ዶሳይስ

“ዶሳይስ” ከደራሲና ገጣሚ ኩሪ አየለ ኃይሌ ከሰሞኑ ለአንባቢያን የቀረበ ምርጥ የመጽሐፍ ጦማር ነው። ከዚህ ቀደም የግጥም መድብሏን ጨምሮ ሁለት መጻሕፍትን ያበረከተችልን ደራሲዋ ለሦስተኛው በዶሳይስ መጥታለች።

የአሁኑ ዶሳይስ መጽሐፏ በአጫጭር ልቦለዶች ታሪክ ተሰባጥሮ የቀረበ ባለ ብዙ የሀሳብ ጅማት ነው። ማኅበራዊ ማኅብረሰብ፣ ሀገራዊ ሀገርና ሕዝብን ጨብጦ የያዘ የንቃት መንገድና መንገደኛም ነው። በማኅበረሰባችን ውስጥ ያሉትን ህጸጾች በተለያዩ መንገዶች እየነቀሰ የመመለሻውን ፍኖት ያንጸባርቃል። ምናልባትም የደራሲዋን ውስጣዊ ስብዕናና የአመለካከት ጮራዎቿን የሚፈነጥቅም ዓይነት ነው። በቅርቧ ሆኖ የሚያውቃት አንድ አንባቢ ምናልባትም ከእርሷ ጋር እያወጋ ያለ ያህል መስሎ ሊሰማው ይችላል። የምረቃ ስነ ስርዓቱ ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 በብሔራዊ የቲያትር አዳራሽ ውስጥ በጉምቱ የጥበብ ባለሙያዎችም ተመርቋል።

ወደ መጽሐፉ ከማቅናታችን በፊት በመጀመሪያ ግን ደራሲዋ ማን ናት?

ደራሲና ገጣሚ ኩሪ አየለ ሀይሌ በአዲስ አበባ ተወልዳና አድጋ በወይዘሮ ቀለመወርቅ፤ ቀጥሎም በየካቲት 12 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃለች:: የመጀመሪያ ዲግሪዋንም በአማርኛ ‘ፎክሎር’፤ እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪዋን ‘በዲፕሎማሲ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽን’ ተቀብላለች:: ሁሌም በመልካም ሥነ ምግባር ትውልዱን የመገንባት ሥራዎችን ሥትሰራ ኖራለች:: በመምህርነት ሙያም አገልግላለች:: አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ውስጥ የግንኙነት ዘርፍ ዳይሬክተር ሆና በመሥራት ላይ ትገኛለች:: ደራሲዋ ለሥነጽሁፋ ላደረባት የተለየ ፍቅር መሠረቱ መላው ቤተሰቡ እንደሆነ ትናገራለች። በተለየ ሁኔታ ደግሞ አባቷን ትጠቅሳለች።

አባቷ መምህር አየለ ኃይሌ በደርግ መንግሥት በነበረው የመሠረተ ትምህርት የዘመቻ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው ሰው ናቸው።

በወቅቱም ማኅበረሰቡን በማስተማርና በሚያከናውኗቸው ሥነጽሁፋዊ እንቅስቃሴም ይታወቃሉ። ከማስተማሩ ጎን ለጎንም በግጥሞቻቸው ወኔ ሲቀሰቅሱም ነበር።

“የአባቶቼ ወኔ ተቀሰቀሰብኝ፤

የእናቶቼ ወኔ ተቀሰቀሰብኝ፤

መሀይምነትን ግጨው ግጨው አለኝ።”

ይህ ግጥማቸውም በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰርጾ በመግባቱና በጣም በመታወቁ በሰፈሩ ውስጥ ልጆቻቸው “የግጨው ግጨው ልጆች” ተብለው ይጠሩ እንደነበረም በደራሲዋ የህይወት ማኅደር ውስጥ ተቀምጧል።

