ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩና የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ባደጉት ሀገራት ትምህርት ቤት ገብተው ለመማር አይቸገሩም:: ክህሎታቸውን ለማዳበር የሚያስችሉ፣ ለእነርሱ ተብለው የተዘጋጁ ማዕከላት ከመኖራቸው ባሻገር በመደበኛው ሥርዓተ ትምህርትም ታቅፈው ለመማር የሚያስችላቸው ቅድመ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸዋል:: ከዚህ በተቃራኒ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ገና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚገኙ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩና የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች የሚማሩባቸውና ክህሎቶችን የሚያዳብሩባቸው ለእነርሱ ተብለው የተዘጋጁ ማዕከላት እምብዛም የሉም::
ያሉት ማዕከላት የተገነቡት ልጆቻቸው በዚሁ ችግር ምክንያት ተጠቂ በሆኑ ወላጆች አማካኝነት ነው:: ልጆቹ በነዚህ ማዕከላት የመግባት እድል ቢያጋጥማቸው እንኳን የመግባባት፣ የንግግር፣ ራስን የመቆጣጠርና ሌሎችንም ክህሎቶችንና እውቀቶችን ካገኙ በኋላ ወደ መደበኛው ትምህርት ለመቀላቀል ችግር ሲገጥማቸው ይታያል:: ይህ ችግር ደግሞ በአብዛኛው መደበኛ ትምህርት የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ልጆቹን ለመቀበል ፍቃደኛ ካለመሆን ይመነጫል። በዚህም ምክንያት በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን የኦቲዝምና የአዕምሮ እድገት ውስንነት መንከባከቢያ ማዕከላት ካቆዩ በኋላ ወደ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለማስገባት ሲቸገሩ ይስተዋላል::
መንግሥት የልዩ ፍላጎት አካቶ ትምህርትን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ ሰንበት ብሏል:: የመንግሥት ትምህርት ቤቶችም ይህን ፕሮግራም ተቀብለው ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ:: ይሁንና ይህ የልዩ ፍላጎት አካቶ ትምህርት በግል ትምህርት ቤቶች በኩል እምብዛም ሲሰጥ አይታይም:: ይሁን እንጂ፣ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ተቀብለው በማስተማር ለሌሎች ትምህርት ቤቶች አርዓያ ለመሆን በቅተዋል::
ወይዘሮ ማርታ ተሾመ ባምላክ ተስፋዬ የሚባል የሰባት ዓመት ልጅ አላቸው:: ባምላክን ወደ ትምህርት ቤት የላኩት የአራት ዓመት ልጅ ሳለ ነበር:: ነገር ግን የጤና ችግር እንዳለበት ያወቁት ዘግይተው ነው:: ሁሌም ትምህርት ቤት ይጠራሉ:: በራሱ መፀዳዳት እንደማይችልም ይነገራቸዋል:: ችግሩ እንዳለ ሆኖ ባምላክ ለስድስት ወራት በትምህርቱ ዘለቀ:: በኋላ ላይ ወይዘሮ ማርታ ትምህርቱን አቋርጠው ሐኪም ቤት ወስደውት ከኦቲዝም ጋር እንደሚኖር አረጋገጡ:: ከዛ በኋላ ልጃቸው ቴራፒ እንዲያገኝ በብዙ ለፍተዋል::
በትርፍ ጊዜ እቤት መጥቶ የሚረዳ ሰው ሲያገኙ ቀደም ሲል የማያወራው ልጃቸው አባባ .. እማማ ማለት ጀመረ:: ተረጋጋ፣ ኤ ቢ ሲ ዲ • • • በደምብ አወቀ:: ወይዘሮ ማርታ እንደገና ሌላ ትምህርት ቤት ባምላክን ለማስገባት ቢፈልጉም አንድም ትምህርት ቤት ሊቀበሏቸው አልቻሉም:: አንድ ዓመት የቴራፒ ማዕከል እንዲቆይ ካደረጉ በኋላ ልጃቸውን ተቀብሎ የሚያስተምር ትምህርት ቤት አገኙ:: ዛሬ ባምላክ ወደ አጋቶስ አካዳሚ ከመጣ በኋላ ምንም እንኳን በትምህርት አቀባበል በኩል ችግር የሌለበት ቢሆንም የባሕሪ መለዋወጥና ችግሮችን መቅረፍ ችሏል:: ትምህርቱ ላይም ይበልጥ በርትቷል:: በራሱ መፀዳዳት ችሏል:: ከተማሪዎች ጋርም ተግባብቶ መጫወትና መማር ይችላል::
የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን በመደበኛ ትምህርት አካቶ የማስተማሩ ሁኔታ በተለይ በግል ትምህርት ቤቶች እምብዛም እንደማይታይ የሚገልፁት ወይዘሮ ማርታ ኦቲዝምና የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ቁጥር እየጨመረ እንደመምጣቱ ትምህርት ቤቶች በራቸውን ክፍት አድርገው መቀበል አለባቸው ይላሉ:: እነዚህ ልጆች ሁሉንም ነገር ማግኘት ይገባቸዋልና ትምህርት ቤቶች ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ይበልጥ ትኩረት በመስጠት በመደበኛው ትምህርት ውጤታማ እንዲሆኑ ሊያግዟቸው እንደሚገቡም ይጠቁማሉ::
ወይዘሮ ሰርክአዲስ አየለ በአዲስ አበባ ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ነዋሪ ናቸው:: የአስራ አራት ዓመት ሴት ልጃቸው ከኦቲዝም ጋር ትኖራለች:: ከዚህ ቀደም ሌላ ቦታ ልጃቸውን ለማስተማር ሞክረው ብዙ ሳትቆይ ነው ያሰናበቷት:: ልጃቸው አጋቶስ አካዳሚ ከገባች በኋላ ተረጋግታለች:: አፏንም ፈታለች:: በትምህርቷም ጎብዛለች:: ዘንድሮ ኬጂ 3ን አጠናቃለች:: ይህን ለውጥ ማምጣት የቻለችው አካዳሚው ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ትኩረት ሰጥቶና ከሌሎች መደበኛ ተማሪዎች ጋር ቀላቅሎ በማስተማሩ ነው:: በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ ልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን መሠረት ያደረጉ ትምህርቶችን በመስጠቱም ነው ልጃቸው ለውጥ ልታመጣ የቻለችው::
አሁን የወይዘሮ ሰርክአዲስ ስጋት ልጃቸው ኬጂ 3 ካጠናቀቀች በኋላ በቀጣይ አንደኛ ክፍል የት ትምህርት ቤት እንደሚያስገቧት ነው:: ምክንያቱ ደግሞ አብዛኛዎቹ ከአንደኛ ደረጃ አንደኛ ክፍል በኋላ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ተቀብለው ስለማያስተምሩ ነው:: በዚህ አጋጣሚ ትምህርት ቤቶች ልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ተቀብለው እንዲያስተምሩ ይጠይቃሉ:: መንግሥትም የልዩ ፍላጎት ትምህርት በግል ትምህርት ቤቶችም ጭምር እንዲሰጥ ማድረግ እንዳለበት ይጠቁማሉ::
ወይዘሮ ሀድራ ሰይድ የአጋቶስ አካዳሚ ልዩ ፍላጎት ትምህርት አስተባባሪ ናቸው። እርሳቸውም ከኦቲዝም ጋር የሚኖር የአስራ አራት ዓመት ልጅ አላቸው:: ከዚህ ቀደም በነህሚያ የኦቲዝም ማዕከል ልጃቸውን አቆይተዋል:: በማዕከሉም ከኦቲዝም ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ወስደዋል:: ከዛ ማዕከል ከወጡ በኋላ ደግሞ ልጃቸውን በአጋቶስ አካዳሚ እያስተማሩና በኦቲዝም ዙሪያ ለመምህራን ሥልጠና እየሰጡና እያበቁ ልጃቸውን ሦስት ዓመት አስተምረው ለአንደኛ የክፍል ደረጃ አብቅተዋል::
እርሳቸው እንደሚሉት ትምህርት ቤቱ አስረኛ ዓመቱን ይዟል:: በሩን ክፍት አድርጎ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ተቀብሏል:: ከዚህ በተቃራኒ ግን ሌሎች ትምህርት ቤቶች ይህን አያደርጉም:: በዘንድሮ ዓመትም 29 የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ተቀብሎ አስተምሯል:: የንግግር ቴራፒ መምህርትም ቀጥሮ በሳምንት ሁለት ግዜ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች እንዲማሩ ተደርጓል:: ነህሚያ ኦቲዝም ማዕከልም ለመምህራን በኦቲዝም ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል:: በመደበኛነት ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ልጆችም ከልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ጋር አብረው በመዋላቸው የተለያዩ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ እገዛ አድርገዋል::
በዚህም ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር ተቀላቅለው እንዲማሩ የተደረጉት የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ሀሳባቸውን የመግለፅ፣ የማውራት፣ ጉዳት ሊደርስባቸው ሲል የመናገርና ሌሎችንም ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ አስችሏቸዋል:: ወላጆችም ከኦቲዝም ጋር በተያያዘ ግንዛቤው እንዲኖራቸው ተደርጓል:: በዚህም ሌሎች ወላጆች ይህን ሰምተው ልጆቻቸውን ወደ ትምሀርት ቤቱ እስከመላክ ደርሰዋል:: ይሁንና ልጆቹ በቀጣይ የአንደኛ ክፍል ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ትምህርት ቤቶች በራቸውን ክፍት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል:: ለዚህ ደግሞ መንግሥት አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም