በዩኒቨርሲቲዎች በሚሠሩ ጥናቶች ላይ አላስፈላጊ ድግግሞሽና ሀብት ብክነትን ማስቀረት ይገባል

አዲስ አበባ፡- በዩኒቨርሲቲዎች በሚሠሩ ጥናቶች ላይ የሚስተዋሉ አላስፈላጊ ድግግሞሽና ሀብት ብክነትን ማስቀረት እንደሚገባ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ገለጹ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አሥራት አፀደወይን (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዘርፎች የተለያዩ የጥናትና ምርምሮችን ይሠራል።

ብዙ ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩ ጥናትና ምርምሮች ተግባራዊነት ላይ ጥያቄ እንደሚነሳ የገለጹት አሥራት (ዶ/ር) ፤ ዩኒቨርሲቲው ይህንን ለመመለስ ሊታተሙና ተግባራዊ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ለሚታሰቡ ጥናትና ምርምሮች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት እየተሠሩ ያሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በዓለም አቀፍ ጆርናሎች እንዲታተሙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲዎቹ የሚሠሩ ጥናቶች ላይ ብዙ ክፍተት የሚታይ ቢሆንም ዋነኛው ችግር ግን እንደ ሀገር የሚሠሩ ጥናቶችን መሰብሰብና መረጃ መለዋወጥ አለመቻል መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም በአንድ ጉዳይ ላይ አላስፈላጊ ድግግሞሾችን በመፍጠር ለሀብት ብክነት እያጋለጠ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሯቸው ጥናቶች በአንድ ላይ የሚያስቀምጡበት መንገድ መፍጠር ላይ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አተኩረው ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ ጎንደር ዩኒቨርስቲ በአሁኑ ወቅት አተኩሮ ከሚሠራባቸው ዘርፎች አንዱ የአየር ንብረት ለውጥ ነው ያሉ ሲሆን በተለያዩ የትምህርት መርሐግብሮች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ቁርኝት ያላቸው ትምህርቶች እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን እንደ መዋቅር አዘጋጅቶ ማዕከል መክፈቱንና በዚህ ማዕከልም ሙሉ በሙሉ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዥ የሆኑ የጥናትና ምርምሮች እንዲሁም ችግሩን ሊያቃልሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ እንደሚሠራ አብራርተዋል።

ለአብነትም በዩኒቨርስቲው በጣና ሐይቅ ይስተዋል የነበረውን እንቦጭ አረምን ወደ ማዳበሪያነትና ለመብራትነት እንዲያገለግል የሚያስችል ቴክኖሎጂን መሥራቱን ጠቅሰዋል።

ሌላኛው ኢፕድ ያነጋገራቸው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኡባህ አደም (ዶ/ር) በበኩላቸው ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን የማኅበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

እንደ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሯቸው ጥናቶች የሚያስተዋውቁበትና የሚወያዩበት መንገድ አነስተኛ ነው ያሉ ሲሆን ይህም ተደጋጋሚ ጥናት እንዲሠራ ምክንያት እየሆነ ይገኛል ብለዋል።

ኡባህ (ዶ/ር)፤ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲም በአሁኑ ወቅት ወደ መሬት ቢወርዱ ለውጥ ያመጣሉ በሚላቸው እንደ ጎርፍ የመሰሉ የድሬዳዋ ችግሮች ላይ ያተኮሩ ጥናቶች እንዲሠሩ በበጀት ጭምር ቅድሚያ እየሰጠ እየሠራ ለከተማ አስተዳደሩ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን በዩኒቨርሲቲው የሚሠሩ የተለያዩ ጥናቶች ወደ መሬት ወርደው መፍትሔ እንዲያመጡ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር መረጃ የመለዋወጥና የመናበብ ችግር መኖሩን አንስተዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You