአስር ሃያ ሰዎች ደሞዝ ሊበልጥ ይችላል። አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች የአንድ ሳምንት ደመወዛቸው የእኔን የዓመት ደመወዝ ሊያክል ይችላል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያገለግሉ ሰዎች በውስጣቸው ሌብነት ኖሮ ፓርላማው አስፈፃሚው በየደረጃው ያለ አመራር ሕይወቱን ጎድቶ ተቸግሮ ነው ሀገሩን የሚያገለግለው። ለዚህ ነው ህዳሴን የምንገነባው፤ ለዚህ ነው 25 ሺህ ኪሎሜትር መንገድ የምንገነባው። እንጂ ብንከፋፈለው እኮ ብሩ ያልቃል። ይህንን ማየት ጥሩ ነው።

በትናንሽ ገንዘብ ሕዝባችሁን እያገለገላችሁ የእናንተን አይነት ሥራ የሚሠሩ ሰዎች በጣም የገዘፈ ነገር እየወሰዱ እኩል መንግሥታዊ ሙስና ከተባለ ይህንን አነፃፅሮ ማየት ይጠቅማል። ይህ ማለት ግን አስር ብርም ይሁን አንድ ሺህ ብር ወይም ሃምሳ ሺህ ብር የሚሰርቁ ሌቦችን ላለመታገል ምክንያት መሆን አይችልም። አቅማችን በፈቀደ መጠን ሌቦችን እየተከታተልን ርምጃ መውሰድ አለብን።

ሌብነት ለኢትዮጵያ አደገኛ ጸር መሆኑን ማስተማር አለብን። ለሌብነት እንዳይመች አሠራሮቻችንን መቀየር አለብን። ለዚህ ነው ከ600 በላይ አሠራሮች እና ሥርዓቶች/ ሲስተሞች አውቶሜት የተደረጉት። ተገልጋይ እና አገልጋይ እንዳይገናኝ ለማድረግ ነው። ይህንን ባላንስ አድርጎ መሄድ ብንችል በጣም ጠቃሚ ይመስለኛል።

ሌብነቱ አለ እናስቀር እንታገል ትክክል ነው፤ ሌብነትን ግን አጋኖ ማሳየት ተገቢ አይደለም። የኛን ኑሮ የምናውቀው እኛ ነን ፣ የየትኛው ሀገር ነው የኛን ሌብነት የሚያጠናልን? የእኛን ኑሮ እናውቀዋለን የነሱን ያውቁታል። እንደዛ ሚዛኑን የሳተ ከሆነ ለእርማትም ስለሚያስቸግር በዚያ መንገድ ማየት ጥሩ ነው

ፕሮጀክቶችን በሚመለከት ፤ የፕሮጀክቶች ሚስጥር ክትትል ነው፤ ቁጭ ብሎ አዳራሽ ፣ በስብሰባ ፣ በውይይት በሚሰሙ ሪፖርቶች ሥራን ማሳካት አይቻልም። ምክንያቱም የውሸት ሪፖርት ልክ እንደ ሌብነቱ አደገኛ ውጤት ስላለው ክትትል ቁጥጥር ፤ እቅድ እና ክንውን መቀራረባቸውን ማየት ያስፈልጋል። ለዚህ ነው እናንተ ሱፐር ቪዥን ትሄዳላችሁ፣ ሚኒስትሮች ይሄዳሉ፣ አፈጉባኤዎች ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፣ ሲመች ሲመች እኔም እንደምታዩት በየሥራዎች ሙከራ አደርጋለሁ፤ እንደናንተ ባይሆን ሙከራ አደርጋለሁ።

በየደረጃው ቁጥጥር የምናደርገው በታሰበው ልክ ሥራ መሠራቱን ለማረጋገጥ ነው። ያ ነው ሚስጥሩ። ለምሳሌ ኮሪደር ልማት ፤ የኮሪደር ልማት ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ፤ ለመላው የአዲስ አበባ ነዋሪ የጋራ ድላችን ነው። በዓይናችሁ እንዳያችሁት አስደማሚ የሆነ ሥራ ነው። በጣም በርካታ ሰው ሥራ አግኝቷል፤ በጣም በርካታ ሰዎች የኑሮ ዘይቤያቸው ተሻሽሏል፤ ሰዎች የሚናፈሱበት ፤ በየቦታው ግሪን የሚያዩበት የአኗናር ዜቤ የቀየሩበትን ነገር ፈጥሯል።

ሥራን በሚመለከት ስንጀምር ግን አዲስ አበባን ማፍረስ ስንጀምር 38 የከተማ ከንቲባዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ አምጥተን እንዴት እያፈረስን እንደሆነ ፤ እንዴት እንደምናስብ ፤ ተወያይተን አስጎብኝተን ነው የላክናቸው። የሞካከሩ፤ የጀማመሩ አሉ። አሁንም ሥራው እያለቀ ስለሆነ በሶስት ወር በአራት ወር ጊዜ የሠራናቸውን ሥራዎች አምጥተን እናሳያቸዋለን። ይሄ በሁሉም ቦታ ልማድ እየሆነ እንዲቀጥል ይሞከራል።

አዲስ አበባ ላይ ስንሠራ ምንም እንከን አልባ ነበርን ማለት አይቻልም። አንዳንዶች እነሱ ተወዳጅ ሆነው መንግሥት ሆነ ግለቦችን ለማጋጨት ፤ ይህ ቤት እንዲፈርስ መንግሥት አዟል ፣ ይሄ ቤት እንዲፈርስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዘዋል እያሉ ሙከራ እንዳደረጉ ይታወቃል፤ እናውቃለን። ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁን የከንቲባዋም ይሁን የሌሎች አመራሮች ኢንቴንሽን ምን እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤የአዲስ አበባ ሕዝብ ይጠፋዋል ብለን አናስብም። ማንም ሰው እንዲጎዳ፤ እንዲያለቅስ ፍላጎት የለንም።

ባለሀብቶች ለምሳሌ ህንጻዎቻችውን ስሩን አፍርሰናል ፤ አጥራቸውን አፍርሰናል ፤ ብርም አውጥተውበታል ፤ሃያ ሰላሳ አርባ ሚሊዮን ብር እውጥተውበታል ፤ ይህ ነገር ዝም ብሎ እሰየው ብለው የሚቀበሉት ጉዳይ አይደለም። በነሱ ፕላን ውስጥ የለም በድምሩ ግን አሁን ሲታይ የከተማዋን ፌስ /ገጽታ ምን ያህል ነው ከፍ ያደረግነው። ይህቺ ከተማ በዚህ መልኩ ለአራት ፣ አምስት ፣ ስድስት ዓመት ከሠራን ምን ልትሆን እንደምትችል አስቡ።

ይሄ ሁሉ ጫካ ከዚህ ቀደም ነበረ እንዴ ? መቼስ ታያላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ይህን ሥራ አጠናክረን እንቀጥ። ሰው እንዳይጎዳ ፣ ግለሰቦች እንዳይጎዱ ጥንቃቄ እና ትምህርት እንውሰድ። የግለሰቦችን ሕይወት በሚቀይር አግባብ እንሥራ። ሥራው ግን ያስፈልጋል። በዚህ ሂደት ድንበር አልፈን የጎዳናቸው ባለሀብቶች እና ግለሰቦች ካላችሁ በተደጋጋሚ እንዳልኩት አሁንም ይቅርታችሁ አይለየን። እኛ የምንሠራው ለጋራ ጥቅም እና ለጋራ ግብ ነው። ከማንም ሰው ጋር ጉዳይ የለንም።

በሂደቱ መከላከያ ነኝ፣ ኢንሳ ነኝ ፣ ፓርላማ ነኝ አይሠራም። ማንም ስው በዚህ ውስጥ ታቅፏል። የተውነው ሰው የለም ። በጋራ የመጣ ጉዳይ ለጋራ ጥቅሞቻችን እንደሆነ ታሳቢ ቢደረግ ጠቃሚ ይመስለኛል። የተሠራው ሥራ ጥሩ ጅምር ነው፣ የተከበረው ምክር ቤት እንደዚህ አይነት ሥራዎች ከሚዛናቸው በላይ ማድነቅ አይኖርብንም። ገና ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል ፤ ብዙ ።

በየከተሞቻችን ማየታችሁ፣ መደገፋችሁ ጥሩ ነው። ግን መግፋት ነው ያለብን ፤ ቀጥሉ ገና ነው እያልን እንጂ ሰዎች ሠርቻለሁ ብለው የትናንትና ሥራቸውን እየነገሩን እንዲኖሩ ከፈቀድን ይበላሻል። አዲስ ህልም ፣ አዲስ ጥረት ፣ አዲስ ሥራዎች ማየት እንፈልጋለን። እና በጅማሮ ደረጃ መልካም ተብሎ ቢወሰድ ጥሩ ነው።

በማጠቃለያ ያለኝ ሃሳብ ፤ የተከበረው ምክር ቤት ቢገነዘብ ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢገነዘብ፣ የኢትዮጵያ ምሁራን ቢገነዘቡ ፣ የሚቃወሙ ሰዎች ቢገነዘቡ፣ በዲያስፖራ ያለው ኢትዮጵያዊ ቢገነዘብ ፣ ቢያስተውል ፣ ቢሰክን ብዩ የማስባቸውን ጥቂት ጉዳዮች አነሳለሁ።

በብዙ ሀገራት፤ ዲፕሎማሲን እዛ ውስጥ ዘንግቻለሁ መሰለኝ ወይም ዲፕሎማሲን ላስቀድም። ዲፕሎማሲ በጥያቄ እንደተነሳው ፤ እኛ ጎረቤት ተኮር ፤ ለጋራ ልማት እና እድገት ነው የምንፈልገው። ጥቂት ሀገራት ስም ስለተጠሩ እነሱን እየጠራሁ ላንሳ።

ለምሳሌ ሱዳን ፤ የሱዳን ሕዝብ በተደጋጋሚ እንዳልኩት ፍቅር የሆነ ሕዝብ ነው። በጣም አዛኝ፣ ደግ ሕዝብ ነው። ግጭት የማይወድ ፣ ሰላም ወዳድ፣ ጎረቤት የሚወድ፣ የጎረቤት ሀቅ የሚያውቅ ፤ብዙ ኢትዮጵውያንን ያቀፈ ፤ በጣም ደግ ሕዝብ ነው።

ግን ሁሉም ሰው እኩል ስላልሆነ ሌሎች ቦታዎች ያሉ ውጊያዎች ሲናፈሱ የሱዳን ጉዳይ ተዘንግቷል። በዚህ ጊዜ እኛ ኢትየጵያውያን እንደ ራሳችን ጉዳይ ጉዳዩን ገባ ብለን ለዚኛው ወገን ለዚኛውም ወገን ፣ በመደገፍ ሳይሆን ፍትሀዊ በሆነ መንገድ እና ሱዳንን አንድ በሚያደርግ መንገድ ሚናችንን ሪስክ ወስደንም ቢሆን ማድረግ አለብን።

ለምን አብዛኛው ግጭት ያለው በሚታረሱና በሚለሙ አካባቢዎች ነው። እርሻ አንድ አመት ሁለት አመት ሳይሰራ ጦም ካደረ መልሶ ወደ እርሻ መመለስ አስቸጋሪ ነገር ነው። በጣም ሀብታም ሀገር ፣ምስራቅ አፍሪካን መመገብ የሚችል ሀገር፣ በተፈጠረው ጉዳይ ችግር ውስጥ እንዳይገባ ማክሲመም ጥረት ኢትዮጵያ ማድረግ አለባት።

