መዲናችንን አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ሌሎች ከተሞቻችንን ጽዱና ማራኪ ሆነው ማየትን ማንኛውም ሰው የሚጠላ አይመስለኝም:: ሁሉም ከተሞች ጽዱና ማራኪ እንዲሆኑ ደግሞ ከመንግስት ባሻገር የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋል። ስለ ሌሎች ከተሞች የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ ባለውቅም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ ሕዝቡ የሚያደርገው ድጋፍና ትብብር የጎላ በመሆኑ እየተሠሩ ካሉት የኮሪደር ልማቶች መካከል አብዘኛዎቹ በአጭር ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
ስለ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ በመገናኛ ብዙሃን ከምንሰማውና ከምናየው በተጨማሪ ውበና ማራኪ ሆነው የተሠሩ ለመሆናቸው በዓይናችን እያየን ስለሆነ ሌላ ምስክር አያስፈልገንም። ከተጀመሩት የኮሪደር ልማት ስራዎች መካከልም የተወሰኑት ተጠናቀው ለመኪና፣ ለብስክሌት እና ለእግረኛ ክፍት መሆናቸው የኮሪደር ልማቱ ፍሬ እያፈራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።
የተጠናቀቁት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች በቀን 8 ሰዓት ብቻ በመሥራት የተጠናቀቁ ሳይሆን 24 ሰዓት በመሥራት የተጠናቀቁ ስለመሆናቸው በመገናኛ ብዙሃን ከምንሰማው ባሻገር የኮሪደር ልማቶቹ በሚሠሩባቸው አካባቢዎች የምንኖር ሰዎች ያለውን እንቅስቃሴ በዓይናችን እናያለን፤ ሌሊቱን ሙሉ ሲሠራም የማሽኖችን እና የሰዎችን እንቅስቃሴ በጆሯች እንሰማለን። በአገራችን 24 ሰዓት መሥራት መጀመሩ ደግሞ የሥራ ባህልን እየተለወጠ ስለመሆኑ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።
የኮሪደር ልማቶቹ 24 ሰዓት መሠራታቸውም ብዙ ጠቀሜታዎችን ይዞ መጥቷል፤ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ ከማድረጉ ባሻገር ለብዙዎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ሥራው በአጭር ጊዜ መጠናቀቅም ሕዝቡ ከልማቱ እንዲጠቀም ያደርጋል። ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል እየፈጠረ ነው ሲባልም በፕሮጀክቶቹ ተቀጥረው ለሚሠሩት ብቻ ሳይሆን በግል ሥራ የተሠማሩ ሰዎችም ሌሊት ለሚሠሩ ሠራተኞች የምግብ እና ሻይ ቡና አገልግሎት ስለሚሰጡ ከፕሮጀክቱ ውጭ ላሉ ሰዎችም የሥራ ዕድል እየፈጠረ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት መጠናቀቅም ጠቀሜታው ለመንግሥትና ለሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለሥራ ተቋራጭ ድርጅቶችም ጭምር ነው። ምክንያቱም የፕሮጀክቱ የመሥሪያ ጊዜ ባጠረ ቁጥር የሥራ ተቋራጮች አንድን ፕሮጀክት ለመሥራት ሲዋዋሉ የተመኑት ዋጋ ባለበት ስለሚቆይ ከኪሳራ ያድናቸዋል። ስለዚህ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ብዙ ተሞክሮዎችን እያለማመደ ይመስለኛል። የኮሪደር ልማቱ በርካታ ቤቶች ቢፈርሱም ሰዎች ከለመዱበት አካባቢ ለቀው በመሄዳቸውና በዚህ ምክንያት አንዳንድ ማህበራዊ መስተጋብሮች ስለቀረባቸው ቅር ከመሰኘታቸው በስተቀር አንድም የልማት ተነሺ ከሞቀ ቤቴ ወጥቼ ሜዳ ላይ ወደቅኩ የሚል ቅሬታ ባለመንሳቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
የመኪና፣ የብስክሌት እና የእግረኛ መንገዶች በየራሳቸው መስመር መሠራታቸውም መኪናዎች፣ ብስክሌቶች እና እግረኞች በትክክል የራሳቸውን መንገድ ጠብቀው እንዲጓዙ ምቹ ሁኔታን ስለፈጠረ እግረኞች እና ብስክሌቶች ከመኪና ጋር እየተገፋፉ መሄዳቸውንም ያስቀራል። የመኪና፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገዶች የየራሳቸውን መስመር ጠብቀው ከመሠራታቸው በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እና የመሸጋገሪያ ድልድዮች በመሠራታቸው እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ለትራፊክ አደጋ መቀነስም አስተዋፅዖ የሚኖራቸው ይሆናል፡፡
የመኪና፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገዶች እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና የመሸጋገሪያ ድልድዮች መሠራታቸው ብቻ ግን የትራፊክ አደጋን ይቀንሳል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም መኪናዎች፣ ብስክሌቶችና እግረኞች የየራሳቸውን መስመር ጠብቀው ካልሄዱ እንዲሁም የተሠሩትን የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና የመሸጋገሪያ ድልድዮችን በአግባቡ ካልተጠቀሙባቸው ችግሩን ስለማይቀርፍ። የመኪና አሽከርካሪዎች፣ በብስክሌትና በእግረኛ መንገዶች የሚያሽከረክሩ ከሆነ ለረጅም ዓመት እንዲያገልግሉ ታስበው የተሠሩ መንገዶች ዕደሜያቸው ያጥራል፤ እግረኞና ብስክሌቶች በመኪና መንገድ የሚሄዱ ከሆነም ለትራፊክ አደጋ መንስኤ መሆናቸው አይቀርም፡፡
