ስፖርትን ባሕሉ ያደረገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር…

በስፖርቱ መስክ የቀረቡ የተለያዩ መዛግብት እንደሚያስረዱት ከሆነ ማኅበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴ “ማስ ስፖርት” ጤናማና አምራች ዜጎችን ከማፍራት ጎን ለጎን፣ ለሀገራዊ ሠላምና አንድነት የሚያበረክተው ፋይዳ ትልቅ ነው። በ1990 ዓ.ም ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የስፖርት ፖሊሲም ማንኛውም ማኅበረሰብ በሚኖርበት፣ በሚሠራበትና በሚማርበት አካባቢ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን የማድረግ መብት እንዳለው ያስቀምጣል።

ይሁን እንጂ ማኅበረሰቡ በተለይም በከተሞች አካባቢ የሚኖረው በስፖርት ፖሊሲው የተቀመጠ መብቱን ለመተግበር የሚችልበት የተደላደለ ነገር የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል። እንደ ሀገር የስፖርት ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅፋት ሆነው ከቆዩ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በተለይም በከተሞች አካባቢ በበቂ ሁኔታ አለመኖራቸው ይጠቀሳል። በተለይም ቀደም ሲል በየሰፈሩ የነበሩ ትንንሽ የጥርጊያ ሜዳዎች እየፈረሱ ለሕንፃ ግንባታ መዋላቸው ያለፈው ሥርዓት በብዙ ሲወቀስበት የኖረ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።

ይህም እንደ ሀገር ስፖርትን ባሕሉ ያደረገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እንቅፋት ከመሆኑ ባሻገር ሀገርን በታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች መወከል የሚችሉ ስፖርተኞች ከየሰፈሩ የሚፈልቁበትን ዕድል ዘግቶ ቆይቷል። ከዚህ ጎን ለጎን ለማኅበረሰብ አቀፍ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችም ይሁን በአጠቃላይ ለስፖርቱ ዘርፍ በመንግሥት ረገድ ይሰጥ የነበረው ትኩረት አነስተኛ ሆኖ መቆየቱ ብዙ ዋጋ ሲያስከፍለን ኖሯል። የዚህ ተፅዕኖም በስፖርቱ ዘርፍ ዛሬም ድረስ ዋጋ እያስከፈለን እንደሚገኝ በርካታ ጥናቶች በየጊዜው ሲቀርቡ ይታያል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት ገደማ በአዲሱ የመንግሥት ሥርዓት ለስፖርቱ ዘርፍ በተለይም ለማኅበረሰብ አቀፍ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እየተሰጠ የሚገኘው ትኩረት እየጨመረ ስለመምጣቱ በተግባር የሚታዩ ማሳያዎችን መደርደር ይቻላል። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተለያዩ የማኅበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ለማበረታታት እየወሰዱ የሚገኙት ርምጃ በጉልህ የሚጠቀስ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብና ተነሳሽነት የማዘውተሪያ ስፍራን በተመለከተ ትልቅ ችግር በሚስተዋልበት በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ተጨባጭ የሆኑ ለውጦች ተመዝግበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተማ አስተዳደሩ የመደመር ትውልድ መጽሐፍን በመሸጥ ለሕፃናትና ወጣቶች የመጫወቻና የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራ ማዕከላትን ግንባታ እንዲያውል ማበርከታቸው ይታወቃል። ይህንን ጨምሮ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ 1236 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በከተማ ተገንብተዋል።

ቀደም ሲል በየሰፈሩ የነበሩ በርካታ የማዘውተሪያ ስፍራዎችም ደረጃቸውን ጠብቀው ለማኅበረሰቡ ምቹና ዘመናዊ ሆነው እንዲሠሩ ማድረጋቸውም ይታወቃል። በዚህም አሁንም በየጊዜው እየተመነደገ ከሚሄደው የሕዝብ ቁጥር አኳያ በቂ ነው ለማለት ባያስደፍርም በየአካባቢው ዘመናዊና አረንጓዴ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማየት እየተለመደ መጥቷል። ይህም ነገ ሀገርን በትልልቅ ዓለም አቀፍ መድረክ አገርን ለመወከል ተስፋ ካደረጉ ታዳጊና ወጣት ስፖርተኞች ጤናቸውን ለመጠበቅ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እስከሚያደርጉ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ምቹ በሆኑ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ተጠቃሚ ማድረጉ የማይታበይ ሐቅ ነው።

