ለአጭር ርቀትና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ውጤታማነት ትኩረት ተሰጥቷል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሃዋሳ ከተማ መካሄድ ከጀመረ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡ በሁሉም የሩጫና የሜዳ ተግባራት ወጣት አትሌቶችን የሚያፎካክረው ውድድሩ ከክልሎች እና ክለቦች የተወጣጡ በርካታ አትሌቶችን በማሳተፍ ላይም ነው፡፡

ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከትላንት በስቲያ በደማቅ ሁኔታ የተጀመረ ሲሆን፤ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ተተኪ አትሌቶች የማጣሪያና የፍጻሜ ውድድራቸውን በማከናወን ላይ ናቸው። ሻምፒዮናው ተተኪ አትሌቶች እርስ በእርስ እንዲፎካከሩ፤ እንዲሁም ሀገርን መወከል የሚችሉበትን ሁኔታ የሚያመቻች ከመሆኑም ባለፈ ለአጭር ርቀትና የሜዳ ተግባራት አትሌቶች ትርጉሙ የተለየ ይሆናል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በእነዚህ የአትሌቲክስ ዘርፎች በአሕጉር አቀፍ ደረጃ ከተሳትፎ የዘለለ የውጤት ታሪክ የላትም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ፌዴሬሽኑ በሰጠው ትኩረት በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናም ጭምር በመሳተፍ የውጤት ፍንጭ ታይቶበታል። ይኸውም ወጣቶች በተነቃቃ መልኩ ውድድራቸውን እንዲያከናውኑ የሞራል ስንቅ እንደሆናቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠል ከአትሌቲክሱ ባለድርሻዎች ጋር ጠንክሮ በልዩ ሁኔታ እንደሚሠራ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባልተለመደ ሁኔታ የአጭር ርቀትና የሜዳ ተግባራት አትሌቶችን በስፋት አካታ የተሳተፈች ሲሆን፤ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴና ውጤት በማስመዝገብ ውድድሯን አጠናቃለች። ከፍተኛ በጀት ተመድቦ የአጭርና የሜዳ ተግባራት አትሌቶችን ያሳተፈው ትልቁ የአሕጉሪቱ መድረክ በዘርፉ ላሉ አትሌቶች ተስፋን የሰጠ ነው። በመሆኑም በትኩረት ከተሠራ ኢትዮጵያ በእነዚህ የአትሌቲክስ ዘርፎችም ውጤት የምታስመዘግብበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አመላክቷል።

ወጣቶች የሚሳተፉባቸው ይህንን መሰል ሻምፒዮናዎች ደግሞ ብዙም የውጪ የውድድር ዕድልን ለማያገኙት የአጭርና የሜዳ ተግባራት አትሌቶች ዕድሉን በማመቻቸት እና ራሳቸውን እንዲያሳዩ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። የሲዳማ ቡናው የዝላይ አሠልጣኝ ኦባንግ ኮድ ይሄንኑ የሚያጠናክር ሃሳቡን አንጸባርቋል።

ዘንድሮ በአጭርና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች የተሰጠው ትኩረት የተሻለ መሆኑንና ለአትሌቶቹ መነቃቃትን ፈጥሯል። በተለይ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ብዙ የአጭርና ሜዳ ተግባራት አትሌቶች ተሳትፎ ያሳዩት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነበር። አሠልጣኙ እንደ ልምድ ከወሰዳቸው ጉዳዮች መካከል የአመጋገብ እና የሥልጠና አሰጣጥ ላይ ብዙ ነገሮች መሻሻል ይኖርባቸዋል። በመሆኑም አሠልጣኞች የማነቃቂያ ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ በማድረግ በዘርፉ ውጤት እንዲመጣ ማድረግ ይገባል።

ከዚህ ቀደም በእነዚህ ውድድሮች የነበረው ተሳትፎ ጥሩ የነበረ ቢሆንም በመሐል ተቀዛቅዞ ዘንድሮ በተሰጠው ትኩረት ዳግም ጥሩ ተሳትፎን ማድረግ ተችሏል።

ጋና እና ካሜሮን በተደረጉት ውድድሮች በዝላይ፣ ውርወራና አጭር ርቀት ሩጫ የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ ሲሆን፤ የሥልጠና ሂደትና የአመጋገብ ሥርዓትን በማስተካከል ውጤታማ አትሌቶችን ማፍራት እንደሚቻል ያመላከተም ነው።

በአሕጉር አቀፉ ውድድር በርዝመት ዝላይ እና ከፍታ ዝላይ ላይ ተመዝግቦ የነበረው የኢትዮጵያ ክብረወሰን የተሻሻለ ሲሆን፤ በሃገር ውስጥ ግን ባለው የልምምድ ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ክብረወሰን ማሻሻል አስቸጋሪ ነበር። ከዓለምና ከአፍሪካ ጋር ያለው ልዩነት ጥቂት በመሆኑ ከዚህ በተሻለ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራ ከሆነ በአጭር ጊዜ በአጭርና ሜዳ ተግባራት ውድድሮች ውጤት ሊመዘገብ ይችላል። ለዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድር ዕድሎችን እንዲያሰፋና ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮችም ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚኖርባቸውም ጠቁሟል።

ለስፖርተኞቹ የሚያስፈልገው ድጋፍ በሙሉ የሚደረግ ከሆነም ውጤታማ በመሆን የማናጀሮችን ቀልብ መሳብ ይቻላል፡፡ በየክልሉ የውድድር እድሎችን በማስፋት ስፖርተኞች ወጥ በሆነ አቋም እንዲቀጥሉና ውጤታማ እንዲሆኑ ማበረታታትም ተገቢ ነው።

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ በበኩላቸው፤ በ23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርካታ የአጭርና የሜዳ ተግባራት አትሌቶች መሳተፋቸው የሞራል መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ አሠልጣኞችንም እያበረታታ በመሆኑ በቀጣይ ጠንክረው በመሥራት በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ ለመሆን በሚያስችል ሁኔታ ውድድራቸውን እያካሄዱ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ፌዴሬሽኑ አሠልጣኞችን ወደ ውጪ በመላክና ዓለም አቀፍ የዘርፉ ባለሙያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በመጋበዝ ሥልጠና እንዲወስዱ አድርጓል። ለክለቦችና ለክልሎች የሥልጠና ድጋፍን፣ ለፕሮጀክቶችና ማዕከላት የትጥቅ፣ የአሠልጣኞችን ደመወዝ እና የአትሌቶች የላብ መተኪያ ድጋፍንም ያደርጋል። ሁሉም የድርሻውን ወስዶ ጠንክሮ በመሥራትና ፌዴሬሽኑ የተለመደውን ድጋፍ በማስቀጠል በአጭርና የሜዳ ተግባራት ውጤት ለማምጣት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You