
ወደ ትናንቱ የአዲስ ዘመን መንገድ ስንመለስ ብዙ የኋላ ትውስታዎች ይኖሩናል። ዓለም አቀፍ፣ አሕጉራዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን ሁሉ ከማኅደሩ መለስ ብሎ ያስቃኘናል። “አቧራ አዋዜ አይደለም” ያለው አዣንስ፤ “መመሳሰል ይገባዋል” ሲል ከአንደኛው ጠቅላይ ግዛት ሁለቱንም ያካፍላል። ስለ 38ቱ ሠርጎ ጎቦች እና ሁለቱ ወንዶች ልጆች እያስታወስን ከወደ ኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት መንደር ስንዘልቅ ደግሞ፤ “ግብፅ ለሶማሊያ ዋና የጦር አቀባይ ሆናለች” የሚሉትን እናገኛለን።
አቧራ አዋዜ አይደለም
በሲዳማ ጠ/ግዛት ዋና ከተማ በሆነው ይርጋለም ከተማ ትልቁን መንገድ በመከተል አልፎ አልፎ በሚገኙት ሰፈሮች ብዙዎች የሉካንዳ ሥጋ የተሰቀለባቸውና ፉርኖ ይህንንም የመሳሰሉት ምግቦች የተደረደረባቸው ቤቶች ይገኛሉ። ሥጋው የሚገኝበት ብዙ ቦታ በረንዳ ስለሆነ ማናቸውም ተንቀሳቃሽና ይልቁንም የማያቋረጠው የመኪና ኃይል ከመንገዱ ላይ የሚነሳው አቧራ በሥጋና በማናቸውም ምግብ ላይ ሲሰፍርበት ይታያል።
ለማስረጃ ያህል በመንገዱ ዳር የሚገኘውን የቡና የሌላውንም ቅጠል የተመለከትን እንደሆነ በአንዱ ቅጠል ላይ ብቻ አንድ ጥርኝ የሚሞላ አቧራ ስለምናገኝ በየቀኑ በያንዳንዱ ብልት ሥጋ ላይ ተደባልቆ ወደ ሆድ የገባውን አቧራ ለመገመት እንችላለን።
ስለዚህ ሥጋና ፉርኖ ይህንንም የመሳሰለ ምግብ የሚያሰናዱ ነጋዴዎች ለዚሁ አገልግሎት በዘመናዊ ዕቅድ በተሰናዳው መስታወት ውስጥ ማኖር ይገባቸዋል። ይህም ባይቻል አቧራ ወደሌለበት ሁለተኛው መንገድ እንዲዛወሩ ማድረግ ስለሚገባ፤ ሥራው የሚመለከተው ባለሥልጣን ያስብበት ዘንድ ሳስታውስ በትሕትና ነው።
መመሳሰል ይገባዋል
በዚሁ ከተማ የሚገኘው የጠቅላይ ግዛቱ በጅሮንድ ጽ/ቤት በሦስት ቦታ ተከፋፍሎ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ ቤቱም በጠላት ጊዜ የተሠራ አሁን መፍረስ የጀመረ ነው። ስለ የውስጥ ዕቃውም አጠባበቅ ከቤቱ ይልቅ ዘበኞቹንና ካዝናውን ማመን ግድ ሳይሆን አይቀርም።
ይኸው ሆኖ ለሥራው የተመጠነ ስፋት ያለው አይደለም። በአካባቢው የሚገኙት ቢሮዎች በአማረና በጥሩ ሕንፃ የተሠሩ ሲሆኑ፤ የተጠቀሰው መሥሪያ ቤት እርጅና የእነሱን ውበት ግርማ አሳንሶታል። ስለዚህ ጓደኞቹን እንዲመስል የክፍሉ ባለሥልጣን ይተጋበት ዘንድ ማሳሰብ የጋዜጣው ፋንታ ነው።
የሲዳማ ጠ/ግዛት አዣንስ
(አዲስ ዘመን የካቲት 20 ቀን 1951ዓ.ም)
ሁለት ወንዶች ልጆች
በደብረ ታቦር ከተማ ዙሪያ ቃናት ማርያም ከተባለው ሀገር የአቶ መኮንን ካሣ ባለቤት ያልጋነሽ አድማሱ የተባለችው፤ ጥር 22 ቀን 1951 ዓ.ም ከሌሊቱ 8 ሰዓት ሲሆን አንድ ወንድ ልጅ ከወለደች በኋላ 10 ቀን ቆይታ የካቲት 2 ቀን 1951 ዓ.ም ከጠዋቱ 1 ሰዓት ሲሆን አንድ ወንድ ልጅ ደግማ መውለዷንና ሁለቱም ልጆች እስካሁን በሕይወት መኖራቸውን የነዚሁ ልጆች አባት አቶ መኮንን ካሣ አስታውቀውናል።
የደብረ ታቦር ከተማ ዙሪያ ምክትል ገዥ ባላምባራስ ኃይሌ ታምራት በቁጥር 100/1951 የካቲት 10 ቀን በተጻፈ ደብዳቤ አረጋግጠውልናል። እኚህ የምክትል ወረዳ ገዥ እንደዚህ ያለው ሁኔታ በጋዜጣ እንዲገለጥ በቶሎ ለአውራጃው ግዛት አዣንስ ጽ/ቤት በማስተላለፋቸው እናመሰግናለን።
ሌላዎችም ምክትል ገዥዎች የርሳቸውን አርዓያ ተከትለው ይህን የመሰለ ጉዳይ ሲያጋጥማቸው በፍጥነት የሚያስታውቁን ቢሆን ከፍ ያለ ምስጋና የሚያገኙበት መሆኑን እንገልጻለን።
የደብረ ታቦር አውራጃ አዣንስ
( አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 1951ዓ.ም)
ግብፅ ለሶማሊያ ዋና የጦር አቀባይ ሆናለች
ዋሽንግተን (ከዜና ወኪሎች)፡- በርከት ያሉ የዓረብ አገሮች በተለይ ግብፅ ለሶማሊያ የጦር መሣሪያዎችን በማቀበል ረገድ ዋነኛይቱ እንደሆነች ውስጥ አዋቂ ምንጮች መግለጣቸው ከዋሽንግተን የደረሰው ዜና ያስረዳል።
ሶማሊያ ከእነዚህ ሀገሮች የጦር መሣሪያ ለማግኘት በመቻሏ ከሌሎች የውጪ ኃያላን መንግሥታት የማግኘቱን አጣዳፊነት የቀነሰላት መሆኑን የዜና ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሃያ አንድ የዓረብ ሊግ አባል ሀገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት ካይሮ ከተማ ስብሰባ እንደሚያደርጉና በዚህም ስብሰባቸው በመካከለኛው ምሥራቅና በቀይ ባሕር አካባቢ የተቀነባበረ የዓረቦች እስትራቴጂ ለማውጣት እንደሚነጋገሩ በካይሮ የተላለፈው ዜና ገልጧል።
“በቀይ ባሕር አካባቢ ፀጥታን ለማስከበር” በሚል ሰበብ የዓረብ ሀገሮች ስለሚያደርጉት ጥረት ስብሰባው ከሚነጋገርባቸው ዋና ነጥቦች አንዱ እንደሚሆን የውስጥ አዋቂ ምንጮች መግለጣቸውን ዜናው ጨምሮ ገልጧል።
ቀደም ሲል በዚህ ዓመት በቀይ ባሕር ጠረፍ አካባቢ የሚገኙ ዓረብ ሀገሮች መሪዎች በእነሱ አባባል “ስለ ቀይ ባሕር ሰላም” ለመነጋገር በሱዳንና በሰሜን የመን ስብሰባ አድርገው እንደነበር ይታወሳል።
የዓረብ ሀገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በማኅበሩ ምክር ቤት ትእዛዝ የሚንቀሳቀስ ስድስት ሺህ ወታደሮች የሚገኙበት ጦር እንዲቋቋም እንደሚስማሙ የዓረብ ሊግ ዋና ጸሐፊ ተስፋ ማድረጉን ለሪፖርተሮች መግለጡ ታውቋል።
ሌሎች የስብሰባው መወያያ አርዕስቶች ለዓረብ ሊግ አባልነት በጅቡቲና በኮሞሮስ ደሴቶች የቀረቡት ማመልከቻዎች እንደሚሆኑና ስብሰባው ከሁለት እስከ ሦስት ቀን እንደሚቆይ ዜናው ጨምሮ ገልጧል።
(አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 ቀን 1969 ዓ.ም)
38 ሠርጎ ገቦች ተደመሰሱ
-በርከት ያሉ ቆስለው ተማረኩ
ሐረር፤(ኢ.ዜ.አ)፡- በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በወበራ አውራጃ በተለያዩ ሥፍራዎች ውስጥ ተሽለኩልከው ከገቡት ሠርጎ ገብ ወንበዴዎች መካከል 38 ሲደመሰሱ፤ ሌሎች በርከት ያሉ ወንበዴዎች ደግሞ ቆስለው መማረካቸው ተገለጠ።
ከእነዚህ መካከል ስምንቱ ወንበዴዎች የተገደሉት በደደር ወረዳ በሰቃ ም/ወረዳ ልዩ ስሙ ራሚስ በተባለው ሸለቆ ውስጥ ሲሆን፤ የቀሩት 30ዎቹ ደግሞ የተደመሰሱት በመልካበሎ ወረዳ ልዩ ስሙ ሸዋ በር በተባለው ሥፍራ መሆኑን ታውቋል።
በእነዚህ ሥፍራዎች ውስጥ በተለያዩ ቀናት ለ3ኛ ጊዜ አሰሳ አድርጎ ይህን ከፍተኛ ውጤት ያገኘው ከመለዮ ለባሹ ጋር የተባበረው የአውራጃው ሕዝባዊ ሠራዊት መሆኑን ተገልጧል።
(አዲስ ዘመን ሰኔ 3 ቀን 1969 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም