የደም ባንክ ይከፈትልን ጥያቄ እና ተስፋ ሰጭ ምላሽ

የዛሬው የፍረዱኝ ዓምድ ዝግጅታችን ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ይወስደናል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመልካም አስተዳደር እና ምርምራ ቡድን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ባደረገው ቅኝት እና ማጣራት በዞኑ ከ20 በላይ እናቶች በደም እጥረት መሞታቸውን ከተለያዩ ወገኖች ሰማ። ጉዳዩን ለማጣራት የዞኑን አስተዳደር እና በዞኑ የሚገኙ በተለያዩ የመንግስት ስራ ኃላፊነት ላይ ያሉ አካላትን አነጋግሮ መረዳት እንደተቻለው በዞኑ ከፍተኛ የደም እጥረት በመኖሩ እናቶች ለሕልፈት እየተዳረጉ ነው። የዞኑ አስተዳዳሪ እንደምክንያት ያነሱት በዞኑ የደም ባንክ አለመኖሩ ነው።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በወርሀ ሚያዚያ 2016 ዓ.ም በቤንች ሸኮ ዞን 20 እናቶች በደም እጦት ሞቱ ሲል ባዘጋጀው ዘገባ እውነታውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳወቀ። ይህን ተከትሎ ጉዳዩ ከሚመከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከዚህም ከዚያም ቅሬታዎች ተነሱ። ቅሬታዎች ግን ሕዝቡን ከመሞት የሚያድኑ አይደሉም።

የዝግጅት ክፍላችን ሕዝቡን በደም እጥረት ሳቢያ ከሚከሰት መሞት ለማዳን በዞኑ ለምን የደም ባንክ መክፈት አልተቻለም? ስንል ለኢትዮጵያ ደምና ሕብረህዋስ ባንክ አገልግሎት ጥያቄ አቀረበ። ከዞኑ የደረሰውን አቤቱታ እና ከኢትዮጵያ የደም ባንክ ያገኘውን ምላሽ እንዲህ ተዘጋጅቷ። መልካም ንባብ ።

የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳዳሪ ሀሳብና ቅሬታ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከተመሰረተ ሶስት ዓመት ገደማ ሆኖታል። ክልሉ ከቀድሞው ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች መቀመጫ ሐዋሳ ከፍተኛ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ እና በተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሳቢያ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት አቅርት ችግር ያለበት ነው። ከለውጡ ወዲህ የሕዝቡ የመልማት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ተመልሶ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ተብሎ ተመስርቷል። በዚህ ክልል ውስጥ ካሉት ዞኖች አንዱ በሆነው የቤንች ሸኮ ዞን ከጤና መሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ችግር ከሚስተዋልባቸው የክልሉ ዞኖች አንዱ ነው።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ፤ በጤናው ዘርፍ ከተደራሽት አንጻር የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት ተደራሽነት በመባል በሁለት ይከፈላል። ከመሰረተ ልማት ተደራሽነት አንጻር በዞኑ ሁለት ሆስፒታሎች አሉ። ከእነዚህ መካከል በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚተዳደረው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያ ሆስፒታል አንደኛው ነው።

ከአገልግሎት ተደራሽነት አንጻር በአዲሱ የጤና ፍኖተ ካርታ የተቀዛቀዘውን የጤና ኤክስቴንሽንና በዞኑ ያለውን የጤና አገልግሎት ለማሳደግ በንቅናቄ ስራዎችን የተሰሩ መሆናቸውን ይናጋራሉ። በተለይም ቀበሌዎችን ጽዱ ከማድረግ አንጻር ከጤና ኤክስቴንሽን ጋር ትስስር እንዲኖራቸው ለማድረግ ዞኑ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው።

አቶ ሀብታሙ እንደገለጹት፤ ከጤና መሰረተ ልማት አንጻር በዞኑ በሚዛን አማን ከተማ አንድ ሪፈራል ሆስፒታል ይገኛል። ይህ ሆስፒታል የተሰራው የበበቃ እርሻ ልማትን መመስረት መሰረት አድርጎ ለ60 ሺ ማኅበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ ነው። ነገር ግን በግምገማ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው አሁን ላይ ከአጎራባች ክልሎች የሚመጣውን ጨምሮ ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሕክምና እየሰጠ ነው። ይህም በዞኑ የሚገኘው ማኅበረሰብ የሚፈልገውን የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኝ አድርጎታል።

ይህ ሆስፒታል በደርግ ዘመን መንግስት የተገነባ ከመሆኑም ባለፈ በኋላም በቂ ማስፋፊያ እና እድሳት ያልተደረገበት ነው የሚሉት አቶ ሃብታሙ፤ አሁን ላይ ሆስፒታሉ አገልግሎት ሊሰጥ ከሚችለው ሕዝብ በላይ አገልግሎት እንዲሰጥ መገደዱን ያስረዳሉ። በዙሪያው ያሉ ዞኖች እና ክልሎች በሙሉ ሪፈር የሚጽፉት ለዚህ ሆስፒታል ነው። የሚዛን ሕዝብ በራሱ ከ170 ሺ በላይ ነው። በመሆኑም ሚዛን ላይ አንድ ጤና ጣቢያ መስጠት ካለበት አምስት እጥፍ በላይ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በየወረዳው ያሉት የጤና ጣቢያ አገልግሎቶች እንዳሉ ሆኖ ሚዛን አማን ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ዋና አስተዳዳሪው ያስረዳሉ።

አቶ ሀብታሙ እንደሚሉት፤ በጤና ተቋማቱ በመሰረታዊነት የመድሃኒት አቅርቦት ችግር አለ። ይህ ደግሞ ከጤና መድህን ክፍያ ጋር ተያይዞ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። በዞኑ ውስጥ በተደረገው ግምገማ ማኅበረሰቡ በተለይም በእናቶች ማግኘት የነበረባቸውን ጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዳገኙ እንቅፋት ፈጥሯል።

ጤና ጣቢያ ላይ የመድሃኒት አቅርቦት ችግር እንዳለ ሆኖ የቀረበውን መድሃኒትም በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር እንደሚስተዋል የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ በቀጣይ መታረም ያለበት በመሆኑ እንደ አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በጤና ጣቢያዎች በእርዳታ መልኩ የሚመጡና በግዥ የሚመጡ መድሃኒቶችን በአግባቡ ለኅብረተሰቡ የመስጠት ችግር ይስተዋላል። አልፎ አልፎ በተወሰኑ የጤና ባለሙያዎች ዘንድ አካባቢያቸው ላይ የራሳቸው የግል ድርጅት በመክፈት መድሃኒቶችን ወደራሳቸው ድርጅት የመውሰድ ዝንባሌ ስላለ ይህን መቅረፍ ይገባል።

በዞኑ ትልቅ ፈተና እየሆነ ያለው የወባ ወረርሽን ሲሆን ወረርሽኙ 74 በመቶ ደርሷል። አንድ ሰው 16 ዙርና ከዚያ በላይ እየታመመ ነው። ይህ በቀጣይ ቶሎ መፍትሔ ካልተሰጠው የማኅበረሰቡን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ያስረዳሉ።

ሚዛን ቴፒ ሆስፒታል በአንድ አልጋ ብቻ አራት ሕጻናት ተኝተው ይታከማሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን በዞኑ አቅራቢያ የደም ባንክ ባለመኖሩ በስድስት ወር ውስጥ በደም እጦት ምክንያት 20 እናቶች በሆስፒታል እያሉ ሕይወታቸውን ማጣታቸው አስረድተዋል።

ከመሰረተ ልማት እጥረት ጋር ተዳምሮ በዞኑ በከፍተኛ ደረጃ የሚስተዋለው የደም እጥረት የደም ባንክ በአቅራቢያቸው ባለመኖሩ የተፈጠረ ችግር መሆኑን ያስረዳሉ። አሁን ላይ በዞኑ የሚስተዋለው የደም እጥረት እጅግ አሳሳቢ ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ፣ በዞኑ የደም ባንክ መከፈት እንዳለበት ያሳስባሉ።