በኛ በኩል ሁለት ነገር ላንሳላችሁ ፣ ጎረቤት ተኮር መሆናችንን ለመገንዘብ። አንደኛ በኛ እና በቲፒእልፍ /ህወሃት/ መካከል ግጭት ሲጀመር የሱዳን መንግሥት ካለአግባብ የምንጨቃጨቅበትን ቦታ ይዞ ነበር፤ ወታደሮቻችን ወደ ውጊያ ሲሄዱ። እኛ መልሰን ያንን ቦታ መውሰድ የሰአታት ሥራ ሊሆን ይችላል ፤ያንን አላደረግንም። በውጊያ በችግር ጊዜያአቸው አናደርግም ፤ ወንድሞቻችን ናቸው። መጀመሪያ ችግራቸው ይፈታ ብለን በትዕግስት እየጠበቅን ነው። ይሄ ለጎረቤቶቻችን ያለንን እይታ ያሳያል።

ሁለተኛ በሰላሙ ጊዜ ለሱዳን ኤሌክትሪክ ኤክስፖርት እናደርጋለን ፤ታውቃላችሁ። የሱዳን መንግሥት ላለፉት ሁለት ዓመታት ሊከፍል አልቻለም፤ ባለው ብጥብጥ ፤ እኛ እስከዛሬ አገልግሎቱን አላቋረጥንም። በችግር ጊዜ አናቋርጥባቸውም። ወንድሞቻችን ናቸው መጠቀም አለባቸው ፤ በሰላሙ ጊዜ እንጠይቃቸዋለን።

ጉርብትና በመልካም ጊዜ ብቻ አይደለም። በችግራችን ጊዜ ሁሉ የረዳን ወንድማችን የሱዳን ሕዝብ ሲቸገር ባለን አቅም መደገፍ እንጂ እንቅፋት መሆን የለብንም። ከሁለቱ ተፋላሚ ሃይሎች መቶ ፐርሰንት ገለልተኛ አቋም ይዘን ሁለቱም ወደ ሰላም እንዲመጡ ስንሠራ ቆይተናል ፤ አሁንም የምንሠራው በዛው መንገድ ነው። ጎረቤት ተኮር መሆናችን በዚሁ መንገድ መገንዘብ ያስፈልጋል።

ሶማሊያን በሚመለከት የሶማሌ ሕዝብ ፤ የሶማሌ ጎሳዎች በአብዛኛው በኛ ውስጥ ስላሉ ጎረቤት ብቻ ሳይሆን ወንድሞቻችን ናቸው። ለሶማሊያ ሰላም ሞተናል፤ ለሶማሊያ አንድነት ሞተናል። ለሶማሊያ ያለንን ክብር ፤ ብልጽግና ከማንም መንግሥታት በላይ አሳይተናል።

ሶማሌን እንደ ኢትዮጵያዊ ቆጥረን ኢን ፓወር ያደረግን እኛ ነን። በሶማሌ አንድነት የኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ የለውም። በኛ እና በሶማሌ ላንድ መካከል የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ለሁሉም ጎረቤቶቻችን ያቀረብነው ጥያቄ ፤ ሁሉን ለምነን ጠይቀን ምላሽ ስናጣ ከመለሰልን አካል ጋር ተፈራረምን እንጂ ከሶማሊያ አንድነት ጋር የተያያዘ ጥያቄ አይደለም።

የሶማሊያ መንግሥት በአንድ ሰአት ፍላይት/በረራ እና በአንድ ሰአት ውይይት ይህን ነገር /ኮንሰርን ካለው/ መልክ ማስያዝ ይችላል። በጣም ቀላል ነገር ነው። ምክንያቱም ከሶማሌ መንግሥት ጋር ምንም ጸብ የለንም። የሶማሌ መንግሥት የመረጠው ግን እኛን ከማናገር በየሠፈሩ እየዞረ እኛን መክሰስ መርጧል። ያለኝ ምክር ብር አታብክኑ ነው። በየ ሀገሩ ስንሄድ፤ በጣም ብዙ ወጪ ይወጣል ፤ ብር ከምናባክን እሱን ሰብሰብ አድርገን አንድ ኪሎ ሜትር ዎክ ዌይ ብንሠራበት፤ አንድ ትምህርት ቤት መቋዲሾ ብንሠራበት ሕዝብ ይጠቅማል።

እኛን ለመክሰስ ሀገር ለሀገር መሄድ አያስፈልግም። አዲስ አበባ መምጣት ይቻላል። ለመነጋገር ዝግጁ ነን። ሶማሊያ እንድትጎዳ ፤ እንድትፈራርስም ፤ እንድትበተንም የሚፈልግ መንግሥት አይደለም። ቢሆን ልጆቹን ልኮ አይሞቱም። የኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ የባህር በር ጥያቄ ነው። ይሄ ልጅትሜት /ሕጋዊ ጥያቁ ነው። ይሄን በሰላማዊ እና በንግግር መልኩ እንደማንኛውም ኮሚዲቲ / ሸቀጥ ለመቀበል ኢትዮጵያ ዝግጁ ነች።

ለምሳሌ ወይ ሶማሌ ፤ ወይ ጅቡቲ ወይም ሌሎቹ ፤ የቀይ ባህር አክሰስ /የባህር በር አላቸው / አላቸው ፤ ግን እንደ ኢትዮጵያ ሊያመርቱ አይችሉም። እኛ የተሻለ መሬት አለን ፤ የተሻለ ውሃ አለን፤ ኢነርጂ ምግብም ፤ ከኛ አቦካዶ ከነሱ ውሃውን ብንጋራ ምንም ችግር የለውም። ንግድ ነው።

ተጠቅመው ተጠቅመን አድገው አድገን ፤ ተባብረን አብረን ብንሄድ ለሪጅኑ/ለአካባቢው ለልጆቻችንም ጠቃሚ ነው። እናንተ እንዲህ አይነት ጥያቄ አታንሱ ቢባል ግን ፤ ጥያቄ አታንሱ ብለህ የምታፍነው ጉዳይ አይደለም፤ እውነት እስከሆነ ድረስ ጊዜውን ጠብቆ ይወጣል።

አሁንም ለኤርትራ፣ ለጅቡቲ ፣ለኬንያ ፣ ለሱዳን ፣ ለሶማሊያ ዛሬ ያለን መልእክት፤ እነሱ መንድሞቻችን ናቸው ክፉዎቻቸውን እኛ አንፈልግም። በሰላም መኖር እንፈልጋለን፤ ይሄ ትልቅ አገር ነው ፤ ትልቅ አርሚ/ሠራዊት ያለው ሀገር ነው ፤ ትልቅ ሕዝብ ነው። ለነሱ ታላቅ ወንድም እና ጋሻ ነው። ለችግራቸው ጊዜ የሚደርስ ነው።

የጥፋት ሃይል አይደለም። ግን ጥያቄ አለብን። ይህንን ያህል ኢኮኖሚ ይዞ መዘጋት አስቸጋሪ ነው። ይሄ ብሄራዊ ጥቅም /ናሽናል ኢንተረስት ነው። ይሄን ብሄራዊ ጥቅም እንዴት አድርገን እናስታርቅ። ሰው ሳይሞት ፣ ሳንሰዳደብ ፤ በየሀገሩ ዞረን ብር ሳናባክን ዊን ዊን አፕሮች እንከተል ከተባለ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሌም ዝግጁ ነው። ለጋራ ጥቅም በጋራ መሥራት።

ኢትዮጵያ ጥቅም ሲሆን ነውር የሌላው ጥቅም ሲሆን ትክክል ሊሆን ግን አይችልም። ለኛ ጎረቤቶች ሰላም እና ብልጽግና እንመኛለን ፤ ከጎረቤቶች ጋር በጋራ ለማደግ እንመኛለን ፤ የነሱን ውጊያና ችግር አንፈልግም ፤ እነሱም በዚህ መልኩ/ ኢኳሊ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል። በዛ አግባብ ነው የምንሄደው።።

እንደተባለው ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት። ኢትዮጵያን ወደ ጎን ብሎ ምንም አይነት አፍሪካ ላይ እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም፤ ቢፈለግም። ያለው ምርጫ በትብብር መንፈስ መሥራት ነው። የምንሰጠው አለ፣ የምንፈልገው አለ ፣ ተቀባብለን በጋራ ለማደግ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፤ የኛ አካሄድ አሱ ነው።

ቅድም የጀመርኩት ሃሳብ በዓለም ላይ ትላልቅ ተቋማት የትሬንድ አናሊስስ ሠርተዋል። የሠሩት የትሬንድ አናሊስስ ፖለቲካ ፣ ሶሾኢኮኖሚ ፣ ቴክኖሎጂካል ትሬንዶችን አይተዋል። በዛሬ እና በሰላሳ ዓመታት መካከል ዓለም ላይ ያለው ጉዞ ምን ሊመስል እንደሚችል የሚያመላክቱ ትሬንድ አናሊሲሶች ተሠርተዋል።

በ2050 የዓለም ሕዝብ ብዛት ወደ 10 ቢሊዮን ይጠጋል ተብሎ ይገመታል። ይህ የዓለም አቅም መሸከም የሚችለው የመጨረሻ ጫፍ ነው። ይህን መሸከም የሚችለው በርካታ ሥራዎች በተገቢው መንገድ ከተሠሩ ብቻ ነው። አለበለዚያ ኢምዲየት ፈተና ተብሎ እየመጣ ያለው ምግብ ነው። የሕዝብ ቁጥር (ፖፕሌሽን) በጣም እያደገ ሲሄድ ምግብ ችግር ይሆናል። መሬት የመስጠት አቅሟ እየቀነሰ ይሄዳል። ጤና ችግር ይሆናል። በተለይ ወረርሽኝ (ፓንዳሚክ) ይሰፋና ሰዎችን ጅምላ ጨራሽ በሽታዎች ይሰፋሉ። የሃይል ፍላጎት (ኢነርጂ ዲማንድ) በጣም ያድጋል። ሁሉም ነገር ሃይል (ኢነርጂ) እየፈለገ ስለሆነ፤ እነዚህን ጉዳዮች ካልፈታን ልጆቻችን በሰላማዊ መንገድ ሊኖሩ የሚችሉበት አውድ አሁን ባሉ ግዛቶች፤ አሁን ባሉ መልክዓምድር (ጂኦግራፊ) ላይቀጥል ይችላል። ብዙ ሀገራት ሊፈራርሱ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች አሉ።

ከእነዚህ ውስጥ አንኳር አንኳር ብቻ ለማንሳት አንደኛው አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ነው። አርተፊሻል ኢንተለጀንስ እኛ እያላገጥን እያሾፍን ልንወጣው የማንችለው አደጋ ሆኖ እየመጣ ነው። አርተፊሻል ኢንተለጀንስ በሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ በመታገዝ አሁን አስፓየር እየተደረገ ያለው አንድ ሰው ጤነኛ ሆኖ ከአንገቱ በታች ቢሞት፣ አንድ ከአንገቱ በታች የጤና ችግር ያለበት ሰው ለጥቂት ደቂቃ ሰርጀሪ አንገቱ ተቆርጦ በሞተ ሰው አንገት ላይ ተገጥሞ ሰው ሆኖ ይቀጥላል የሚሉ አይነት ለማመን የሚያስቸግሩ ጉዳዮች እየታሰቡ ነው ያሉት። እግር የሌለው ሰው እግር ያለው ሰው ሲሞት አንገቱ ተቆርጦ ተቀይሮለት ማለት ነው። ሰው ሲቆረጥ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት። ይሆናል አይሆንም ሲደርስ እናየዋለን። በጣም ብዙ ነገሮች የሚነካ ነገር እየሆነ ነው። እንደባለፈው ችላ የምንለው ሳይሆን፤ ችላ ካልነው ልጆቻችን ዋጋ የሚከፍሉበት ጉዳይ እየሆነ ነው።