ይህን የምለው እንዲሁ ከመሬት ተነስቼ አይደለም። በእግረኛ እና በብስክሌት መንገዶች መኪና ሲነዳበት፣ በመኪና በብስክሌት መንገዶች እግረኛ ሲሄድበት፣ በመኪና እና በእግረኛ መንገዶች ብስክሌት ሲጋለብበት ስለተመለከትኩ ነው። የሞተር ብስክሌቶች ነገር ደግሞ እጅግ በጣም የከፋ ነው። መኪና በመብራት ምክንያት ቆሞ እያዩ እነሱ ሹልክ ብለው ስለሚገቡ ለትራፊክ አደጋ ስጋት መሆናቸውን ሁሌ እታዘባለሁ። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት ቀድመው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት የሚኖርባቸው ሲሆን ከግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቱ በኋላ መንገዶችን በሥርዓቱ በማይጠቀሙት ላይ እርምጃ መውሰድም ስለሚያስፈልግ የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው የሚል አስተያየት አለኝ፡፡
የኮሪደር ልማቱ በተሠራባቸው አካባቢዎች ለዓይን ማራኪ የሆኑ አበባዎች እና አረንጓዴ ተክሎች መኖራቸውም ሰዎች ሲጓዙ ቆይተው በሚደክማቸው ጊዜ ውብ አበባዎችንና አረንጓዴ ተክሎችን እየተመለከቱ ማረፍ እንዲችሉም ዕድል ይሰጣቸዋል። ሕፃናት ልጆቻቸውን ይዘው የሚጓዙ ወላጆችም ሕፃናቱ የሚጫወቱበት ቦታ ስለሚያገኙ ያለምንም ጭንቀት አረፍ ብለው ትንፋሽ እንዲወስዱ ይረዳቸዋል። በኮሪደር ልማቱ አካባቢ የሚገኙ ሕንፃዎች፣ የመንገድ መብራቶች እና የመሳሰሉት እየታደሱ መሆናቸውም የኮሪደር ልማቱ ሲጠናቀቅ ለአዲስ አበባ ከተማ ተጨማሪ ውበት የሚፈጥሩ ናቸው፡፡
በካፌዎችና በሬስቶራንቶች ሻይ ቡና እያሉ መዝናናት ለሚፈልጉ ሰዎችም በየመንገዱ ዳር በተከፈቱ ካፌዎችና በሬስቶራንቶች አረፍ ብለው ለመዝናናትም ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል። የኮሪደር ልማቱ በተጠናቀቀባቸው በአራት ኪሎና በፒያሳ አካባቢ በየመንገዱ ዳር በተከፈቱ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች ሰዎች ሻይ ቡና ሲሉም ተመልክቻለሁ።
በሌላ በኩል የሰው ልጅ እንደሌሎች እንስሳት በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀስ ሳይሆን የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አስቦና አልሞ የሚተገብር ቢሆንም ቸልተኛ ሰዎችን ሳይጨምር በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች መንገድ ላይ ሲሄዱ በሚገጥማቸው ሕመም አለያም ተፈጥሮ አስገድዷቸው መቋቋም ሲያቅታቸው መንገድ ላይ ስለሚፀዳዱ (ሽንታቸውን ስለሚሸኑ) ከተሞችን ያቆሽሻሉ፡፡
መንግሥት ይህን ተገንዝቦ ይመስለኛል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚሠሩ የኮሪደር ልማቶች በተለያዩ አካባቢዎች 120 ዘመናዊ የመፀዳጃ ቤቶችን አካቶ ለመሥራት ያቀደው። እነዚህ ዘመናዊ መፀዳጃ ቤቶች መሠራታቸው የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት ለመጠበቅ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ የሚል ተስፋ ቢኖረኝም ትክክለኛ የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ካልኖረ የመፀዳጃ ቤቶቹ መሠራት ብቻ የከተማዋን ጽዳት ይጠብቃል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም የመፀዳጃ ቤቶቹ አጠቃቀም እና አያያዝ ችግር ካለባቸው ለከተማይቱ ፅዳት መጓደል የባሰ መንስኤ እንዳይሆንም ሥጋት ስላለኝ መፀዳጃ ቤቶቹን የሚያስተዳድሯቸው አካላት እና እያንዳንዱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ መፀዳጃ ቤቶቹን በአግባቡ ለመጠቀምና ለመያዝ ኃላፊነቱን በመወጣት ድጋፍና ትብብር ማድረግም ይጠበቅበታል።
ከዚህ ቀደም በመንግሥት ቁጥጥር ሲደረግባቸው የነበሩ የአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች አሁን ካሉት የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች በአንፃራዊነት ጽዱ ነበሩ ማለት ይቻላል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ጥቅም እየሰጡ ያሉ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ሕመም ወይም ተፈጥሮ ስለሚያስገድድ እንጠቀምባቸዋለን እንጂ ንፅህናቸው በጣም የወረደ መሆኑ እሙን ነው። መፀዳጃ ቤቶችን የሚያስተዳደድሩት አካላትም ከተጠቃሚው ገንዘብ ይሰበሰባሉ እንጂ ስለንፅሕናቸው ሲጨነቁ አይስተዋልምና ሊታሰብበት ይገባል።
በኮሪደር ልማቱ የሚሠሩ መፀዳጃ ቤቶችን ንፅህና ለመጠበቅ መፀዳጃ ቤቶችን ከሚያስተዳድሩ አካላት እና ከእያንዳንዱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ትልቅ ኃላፊነት የሚጠበቅ ይመስለኛል። እያንዳንዱ ዜጋ መፀዳጃ ