ሀገራዊ መረጃዎች እንዳይጠፉ ተቋማት ለሰነድ አያያዝና አወጋገድ ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፡- ሀገራዊ መረጃዎችን የያዙ ሰነዶች በእርጅና ምክንያት እንዳይጠፉ ተቋማት ለሰነድ አያያዝና አወጋገድ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት ጠየቀ፡፡

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት ዋና ዳሬክተር አቶ ይኩኑአምላክ መዝገቡ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የተለያዩ ተቋማት ለሥራ የሚያመነጯቸው ሰነዶች ከጊዜ በኋላ ሀገራዊ መዛግብት በመሆናቸው ተቋማት ለሰነድ አያያዝና አወጋገድ ልዩ ትኩረት ሊሠጡ ይገባል፡፡

እንደ አቶ ይኩኑአምላክ ገለጻ፤ በርካታ ተቋማት የቦታ ጥበት አጋጥሞናል በሚል ምክንያት መዛግብቶችን በጆንያ እያከማቹና ከሕግ አግባብ ውጪ ጥቅም አይሰጥም በሚል እስከማቃጠል የደረሱ አሉ፡፡

የሰነዶችን አያያዝ በሚመለከት የወጡ ጥብቅ ሕጎች ቢኖሩም ከግንዛቤ ማነስና በሌሎች ምክንያቶች አስፈላጊ ሰነዶች እየጠፉ ናቸው ብለዋል፡፡

ተቋማት የሥራ አካባቢያቸውን ማስዋባቸው ጥሩ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በማስዋብ ሂደት ውስጥ ለመረጃ ሀብቶች ልዩ ጥንቃቄ ማድረግና በአግባቡ መጠበቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ሰነዶች የምርምር ሥራዎችን ለመሥራት ትልቅ ጥቅም እንዳላቸው ጠቅሰው ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የመጡ ሰነዶችን በአግባቡ የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ተቋማት ሰነድ አያያዝን በዘመናዊ መንገድ መሰነድ እንደሚገባቸው ገልጸው አገልግሎቱ ያገለገሉ ሰነዶች ከሥርዓት ውጪ እንዳይወገዱ ክትትል እያደረገ መሆኑን አቶ ይኩኑአምላክ አስረድተዋል።

በርካታ ሰነዶች እለታዊ ፋይዳ ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው ከነዚህ ውስጥ ወቅትን፣ ባሕልንና ትውፊትን የሚገልጹ አመላካች ሰነዶች ወደ መዛግብትነት ተቀይረው እንዲጠበቁ ይደረጋል ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ ከእንቅስቃሴ ውጪ የሆኑ ሰነዶችን በሕጋዊ መንገድ ለማስወገድ የሚያስችል ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንደሚሠራ አስረድ ተዋል፡፡

በቀጣይ ስለሰነዶች አወጋገድ ግንዛቤ የማስጨበጥ፤ ሕጉን በተጠናከረ መልኩ የማስፈጸም፣ የመረጃ ሀብቶች በአግባብ እንዲጠበቁ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ስለመዛግብትና ሰነዶች አወጋገድ የሕግ ማዕቀፍ ጥናት ያቀረቡት የሕግና የታሪክ ተመራማሪው አልማው ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ሰነዶችን ለማስወገድም ሆነ ለመጠበቅ ባሉበት ተቋም እስከ 25 ዓመት መቆየት ይኖርባቸዋል፤ ከዚያ በኋላ ግን ወደ አገልግሎቱ እንዲመጡ ተደርጎ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት የማስወገድና የመጠበቅ ሥራ ይሠራል፡፡

እንደ ሀገር መዝገብ ቤት ለሚመደብ ባለሙያ የተሳሳተ ግምት የመስጠት ልማድ መኖሩ ለሰነዶች መበላሽትና መጥፋት ምክንያት ሆኗል ያሉት አልማው (ዶ/ር) ለመሰል ድርጊቶች ተቋማት በተገቢው ትኩረት ካልሰጡ ትልቅ ጉዳት እንደሚያስከትል ተናግረዋል፡፡

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You