ሁለተኛው ኮኔክቲቪቲ ነው፤ ሁሉ ነገር ኮኔክት እያደረገ ነው። አሁን እና ፓስፖርት እንላለን፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አያስፈልግም። መታወቂያ እንላለን፤ አያስፈልግም። የትም ሀገር ለመሄድ ሰው ቤት ተቀምጦ ቪዛውን ቤት አግኝቶ የፈለገበት ሀገር ሲሄድ የአይኑን ዐሻራ ብቻ አይቶ ዐቢይ ይለዋል ሲስተሙ። ምንም ፓስፖርት አያስፈልገግም፤ እያንዳንዱን ሰው መለየት የሚያስችል ኮኔክቲቪቴ እየተፈጠረ ነው።

ታስታውሳላችሁ የዛሬ አስራ አምስት፣ ሃያ፣ ሰላሳ አምስት ዓመት ከዚህ አጋሮ መቶ ብር ለመላክ እኔ ብፈልግ

መጀመሪያ ባንክ ቤት እሔዳለሁ። መታወቂያ አሳያለሁ። የባንክ ደብተር አሳያለሁ። ከዚያ በኋላ መቶ ብር ይተላለፍ እላለሁ። ርሲት እወስዳለሁ። ቤት ከገባሁ በኋላ ኦፕሬተር ጋ እደውላለሁ፤ ስልክ የለም። ስምንት ሰዓት ስለምደውል አገናኘኝ እላለሁ። ስምንት ሰዓት ደውዬ በባንክ ብር ልኬያለለሁ እላለሁ። በማግስቱ ሰውዬው ባንክ ቤት ይሄዳል። መታወቂያ ያሳያል። አይ! አሁን ፋክሱ ስላልመጣ ከሰዓት ና ይባላል።

ዛሬስ?! ለልጆቼ ይህን ታሪክ ባወራቸው ‘ትቀልዳለህ እንዴ?! በሞባይል ለምን አታስተላልፍም? ምን አደከመህ?’ ይላሉ፤ አይገባቸውም። ብዙ ነገር ኮኔክቲቪቲ እያደገ ነው። ይህ በአንድ በኩል ሥራ ያቀላል። ሕይወትን ቀለል ያደርጋል። ቢዝነስ ያቀላል። በሌላ በኩል ግን ሁሉ ነገራችን ሲስተም ውስጥ ከገባ አንድ ቀን ፓወር ቢጠፋ ፤ አንድ ቀን የሆነ ሰው ቢቆርጥብን ምንድን ነው የምንሆነው? በር የሚከፈተው በአይን ዐሻራ፣ መኪና የሚከፈተው በድምጽ በአይን ዐሻራ፣ መኪና የሚነሳው ሰውዬውን አውቆት በአይን ዐሻራ፤ መኪና ዝግት፣ ቤት ዝግት፣ ሕይወት ዝግት ቢል ምን እንሆናለን? ኮኔክቲቪቲ ከምናስበው ፍጥነት በላይ እየፈጠነ እየመጣ ነው። ይህን የማያስብ ኤሊት ፤ይህን የማያስብ ምሁር ይህን የማያስብ ፖለቲከኛ ዝም ብሎ እንትና ወረዳ እንትና ወረዳ እያለ ሲባላ ቢኖር ልጆቻችን አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ። መጨነቅ የሚገባን ብዙ ጉዳዮች አሉ፤ ለአልባሌ ጉዳይ ጊዜ ከምናባክን።

ሶስተኛው ባዮኢንጂነሪንግ ነው። ባዮኢንጂነሪንግ ከዚህ ቀደም ስናወራውም፤ ስንሰማውም እንደወዋዛ ነበር የማናስበው። አሁን ዲኤንኤ ማኑፑሌሽን እየተጀመረ ነው፤ የሰውን የዲኤንኤ ሲኩየንስ ማኑፑሌት ማድረግ የሚያስችሉ ኮራፕት ማድረግ የሚያስችሉ አቅሞች እየተፈጠሩ ነው። ከዚያ በላይ የሚያስፈራው ክሎኒንግ የተባለው ቴክኖሎጂ ነው። ለምሳሌ የተከበሩ አፈጉባኤን 10 አፈ ጉባኤ አድርጎ መፍጠር ይቻላል ። አንደኛው አፈጉባኤ አሜሪካ፤ አንደኛው ራሻ አንደኛው አርባምንጭ። የትኛው ነው ትክክለኛ እንደሆነ መለየት አይቻልም። ዓለም እየሄደበት ያለው ርቀትና እኛን ቢዚ እያደረገ ያለው ነገር የተለያየ ነው። እኛ አርሰን ለማንጨርሰው መሬት ነው የምንጨቃጨቀው። ዓለም እየሄደ ያለው ማርስ ላይ እንዴት ማልማት እችላለሁ ነው። ስፔስ ቴክኖሎጂ በራሻ ዩክሬን ጦርነት አይታችሁ እንደሆነ የዩክሬን ኔትወርክ እንዳለ ዳውን ሲሆን በሳተላይት ኮሙኒኬሽን ነው በአንድ ጊዜ እንዲቀጥል የተደረገው። እንደከዚህ ቀደሙ ስፔስ ሌግዠሪ አይደለም። ስፔስ ቴክኖሎጂ ለአንድ ሀገር ኤግዚስታንስ በጣም አስፈላጊ ነው።

