
ዛሬ ላይ ሆነን የኢትዮጵያን ትናንት ማወቅ ከፈለግን የትም መሄድ አይጠበቅብንም፣ ምስሏ አዲስ ዘመን ላይ እናገኘዋለን፡፡ ረሃብና ጠኔ፣ ችግርና እጅ ማየት ሳይሆን እጅ ነስተው ከእጇ ላይ የጎረሱ ሀገራት ብዙ ነበሩ፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ለእንግሊዝ ርዳታ ሰጥታ ነበር ቢባል ማናችን እናምናለን…አዲስ ዘመን ግን ከነደብዳቤው አስረግጦ ያስታውሰናል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ቤቶች በሙሉ አንድ ዓይነት ትዕዛዝ፣ አንድ ዓይነት ቀለም እንዲቀቡ ተወስኗል፡፡ 250 ዓመታት ዕድሜ የነበረው መስቀል ከሀገር ሊወጣ ሲል… እንዲሁም የሥራ ፈቶቹን ጉዳይ የሚያጠና ኮሚቴም ተቋቁሟልና ሌሎች ወንጀል ነክ የጋዜጣውን ዘገባዎችንም ለዛሬ እናስታውስ።
ኢትዮጵያ እንግሊዝን ረዳች
…
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በክረምቱ ኃይለኛነት ምክንያት ጉዳት ለደረሰበት ሀገር የገንዘብ ርዳታ ልከዋል። ይህም ርዳታ በሌጋሲዮናችን በኩል ሲላክ ቀጥሎ ያለው ደብዳቤ አብሮ ተልኳል፡፡
ለሎርድ ሜዮርክ ናሽናል ዲስትሪክት ፈንድ ለንደን
…
“ምንም እንኳን እኛም ራሳችን በሕዝባችን ላይ ያለአግባብ የደረሰበትን ጉዳት በማቃለል ሥራችን ላይ ብንሆንም ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቀው ኃይለኛና ጨካኝ በሆነው ክረምት ሁልጊዜ በምናስባት በለምለሟ ውብ በሆነች ሀገርዎ ላይ ለደረሰው ጥፋት መጠነኛ የገንዘብ ርዳታ መጠየቅዎን ስለሰማን የገንዘቡ ቁጥር ምንም ከፍ ያለ ባይሆን የኛንና የሕዝባችንን ርዳታ ለመግለጽ ያህል አንድ ሺህ ፓውንድ በሌጋሲዮናችን በኩል ልከንልዎታል፡፡”
(አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 1940ዓ.ም)
…
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ቤቶች ተመሳሳይ ቀለም እንዲቀቡ ትዕዛዝ ተላለፈ
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድና የሌላም ዓይነት ተግባር ማከናወኛ መደብሮች ከዚህ ወር ጀምሮ ለአካባቢው የሚስማማ ቀለም እንዲቀቡ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ክፍሎች ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። ይህን ማሳሰቢያ የሰጡት ክቡር ሚኒስትር ኃይለ ጊዮርጊስ ወርቅነህ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ናቸው።
የሚቀቡትም ቀለም አልባሌ ሳይሆን በዓይነቱና በጥራቱ የተሻለ መሆን አለበት። የቀለሙንም ዓይነት በየክፍሉ የሚገኙ ማዘጋጃ ቤቶች ሊሰጡ ይችላሉ ሲል የማዘጋጃ ቤቱ የማስታወቂያና የሕዝብ ኅብረት ማስፋፊያ ክፍል በተለይ ለአዲስ ዘመን ገልጧል።
የአዲስ አበባ ከተማ በአየርና በከፍተኛ ሥፍራ ሆነው ሲያዩት አብዛኛውን ቤት ጣራው የቆሸሸ፤ ቀለሙ የዛገ ሆኖ ይታያል። ስለዚህ እንደ ባለቤቱ መራጭነት አረንጓዴ ወይም በቀይ ቡናማ ቀለም መቀባት አለበት የሚል ማሳሰቢያ ክቡር ከንቲባው መልዕክት ውስጥ ይገኛል። ያረጀውም ጣሪያ እንዲለወጥ የክፍሉ ባለሥልጣኖች በጥብቅ ታዝዘዋል።
(አዲስ ዘመን፣ መስከረም 7 ቀን 1964 ዓ.ም)
የሥራ ፈቶችን ጉዳይ የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቋመ
የሥራ ፈቶችንና ትምህርታቸውን እያቋረጡ የሚወጡትን ልጆች የወደፊት ዕድል የሚወስን “ኦፖርቹኒቲዝ ኢንዱስትራላይዜሽን ሴንተር” የተባለ ድርጅት በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ማቋቋሙን የድርጅቱ መሪ ዶክተር ሊአን ኤች ሱሊቫን ትናንት አስታወቁ። የድርጅቱ ዋና ዓላማ የሰው ልጅ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበትንና ከጤናማው ህብረተሰብ የማይለይበትን መንገድ በመፈለግ የአዕምሮና የተግባር እውቀት ሰጥቶ ሥራ ለማስያዝ መሆኑ ተረጋግጧል።
የሥራ ፈቶችና ትምህርት የሚያቋርጡ ልጆች ማሰልጠኛና መደገፊያ ድርጅት ከአፍሪካ መሬት በናይጄሪያና በጋና ሥራ መጀመሩ ታውቋል።
…
( አዲስ ዘመን ግንቦት 25 ቀን 1963 ዓ.ም)
ሁለት መቶ ሃምሳ ዓመት ዕድሜ ያላቸው መስቀሎች ወደውጪ ሲወጡ ተያዙ
በግምት ሁለት መቶ ሃምሳ ዕድሜ ያላቸውን ሁለት የእንጨት መስቀሎች አንድ የውጪ አገር ዜጋ ገዝተው ወደ ሀገራቸው ለመውሰድ ሲዘጋጁ መስቀሎቹ ተይዘው እዚሁ እንዲቀሩ መድረጉን ከብሔራዊ ሙዚየም የተገኘው ዜና አስታወቀ፡፡
መስቀሎቹን እዚሁ ለማስቀረት የተቻለው ከአዲስ ከተማ በገንዘብ የገዟቸው አንድ የውጪ ሀገር ዜጋ ወደ ብሔራዊ ሙዚየም ሔደው ወደ ውጪ ለማውጣት የሚያስችል ፈቃድ በጠየቁበት ወቅት መሆኑ ተገልጧል።
….
የተጠቀሱት የውጪ ሀገር ተወላጅ መስቀሎቹን ከየት እንደገዙ ተጠይቀው የገዙበትን ቦታ አሳይተዋል። በዚሁ መሠረት የሸጠው ሰው እንዲያዝ ተደርጎ ወደ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱንና መስቀሎቹም በጣቢያው እንደሚገኙ ዜናው አስረድቷል፡፡
(አዲስ ዘመን ታህሳስ 13 ቀን 1964ዓ.ም)
…
በጋቢ እየሸፈኑ የሚቀሙ ለፍርድ ቀረቡ
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከመሃል አራዳ ተላላፊ መንገደኞችን በራሳቸው ጋቢ እያከናነቡ ገንዘብና ልዩ ልዩ ዕቃዎች የሚቀሙት በፖሊስ ተይዘው ለፍርድ ቀረቡ፡፡
ተከሳሾቹ ኃይሉ አሸናፊና ጌታቸው ኃይሌ የተባሉት ወንጀሉን ፈጽመዋል በመባል የተያዙት አዲስ አበባ ደጎል ዓደባባይ አጠገብ መሆኑን ከፍተኛው ፍርድ ቤት የቀረበባቸው የዓቃቤ ሕግ ክስ ይዘረዝራል። ወንጀሉ ተፈጽሞበታል የተባለው አቶ ጫኔ አበበ የተባለው ሰላማዊ ሰው ሲሆን፤ ተከሳሾቹ የግል ተበዳዩን በጋቢ አፍነው የነጠቁት ኅዳር 4 ቀን 1965ዓ.ም ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ መሆኑ ተገልጧል፡፡
…
(አዲስ ዘመን ህዳር 10 ቀን 1965ዓ.ም)
የሕዝብ ማመላለሻ ወይንስ የእንጨት?
የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች በተለይ የከተማዎቹ የሕዝብ እንጂ የእንጨት ማመላለሻ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይሁንና በአዲስ አበባ ከተማ በ6/12/1979 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ የሠሌዳ ቁጥር 12192አ-አ በሆነ በ30 ቁጥር አውቶብስ ሲሠራ በዋለ አውቶብስ ላይ፣ አውቶብስ ተራ ላይ እንጨት ተጭኖበት አንድ መኖሪያ ቤት ደርሶ ሲራገፍ አይቼ ሁኔታው ገርሞኛል፡፡ …ታዲያ የሕዝብ ወይንስ የእንጨት ማመላለሻ?
(አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 1980ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ.ም