ማኅበሩ በሀገሪቱ የሚስተዋሉ አብዛኞቹ ችግሮች ከአስተሳሰብ መዛነፍ የሚመነጩ መሆናቸውን ገለጸ

አዲስ አበባ:- በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ከአስተሳሰብ መዛነፍ የመነጩ መሆናቸውን የአዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ማህበር ገለጸ።

የአዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ማህበር 1ኛ ዓመት የምስረታና የመጽሔት ምረቃ በዓል ትናንት ተካሂዷል። የአዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በቀለ ጸጋዬ በመድረኩ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በአብዛኛው ከአስተሳሰብ መዛነፍ የመነጩ ናቸው።

ማህበሩ የሀገርን ጉዳይ ከዳር ሆኖ ከማየት የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የተቋቋመ ነው ያሉት አቶ በቀለ፤ በሀገሪቱ የሚስተዋሉ አብዛኞቹ ችግሮች ከአስተሳሰብ መዛነፍ የሚመነጩ በመሆናቸው ችግሮችን ለመቅረፍ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም ከሚዘጋጁ ውይይቶች ባሻገር የተለያዩ አወንታዊ ሃሳብ ላይ የሚሠሩ ሥርዓቶች እንደሚዘረጉ አመላክተዋል። አወንታዊ ሃሳብ ላይ ከሚሠሩት ሥራዎች መካከል አንዱ የመጽሔት ህትመት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የአዎንታ መጽሔቱ በየሶስት ወሩ ወይም በስድስት ወር የሚታተም ይሆናል ያሉት ሰብሳቢው፤ መጽሔቱ ተነባቢ እንዲሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል። በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮች ምንጭ በአሉታዊ አስተሳሰብ የሚገናኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በሀገራዊ ጉዳይ በሰላምና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ምክረ ሃሳብ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ከአስተሳሰብ መዛነፍ የመነጩ ናቸው ያሉት አቶ በቀለ፤ ብሔራዊ የአስተሳሰብና የባህል ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ብለዋል። ማህበሩ ለዴሞክራሲ ግንባታ የባህል እድገትን ለማጎልበት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ሰላምን በማስገኘት ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን የሚያስችል ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

አዎንታዊ አስተሳሰብ ለሕዝባዊ እድገት በሚል መሪ ሃሳብም የፓናል ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በዘርፉ በተሠማሩ ባለሙያዎች በአስተሳሰብ ዙሪያ ለውጥ ለማምጣት ሁሉም ባለድሻ አካላት ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባ ተመልክቷል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You