ከመሰረተ ልማትር ጋር በተያያዘ ሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት በሚዛን አማን ከተማ 13 ሺ ሄክታር ላይ ያረፈ ሆስፒታል ለመገንባት እቅድ መያዙን አመላክተዋል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ታካሚዎች ቅሬታ

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሆስፒታሉ ታካሚዎች እንደሚሉት፤ ሆስፒታሉ ዕድሜ ጠገብ ከመሆኑ ባለፈ የእድሳት እና የማስፋፊያ ስራዎች ያልተደረገለት ነው። ከፍተኛ የታካሚ ቁጥር በመኖሩ ሕክምና ሳይገባ የሚሞት ሰው አለ። ታካሚዎች ወረፋ የሚጠባበቁባቸው ወንበሮች ሳይቀር የተሰባበሩ ናቸው። የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት ተቋም አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል።

ሐኪም የሚያዝዛቸውን መድሃኒቶች በሆስፒታሉ ፋርማሲዎች አናገኝም ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ መድሃኒት የለም ውጭ ግዙ እንደሚባሉ እና ውጭ ላይም መድሃኒቶችን በቀላሉ ማግኘት አንደማይችሉ ያስረዳሉ። በሆስፒታሉ ባለሙያ ብቻ ነው ያለው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ከመድሃኒት በተጨማሪ ውሃና መሰል መሰረተ ልማቶች በሆስፒታሉ አለመኖሩን ይገልጻሉ።

ከላይ የተጠቀሱ ችግሮችን በአንድም በሌላ መፍትሔ እየፈለጉ እንደሚያልፉት የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ከደም ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው ችግር ግን ለብዙ ወገኖች ሞት ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ። በሆስፒታሉ ብሎም በዞኑ በቂ የደም አቅርቦት ባለመኖሩ የደም እጥረት ሲያጋጥም ወጀ ጅማ ሪፈራል ሆስፒታል እንደሚላኩ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ጅማ ላይም ደም የለም ስለሚባሉ የሕሙማን ሕይወት ለማትረፍ ደምን በኮንትሮባንድ እስከመግዛት መድረሳቸውን ያስረዳሉ።

ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሚዛን አማን ከተማ ላይ የደም ባንክ እንዲገነባላቸው ይጠይቃሉ።

የሚዛን ቴፒ ሆስፒታል ምላሽ

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሚዛን ቴፒ ሆስፒታል

ድንገተኛ ሕክምና ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሲሳይ መንግስቱ ማኅበረሰቡ በሚያነሳቸው ቅሬታዎች ላይ ማብራሪያዎችን ሰጥተውናል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በአዋቂዎች የድንገተኛ ሕክምና በቀን ማስተናገድ ከሚችለው ከ60 እስከ 70 በላይ ታካሚዎች ነው። ነገር ግን አሁን ላይ ሆስፒታሉ እያስተናገደ ያለው ማስተናገድ ከሚችለው አቅም እጥፍ ነው። ሆስፒታሉ በደርግ ዘመነ መንግስት የበበቃ እርሻ ልማትን ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ነው። በወቅቱ ሆስፒታሉ ሲገነባ 60 ሺ ዜጎችን ለማከም ታስቦ ነው። ዛሬ ላይ ግን ሆስፒታሉ ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆን ሕዝብ አገልግሎት እየሰጠ ነው።

በዚህም በአንድ አልጋ ከሁለት እስከ አራት ሕጻናት ተኝተው እየታከሙ ነው። የጽኑ ሕሙማን ሕክምና መስጫ እጥረት በመኖሩ ጽኑ ሕክምና ክፍል ገብተው ሊታከሙ የሚገባቸው ሰዎች ተገቢውን ሕክምና ሳይደረግላቸው ይቀራል።