ደራሲና ገጣሚ ኩሪ አየለ ኃይሌ ዶሳይስን ጨምሮ አንድ የግጥምና ሌላ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ፤ በአጠቃላይ ሦስት መጻሕፍትን ለህትመት ብርሃን አብቅታለች። እነዚህ ለመታተም የበቁ እንጂ በህይወት ደረጃ እስከዛሬ ድረስ በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች የሰነገቻቸው የጥበብ ሥራዎቿ እልፍ ናቸው:: ለአብነትም በ199ዐዎቹ አጋማሽ “ወንደላጤዎቹ” የተሰኘ ተከታታይ የግጥም ሥራዋን ረዘም ላለ ጊዜ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ስታቀርብ ቆይታለች። “የዓባይ ዘመን ብዕር” በሚል ርዕስ በዓባይ ግድብ ዙሪያ የተጻፋ ግጥሞች ስብስብ እትም ውስጥም “ዓባይ ትዳር ሆነ” የሚለው የግጥም ሥራዋ ተካቶላታል።

አሁን ደግሞ “ዶሳይስ” ብላናለች:: ገና ርዕሱን ስንመለከትም ሆነ ስንሰማ መቼም ስለ ትርጓሜው መጠየቃችን አይቀርም:: “ዶሳይስ” ምንድነው? ከየትስ መጣ? … የቃሉ ሀረግ የተመዘዘው ከወላይትኛ ቋንቋ ውስጥ ሲሆን ትርጓሜውም “እወዳችኋለሁ!” እንደማለት ነው:: ትልቅና ደስ የሚል ፍቅር መግለጫ ፅንሰ ሀሳብ ነው:: ለማንስ? … ስለምኑ? ካላችሁ ምላሹን መጽሐፉ ራሱ ይነግራችኋል::

በዶሳይስ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ውስጥ ተካትተው የሚገኙት ይዘትና ጭብጦች በርከት ያሉ ናቸው:: አብዛኛዎቹም የማኅበረሰቡን ባህላዊ እሴትና ወግ አሁን ባለውና በሚመጣው ትውልድ ውስጥ ለማስረጽ የሚቃትቱ ናቸው:: ደራሲዋ ጥንት የለመድናቸውን ማኅበረሰባዊ መስተጋብሮቻችንን ከፍ ባለደረጃ አጉልቶ ለማሳየት የተጨነቀችበት ይመስላል:: ዘመድ ከዘመዱ፣ ጎረቤት ከጎረቤቱ፣ ወዳጅም ከወዳጁ ጋር ተሰባስቦ በጋራ የፍቅር ጨዋታ ሲያነሆልሉ በማሳየት ከጥንቱ፤ ከረሳነው ላይ እንድንመለስበት ጥራ ታጣጥረናለች::

በዕድርና በዕቁቡ፣ በደስታና በሀዘኑ ሁሉ አንዱ ከአንዱ ጋር የሚቆምበትን የማኅበራዊ ህይወት መደላድሎቻችንን በመክፈት ከገጸ ባህሪያቱ ውስጥ ቁልጭ አድርጎ ዶሳይስ ያስመለክተናል:: በበዓላቱ ሁሉ እስላም ክርስቲያን ሳይል የአንዱን ደስታ ሌላውም አብሮ ያከብራል:: ቡናውንም በጀማ እየተጠራራ፣ ከረከቦቱ ፊት እጣን ጢሱ እየተግተለተል ጨዋታው ደርቶ ልብን ሲያሞቅ የተለየ ስሜትን የሚፈጥር ትዕይንት ነው:: አንዷ ወደ ገበያ ስትሔድ ልጇን ለሌላኛዋ እመጫት ጎረቤቷ ሰጥታ የአንዷን ልጅም ሌላኛው እናት ስታጠባው አድጓል:: መሶብሽ መሶቤ ነው ተባብለዋል::

ደግሞ ከልጅነት ትዝታዎቻችን ጋርም ያጋፍጠናል:: ከመሀከል አንደኛው ልቦለድ የሚወለደውም ከአንቆርጫ ሰፈር ተራራ ላይ ይሆንና ወደዚያው ይዞን ይነጉዳል:: የአንቆርጫ ልጆች ከአንቆርጫ ተራራ ስር ተሰባስበው … በአንቆርጫ ማኅበረሰብ ምግቦች የተገነባውን የልጅነት ጡንቻዎቻቸውን ይፈታተሻሉ:: ሁሉም በተቻለው አቅም ትንፋሹን አምቆ ጡንቻውን አጠንክሮ በመወጠር ለአሸናፊነትና ለበላይነት ይታገላል::

