የጋዛው ጦርነት የሚቆም ከሆነ ሄዝቦላ በእሥራኤል ላይ ጥቃት መሰንዘሩን እንደሚያቆም አስታወቀ

የጋዛው ጦርነት የሚቆም ከሆነ ሄዝቦላ በእሥራኤል ላይ ጥቃት መሰንዘሩን እንደሚያቆም አስታወቀ፡፡

የቡድኑ ምክትል መሪ ሼክ ናይም ካሲም “በግጭቱ የተሳተፍነው ለሀማስ እና ለፍልስጤማውያን ያለንን አጋርነት ለማሳየት ነው፤ እሥራኤል ውጊያውን የምታቆም ከሆነ ያለምንም ውይይት እኛም ጥቃት ማድረሳችን እናቆማለን” ብለዋል፡፡

እሥራኤል በጋዛ የምድር ውጊያ ከጀመረች ከባድ ዋጋ ትከፍላለች – ሄዝቦላህ

ከአሶሼትድ ፕሬስ ጋር ለ40 ደቂቃ ያክል ቃለ ምልልስ ያደረጉት የቡድኑ ምክትል መሪ እሥራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ፍትሐዊ ያልሆነ ጦርነት የምትቀጥል ከሆነ በሊባኖስ እና እሥራኤል ድንበር ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አትችልም ሲሉ ዝተዋል፡፡

ባለፈው ወር የእሥራኤል መከላከያ በሊባኖስ ሙሉ ጥቃት ለመሰንዘር የሚያስችል ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ማጠናቀቁን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

ይህን አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት የሄዝቦላ ምክትል መሪ ሼክ ካሲም እስራኤል በሄዝቦላ ላይ ሙሉ ጦርነት የማወጅ አቅም የላትም ብለዋል፡፡

የተገደበ ጦርነት አደርጋለሁ በሚል በሊባኖስ ድንበር ውስጥ ገብታ የምትንቀሳቀስ ከሆነ ደግሞ ጦርነቱን ወደግዛቷ እንደምወስደው ልታውቅ ይገባል ነው ያሉት፡፡

እሥራኤል ሙሉ ጦርነት የምታወጅ ከሆነ በጦርነቱ እነማን ሊሳተፉ እንደሚችሉ መቆጣጠር አትችልም ሲሉ የግጭቱ መጠን ሊሰፋ እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል፡፡

የሄዝቦላ አጋር ናቸው የሚባሉ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚንቀሳቀሰው አክሲስ የተሰኘው ታጣቂ ቡድን እንዲሁም በኢራቅ ፣ በሶሪያ እና የመን ያሉ ተዋጊዎች ኢራንን ጨምሮ በዚህ ጦርነት ሊሳተፉ እንደሚችል ስጋት አለ፡፡

ቴልአቪቭ በጋዛ ጦርነት ካወጀች አንስቶ ላለፉት 9 ወራት ከእሥራኤል ጋር በተካረረ ውጥረት ውስጥ የሚገኘው ሄዝቦላ ለሃማስ ያለውን ድጋፍ ለማሳየት በእሥራኤል ላይ የተለያዩ የሮኬት እና የድሮን ጥቃቶችን ሰንዝሯል፡፡

ሁለቱ አካላት የሚገኙበት ሁኔታ ወደ ለየለት ጦርነት ተቀይሮ ቀጣናዊ ግጭትን እንዳያስከትል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስጋቱን እየገለጸ ይገኛል፡፡

ሆኖም ሁለቱም አካላት እርስ በእርስ የሚሰጧቸው መግለጫዎች እና ወታደራዊ ዝግጅቶች የጦርነቱን አይቀሬነት የሚያሳብቁ ናቸው ያሉ ተንታኞች ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በመተንተን ላይ ናቸው፡፡

በእሥራኤል እና ሄዝቦላ መካከል ዝቅተኛ ነው በሚባለው አሁን ባለው ግጭት በሁለቱም ወገን ድንበር ላይ የሚኖሩ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ሲፈናቀሉ በሊባኖስ በኩል 450 ንጹሐን ሰዎች እና ታጣቂዎች ተገድለዋል በእሥራኤል በኩል ደግሞ 16 ወታደሮች እና 11 ንጹሐን ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ሀማስ በጋዛ ያለው ጦርነት እንዲቆም እና ስምምነት ላይ እንዲደረስ ፍላጎት ያለው ሲሆን ለዚህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በእሥራኤል ላይ ጫና እንዲያሳድር በመጠየቅ ላይ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው የሀማስ ወታደራዊ እና የአስተዳደር አቅም ሳይበታተን የጋዛው ጦርነት አይቆምም በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል፡፡

የሊባኖሱ ሄዝቦላህ እሥራኤል በጋዛ የምድር ውጊያ ከጀመረች ከባድ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል ማለቱ የሚታወስ ነው።

የቡድኑ ምክትል መሪ ሼክ ናይም ካሴም ማስጠንቀቂያ የተሰማው የእሥራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመው ጥቃት ስድስት የሄዝቦላህ ተዋጊዎች በተገደሉበት በትናንትናው እለት ነው።

“የእሥራኤልን ጦር ለማዳከም ጥረት እያደረግን ነው፤ ዝግጅታችን ምን እንደሚመስልም አሳይተናቸዋል” ብለዋል ምክትል መሪው።

በኢራን የሚደገፈውና በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች፣ ሚሳኤሎች እና የተለያዩ ድሮኖች የታጠቀው ሄዝቦላህ በሰሜናዊ እሥራኤል አዲስ የጦር ግንባር እንደከፈተ ይታወቃል።

እሥራኤልም በድንበር ላይ በርካታ ታንኮች እና ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን ተክላለች። የእሣራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ለፍልስጤሙ ቡድን አጋርነቱን ያሳየው ሄዝቦላህ በየቀኑ ወደ እሥራኤል ሮኬቶችን ከመተኮስ አላረፈም።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You