በሆስፒታሉ ከሚገኙ ማሽኖች ውስጥ አብዛኛዎቹ በኬሚካል ‹‹ኮንስትሬንት›› እና ‹‹ሪጀንት›› እጥረት ምክንያት አገልግሎት እየሰጡ አይደለም። ዞኑ ከአዲስ አበባ ርቀት ያለ በመሆኑ በደም የሰው ሕይወጥ እየጠፋ ነው። በዞኑ ደም ብንሰበስብም በቅርበት ደም ባንክ ባለመኖሩ ደም የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በደም እጥረት እየሞቱ ነው። ሬጀንት የሕክምና ማሽኖች እንዲሰሩ የሚያግዝ ኬሚካል ሲሆን ከፍተኛ እጥረት መኖሩን ያስረዱት ዶክተሩ፤ ማሽኖች እያሉ ሬጀንት የተባለ ኬሚካል ባለመኖሩ ያለ ስራ ቆመዋል። ይህን ችግር የሚመለከተው አካል እንዲፈታ ይጠይቃሉ።

በቀጠናው አማራጭ ሆስፒታል ባለመኖሩ በሆስፒታሉ ከደቡብ ሱዳን ድረስ የሚመጡ ታካሚዎች መኖራቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ አብዛኛው የጋምቤላ ሕዝብም በዚህ ሆስፒታል እንደሚታከሙ ያስረዳሉ። ሆስፒታሉ ካለው አቅም በላይ ሕሙማንን እንዲያስተናግድ ተገዷል።

የጨቅላ ሕጻናት፣ ጽኑ ሕክምና፤ የእናቶችና የሕጻናት አጠቃላይ አገልግሎቱ የሚሰጠው በነጻ ነው። በነጻና በእርዳታ መልኩ የሚመጣው መድሃኒት አጠቃላይ ዋጋ ከ30 እስ 35 ሚሊዮን ብር የሚገመት ነው። ይህም በቂ ስላልሆነ ታካሚዎች ላይ ቅሬታ እያስነሳ ነው። የመድሃኒት እጥረትም አለ፤ ለመግዛትም አሰራሩ የተንዛዛ ስለሆነ አስቸጋሪ ነው ይላሉ።

ቅሬታ አቅራቢዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸው መሆናቸውን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ በሆስፒታሉ ከሚገኙ ሕሙማን የሚታከሙባቸው ስድስት ወሳኝ ማሽኖች ሁለቱ ብቻ የሚሰሩ በመሆናቸው ጽኑ ሕሙማን ክፍል መግባት የነበረባቸው ታካሚዎች አገልግሎቱን ሳያገኙ ለሕልፈት የሚዳረጉ እንዳሉ ዶክተሩ ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ምላሽ

በቤንች ሸኮ ዞን ለተነሱ ጥቄዎች ምላሽ የሰጡን የኢትዮጵያ ደምና ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ናቸው።

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ከደም ለጋሾች ደም እንዲሰበሰብ ተደርጎ ወደ ጅማ ይላካል። ነገር ግን በዞኑ ደም በሚያስፈልግበት ወቅት ከጅማ ቅርንጫፍ ለምነው እንደሚወስዱ በቤንች ሸኮ ዞን የሚገኙ ነዋሪዎች ቅሬታዎችን ያነሳሉ። በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው ? በየክልሎቹ የደም ባንክ ማዕከላት መገንባት ያልተቻለው በምን ምክንያት ነው ? የሚሉ እና መሰል ጥያቄዎች በዝግጅት ክፍላችን የተጠየቁት ምክትል ዳይሬክተሩ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥውናል።

የደም ባንኮችን ለመክፈት ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ ነው። ለምሳሌ ከአንድ በጎ ፈቃደኛ ደም ተሰብስቦ ምርመራውን እና ዝግጅቱን ጨምሮ ለተጠቃሚ እደስከሚደርስበት ባለው ሂደት ከ45 ዶላር በላይ ወጪን የሚጠይቅ ነው። ይህን ያህል ወጪ የተደረገበትን ደም ለግልም ሆነ ለመንግስት ሆስፒታል ታካሚዎች በነጻ የሚሰጥ ነው።

በአጠቃላይ የደም ሕክምና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ስለሆነ የዓለም የጤና ድርጅት እና ደም ላይ የሚሰሩ ሌሎች ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት የሚመክሩት አንዳንድ አገልግሎቶችን ማማከል ያስፈልጋል በማለት ይመክራሉ። የማማከል ከሚገባቸው ውስጥም የላብራቶሪ አገልግሎት እና የደም ተዋጽኦ ዝግጅት በቀዳሚነት ያነሳሉ።

እንደ አቶ ሀብታሙ እንደሚሉት፤ የደም ማዕከል ሲከፈት የራሱ የሆነ መለኪያ መስፈርት አለው። ከእነዚህ መስፈርቶች መካከል የደም ባንክ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሲቋቋም ከ150 እስከ 200 ኪሎ ሜትር ራዲየስ መሸፈን አለበት የሚለው አንዱ ነው። ነገር ግን ተቋሙ በጣም ብዙ ደም እየሰበሰቡ ‹‹ቴስት›› የሚያደርጉበት ማዕከል የሚያጡ ከሆነ ከ150 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ የሚለው መስፈርት የግዴታ አይሆንም። የደም ማሰባሰብ ልምዱ ግን እንደዛ አይደለም።

አሁን ካሉት 7 ማእከላት የተሻለ ‹‹ቴስት›› የሚያደርገው አዲስ አበባ ያለው ነው። ከደብረ ብርሃንን፣ ከወሊሶን እና መሰል በዙሪያ ከሚገኙ ከተሞች የሚሰበሰብን ደም “ቴስት” እናደርጋለን። አዲስ አበባ ላይ ያለው አንድ ማሽን ከሁሉም የሀገሪቱ አካበቢዎች የሚሰበሰብን ደም “ቴስት” የማድረግ አቅም ያለው ነው።

በጣም ብዙዎቹ የደም ባንኮች የሚሰበሰበው ደም ትንሽ ስለሆነ ያንን ብቻ ‹‹ቴስት›› ያደርጋሉ። ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን በተመለከተ ጅማ ማስተባበሪያ እስከ ቦንጋ ያለው ርቀት ምን ራዲየሱም 150 አይሆንም። ቦንጋ ላይ በጣም በቂ ደም የሚሰበስቡ ከሆነ አሁን ዲስታንስ (ርቀት) የሚለው ላይወስነን ይችላል። ነገር ግን በውድ ዋጋ የተገዙ ማሽኖች በቂ የሆነ ደም ካልተሰበሰብ “አይድል” ሊሆኑ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

ከእርቀት በተጨማሪ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ሕዝብ በላይ ለሚያስተናግዱ እንደ ሚዛን ቴፒ አይነት ሆስፒታሎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሕዝብን ቁጥር ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለምን የደም ባንክ አይቋቋምም? ተብለው በዝግጅት ክፍላችን ጥያቄ የተነሳላቸው አቶ ሀብታሙ በምላሻቸው፤ የደም ማዕከል ለመገንባት ከእርቀቱ በተጨማሪ በሆስፒታሎች ያሉትን የአገልግሎት ተጠቃሚዎች ወይም የሕዝብ ብዛቱን እናያለን። ማነው የደም ባንክ መስራት የሚገባው? የሚለውንም ይታያል።

ከዚህ አንጻር ሚዛን ላይ የደም ማሰባሰቢያ ጣቢያ እና የደም ባንክ እንዲኖራቸው እንደሚፈልጉ አመላክተዋል።

ለሌሎች ክልሎች እንደሚያደርጉት ዞኑ የደም ባንኩን ገንብቶ ባንክ አምጡልን የሚል ከሆነ፤ አስፈላጊው ግብዓት ሁሉ ለማሟላት ዝግጅ መሆናቸው ይናጋራሉ። የደም ባንክ የመገንባት ኃላፊነት የክልሉ ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ የደም ባንኩን ገንብተው የፌደራል ተቋሙን ድጋፍ ቢጠይቁ መስሪያ ቤታቸው ድጋፍ የማያደርግበት ምንም ምክንያት እንደሌለ አብራርተዋል።

