አዲስ ዘመን ድሮ

ከትላንቱ ለዛሬ፤ በአዲስ ዘመን ድሮ ከወጡ ልዩ ልዩ ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹን በመምረጥ አቅርበንላችኋል። በሀገራችን ውስጥ የጥንታዊ ታሪክ ከመገኘቱ ጋር በተያያዘ በወቅቱ የነበረው ጭምጭምታ፣ ተቆጣጣሪ በመምሰል የሚያጭበረብረው ሰው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳዩ የጤና ባለሙያዎችን እያከራከረ የነበረን አንድ ጉዳይ ልናስታውስ ነው። እንዲሁ ደግሞ “አዲሱ ትውልድ ለምን ቶሎ ይገረጅፋል?” ምርምር ባዘለው ጥያቄ ከአዲስ ዘመን ሌላኛውን ገጽ እናስታውስበታለን።

የጥንታዊ ታሪክ ቦታ መገኘት

ጭምጭምታ

በአሩሲ ጠ/ግዛት፣ በጭላሎ አውራጃ፣ በጢዮ ወረዳ በዱግዳ ም/ጠቅላይ ግዛት ባላምባራስ ዓምደ ቡታ ባላባትነት ልዩ ስሙ ቲሮ ኞሮ በተባለው ጭው ያለ በረሃ አገር ይገኛል።

………….

በዚሁ ቀበሌ ገለቶ ጦሪ የተባለው ሰው በበረሃው ውስጥ ሲዘዋወር አንድ ከፍተኛ ቦታ ላይ ይበቅላል ተብሎ በማይታሰብበት የደጋ እንጨት ጥድና የመሳሰለውም ጫካ ሆኖ በቅሎ አገኘው። በዚሁ ነገር ተደንቆ ወደ ጥዱ ጫካ እገባለሁ ሲል በማይታሰብበት ቦታ የጠራ ውሀና በዚያው አጠገብ ፍልውሃ አገኘ። ከውሃውም አጠገብ አጽፍ(ቆዳ) የለበሰ ፀጉሩ እንደ ባሕታዊ በትከሻው ላይ የወረደ ለአራዊት ውሃ መጠጫ ቦታ ሲያዘጋጅ በደረስሁበት ጊዜ በቁጣ ቃል “ምን ልታደርግ መጣህ? ከመጣህበት ተመልሰህ ሒድ፤ ያየኸውንም ሁሉ እንዳትናገር የተናገርህ እንደሆነ እስከ ሕይወትህ ያሠጋሃል” ብሎ ተናገረ።

ከዚህም በቀር ሌሊቱን በሕልሜ በመዓልት (ቀን) እንደ ገሠጸኝ አደርሁ። በዚሁ ሳልወሰን ተግሣጹን ሳላከብር በማግሥቱ ቦታው እንዳይጠፋብኝ እንጨት እየሰበርሁ በመንገድ እየጣልሁ ተመልሼ ነበርና ያንን ምልክት በመከተል በዚያ ቦታ ስደርስ ከየት መጣ ሳልል ድምፁን በመስማት ብቻ በጥፊ ቢመታኝ አንድ ዓይኔ ታወረ። አንድ ዓይኑ እስካሁንም እንደታወረ ነው።

ዳግመኛ እንደዚሁ ቦባሳ በዳሳ የሚባለው ይህንኑ የጥንታዊ ታሪክ ቦታ በማግኘት በዚያ ቦታ በመገኘቱ ብርቱ ተግሣጽ አግኝቶት እንዳይናገርም መከልከሉንና ሊናገር ጥቂት ጊዜ ቀርቶታል ተብሎ መነገሩን ገልጿል።

ብዙዎች ሰዎች እንዲያሳዩኝ ስጠይቃቸው የበቃ መነኩሴ አብሮ ካልሔደ አይሆንም በማለት ለመሔድ አይፈቅዱም። ይህንንም ሁኔታ ያገኘሁት ከባላምባራስ ዓምደ ቡታ ልጅ ከአቶ ገና ዓምደ ነው። በዚሁ በተባለው ቦታ አካባቢ ኃይለኛ እንደ አውሎ ነፋስ የሚተፋ ዋሻ የሚገኝበት መሆኑን በማስረዳት ነግሮኛል።

ከዚህም ጋር በአጠገቡ የድንጋይ ከሰል በብዛት መገኘቱንና በመሐንዲስ ለመመርመር የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጿል።

(አዲስ ዘመን፣ ሰኔ 16 ቀን 1944 ዓ.ም)