እነዚህ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባታቸው ብቻ ግን ስፖርትን ባሕሉ ያደረገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በቂ አይደሉም። እንደ ሕዝብ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ለመሳተፍ ተነሳሽነትን ወስዶ የሚቀሰቅስና የሚመራ አካል ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ፖለቲከኞች፣ ታዋቂ ሰዎችና ሌሎችም አርዓያ የሚሆኑ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች ሚና የጎላ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን ከመገንባት ባሻገር ራሳቸው በተለያዩ የማዘውተሪያ ስፍራዎች እየተገኙ ኳስ በመጫወት ለሌሎች አርዓያ ለመሆን የሚያደርጉት ጥረት ፋይዳው ብዙ ነው።

ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደው የሸነን አፍሪካ ፌስቲቫል ላይ ለመሳተፍ ከመጡት ንዋንኮ ካኑን ጨምሮ ሄንሪ ካማራ፣ ዳንኤል አሞካቺና ሌሎች በርካታ የቀድሞ የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋቾች ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረጋቸውን በፌስ ቡክ ገፃቸው ባጋሩት መረጃ ተመልክተናል። ይህ ትልቅ ስምና ዝና እንዲሁም በእግር ኳሱ ዓለም ተሰሚነት ባላቸው የቀድሞ ከዋክብት የሀገርን ገፅታ በበጎ ለማስተዋወቅ የማይናቅ ሚና አለው።

በቅርቡ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ሀሳብ እንዳላት መናገራቸው ይታወሳል። ይህን ሀሳብ ብዙዎች ሊሆን እንደማይችልና እንደ ቀልድ ቢመለከቱትም ፈፅሞ ሊሆን የማይችል ጉዳይ ግን አይደለም። ብዙ የቤት ሥራ ግን ይጠይቃል። የአፍሪካ ዋንጫውን ለማዘጋጀት ከካፍ ይሁንታ የሚገኘው ደረጃውን የጠበቀ ስቴድየም በመገንባት ብቻ አይደለም። የገፅታ ግንባታና የማሳመንና የመቀስቀስ ሰፊ ሥራ ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ትልቅ ስም ያላቸው የእግር ኳሱ የቀድሞ ኮከቦችን መጠቀም አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን አዲስ አበባ ከተገኙት የቀድሞ የአፍሪካ ኮከቦች ጋር ያደረጉት የወዳጅነት ጨዋታም ለመቀራረብና ገፅታን ለመገንባት እንዲሁም ኢትዮጵያ ለእግር ኳስ ያላትን ስስ ልብ ለማሳየት መልካም አጋጣሚ ሊሆን ይችላል። በቅርብ ዓመታት ለማዘጋጀት ለታሰበው የአፍሪካ ዋንጫ ሎቢስት እንዲሆኑ ከነዚህ የቀድሞ ከዋክብት ጋር መቀራረቡም ነገ ብንፈልገው በቀላሉ ልናገኘው የማንችለው ጥሩ አጋጣሚ ነውና ጠቅላይ ሚኒስትሩን አበጁ ማለት ክፋት የለውም።

የማኅበረሰብ አቀፍ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ተደራሽ ለማድረግ አመራሩ የበኩሉን ሊያበረክት እንደሚገባ ተደጋግሞ ተነግሯል። በዚህም ረገድ ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ በመላው ኢትዮጵያ ከወረዳና ቀበሌ ጀምሮ ሀገር አቀፍ የማኅበረሰብ ስፖርት እንቅስቃሴዎች በየዓመቱ በስፋት ሳይቋረጡ ሲካሄዱ መመልከት እየተለመደ ይገኛል። ቀደም ባሉት ዓመታት የማኅበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴ ጉዳይ የለም ለማለት አይቻልም። ይሁን እንጂ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ተጀምሮ ብዙ ሳይገፋ ወረት ሆኖ ሲቀር መመልከት የቆየ ታሪክ አይደለም።

ባለፉት አራት ዓመታት ግን ይህ ባሕል እየተቀየረ የመጣ ይመስላል። በየጊዜው የማኅበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴ ጉዳይ ከወሬ ባለፈ በየአካባቢው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እያሳተፈ ወጥ ሆኖ ይካሄዳል። ለወረት አንዴ ተጀምሮ በዚያው ደብዛው ይጠፋል የሚለው ስጋትም እየጠፋ የሁልጊዜ አጀንዳ እየሆነ መጥቷል።

ይህ ትልቅ ለውጥ ነው። በቅድሚያ አስተሳሰብ ላይ የተለወጠ ነገር ወደ ተግባር ተለውጦ ባሕል ሆኖ እንዲቀጥል መሠረት መጣል በሚቻልበት በትክክለኛው ሐዲድ ላይ እየተጓዘ ነው ማለትም ይቻላል። ይህን አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ ነገ መንግሥት ልተወው ቢል እንኳን አንዴ በሕዝብ ዘንድ ሰርጿልና ይቀጥላል።

ልዑል አበበ

አዲስ ዘመን ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You