ሀገራዊ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተገልጋይ ርካታ 68 በመቶ ደርሷል

አዳማ:- በጤና መድኅን አገልግሎት ሥር የሚሰጠው የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን የተገልጋይ እርካታ በሀገር አቀፍ ደረጃ 68 በመቶ መድረሱ ተገለጸ። በአዲስ አበባ ያለው የአገልግሎት ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑንም ጥናት ጠቁሟል።

በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተገልጋዮች እርካታ፣ ግንዛቤ እና አመለካከት ዙሪያ የተጠና ጥናት ትናንት ይፋ ተደርጓል።

በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ፤ በጤና መድኅን አገልግሎት ሥር የሚሰጠው የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተገልጋይ እርካታ፣ ግንዛቤ እና አመለካከት ዙሪያ የተጠናው ጥናት የክትትልና ቁጥጥር ሥራችንን እንድናጠናክር ይረዳናል ሲሉ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ወርቀሰሙ በመርሐግብሩ መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተገልጋይ እርካታ ዙሪያ የተጠናው ጥናት የተጠቃሚውን ሕዝብ እርካታ በነሲብ ሳይሆን በሳይንሳዊ ጥናት ላይ በተመሠረተ መልኩ እንዲታይ ያደርገዋል። ይህም የክትትልና ቁጥጥር ሥራውን ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል።

በዘርፉ ተገልጋዮች በወረፋ እንዳይጉላሉ ለብቻቸው አንድ መስኮት ተዘጋጅቶላቸው እንዲጠቀሙ መደረጉ ለአብነት የሚጠቀስ እርካታን የሚያሳድግ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፤ ሆኖም ከዚህ የተሻለ ርካታን ለመፍጠር በመድኃኒት ግዢ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ሊስተካከሉ ይገባል ብለዋል።

የጤና መድኅን አገልግሎት ዜጎች በችግር ምክንያት ሳይታከሙ እንዳይቀሩ በፓይለት ደረጃ በጥቂት ወረዳዎች መጀመሩን አንስተው፤ በፓይለት ደረጃ የተወጠነው ውጤታማ መሆኑን ተከትሎ ወደ ትግበራ መግባት መቻሉን አብራርተዋል።

አሁን ባለበት ደረጃ የአገልግሎቱ ሽፋን ጥሩ የሚባል መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ወርቀሰሙ፤ በተገልጋዩ ርካታ ላይ ይበልጥ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በተለይ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ማነቆ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ምክንያት የመድኅን አገልግሎቱ ወደኋላ እንዳይመለስ ስጋት አለኝ ሲሉ ተናግረዋል።

ጥናቱን ያቀረቡት በአገልግሎቱ የፈንድ ስጋትና የኢንቨስትመንት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አዳሙ ወንድምተካ በበኩላቸው፤ በሥርዓቱ 12 ሚሊዮን አባወራና እማወራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። 56 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

ጥናቱ በስምንት ክልሎች የተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ሀገራዊ የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች እርካታ 68 በመቶ መድረሱን በጥናቱ አመላክተዋል።

ዝቅተኛው የተገልጋዮች እርካታ በደቡብ ክልል የተመዘገበ ሲሆን፤ ከፍተኛው የተገልጋዮች እርካታ ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስለመሆኑም በጥናቱ ተመላክቷል።

ማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ግንዛቤ በሀገር አቀፍ ደረጃ 63 በመቶ እንደሆነም በጥናቱ ተጠቅሷል።

በጥናቱ በተመላከተው መሠረት ስለአገልግሎቱ ዝቅተኛ ግንዛቤ የተመዘገበባቸው አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ሲሆኑ ከፍተኛው ግንዛቤ የተመዘገበው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልሎች ነው።

በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ዘንድ እርካታ ዝቅ እንዲል ካደረጉት መካከል የመድኃኒት አቅርቦትና የላቦራቶሪ አገልግሎቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን ጥናቱ አሳይቷል።

የኢትዮጵያ የጤና መድኅን አገልግሎት ዜጎች እንዳቅማቸው አዋጥተው እንደሕመማቸው እንዲታከሙ እና የዓለም የጤና ድርጅት ያስቀመጠውን የጤና ሽፋን ለማዳረስ የተቀረፀ የዚሁ አካል የሆነው የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት የሙከራ ትግበራውን የጀመረው በ2013 በሦስት ወረዳዎች ነበር። በተያዘው 2016 በጀት ዓመት 1052 ወረዳዎችን በመሸፈን ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን መረጃዎች ያሳያሉ።

ውብሸት ሰንደቁ

አዲስ ዘመን ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You