ምንድን ነው እንደ መንግሥት ምንድን ነው እደረግን ያለነው? ፤ምሁራኖቻችን ምን እያሰቡ ነው?ወጣቱ ምን እያሰበ ነው ?ዲያስፖራው ምን እያሰበ ነው? ብለን መጠየቅ አለብን ። ዝም ብለን ብንሻኮት ልጆቻችን ጣጣ ውስጥ ይወድቃሉ። ከአሁኑ መሠረት መጣል አለብን። ሮቦቲክስ እና ሀገር የሆኑ ወጣቶች ሶፍያ በምትባለው ሮቦት ጥሩ ሙከራ አድርገዋል። ብዙ ሙከራ ማድረግ የሚችሉ ሰዎች እንዳሉ አይተናል። በቂ ድጋፍ ስለማይደረግ ግን ዕውቀታቸውን ይሸጣሉ። ሮቦቲክስ ዛሬ ቀላል ነው፤ ነገር ግን ነገ ከባድ ነው። እናት ሀገር ኢትዮጵያ ሮቦቴክስ ካላደገ የለችም። ውጊያ በሰው አይደለም። አንድ ሀገር ሮቦቶቹን ልኮ እኛ ውጊያውን የምናደርገው ከማሽን ጋር ነው። ስለዚህም እየተዋጋን ሊጨርሰን ይችላል። የሚዋጉ ሮቦቶች እየተፈጠሩ ነው። ምንም ከሌለን ፤ ሮቦቶችን እንዴት መጠቀም እንዳለብን እውቀቱ ከሌለን ልጆቻን ችግር ውስጥ ይገባሉ።

ነገር እየተገለባበጠ ነው ያለው። እኛ በተኛንበት መንገድ አይደለም እየሄደ ያለው፡ ፡ስማርት ማኑፋክቸሪንግ፤ ኢንዱስትሪ ፤ ይደክመናል እኛ። ስማርት ማኑፋክቸሪንግ በአንድ ሰዓት አንድ ሚሊዮን ኮት የሚያመርት ከሆነ እና በለመድነው መንገድ አንድ ሺህ ብናመርት ገበያ ላይ እኩል ልናመርት አንችልም። አሁን ያለው ማኑፋክቸሪንግ ስማርት ካልሆነ በቀር በርካታ ከሚያመርቱ ተቋማት ጋር ሊወዳደር አይችልም። ኳንተም ኮምፒቲንግ፤ ሳይበር ሴኩሪቲ በጣም ብዙ ነገር ነው እየተቀየረ ያለው። ፍጥነቱ ደግሞ የሚያስፈራ ነው። ብዙ እኮ አይደለም 20 አመት -30 አመት ። ብዙዎቻችሁ የምትኖሩበት ዕድሜ ነው። በሕይወት እያለን የምናየው ነው ማለት ነው።

ሌላው ኦግመንትድ ሪያሊቲ ነው። ብዙ ነገር የሚያዛባ ነው። በፊት እንደቀልድ የሚታ ነበር፤ አሁን በተጨባጭ ወጥቷል። ለምሳሌ አንድ ዶክተር የአንድን ሰው ልብ ሰርጄሪ ለመሥራት ቢፈልግ በኦግመንትድ ሪያሊቲ ቀጥታ ቀዶ ጥገና አያካሂድም፤ የሰውየውን ልብ ሲሙሌሽን ሠርቶ ከተለማመደ በኋላ ነው ወደ ትክክለኛወ ቀዶ ጥገና የሚመለሰው። ከዚህ አንጻር ለሰርጀሪ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው። ከዲዛይን አንጻር ብንመለከተው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዲዛይን በርካታ ችግሮች ያሉበት ነው። በኦግመንትድ ሪያሊቲ ግን ቤቱን እንዳለ ነው የሚያሳይህ። ቀለሙን ስፋቱን ተመልክተን ይሄንን ሥራልን ነው የምንለው። እንዳሁኑ ስኬች ሳይሆን ቪዢዋል አቅም ያለው ማለት ነው። ይህ ዕውቀት ለማርኬቲንግ፤ ለቱሪዝም ፋይዳው ብዙ ነው ። እኛ ግን የት ነው ያለነው ። አሁንም ወረዳ እና ክልል እንሁን እያልን መቀጠል እንችላለን ወይ ?

የተከበረው ምክር ቤት ይህንን ጉዳይ በአግባቡ ማየት ካልቻለ እነድ ችግር አለ። ችገሩ ምንድን ነው ቴክኖሎጂዎቹ በ10 እና በ15 አመት የሰውን እሴት ፤ የሰውን አመለካከት ይቀይሩታል። አሁን እኛ የምናደርገው ነገር ሁሉ ዋጋ ቢስ ነው የሚሆኑት። ዛሬ ፓስፖርት ዋጋ አለው የዚያን ጊዜ ዋጋ የለውም። አሁን ሞባይል መኒ ተአምር ነው የዛን ጊዜ ደግሞ በሌላ ይተካል። የገንዘብ ትራንዛክሽን በተለየ መልኩ ተግባር ላይ ይውላል። አሁን እንኳን እየተሞከረ ያለው አንዳንድ ዘመናዊ ሞሎች ውስጥ ገና ከበር ሲገባ የእያንዳንዱ ሰው የአይን ዐሻራ ስለሚለያይ አይንን ወስዶ ሰዎችን ይለያል። የአንድ ሰው የፈለገውን እቃ ቢያነሳ ወዲያው ከአካውንቱ ይቀንስበታል። ንግግር የለም። አንድ ሰው ቤት ተቀምጦ መርካቶ ሳይሄድ ሽንኩርት ያዛል፤ ሽንኩርቱ ተጭኖ በሩ ላይ ይራገፍለታል፤ ገንዘቡ ከአካውንቱ ይቀነስለታል። እነዚህ ጉዳዮች አሁን እኛ የምንሰቃይባቸውን ጉዳዮች ዜሮ ስለሚያደርጉት የሰው ልጅ እሳቤም ሆነ አመለካከት ይቀየራል።