ተቆጣጣሪ በመምሰል

ያጭበረበረው ተቀጣ

ደሴ፤ ኢዜአ፡- በደሴ ከተማ ውስጥ ምንም አይነት ሥልጣን ሳይኖረው የአሥር አለቃ ነኝ በማለት ከገጠር ወደ ከተማ የሚገባውንና የሚወጣውን እህል፣ ስኳርና ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጦች በመፈተሽ ሲያወናብድ የተገኘው ዓሊ መሐመድ በ3 ወር እስራት እንዲቀጣ የ04-01-01 ቀበሌ ማኅበር የፍርድ ሸንጎ ከትናንት በስቲያ ወስኖበታል።

በተከሳሹ ላይ የእስራት ቅጣት ሊወሰንበት የቻለው ባልተሰጠው ሥልጣን በመንገድ ላይ እየጠበቀ ስኳርና ሸቀጥ ጭነው ወደ ገጠር የሚወጡትንና እህል ጭነው ወደ ከተማ የሚገቡትን መኪናዎች እያስቆመ በመፈተሽ የተመቸውን ጥቅም በመቀበል ሲለቅ ያልተመቸውን ደግሞ ወደ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ በማቅረብ አወናብዶ ለማስቀጣት ሞክሮ እንደነበር በማረጋገጡ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፣ የካቲት 19 ቀን 1969 ዓ.ም)

ጉዳዩ የጤና ባለሙያዎችን

እያከራከረ ነው

ጫት አነቃቂ ከሆኑት ከሻይ፣ ከቡናና ከአልኮል እንጂ ከአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ጋራ አይመደብም ሲሉ በመስኩ ጥናት ያደረጉ ምሑር አስታወቁ። አንድ የጤና ጥበቃ ኤክስፐርት ደግሞ ጫት ከአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች እንደሚመደብ ገለጹ።

ዶ/ር መኮንን ሐጎስ፣ በመመኮ የተባለው የግል ድርጅት አማካሪ ሰሞኑን ለጋዜጣዊ ሪፖርተር በሰጡት መግለጫ ጫትን ጨምሮ በአንድ ሺ አምስት መቶ ዕፅዋት ላይ ጥናት ሲያደርጉ መቆየታቸውንና በጥናታቸውም ጫት ከአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ሊመደብ እንደማይቻል ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

ማንኛውም ነገር ከመጠን በላይ ከተወሰደ ጎጂነት እንዳለው የገለጹት ዶ/ር መኮንን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች መቆጣጠሪያ፣ መከላከያ ቡድን ከፍተኛ ኤክስፐርት የሆኑት አቶ አብርሃም ገብረ ጊዮርጊስ ጫትን ከካናቢስና ኮኬይን ጋር ይመደባል በማለት ለመገናኛ ብዙኃን በቅርቡ የሰጡት መግለጫ የተሳሳተ ነው ብለዋል። ጫትን ከአደንዛዥ ዕፆች መመደብም ፍጹም ኢ-ሳይንሳዊ መሆኑንም አስምረውበታል፡፡

(አዲስ ዘመን፣ ታኅሣሥ 29 ቀን 1990 ዓ/ም)

አዲሱ ትውልድ ለምን

ቶሎ ይገረጅፋል

“ለተሟላ ጤንነት ለእድሜ ብልፅግና የተመጣጠነ ምግብ ተመገቡ” ይለን ነበር እስከቅርብ ጊዜ ሳይንስ አሁን ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሊሆን ምንም አልቀረውም። ከወላጆቹ ይልቅ እንደ ነገሩም ቢሆን የሚመገበውን ምግብ የተመጣጠነ ለማድረግ የሚጥረው አዲሱ ትውልድ “ፋፋ ጀነሬሽን” ለእርጅና ሲጣደፍ ልብ ሳይሉ አልቀሩም። አባት በ30ኛው የእድሜ ዘመኑ የወለደው ልጁ ገርጅፎ የአባቱ የረዥም ጊዜ ጓደኛ መስሎ ሲታይ የትላንትዋ ማሚቱም ገርጅፋ አምስት የወለዱ እናትዋን ልትመስል መከጀልዋን ሲታዘቡ “ዋ እቴ የዛሬ ዘመን ልጆች ቶሎ ይወድቃሉ (ያረጃሉ)” ሲባል መሠማቱ የተዘወተረ ሆኗል፡፡

……………………………..

ለረዥም ጊዜ በእንስሳት ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት “አይጦችም ሆኑ ሌሎች እንስሳት ዝቅተኛ የኃይል መጠን ያላቸውን ምግቦች ሲመገቡ ረዥም ዕድሜ ይኖራሉ። ጤነኛ ይሆናሉ”

(አዲስ ዘመን፣ ኅዳር 20 ቀን 1992 .)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You