እንደ ስታንዳርድ ራዲየሱን ብናስቀምጥም የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ስናይ ተራራ ምናምን አለ፤ አንዳንድ ቦታ ላይ ሰዎች በጣም ተጠራቅመው ሲኖሩ አንዳንድ ቦታ ላይ ተራርቆ ይኖራል ባስቀመጥነው ራዲየስ ብቻ ብለን አንሄድም። አሁንም ያሉት ባንኮች አቀማመጣቸው እንደዛ አይደለም።

ክልሎች የደም ባንክ እንዲኖራቸው ከነሱ የሚጠበቀው ኃላፊነት ምንድነው? ተብሎ የተነሳላቸው ጥያቄ ምክትል ዋና ዳሬክተሩ፤ የሰው ኃይል ማቅረብ አለባቸው። ደም የሚቀዳውና ደም ባንኩ ካለ እኛ ጋር የተሻለ እውቀትና ክህሎት ስላለ ስልጠና ሰጥተን፣ ደም የሚቀዱበትን ቁሳቁስ ሰጥተን “ቴስት” ማድረጊያ ማዕከሉን ለስራ እናመቻቻለን።

የትም ቦታ ሰው በደም እጦት እንዲጎዳ አንፈልግም ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ የምንከተለውም አሰራር የትኛውም ሰው በደም እጦት እንዳይጎዳ የሚያደርግ ነው።

በሚዛን ቴፒ ሆስፒታል በስድስት ወር ውስጥ 20 እናቶች በደም እጦት ምክንያት ሕይወታቸው አጥተዋል በሚል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያወጣውን ዜናን መመልከታቸውን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ፤ ጉዳዩን ለማጣራት የኦዲት ሪፖርት እየተመለከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን እንደ ሀገር በደም እጦት በዛ ልክ ሰው ሊሞት እንደማይችል ያስረዳሉ።

በደም እጦት ሳቢያ 20 እናቶች መሞታቸውን የጤና ዘርፍ የሚመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ በሚዛን አማን ከተማ ተገኝቶ የዞኑ ጤና መምሪያ ሪፖርት ቀርቦለታል። ለዚህ በደም እጦት 20 እናቶች ሊሞቱ አይችሉም ለማለት እንዴት ይቻላል? ተብለው የተጠየቁት ዳሬክተሩ መረጃውን ያየሁት በሚዲያው ነው። በደም እጦት አንድ ሰው ሲሞት ሪፖርት ሊደረግልን ይገባ ነበር። ለምን 20 ሰው እስኪሞት መጠበቅ አስፈለገ ? የሞቱት ሰዎች በትክክል በደም ምክንያት ስለመሞታቸው ኦዲት ተደርጎ መቅረብ አለበት። እሱ ሪፖርት ከሰማን በኋላ ኦዲት አድርገው እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውን አመላክተዋል።

እንደ ሀገር 50 የደም ባንኮች አሉ። ይህ ባለበት አንድም ሰው በፍጹም በደም እጦት መሞት የለበትም። ደም ካለበት ቦታ በአየርም ቢሆንም መድረስ አለበት። ጅማ ለቦንጋ 100 ኪሎ ሜትር አካባቢ ነው። ሚዛን ከቦንጋ ጋር ያውም ርቀት እንደዛ ነው የሚሆነው። የደም እጥረት ሲገጥማቸው ከጅማ መጠየቅ ይችሉ ነበር ። ከጅማ ማግኘት ባይችሉ እንኳን አዲስ አበባ ደውለው በደም እጦት እየተቸገርን ነው ማለት ነበረባቸው። አዲስ አበባ ከሌለ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል ካለው በማቅረብ ችግራቸውን ይፈታ እንደነበር ጠቁመዋል።

ጅማ ላይ የደም የኮንትሮባንድ ንግድ እንዳለ ሰምተናል፤ እናንተ መረጃው አላችሁ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ሀብታሙ፤ “በፍጹም መረጃው የለንም” ሲሉ መልሰዋል።

ደም ከበጎ ፈቃደኞች ይሰበሰባል፤ መንግስት እሴት ጭምሮ ለመንግስትም ለግልም ተቋማት በነጻ ይሰጣል። ደም ባንኮች ደግሞ ከሁሉም የጤና ተቋማት ጋር ውል አላቸው። 723 ደም ባንኮች አሉ። እነዚህ ባንኮች የግል የመንግስት የጤና ተቋማት በነጻ አገልግሎቱን መስጠት እንዳለባቸው ውል ይገባሉ። ይሄንን ማኅበረሰቡም ማወቅ አለበት።

የጤና ስርዓቱን ደም ጋር አምጥቶ ማላከክ እንዳይኖር በጣም ጥንቃቄ መደረግ አለበት ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ እናቶች የሚሞቱባቸው ምክንያቶች በርካታ ናቸው። ደም የሚሰጠው ከ1000 ሚ.ሊ በላይ ሆኖ ከፍተኛ የደም መፍሰስ ሲኖር ነው። ከዛ በታች ከሆነ ራሱ የደም ሕክምናው አይሰጥም። ያንን ደም እንዳይፈስ ሌሎች ብዙ ስልቶች አሉ። ሰው የደም ሕክምና መጠቀም ያለበት የመጨረሻ አማራጭ ከሆነ ብቻ ነው። ምክንያቱም ደም ውስጥ የራሱ ተያያዥ ችግሮች ሊኖሩት ይችላል። ደሙን እንመረምራለን ብንልም ተላላፊ በሽታዎች ስላሉ ማሽኑ ላያገኘው ይችላል። ይህም የእኛ ብቻ ሳይሆን ዓለም ላይ ያሉ ማሽኖች ሁሉ ተግዳሮት መሆኑን ያስረዳሉ።

ለአንድ ሰው ጥሩ ደም የሚባለው የራሱ ደም ብቻ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከሱ ተላልፎ የሚሰጥ ደም ተመሳሳይ ቢሆን እንኳን አደጋ አለው።

አንድ ተቋም ላይ ይህ ሁሉ ሰው በደም ምክንያት ብቻ አይሞትም። ከጤና ስርዓቱ ጋር የተያያዘ ችግር ሁሉ ከደም ጋር ማያያዝ ትክክል አይደለም። እርሳቸው ይህን የሚሉት ከተጠያቂነት ለመሸሽ አለመሆኑን የሚናገሩት አቶ ሀብታሙ ተጠያቂነት ጉዳይ ከመጣም ጉዳዩ የሚመከታቸው አካለት በሙሉ ችግሩን መጋራት አንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

በመጨረሻም በክልሉ ወይም በዞኑ በኩል መሟላት ያለባቸው ነገሮች ከተሟሉ የኢትዮጵያ ደምና ሕዋስ ባንክ አገልግሎት አስፈላጊውን ግብዓት ለማሟላት ዝግጁ መሆኑን አቶ ሀብታሙ ገልጸዋል።

የጋዜጠኞች ትዝብት

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በታካሚዎች የተጨናነቀ ሲሆን ማስተናገድ ከሚችለው በላይ እያስተናገደ ነው። የአልጋ እጥረት ከመኖሩም በላይ ያለው አልጋም ቢሆን በጣም ያረጀ ነው። አንድ አልጋ ላይ ሶስትና አራት ሕጻናት ተኝተዋል። ሕንጻው ያልታደሰ ከመሆኑም ባሻገር ኮርኒሱ የተሸነቆረና የፈራረሰ ነው። በቂ የሕሙማን አገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶች የሉትም ። ያሉትም ቢሆን ያረጁ ናቸው።

ሞገስ ተስፋ እና መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You