ለልጆቹ የማያስብ አባት፤ ለነገ የማያስብ ሰው መሆን የለብንም። ይሄንን ነገር አስበን ተጨንቀን ገንዘብ አስቀምጠን እንድንሰራ ካስፈለገ አንደኛ የሀገር አንድነት ፤ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር እደ ሀገር የመጽናት የመቀጠሏ ጉዳይ የሁላችን የጋራ አቋም መሆን አለበት። ለንግግር እንኳን ኮምፕሮማይዝ የምናደርገው ነገር መሆን የለበትም። ከጎረቤት ሀገራት ያለውን ግንኙነት አሁን ካለው ድንቁርና እና ጭቅጭቅ ወጥተን ሪግኑን በጋራ የምናድግበት እንዲሆን ከፍ ወዳለ አጀንዳ ማደግ አለበት። ከጥርጣሬና ከሽኩቻ እንዲሁም ከክስ ወጥተን ስለአንድነት ማሰብ አለብን። ልጆቻችን ከታች ብዙ ነገር አውቀው እንዲመጡ ማድረግ አለብን።

የሳይንስ ሙዚየም ሰርተን ሁለት አመት ሙሉ ክፍት ያደረግነው በክፍያ ቢሆን ሰዎች በገንዘብ ምክንያት መግባት እንዳይቸገሩ ነው። ላይብረሪ መገንባት አለብን፤ ሳይንስ ሙዚም መገንባት አለብን መማርያ ኪቶች ማስፋት አለብን ። ልጆቻችን እንደ ሀብታሞቹ በተሟላ ባይወዳደሩ እንደእኛ የሚደናበሩ መሆን የለባቸውም። መሠረታዊ ዕውቀት ያስፈልጋቸዋል። በነገራችን ላይ አንዳንድ ሀገራት በአርቴፊሻል ኢንቴለጀንስ መሠረታዊ ዕውቀቶች ያልተፈተነ ሰው ሚኒስትር አይሆንም፤ ጄኔራል አይሆንም ፤ ለፓርላማ አባል ዕጩ ሲወዳደር ፈተና ይገጥመዋል። መሠረታዊ ዕውቀት ካልጨበጠና ትናንሽ ኮርስ ካልወሰደ ፈተና ይገጥመዋል። ለምን እሳቤው ወደ እዛ ማደግ ስላለበት ነው።

እናንተ ከሺህ አመታት ዘለቀ ሀገር የተረከባችሁ የፓርላማ ሰዎች ይሄንን ነገር ማሰብ ዋነኛ ሥራችሁ መሆን አለበት። ቴክኖሎጂ በጂዲፒአችን ያለውን ሼር እያሳደግን መሄድ አለብን። ይሄ ከሆነ የጸናች ኢትዮጵያን ማቆየት እንችላለን። ለምሳሌ አሁን ያለው ኢነርጂ አይበቃም ኒውክለር ፊውዝን መጀመር አለበት ብለው አለማት እየተንቀሳቀሱ ነው። ያ በጣም የራቀ ነው። እኛ ግን ዳገት አለን፤ ውሃ አለን ፤ነፋስ አለን ጸሃይ አለን። እንዴት ኢነርጂ ላይ ኢንቨስት አድርገን ማበራከት አለብን። ምግብ ፤ ልብስ ፤ኢነርጂ ፤ቴክኖሎጂ መድሃኒት በጣም ክሪቲካልስ ኤሪያስ ናቸው። ዛሬ ከምናገኘው ጉርሻ ይልቅ በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ላይ ኢንቨስት አድርገን ልጆቻችን ነገ እንዳይጨነቁ የምናስብ ወላጆች መሆን አለብን። እንደመንግሥት እንዲዚህ ካላሰብን መጪው ዘመን በጣም፤ በጣም አስጊ ነው።

እኛ የምንባላበት ጊዜ የምናባክነበው አልባሌ ነገር ደግሞ ፓርላማ ተሰብስቦ ፤ ምሁራኑ ከጭቅጭቅ ወጥተው ይሄንን ቢያስቡ ችግር አልነበረውም። ኢትዮጵያ ውስጥ ምሁሩም፤ ወጣቱም ቄሱም፤ ሼኪውም፤ ሁሉም ያለው መንደር ውስጥ ነው። ይሄ ነገር ልጆቻችንን ይጎዳል። ልብ ልን ይገባል፤አርቀን ልናስብ ይገባል፤ ነገን ልናይ ይገባል፤ በጀመርነው የአረንጓዴ ዐሻራ የምንተክለው ችግኝ ለልጆቻችን እንደሆነው ሁሉ ቴክኖሎጂም ላይ ተመሳሳይ እሳቤ ካልጨበጥን በስተቀር ልጆቻችን ለማኝ መሆናቸው አይቀርም። የሚለምን ልጅ ከምንወልድ አለመውለድ ይመረጣል። ከወለድን ደግሞ በኃላፊነት ማሳደግ ይጠበቅብናል።

በአጠቃላይ ይሄንን ነገር በስድስት ‹‹መ›› ማስቀመጥ ይቻላል። አንደኛው መምከር፤ መመክካር ፤መወያየት፤ ያስፈልጋል። ኦሮሞ ነው እንደዚህ የሚያደርገው፤ አማራ ነው፤ ፤ትግራይ ነው እንደዚህ የሚያደርገው ለሚለው ጉዳይ መወያየት ያስፈልጋል። ውይይት አብዛኛውን ነገር ይፈታዋል። ውይይት አለመሸሽ፤ ምክክርን ጸጋና ባህል ማድረግ ያስፈልጋል።

ሁለተኛው ደግሞ መትከል ነው። ችግኝ መትከል፤ ተቋማት በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ መትከል፤ተሻጋሪ ሕጎች መትከል፤ ያስፈልጋል። መተከል የሚገባቸውን እመከርን መትከል ይገባናል።

ሶስተኛው መታደስ የስፈልጋል። ጭንቅላታችን፤ እሳቤያችን ፤ከተማችን አኗኗራችን ፤ገንዘብ የምናወጣባቸው መንገዶች መታደስ አለባቸው። ኢትዮጵያውያን ለሳሎን የማንጠቀምባቸውን ሶፋ እየደረደርን ሽንት ቤት የማንሠራ ከሆነ መታደስ አለብን። ሶፋ አይደለም የሚያስፈልገው፤ ንጹህ ሽንት ቤት ያስፈልጋል ጤና ስለሆነ። ቲቪና ብፌ ከምንደረድር ደንበኛ አልጋ ያስፈልጋል። ይሄ መታደስ አለበት፤ መነጋገር አለብን፤ መታደስ አለብን። ከተሞቻችንን አሁን ያለው የኑሮ ዘዬ መታደስ አለባቸው። ያ ካልሆነ ፋውንዴሽን ካልተውን እንቸገራለን።

አራተኛው መሰብሰብ አለበት። ምን ግብር፣ ምን ምሁር፣ እውቀቱ፣ ሀብቱ፣ እሳቤው፣ ጉልበቱ ሰብሰብ ብሎ ኢትዮጵያን በሚያጸና፤ በሚያሻግር ቁምነገሮች ላይ መተከል አለበት። ያልተሰበሰበ ግብር፤ ያልተሰበሰበ ሀብት ከንቱ ነው። ለምሳሌ አንድ ኮምፒውተር ብቻውን ያለው አቅም ውስን ነው። እዚህ ያለን አንድ ሺህ ሰዎች እያንዳንዳችን አንዳንድ ኮምፒውተር ብንይዝ በጣም ውስን ነገር ነው አክሰስ የምናደርገው፤ ውስን ነገር ነው በፈጣን ስፒድ ፌስ ማድረግ የምንችለው። የእኛ ኮምፒውተር ቢደመር ግን እርሱ ጋር ያለው ፎቶ፤ እርሷ ጋር ያለው ማፕ እርሱ ጋር ያለው ቴክስት ሁሉን መቀያየር እንችላለን። ሲደመር ወደ ክላውድ ሲመጣ ብዙ የሚጠቅም ነገር አለው። እውቀትም እንዲያ ነው፤ ገንዘብም እንደዚያ ነው መሰብሰብ አለበት።

አምስተኛው መነጠል አለብን። ክፉ ሃሳብ፣ ጦረኝነት፣ ሰፈርተኝነት፣ ዘረኝነት፣ እኔ ብቻ የሚሉ እሳቤዎች መነጠል አለባቸው። ሕዝቡ እነዚህን እሳቤዎች ይብቃን ብሎ መነጠል አለበት። ስለሚያጠፉ።

ስድስተኛው መዘጋጀት አለብን። ጠንካራ ዲፌንስ ያስፈልገናል። በግልጽ ነው እያወራሁ ያለሁት። ዓለም የራሱን ዲፌንስ ለማሻሻል ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ነው ። መፍረስ ልምምድ እየሆነ ነው። መፍረስ አንፈልግም። እንደ ሀገር ድሃም ብንሆን መቀጠል እንፈልጋለን። ዲፌንሳችን ሳይበር ሴኪዩሪቲ ላይ ስፔስ ላይ የሚወራጭ መሆን አለበት። ዝም ብሎ በክላሽ ብቻ አይሆንም። መዘጋጀት አለብን ። በሳይኮሎጂ መዘጋጀት አለብን። በትምህርት ሥርዓታችን መዘጋጀት አለብን። በአካባቢያችን ያንን ማድረግ ካልቻልን ትናንት አለ የምትሉት ችግርና መከራ በብዙ እጥፍ ነገም ይጨምራል። ነገን ለመሻገር የተሻለች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማስረከብ ቢያንስ የጸናች ሀገር ጸንታ እንድትቀጥል ለማድረግ ኢትዮጵያውያን ከቻልን ማገር እንጂ መጋዝ መሆን የለብንም። ኢትዮጵያን ለማጽናት ማገር ነው መሆን ያለብን። መጋዝ እየሆንን እርስ በእርስ ብንበላላ ልጆቻችንን ሀገር አልባ እናደርጋለን።

የተከበረው ምክርቤት፤ የኢትዮጵያ ምሁራን ያገባኛል ይህንን ጉዳይ አውቃለሁ የሚል ሰው ሁሉ በዚህ ጉዳይ ደጋግሞ እንዲያስብና ለልጆቹ መልካም ዘርን ዘርቶ በተሻለ ፍሬ እንዲኖሩ ለማስቻል ቢያንስ የውስጥ ዝግጅት ፤ ጥረትና ሙከራዎች በውስጣችን መኖር እንዳለባቸው ይሰማኛል። ይህንን ብናደርግ የሁላችን ቁጭት የሁላችን ፍላጎት የሆነችው ኢትዮጵያ ትሻገራለች። ይህንን ለማድረግ ግን ከዚህ ቤት በላይ ባለቤት ሆኖ የሚጨነቅ ፖሊሲ፣ አዋጅ፣ ሕግ የሚያወጣ የሚያስተምር ሲሄድ የሚቆጣጠር ሌላ አካል የለም።

ዋናው የዚህ መንግሥት የመጨረሻው የሕዝብ ድምጽ እናንተ ናችሁ። እናንተ ይህንን ጉዳይ ይዛችሁ እኛንም ጋይድ እያደረጋችሁ ፤ ሕዝቡንም እያስተማራችሁ ብትሄዱበት ለልጆቻችን መልካም ሀገር የምንተው ሪስፖንሲብል ዜጎች ስለምንሆን ይህንን ከአደራ ጭምር እያሳሰብኩ ለዘንድሮ ያቀረብነው በጀት ተጨማሪ ሀብት አግኝተን እስክናሻሽለው ድረስ የተከበረው ምክርቤት ካጸደቀልን በጀመርነው መንገድ ቀንና ማታ በመሥራት የገባነውን ቃል በተግባር ለመፈጸም አስፈላጊውን ጥረት እንደምናደርግ በድጋሚ ቃል ልገባላችሁ እፈልጋለሁ። እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።

 

 

አዲስ ዘመን ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You