ተረጂነት ይብቃ !

ኢትዮጵያ የጀግኖች መፍለቂያ ናት። በየዘመናቱ ‹‹የሀገሬን ሉአላዊነትና ዳር ድንበር አላስደፍርም›› ያሉ ጀግኖች ልጆቿ እምቢ ለሀገሬ በማለት አጥንታቸውን ከስክሰው፤ ደማቸውን አፍስሰውና ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገው የሀገራቸውን ሉአላዊነት አስጠብቀዋል፤ ለተተኪው ትውልድም ነፃ ሀገር አስረክበዋል።

ኢትዮጵያ ታሪካዊት አገር፤ ሕዝቧም የዚህ ታላቅ ጀብዱ ባለቤት ነው። ይህ ጀግና ሕዝብ ታዲያ ስሙ ሁልጊዜ መነሳት ያለበት ከመልካም ነገር ጋር ነው። ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር እንጂ ኢትዮጵያ ‹‹የለማኞች ሀገር›› ተብላ መነሳት የለባትም፤ ክብሯንም የሚመጥን አይደለም።

ኢትዮጵያዊነት ኩሩነት ነው። ኢትዮጵያ ለጊዜው ድሃ ብትሆንም ክብሯን አሳልፋ የምትሰጥ ሀገር አይደለችም። የኢትዮጵያዊነት መገለጫም ጀግንነትና ክብር ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ ድሃ ቢሆንም በክብሩ ግን ድርድር አያውቅም። ለአንድ ኢትዮጵያዊ ‹ምፅዋዕት ጠባቂ› መባል ሞቱ ነው።

ይህ ደግሞ ከባህል፣ ከእምነትና ከእሴት ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት ነው። ኢትዮጵያዊነት ከተቀባይነት ይልቅ ሰጪነት ነው። ኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም የሰጠች፤ ሉሲን ለዓለም ሕዝብ ያበረከተች፤ በዓለም ላይ አንዲትም ቅንጣት ታክል ውሃ ሳትወስድ ለጎረቤቶቿ 12 ወንዞችን የምታበረክት፤ ስልጣኔን ያስተማረች፤ ሕይወታቸውን በየጊዜው በሚሰው ጀግኖች አማካኝነት ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ፋና ወጊ የሆነች ሀገር ነች። ስለዚህ ኢትዮጵያ በተፈጥሮዋ ሰጪ እንጂ ተቀባይ ልትሆን አትችልም።

ኢትዮጵያ ከ98 በመቶ በላይ የሆነው ሕዝቧ አማኝ ነው። ይህ አማኝ ሕዝብ የሚከተላቸው ኃይማኖቶች ከመቀበል ይልቅ ለመስጠት ከፍተኛ ክብርን የሚሰጡ ናቸው። ‹‹ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው›› የሚለው ኃይማኖታዊ አስተምሮም ገዢ ነው።

ከኃይማኖታዊ አስተምሮ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ የመስጠት ታሪክ ያላት ሀገር ነች። ሀገራት በተቸገሩ ቁጥር የኢትዮጵያን እጅ ሲናፍቁ ኖረዋል። የተፈጥሮ አደጋ ሲደርስባቸው፤ የእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭት ሲያጋጥማቸው ኢትዮጵያውያን ቀድመው ይደርሳሉ። ስለዚህም የኢትዮጵያውያን ተፈጥሮ መስጠት እንጂ መቀበል አይደለም።

እርዳታ ጠባቂነት ከክብርም በላይ የስነልቦናም ጦስ ይዞ ይመጣል። ምጽዋት ጠባቂ ማኅበረሰብ የስነልቦና የበላይነት አይኖረውም። ከሰው ፊትም መቆም አይቻለውም። እየለመኑ መኩራራት አይቻልም፤ እየለመኑ ስለ ጀብዱና ጀግንነት ማውሳት ውሃ አይቋጥርም።

ሰፊው ሕዝብ ምጽዋዕት ጠባቂ የሆነበት ሀገር እንደሀገርም ውርደትን ያስከትላል። በየትኛውም መድረክ ላይ ተገኝቶ ስለ እራሱና ስለሀገሩ መናገር ይቸገራል። በስነልቦና የተሸነፈ ሀገር ደግሞ በሁሉም ዘርፍ ተሸናፊ መሆኑ አይቀርም።

ስለዚህም እራስን ከተረጂነትና ከተመጽዋችነት ማውጣት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም። ለዚህ ደግሞ በቅድሚያ ተረጂነት ሉአላዊነትን የሚጋፋ፤ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ፤ ነጻነትን የሚያዋርድና ስነልቦናን የሚጎዳ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ይህን የነጻነትና የሉአላዊነት ጠላት ለማሸነፍ ደግሞ ሁሉም ወገቡን ጠበቅ አድርጎ መስራት አለበት።

በተለይም ሀገራችን ኢትዮጵያ ለግብርና ስራ ምቹ የሆነ ለም መሬትና አየር ያላት በመሆኑ ለግብርና ስራችን ትኩረት በመስጠት በሰፊው ማምረት መጀመር አለብን። የተጀመሩ የግብርና ልማት እንቅስቃሴዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ያልተገደበ ጥረት ማድረግ ይገባናል።

ታሪክ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ ግብርናን ከፈጠሩ ሀገሮች አንዷ ነች። ይህ ብቻም ሳይሆን በወቅቱ ለግብርና ሥራ መዋል ይችላሉ የተባሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንም ትጠቀም ነበር። ሆኖም ኢትዮጵያውያን እንደአጀማመራቸው ግብርናውን ማዘመን ባለመቻላቸው ጉዞው የኋሊት እንዲሆን አስገድዶታል።

ይባስ ብሎም ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች መነቃቃት ከማበርከት ይልቅ በየጊዜው እያደገ የሚሄደውን የሕዝብ ቁጥር መመገብ አቃተው። በዚህ የተነሳም ድርቅና ረሃብ ፈተና ሆኑ። የኢትዮጵያም ስም ከርሃብ ጋር መነሳት ጀመረ። ከዚህ ችግር ለመውጣት በኢህአዴግ ዘመን ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቀይሶ ሲሰራበት ቆይቷል። በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ መጠነኛ መሻሻሎች ቢታዩም ኢሕአዴግ ስልጣን እስኪለቅ ድረስ በሴፍትኔትና መሰል ስርዓቶች ድጋፍ የሚደረግለት የሕዝብ ቁጥር 13 ሚሊዮን ደርሶ ነበር።

በዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የግብርናው ዘርፍ ነው። በተለይም የኩታ ገጠም የአስተራረስ ስርዓትን በማላመድ የተበጣጠሱ መሬቶች በቅንጅት እንዲታረሱ ተደርጓል። በዚህም አጥጋቢ ውጤት ተገኝቷል።

ቀደም ሲል በብጣሽ መሬት ላይ በተናጠል ሲዳክር የነበረው አርሶ አደር ከአዋሳኝ መሬቶች ጋር በቅንጅት እና በትብብር ወደሚያመርትበት ስርዓት ገብቷል። ትራክተር እና ውሃ መሳቢያ ሞተር የመሳሰሉ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን በጋራ በመጠቀም አርሶ አደሩ ከባህላዊ አስተራረስ ዘዴ እንዲላቀቅ በመደረጉ እንደሀገርም ለውጦች መጡ።

ለአብነትም ጤፍ በርካታ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ የሚመገበው እና አብዛኛውን የእርሻ መሬት የሚሸፍን ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት ይሄ ነው የሚባል የምርት ዕድገት ሳያሳይ ቆይቷል። የለውጡ መንግስት እውን እስከ ሆነበት ጊዜ ድረስ በአጠቃላይ የነበረው ዓመታዊ ምርት ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ብዙም የዘለለ አልነበረም። ባለፉት አምስት ዓመታት ጤፍን በኩታ ገጠም ማረስ በመቻሉ ምርቱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዓመታዊ ምርቱ 639 ሚሊዮን ኩንታል ሊደርስ ችሏል። በቅርብ ዓመታት ውስጥም 1 ቢሊዮን ኩንታል ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ከጤፍ ባሻገር ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በአዲስ የልማት ጎዳና እንድትራመድ ካደረጓት የግብርና እንቅስቃሴ አንዱ የስንዴ ልማት ነው። ቀደም ሲል በጥቂት መጠን፤ በተወሰኑ አካባቢዎች፤ በክረምት ብቻ ይመረት የነበረውን የስንዴ ልማት ወደ በጋም በማሸጋገር የስንዴ ምርትን ከራስ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያም የማቅረብ አቅም ላይ ተደርሷል።

የስንዴ ምርት ሽፋን በ2014/15 ዓ.ም የምርት ዘመን ወደ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማሳደግ የተቻለ ሲሆን በሄክታር ሁለት ቶን ይገኝ የነበረውን የስንዴ ምርትም ወደ አራት ቶን ማሳደግ ተችሏል።

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በ2016 ምርት ዘመን ወደ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 117 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማምረት እየተሠራ ነው። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ቀዳሚ ስንዴ አምራች ለመሆን በቅታለች። በ2015 ብቻ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ መቅረቡ የዚሁ ስኬት አንዱ ማሳያ ነው።

ስንዴ በዓለማችን ላይ በድሃም ሆነ በሃብታም ሀገራት እጅግ ተፈላጊ የሆነ ሰብል ሲሆን ከምግብነት ባሻገርም ለአገራት ሰፊ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት በኩልም ሚናው ላቅ ያለ ነው :: ይህንን ተመርኩዞም በስንዴ ምርት ውጤታማ የሆነ ሀገር ከተረጂነት ነጻ የሆነ በምግብ እህል ራሱን የቻለ ስለሚሆንም ነጻነቱ እንዲረጋገጥ አስተማማኝ የገንዘብ ምንጭ እንዲፈጥር ያደርጋል። ለዚህም ይመስላል በርካታ ሀገራት ስንዴን ከምግብም በላይ የሆነ ግምት የሚሠጡት።

ኢትዮጵያ ለዘመናት ያህል ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ብትሆንም በምግብ ሰብል እራሷን ባለመቻሏ ነጻነቷን በሚገባ ሳታጣጥም ኖራለች። በአድዋ የተገኘው ድል በቅኝ ገዢዎች የፈረጠመ ኢኮኖሚ ሲጠመዘዝ ኖሯል። የኢትዮጵያ ኩራትና ድል በስንዴ ልመና ኮስሶ በዓለም መድረኮች ሁሉ ለምናቀርበው ጥያቄና ለምናሰማው ድምጽ ‹‹መጀመሪያ ሆዳችሁን ሙሉ›› የሚል ምላሽን ስናገኝ ኖረናል።

ዛሬ ግን የአድዋ ድል በተገቢው ቦታው ላይ እንዲነግስ የሚያስችል አኩሪ ታሪክ መጻፍ የምንችልበት ደረጃ ላይ የደረስን ይመስላል። ኢትዮጵያ ዳግም ነጻነቷን ልታውጅ፣ በስንዴ ምርት ራሷን ችላ ወደውጭ ገበያ ልትልክ፤ ከስንዴ ለማኝነት ወደ ስንዴ ላኪነት ልትሸጋገር ዳር ዳር እያለች ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ስንዴ ሸማች ከሆኑ ሀገራት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የምትታወቅ ስትሆን በየዓመቱም እስከ 107 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በማስገባት አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ታወጣለች። ሆኖም ባለፉት አራት ዓመታት መንግስት ለስንዴ ምርት በሰጠው ትኩረትም ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ማስገባት አቁማለች። ይህ ጥረቷም በዓለም ላይ ስንዴ በማምረት ተጠቃሽ ከሆኑ 18 ሀገራት ተርታ ያሰልፋታል።

ኢትዮጵያ ከስንዴ ተቀባይነት ወደ ስንዴ ላኪነት እራሷን በመለወጥም ታሪክ ሰርታለች፤ ለቀጠናው ሀገራትም ኩራትና ተስፋ ሰርቶ የማሰራት ተምሳሌትም ሆናለች። እንደ ስንዴው ሁሉ ለሩዝ ምርት ትኩረት በመስጠት ከሀገራዊ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ለመላክ በትኩረት በመስራት ላይ ትገኛለች። በተለይም ሀገሪቱ ለሩዝ ምርት ተስማሚ የሆነ የአየር ጸባይና ምቹ መሬት ያላት መሆኑ ያቀደችውን ወደ ተግባር ለመለወጥ እንደማያዳግታት የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።

ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተውም በኢትዮጵያ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር በሩዝ መልማት የሚችል መሬት ቢኖርም፣ በየዓመቱ ከ200 ሺህ ቶን በላይ ሩዝ ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት በየዓመቱ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ታደርጋለች።

ሆኖም በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ስርዓት መተግበር ከጀመረ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግስት ፊቱን ወደ ሩዝ ምርት በማዞር በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል። ከሩዝ አኳያ አምና ከስምንት ሚሊዮን ኩንታል ያልበለጠ ነበር፤ የተመረተው ዘንድሮ በዘጠኝ ወራት ብቻ 38 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት ተችሏል።

በተለይ በአማራ ክልል (ፎገራ)፣ በጅማ እንዲሁም በሶማሌ ክልል እየተከናወነ ያለው የሩዝ ምርት ኢትዮጵያን ከሩዝ ተቀባይ ሀገርነት ወደ ላኪነት የሚያሸጋግራት ነው።

እነዚህ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ኢትዮጵያ በአጭር ግዜ ውስጥ ከተረጂነት ተላቃ እራሷን በምግብ እንደምትችል አመላካቾች ናቸው። መንግስት ‹‹ተረጂነት ይብቃ››በሚል መርህ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ከተመጽዋችነት ለማላቀቅ አዲስ ዕቅድ ይዞ መጥቷል።

በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እስከ 250 ሺ ሄክታር በማረስ ኢትዮጵያ በቂ እህል ለማምረትና ከእርዳታ ተቀባይነት ለመላቀቅ አቅዳለች። ለዚህ ደግሞ አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከእርዳታ እሳቤ እራሱን ማውጣትና እራስን በምግብ ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ሊያግዝ ይገባል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You