የተሸነፈውም ይኮረኮማል:: ከመጽሐፉ ውስጥ ከአንደኛው ስፍራ ስንደርስም “የእነ ጋሽ ጦና ቤት ፎሰሴና ቁርጥ፣ የእነ ጋሽ ሌጋሞ ቤት በሶቤና ጩከቤ፣ የእነ እትየ ኪሮስ ቤት ጥህሎና አንባሻ … የኛ ቤት መርቃ፣ የእነ ፎዚያ ቤት ሙሸባህ ከጎረቤት ወደ ጎረቤት የሚላላከው የገብሱ፣ የበቆሎው፣ የባቄላው፣ የሽንብራ ቆሎው፣ አነባበሮውና ሌሎችም… እኛ የዛሬ አበቦች የነገ ፍሬዎች ያልተጋራ ነው፣ ያልተሻማ ነው … ጡንቻችንን ያላዋቀርንበት የምግብ ዓይነት የለም::” እያለች ደራሲዋ በገጸ ባህሪዋ አማካኝነት ትነግረናለች::

መስዋዕትነት የተከፈለበት እናትነት … ከኢትዮጵያዊ ወግ፣ ሥርዓትና ባህል ጋር ተቆራኝቶ ልጅ ስለምን? እንዲህ ይሆናል እያለ ከዚያ ከተለመደው ሥርዓት ጋር ሲሟገትና ሲሞግትም እንመለከታለን:: “አንቺን የመሰለች ሴት ጓዳ ውስጥ አስቀምጦ፣ ትምህርትሽን እንዳትጨርሺ ፍላጎትሽን፣ ርእይሽን እንዳታገኚ አድርጓል:: መኖር ያለብሽን እንዳትኖሪ አድርጎሻል:: እንድትኖሪ አልረዳሽም። በአጠቃላይ … አለና ድንገት የሚቆጨውን ነገር አፈረጠው::” እናት በበኩሏ “… ከተመደበልን ኑሮ በላይ አታግዝፈኝ:: መኖር ያለብኝ እንደ ባህሌ፣ ወግና ሥርዓቴ ነው አለችው::” በማለት በሁለቱ መሀከል ያለውን የአስተሳሰብ ልዩነት ልታሳየን ትሞክራለች:: በርካታ የሆኑ የኑሮ ማሰሪያዎቻችንን መሳጭ በሆነ መልኩ ታስነብበናለች:: እያነበብንም የማንናፍቀውና የማናጣጥመው የሕይወት ጣእም የለም:: ከገጽ ወደ ገጽ በተሸጋገርን ቁጥር ሁሉ የምናነበው የራሳችንን ሕይወትና ማንነት ነው::

ከሌላኛው ገጽና ገጽታ ውስጥ “ዱላው ቂ” የተሰኘውን አንድ ወጣ ያለ ገጸ ባህሪ እናገኛለን:: ባህሪው፣ ግብሩና ማንነቱ ከአብዛኛው የተለየ ነው:: ዱላው ቂ ማለት ኮራጅና ጫፍ በነካ የኩረጃ ጥበቡም እስከ ጥግ ድረስ የወጣ ተማሪ ነው:: ይህች ዓለም ፍትሐዊና ሀቀኛ አይደለችምና አንዳንዴ መጥፎ በምንለው ነገር ላይ ቆመው በኑሯቸው ግን የሚያስቀና የሕይወት ከፍታ ላይ ሊቆሙ ይችላሉ::

በመጽሐፉ ውስጥ የተቀመጠው ይህ ገጸባህሪ ብዙ እይታዎቹ እኛ እውነትን ከምናይበት መነጸር በተለየ መንገድ ነው:: ድርጊቶቹ ሊያስቁና ሊያዝናኑን፤ ሊያናድዱንና ብስጭት ሊያደርጉንም ይችላሉ:: የባህሪው አንኳር ዘረመል በአንባቢው እይታና አስተሳሰብ አኳያ የሚገለጽም ዓይነት ነው:: እንደ አንድ ጥበባዊ እይታ ግን በጣም የምንወደውና ለማንበብ የሚያስደስት መልክ አለው:: የልቦለዱን ዳራ ስንመለከት በዶሳይስ ውስጥ ከሚገኙ ገጸ ባህሪያት ሁሉ “ዱላው ቂ” አንድ የተለየ ነገር አለው::

እንዲህ ዓይነት ገጸባህሪያት ከአጭር ይልቅ ለረዥም ልቦለድ ተመራጭ ናቸው:: በረዥም ልቦለዶች ውስጥ የምናገኛቸው አብዛኛዎቹ መሪ ገጸባህሪያት እጅግ ሞገደኛና ከቀሪው ማኅበረሰብ ወጣ ያለ ስብዕናና አስተሳሰብ ያላቸው ናቸው:: በጊዜው ልክ በማይመስሉ ነገሮች ውስጥ እያለፉና ብዙዎችንም እያስቆጡ በመጨረሻም ድንቅ የሆነ አዲስ ነገር ሠርተው ያሳዩናል:: ለአብነትም በዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ”፣ በበዓሉ ግርማ ″ኦሮማይ″ ውስጥ ደግሞ “ፊያሜታ ጊላይ”ን ለማንሳት እንችላለን:: ከዚህ ለየት ባለ መንገድ ደግሞ እስከመጨረሻው ድረስ እጅግ አስቀያሚና መጥፎ ሆነው በክፋታቸው ዝነኛ የሆኑ በርካታ ገጸ ባህሪያትም አሉ:: ሁሉንም የሚያመሳስለው አንድ ነገር ግን በአስተሳሰብ፣ በዕውቀትና በጥበብ የተካኑ መሆናቸው ነው:: ከእነዚህ አንጻርም “ዱላው ቂን”ን አንደኛውን መልክ ሰጥተን በረዥም ልቦለድ ውስጥ ብናስቀምጠው የተዋጣለት ድርሰት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም::

ከዚህ ወደዚያ እያልን ወደ መጽሐፉ ምረቃ ዕለት ስንመለስ፤ የምረቃ ዝግጅቱ እጅግ ውብ ነበር:: ከዚህ ቀደም እምብዛም ባልተለመደ መልኩ አዳዲስ ነገሮችን አሳይቶናል:: ለአብነትም ብሔር ያልገታቸው የብዕር ጠብታዎች በተለያዩ ቋንቋዎች ተከሽነው መቅረባቸው ነው:: በአማርኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በትግሪኛና በጉራጊኛ ቋንቋዎች ከተለያዩ ገጣሚያን አንደበት ጣፋጭ የስንኝ እንጆሪዎች ተራግፈዋል:: ከአንድ መድረክ ላይ ሆኖ እንዲህ ያለውን ኢትዮጵያዊነት መመልከት እጅጉን አስደሳች ነው::

በብሔራዊ ቲያትር ሙዚቀኞች ጥኡም ሙዚቃዎችም ተንጎራጉረዋል:: በየዘመናቱ በብዕራችው ትውልድና ሀገርን ሲገነቡ የነበሩና ያሉ ደራሲያንም ተገኝተው ከአዲሱ ፍሬ ቀምሰዋል:: የመጽሐፍ ምረቃው ከታሰበበት ዓላማ አንዱ እኚህኑ እንቁና አንጋፋ ደራሲያንን ስለሰጡን ሁሉ ምስጋናን ማቅረብ ነበር:: እየደበዘዘ የመጣውን የመጽሐፍ ብርሃን ለመመለስ ታላላቆቹ መንገዱን የማቅናት የመጨረሻው ትልቅ ኃላፊነት ከእነርሱ እጅ ላይ ናት:: ካሳለፉትና ከነበሩበት የንባብ ዘመን አንጻር የተሻለውን ለማምጣት ከእነርሱ የሚቀርብ የለም::

በምረቃው ከተገኙ አንጋፋ የጥበብ ባለሙያዎች መሀከል አንዱ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት አበረ አዳሙ ነበር:: “በማኅበራችን ውስጥ አንድ መጽሐፍ ታተመ ሲባል በቤተሰብ ውስጥ አንድ ተጨማሪ ልጅ እንደተወለደ ያህል እንቆጥርና ደስ ይለናል::” በማለት አንብ፤ የምታነበውንም እወቅ፤ አንባቢ ስንሆን በወጣ በወረደ ሁሉ አንተራመስም የሚል ሀሳብም አክሎበታል::

ለመድረኩ ቆንጆ የሀሳብ ምልከታውን ያጋራው ሌላኛው ብርቱ የብዕር ፈርጥ ኃይለ መለኮት መዋዕል ነበር:: በርካታ የመጻሕፍት ደሴቶቹን በአይነት በአይነት ሰጥቶናል:: አብዛኛዎቻችንም “ጉንጉን” በተሰኘው ረዥም ልቦለዱ እናውቀዋለን::

“ተጽፎላቸው መጻሕፍትን ለማይገዙ ልብ ይስጥልን … ወጣቶችን ለማያበረታቱ ልብ ይስጥልን፤ በማንኛውም አቅጣጫ የጥበብ ሥራዎችን ለሚኮረኩሙና ለማይደግፉ ልብ ይስጥልን … ልብ ይስጣቸው … ብዙውን ጊዜ ከሚያሳስቡኝ ጉዳዮች አንዱ የመጽሐፍ ምረቃ ነው:: ቧልትና ቀልድ ሲሆን … እስቲ ደግሞ እንሄድና ትንሽ ተጫውተን እንምጣ የሚባልበት አካባቢ ይኼ አዳራሽ ግጥም ብሎ ሲሞላ አውቃለሁ:: አንድ ደራሲ ግን ለዓመታት ያህል አስቦ፣ አሰላስሎ ጽፎ፣ ስንት መከራውንና ፍዳውን አይቶ ያሳተመውን መጽሐፍ ለማስመረቅ ግን የእርግማን ያህል ይቀራል:: … እራሳችንን ልናርምና ልንወቅስ ይገባል:: … ደራሲ ጽፎ እንጂ አትርፎ አያውቅም::

ሕዝብ በአክብሮት ተጠርቶ ሳይመጣ መቅረት ማለት የደራሲያኑ ጉድለት ሳይሆን የማኅበረሰቡ የሀፍረት ማቅ ነው::” ሲል ነበር ያሳሰበውን የመጻሕፍቱን ዓለም ሰቆቃ ይገለጸው:: ደራሲ ኃይለመለኮት “ዶሳይስ”ን በተመለከት ጠለቅ ያለ ሙያዊ አስተያየቱን ባያጋራም እንደ አንድ አንባቢ በብዙ ጉዳዮች የተሻለ መጽሐፍ ስለመሆኑ አንስቷል::

ጸሀፊ ተውኔትና ባለቅኔ አያልነህ ሙላት እንዲህ ባሉ ስፍራዎች ላይ እየተገኙ ለጥበብ የሚገባትን፣ ሙያውም የሚወደውን ነገር በመስጠት ደረጃ ምናልባትም ከአንጋፋዎቹ ግንባር ቀደም ነው ለማለት ይቻላል:: የደራሲያኑን አዳዲስ የመጻሕፍት ሥራዎቻቸውን አስቀድሞ በመመልከትና ሙያዊ አስተያየቱን ለማጋራትም የሚቀድመው ያለ አይመስለኝም:: እሱም ገና ወደ መድረኩ ሲወጣ “መጽሐፉን ግን ከሁላችሁም በፊት አግኝቼ ተመልክቼው ነበር፤ ኃይለመኮት እንኳን ሁል ጊዜም እኔን ቀዳሚ እርሱ ነው” ሲል በጨዋታ መልክ ቢያነሳትም፤ ከዚህ ረገድ ትልቁን ምስጋና ሊቸር ይገባዋል:: በ”ዶሳይስ” የመጽሐፍ ሽፋን ላይም ምልከታውን አኑሮበታል:: “እኔ እንኳን ስጠራ መጽሐፉን ትመርቃለህ ተብዬ ነውና የሽማግሌ ምርቃት እመርቃለሁ … ከምንም በላይ ዛሬ እዚህ መድረክ ላይ በተለያዩ ቋንቋዎች የቀረበውን ግጥም ስሰማ እጅግ ደስ ብሎኛል::

ኪነ ጥበብ የሚያድገው እንደዚህ ነው:: … ፖለቲካ አይደለም ሕዝብን ከህዝብ ሊያገናኝ፤ ሊያቀራርብ የሚችለው። እንደዚህ አይነት የጥበብ ሥራዎች ናቸው:: ዛሬ የተመለከትነው ነገር ነገ መቀጥል ያለበት ጥሩ ጅምር ነው:: አስቀጥለንም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወርን፤ እንዲህ እያሰባጠርን ብናቀርብ ኪነጥበብ የማይቀርፈው የለምና ብዙ ችግሮቻችንን ለመቅረፍ የምንችል ይመስለኛል::” በማለት ገዘፍ ያለውን ልባዊ ምስጋናውን ለኩሪ ቸሯታል:: ይህ የአንባቢያንና የመጻሕፍት ጉዳይ ግን አያልነህ ሙላትን ጨምሮ ሁሉንም ያሳሰበ ጉዳይ ነበር::

በነበረው የምረቃ ስነስርዓት ወቅት ደራሲዋ አንድ ቅር ያሰኛት ጉዳይ ነበር:: ቀደም ሲል ከኪነጥበብ ሰዎች ባሻገር የትምህርት ቤት የኪነጥበብ አባላት፣ ተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆችም ጭምር በመጽሐፍ ምረቃው ላይ እንደሚገኙ ነበር። ዝግጅቱም ሆነ የጥሪ ካርዱም ረዘም ላለ ጊዜ የተሰናዳው በዚሁ መልክ ነበር:: ነገር ግን ለምረቃው ሦስት ቀናት ብቻ ሲቀሩት የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ በዝግጅቱ ላይ ሊገኝ እንደማይችል ከትምህርት አስተዳደሩ ለደራሲዋ ተገለጸላት:: የእነርሱ የመገኘት ጉዳይ ታዳሚው እንዲበረክት፣ ለጊዜያዊ ድምቀትና ለግርግሩ አልነበረም::

ከላይ እንደተመለከትነውም አንጋፋዎቹን ጨምሮ የሁሉም ጭንቀት የነበረው የትውልዱ ከመጽሐፍ ዓለም ተሰዶ በንባብ ላይ ማፈንገጡ ነው:: ለዕለቱ ታስቦ የነበረው አቢይ ጉዳይ “ዶሳይስ”ን ማስመረቅ ብቻ ሳይሆን የተጋረጠውን ችግር ለመቅረፍ አንድ እርምጃ ትውልዱን የማቅናት ሀሳብም የያዘ ነበር:: ደራሲና ገጣሚ ኩሪ አየለ ደግሞ በተለየ መንገድ ከትምህርትና ተማሪዎች ጋር ቅርበት ያላት ናት:: ጥቂት ለማይባሉ ዓመታት በመምህርነት አገልግላለች:: በተለያዩ የመማሪያ መጻሕፍቶች ውስጥ ግጥሞቿ በማስተማሪያነት ተካተዋል:: ለዚህም ነው የንባቡን ጎጆ ለማቅናት ከየቱ ጋር መጀመር እንዳለባት ተረድታ እንዲገኙ ጥሪ ማቅረቧ::

እናም በዚህ ዝግጅት ላይ ተማሪዎቹ ለመገኘት እንደማይችሉ በተነገራት ጊዜ ግራ በመጋባት ለምን? ስትል ጠየቀች:: “ምክንያቱም የኛ ተማሪዎች የማንበብ ችግር የለባቸውም:: ባይሆን ሌሎች ያለባቸውን …” የሚል ምላሽ እንደተሰጣት ኩሪ ተናገረች:: ነገሩ የሚያስገርም ነው፤ አለመገኘታቸው ሳይሆን ምላሹ … ከአንድ ትውልድን ለመገንባት ከሚሠራ አካል እንዲህ ያለውን ምላሽ መስማት ለጆሮም ሰቅጣጭ ነው:: ለፈተናው ብቻ የሚጠቅመውን መደመርና መቀነስን ብቻ እያነበበ የኖረ ተማሪ ነገ ላይ እንዴት ያለው ትውልድ ነው የሚሆነው?

መጽሐፍ ሲባል የሚጠራው ብዙ፤ የሚገኘው ግን ጥቂት አይሁን:: የኋላ ኋላ የጥበብ ቀንዳችን ታጥፎና ቁልቁል ተጠማዞ ወደ ከፋው እንዳንገባም እናስብ፤ እናሰላስል::

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You