8 ክፍሎች፣ 57 አንቀጾችና ዝርዝር ሕጎች ያሉት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ለተጨማሪ ምክክርና ውይይት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡና ለቋሚ ኮሚቴ መመራቱ ይታወሳል።
ከፍትህ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የረቂቅ አዋጁ ዋና ዓላማ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ወይንም ትርፍ ለማግኘት ተብሎ የሚፈፀም ወንጀልን ለመከላከልና ወንጀል አትራፊ መሆን የለበትም የሚል መርህ እውን ለማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ ሀብት ማስመለስን የተመለከተ ነው፡፡
በዚህ በኩል ተበታትነው የተቀመጡና ወጥነት የጎደላቸውን የሕግ ድንጋጌዎች ወጥና ሙሉዕ የሆነ የሕግ ማእቀፍ እንዲኖር ማስቻል ነው።
በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ሁሉን አቀፍ የሆነ የተሟላ ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ፣ አራተኛው ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን የተመለከተ እና ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን ለመወጣትና ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችንም ለማሟላት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግ ነው።
ረቂቅ አዋጁን ለማዘጋጀት ከአንድ ዓመት ጊዜ በላይ የወሰደና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ወይንም ተሞክሮ መሠረት ያደረገ ስለመሆኑና የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮና አግባብነት ያላቸው ሰነዶች መዳሰሱን፣ በጥናቱም ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን በማሳተፍ በተቻለ መጠን ቀደም ሲል የነበሩ የሕግ ክፍተቶችን ለመመለስ በሚያስችል መልኩ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን መረጃው አመልክቷል።
የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነትና ዋና ዓላማ እንዲሁም ይዘቱንና ረቂቅ ሕጉ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶክተር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም እንዳስረዱት፤ ረቂቅ አዋጁ ካካተታቸው አራት መሠረታዊ ዓላማዎች አንዱና ቀዳሚው ኢኮኖሚያዊ ወንጀሎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን አመላካች የሆኑ ነገሮች መኖራቸው ነው። ሰዎች የኢኮኖሚያዊ ጥቅም ወይንም ሀብት ለማግኘት ብለው የሚፈጽሟቸው ወንጀሎች እየተበራከቱና ውስብስብ የመሆናቸው ጉዳይም እየጨመረ መምጣቱ ነው፡፡
ሰዎች ከሕገወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ጥቅም እንዳያገኙ ማድረግ በአጠቃላይ እንዲህ ያሉ ወንጀሎችን ለመከላከል አዋጁን ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በወንጀል ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ጉዳያቸው ወይንም ነገራቸው በእስራት ብቻ የሚያልቅ ሳይሆን፣ በወንጀል ተግባር ያፈሩት ሀብትም የሚነጠቅ፣ የሚወሰድ፣ የሚወረስ ከሆነ ወደ ወንጀል ተግባር የመሰማራት እድላቸውም ሊቀንስ የሚችል ስለሆነ እንዲህ ያሉ የረቀቁና በተደራጀ ሁኔታ የሚፈጸሙ ኢኮኖሚያዊ ወንጀሎችን መከላከል አንዱ የረቂቅ አዋጁ ዓላማ ነው። ወንጀል አትራፊ መሆን የለበትም የሚለውን መርህ እውን ለማድረግ ጭምር የታሰበበት ነው፡፡
ሀብት ማስመለስ ላይ ከዚህ ቀደም የሕግ ድንጋጌዎች ቢኖሩም ተበታትነው የተቀመጡ በመሆናቸው አፈፃፀም ላይ ክፍተት ማምጣታቸውን ነው ሚኒስትሩ የጠቀሱት። እንደርሳቸው ገለጻ የሚመለስ ሀብት እንዴት ይለያል፣ ይመረመራል፣ ይጠናል፣ ይታገዳል፣ እንዴትስ ይያዛል፣ ንብረቱ በሚታገድበት ወቅት እንዴት ይተዳደራል የሚለውን የተመለከቱ ድንጋጌዎች አሁን ባሉ በተወሰኑ አዋጆች ላይ ተበታትነው ይገኛሉ። ለአብነትም ሙስና፣ ሽብርን፣ በሰዎች መነገድን ለመከላከል የሚሉት አዋጆች ይጠቀሳሉ። በነዚህ መሠል አዋጆች ተበታትነው የሚገኙ ድንጋጌዎች አሉ፡፡
የተበታተኑ አዋጆች መኖራቸው ለአፈፃፀም አስቸጋሪ ሆነው ከመገኘታቸው በተጨማሪ ከአንዱ አዋጅ ወደሌላኛው አዋጅ በሚኬድበት ወቅት አፈፃፀማቸው ወጥ አይደለም። በአንደኛው አዋጅ የተከሰሰ ሰው ንብረት የሚመለስበት ሂደትና በሌላኛው አዋጅ የተከሰሰ ሰው ንብረት የሚመለስበት አካሄድ ወጥነት የሚጎለው መሆኑ እንደ አንድ ክፍተት ታይቷል፡፡
ይሄ ደግሞ በአንዳንድ ወንጀሎች የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ወይንም ሀብት ማስመለስ የሚያስችል ሥርዓት እንዳይኖረን ያደርጋል። ሙሉዕ ወጥ የሆነ የሕግ ማእቀፍ እንዳይኖርም አድርጓል። ማንኛውንም በወንጀል የተገኘ ሀብትን የሚመለከት ሙሉዕ የሆነ የሕግ ማእቀፍ ያስፈልጋል የሚለው ሌላው የረቂቅ አዋጁ መነሻ ነው፡፡
ሶስተኛው የረቂቅ አዋጁ መነሻ፤ ሁሉን አቀፍ የሆነ የተሟላ ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን የተመለከተው የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ ነው። ሆኖም ይህ ሕግ ሙሉ ለሙሉ አዲስ ሆኖ የመጣ እንዳልሆነ መረዳት ይገባል። አንዳንዴ ሰፋ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጠበብ እያለ በተለያዩ አዋጆች ተካትቶ ሲፈፀም ነበር። ሆኖም የአፈፃፀም አድማሱ ላይ የተወሰነ ልዩነት እንዳለው መረዳት ይገባል ብለዋል።
እዚህ ላይ የሚስተዋለው ክፍተት ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን የተመለከተው አሁን በሥራ ላይ ያለው ድንጋጌ ተፈፃሚ የሚሆነው የሕዝባዊ ድርጅቶች ሠራተኞችና ኃላፊዎች ላይ እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞችና ኃላፊዎች ላይ ነው። ይሄ መሆኑ ያስከተለው ክፍተት አንድ ሰው አሁን ባለው የሕግ ድንጋጌ ምንጩና ምክንያቱ ያልታወቀ ሀብት ቢኖርህ ሕጉ በወንጀል ተጠያቂ ነህ ቢለውም ተጠርጣሪው በተለያየ ሕገወጥ መንገድ ያገኘውን ሀብት በሌላ ሰው ስም በማድረግ ከተጠያቂነት ወይንም ከሕጉ ተፈፃሚነት ማምለጥ ይችላል። የመንግሥት ሠራተኛ ወይንም ኃላፊ ሀብትህን አስመዝግብ ሲባል ካለው ሀብት ጥቂቱን ብቻ ነው የሚያስመዘግበው።
ይህ ነው የሚባል ሥራ የሌለው ግን ደግሞ በሚሊዮን ብር የሚያንቀሳቀስ ሀብት የፈጠረ ሰው በማኅበረሰብ ውስጥም ጥያቄ እያስነሳ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አጠራጣሪ የሆኑ ነገሮች ሲያጋጥሙ የሚጠየቅበት የሕግ ማእቀፍ የለም። ይሄ በሕግ ሥርዓት ውስጥ ትልቅ ክፍተት በመሆኑ ሙስናንም ሆነ ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል፣ በአጠቃላይ ሕጋዊነትን ለማሳደግ ክፍተቱንም ለመድፈን ሌላው የረቂቅ ሕጉ መነሻና ዓላማ ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡
አራተኛው ዓላማ ዓለም አቀፍ ግዴታዎቻችን ለመወጣትና ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ለማሟላት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ሀብት ማስመለስን በተመለከተ ሀገራት ምን አይነት የሕግ ማዕቀፍ ሊኖራቸው ይገባል የሚለውን የተመለከተ ድንጋጌ ያላቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መኖራቸውን ነው የገለጹት። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሙስናን ለመከላከል በብዙ ሀገራት የፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት መኖሩን አመልክተዋል፡፡
የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንጀሎችን የተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ ስምምነት መኖሩንና እኤአ ከ2000 በኋላ ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት ይሄን ጉዳይ የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ሰነዶች እየወጡ ስለመሆናቸው አስረድተዋል። ዓለም አቀፍ አደረጃጀቶችና ሌሎችም መሰል የሚጠቀሱ አደረጃጀቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በዓለም አቀፍ ስምምነትና አደረጃጀቶች በሚያወጧቸው ምክረሀሳቦች ሀገራት ንብረት ማስመለስን የተመለከተ ሕግ ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ ሕጎቹ ደግሞ ሊኖራቸው ስለሚገባው ይዘት የተቀመጡ መስፈርቶችና ግዴታዎች መኖራቸውን፣ ግዴታዎችና መስፈርቶቹም ሰነዶች ላይ ብቻ ተቀምጠው የሚቀሩ እንዳልሆኑ፣ ሀገራትም ግዴታዎቻቸውን በአግባቡ ስለመውጣታቸው ይገመገማል ሲሉም አስረድተዋል።
እንዲህ ያለ ሕግ በሌለ ቁጥርና አሁን ያሉት የሕግ ክፍተቶች ላይም ማሻሻያ ካልተደረገ እና እርምጃ ካልተወሰደ የኢኮኖሚ ወንጀሎች እየተበራከቱና እየተራቀቁ ይሄዳሉ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ወንጀሎቹ በገነገኑ ቁጥር አጠቃላይ ፖለቲካል ኢኮኖሚው የነጣቂ፣ የዘራፊና የቀማኛ የማድረግ እድሉ ሰፊ እንደሚሆን አመልክተዋል።
ሕግ አክብረው ለሚሰሩ የማይመች፣ ሕግ ለማያከብሩ ደግሞ እንደልባቸው ሀብት የሚያፈሩበት ኢኮኖሚ እንዳይሆን እንዲህ ያለ አዋጅ አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበታል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት ያመኑበት አካላት ቢኖሩም በተቃራኒው የተወሰኑ ወገኖችን ለመጉዳት ታስቦ የተዘጋጀ አዋጅ እንደሆነ በማንሳት የሚከራከሩ አልጠፉም። በዚህ መልኩ ረቂቅ አዋጁ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል።
አዋጁን መሠረት አድርጎ እየተነሱ ባሉ ጉዳዮችና ኢኮኖሚውን ለመጠበቅ አዋጁ ያለውን ፋይዳ ሀሳባቸውን እንዲሰጡን የጋበዝናቸው በኢፌዴሪ የሕገመንግሥት አጣሪ ጉባኤ ከፍተኛ የሕገመንግሥት ተመራማሪ አቶ ዓምደገብርኤል አድማሱ እንደሚከተለው አብራርተዋል።
እንደ አቶ ዓምደገብርኤል፤ አዋጁ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊም የተለያዩ ሀሳቦችን እያስተናገደ በባለሙያዎችም የተለያዩ ትችቶች እየቀረቡ እንደሆነ መከታተላቸውን ገልጸዋል። እርሳቸው እንዳሉት አዋጁ ገና በውይይት የሚዳብር በመሆኑ ያለቀለት ሕግ ተደርጎ መውሰድ የለበትም። በረቂቅ አዋጁ በስፋት በትችት የተነሱትም በውይይት የሚዳብሩበት እድል ይኖራል የሚል እምነት አላቸው።
የተወሰኑ አካላትን ለመጉዳት የወጣ አዋጅ ነው ብለውም አያምኑም። አንድ ወቅት ላይ የፀረሙስና አዋጅ ሲወጣ ለምን ታስቦ እንደወጣ ይታወቅ እንደነበር ከሚያስታውሱት ውጭ የሆነ አካል ለመጉዳት የወጣ አዋጅ በታሪክ እንደሌለ ነው የገለጹት።
ንብረት የማስመለስ ረቂቅ አዋጅ በጥቅሉ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከማስጠበቅ አንጻር ፋይዳው የጎላ ሆኖ እንዳገኙት የሚናገሩት አቶ ዓምደገብርኤል፤ በተለያየ መንገድ የሕዝብ ሀብትና ንብረት ተዘርፎ የተለያዩ ሰዎች ከብረውና በልጽገው የታየበት ጊዜ ያለፉት 30 እና 40 ዓመታት ተሞክሮን እንደማሳያ አንስተዋል። የሕዝብ ሀብት ዘርፈው የከበሩ ሰዎች ሀብቱን በምን መልኩ እንዳገኙ ወይንም እንዳካበቱ ተጠያቂ ሲሆኑም ሆነ፣ በሕገወጥ ያፈራችሁት ሀብት ነው ተብለውም ሲወሰድባቸው ወይንም ሲወረስ አለመታየቱን ነው ያስረዱት።
እንደ ሀገር ጉዳት እያስከተሉ ካሉ ወንጀሎች በሕገወጥ መንገድ የሚፈጠር ሀብት እንደሆነ ያነሱት አቶ ዓምደገብርኤል፤ ጉዳቱም የሀገር ኢኮኖሚ እድገት እንዲጎዳ፣ እንዲጓተት ብልሹ አሰራርም እንዲስፋፋ፣ ሕገወጦች እንዲከብሩ፣ በማድረግ ይገለጻል ብለዋል።
አሁን ላይ የተዘጋጀው ንብረት የማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ኢኮኖሚውን ይታደገዋል የሚል እምነት አላቸው። አዋጁ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማፋጠን፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ዜጎች ሀብትን በሕጋዊ መንገድ ለማፍራት እንዲነሳሱ፣ በአንድ ጀንበር ሚሊየነርና የሕንፃ ባለቤት የሚኮንበት ታአምራቶች እንዲቆሙ በማድረግ ሚናው ከፍተኛ እንደሚሆን ገልጸዋል።
አቶ ዓምደገብርኤል፤ እንደስጋት ያነሱት የሕግ ተፈፃሚነቱ ላይ ነው። የሕግ የበላይነት መላላት ሳይሆን፣ የሕግ መፈጸም ችግር መኖሩንና እስካሁን ባለው ሁኔታም ሕግ እንዲፈጸም ምቹ እንዳልነበር አውስተዋል። ይሄም በጠንካራ ተቋም ያለመመራት ክፍተት እንደሆነ ይገልጻሉ። ንብረት የማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ፀድቆ ሥራ ላይ ሲውል ሕጉ በአግባቡ ከተፈጸመ እንደሀገር ጥቅሙ የበዛ ሊሆን እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ አስፈላጊ መሆኑንና አሰራሩ በሌሎች ሀገሮችም መኖሩን ነው የገለጹት። በኢትዮጵያ ሙስና መንሰራፋቱን አመላካች የሆኑ ነገሮች መኖራቸውንና ቀድሞ መሰራት የነበረበት እንደነበር አመልክተዋል።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ‹‹አንድ ሰው አላግባብ በሆነ መንገድ ሀብት ሲያፈራ መንግሥት በተለያየ መንገድ መቆጣጠር አለበት›› ብለዋል። አሁንም ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አጋጥሟት፣ የኢኮኖሚ ጭንቀት በተፈጠረበት ወቅት በአንዳንድ ሱቆች ውስጥ የሚያዙት የእቃ አይነቶችና የመሸጫ ዋጋቸው ጥያቄ የሚፈጥሩ መሆናቸውንና ከጀርባ ያለው ነገር እየተፈተሸ እንዳልሆነ አንስተዋል።
ምሁሩ አክለውም ከዘረፋ ጋር በተያያዘ በተለይም የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ በኋላ ብዙ ነገሮች መሰማታቸውን ገልጸዋል። አሁንም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ ሰዎችን እያስፈራሩ ገንዘብ የሚቀበሉ ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ብዥታንም እየፈጠረ መሆኑንና በዚህ በኩልም ግንዛቤ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ከውጭ በሚመጣ ገንዘብ ላይ በተለያየ መንገድ የሚሰራጨው መረጃ በዋናነት ዲያስፖራውን እንዳስደነገጠው ጠቁመዋል። እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያው ገለጻ፤ እንዲህ አይነት ሕጎች ሲወጡ የሙያ ማኅበራት የተሳተፉበት ሕዝባዊ ውይይቶች ያስፈልጋሉ።
ከሙስናና ምዝበራ ጋር በተያያዘ አፍሪካ ሀገሮች ስማቸው በመልካም ነገር አይነሳም ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ የመንግሥት ኃላፊዎች ስልጣናቸውን ተጠቅመው ብዙ ነገር እንደሚያደርጉ በየጊዜው የሚነገር እንደሆነም ጠቁመዋል።
በሙስና ወንጀል ስማቸው ከፍ ብሎ ከሚነሱ ሀገራት ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬኒያ ለአብነት ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ሙስናን ለመከላከል ጥሩ ተሞክሮ ያላቸውን ሀገሮች ልምድ ለመቅሰም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሲንጋፖር መሄዳቸውን አስታውሰዋል።
ዓለም ውስጥ ሙስናን እየተዋጉ ያሉት ኢንቨስትጌቲቭ ሚዲያ (የምርመራ ጋዜጠኝነት) እና የሲቪክ ማኅበራት ናቸው። እንደ እድርና መሰል ማኅበራት በማኅበረሰብ ውስጥ ምን እየተፈፀመ እንደሆነ ያውቃሉ ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ኢትዮጵያ ውስጥም የሲቪክ ማህበራት ተደራጅተው ሙስናን ለመከላከል መስራት እንዳለባቸው፣ የምርመራ ጋዜጠኝነትም መጠናከር እንዳለበትና በነዚህ አካላት ትብብር ኢኮኖሚውን መታደግ እንደሚቻል ገልጸዋል። መንግሥትም ለነዚህ ተቋማት ከለላ በመስጠት ማበረታታት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
ሙስና የሕዝብን የእለት ተእለት ኑሮ የሚጎዳ እንደሆነ ግንዛቤ ተይዞ ካልተሰራ መንግሥትም በዚህ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ካልወሰደ ሕዝብ በምርጫ እንዳያሸነፍ ሊያደርገው እንደሚችልም ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገልጸዋል፡፡
በንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ላይ እንዲህ ሀሳባቸውን የሰጡት ባለሙያዎች በሕጉ ተፈጻሚነት ላይ ትኩረት እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም