የሠራተኛው የበጋ ወራት ውድድር አሸናፊዎች

ካለፈው ጥር ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የ2016 ዓ.ም የሰራተኞች የበጋ ወራት ውድድር ወደ መቋጫው ተቃርቧል፡፡ ከሰላሳ በላይ የሰራተኛ የስፖርት ማህበራትን በአስር የስፖርት አይነቶች ሲያፎካክር የከረመው አንጋፋው የስፖርት መድረክ በውድድሩ መዝጊያ እለት ፍፃሜ ከሚያገኙ ጥቂት ውድድሮች በስተቀር በሌሎች በርካታ የስፖርት አይነቶች አሸናፊዎች ታውቀዋል፡፡

አጠቃላይ የውድድሩ አሸናፊዎች ከተለዩባቸው መካከል የቤት ውስጥ ውድድሮች ዋነኞቹ ናቸው። ጠንካራ ፉክክር በሚታይበት የቮሊቦል ውድድርም አሸናፊዎች ተለይተዋል፡፡ በዚህም መሰረት በወንዶች አንደኛ ዲቪዚዮን የቮሊቦል ውድድር ከስድስት ጨዋታዎች አራቱን ድል ማድረግ የቻለው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በአስራ ሦስት ነጥብ አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ብርቱ ፉክክር ሲያደርግ የቆየው አዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ በአስር ነጥብ ሁለተኛ፣ ኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በዘጠኝ ነጥብ ሦስተኛ ሆነው ፈፅመዋል፡፡

በተመሳሳይ በሁለተኛ ዲቪዚዮን የወንዶች ቮሊቦል ፋፋ ምግብ አክሲዮን ማህበር ስድስቱንም ጨዋታ አሸንፎ በአስራ ስምንት ነጥብ ቀዳሚ ሆናል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም አራት ጨዋታ በማሸነፍ በአስራ ሁለት ነጥብ ሁለተኛ፣ ሁለት ጨዋታ ያሸነፈው ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ በስድስት ነጥብ ሦስተኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡

በሴቶች ቮሊቦል ከአስር ጨዋታ በአንዱ ብቻ ሽንፈት የገጠመው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በሃያ ሰባት ነጥብ አንደኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ ስምንት ጨዋታ ያሸነፈው አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ በሃያ አራት ነጥብ ሁለተኛና ሰባት ጨዋታ ያሸነፈው መከላከያ ኮንስትራክሽን በሃያ አንድ ነጥብ ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

በአንደኛ ዲቪዚዮን ጠረጴዛ ቴኒስ ወንዶች ውድድር ኢትዮ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀበትን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያደረጋቸውን አስር ጨዋታዎቹ ሁሉንም በማሸነፍ ሃያ ነጥብ ሰብስቦ በአንደኛነት ሲያጠናቅቅ፣ ከአስር ጨዋታዎች ስምንቱን አሸንፎ በሁለቱ ብቻ ሽንፈት የገጠመው ኢትዮ ቴሌኮም በአስራ ስምንት ነጥብ ሁለተኛ ሆኖ ፈፅሟል፡፡ አምስት ጨዋታ አሸንፎ በአምስቱ ደግሞ የተሸነፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአስራ አምስት ነጥብ ሦስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ቡድን ሆኗል፡፡

በተመሳሳይ በሁለተኛ ዲቪዚዮን የወንዶች ጠረጴዛ ቴኒስ ፉክክር በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች ስድስቱን በድል የተወጣው ፋፋ ምግብ አክሲዮን ማህበር በአስራ አራት ነጥብ አንደኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ እስከ ውድድሩ መጨረሻ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ተመሳሳይ ነጥብ ማስመዝገብ የቻለው ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በሁለት የግብ ልዩነት ብቻ ተበልጦ ተከታዩን ደረጃ ሲይዝ፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ አምስት ጨዋታ አሸንፎ በሦስቱ በመሸነፉ በአስራ ሁለት ነጥብ ሦስተኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡

በሴቶች ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ስምንቱንም ጨዋታ ማሸነፍ የቻለው አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት በአስራ ስድስት ነጥብ ቀዳሚውን ደረጃ በመያዝ አጠናቋል፡፡ በሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት የገጠመው ኢትዮ ቴሌኮም በአስራ አራት ነጥብ ሁለተኛ፣ አራት አሸንፎ በአራቱ የተሸነፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአስራ ሁለት ነጥብ ሦስተኛውን ደረጃ ይዟል፡፡

በወንዶች የዳርት ውድድር ከአስር ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት ያልገጠመው አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ በሃያ ነጥብ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ እሱን ተከትሎ ጂኦ ሴንቴቲክ ኢንደስትሪያል ሰባት ጨዋታዎችን አሸንፎ በአስራ አራት ነጥብ ሁለተኛውን ደረጃ ይዟል፡፡ መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ስድስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ በሰበሰበው አስራ ሁለት ነጥብ ቀጣዩን ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡

ተቀራራቢና ጠንካራ ፉክክር ሲያስተናግድ በቆየው የወንዶች ከረንቦላ ውድድር አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ከስድስት ጨዋታ ሦስቱን አሸንፎ በቀሪዎቹ ቢሸነፍም በዘጠኝ ነጥብ የግብ ክፍያ ሳይኖርበት ቀዳሚ ሆኖ አጠናቋል፡፡ የቅርብ ተፎካካሪው የሆነው ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ተመሳሳይ ነጥብ ቢያስመዘግብም አንድ የግብ እዳ ይዞ በሁለተኛነት ለማጠናቀቅ ተገዷል፡፡ ሁለት ጨዋታ ብቻ ማሸነፍ የቻለው የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ በስድስት ነጥብ ሦስተኛውን ደረጃ መያዝ የቻለ ቡድን ነው፡፡

በወንዶች የዳማ ውድድር በተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች አራቱን ያሸነፈው የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ በአስራ ሁለት ነጥብ አንደኛ፣ ሦስት ጨዋታ ያሸነፈው የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በዘጠኝ ነጥብ ሁለተኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡ ስድስት ጨዋታዎችን ባስተናገደው የወንዶች የቼስ ውድድር ሁሉንም በማሸነፍ አስራ ስምንት ነጥብ የሰበሰበው ኢትዮ ቴሌኮም በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፣ አራት ጨዋታ ያሸነፈው የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ በአስራ ሁለት ነጥብ ሁለተኛ፣ ሁለት ጨዋታ ያሸነፈው የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ደግሞ በስድስት ነጥብ ሦስተኛ መሆን ችሏል፡፡

ቀኑ ለጊዜው ባልተገለፀ የሰራተኛው የበጋ ወራት ውድድሮች የመዝጊያ መርሃግብር ከቤት ውጪ በሚደረጉ ስፖርቶች የፍፃሜ ፍልሚያ እንደሚደረግ ይጠበቃል። በተለይም በሁለት ዲቪዚዮን በሚካሄደው የእግር ኳስ ውድድር ከወዲሁ አጓጊ ሆኗል፡፡

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You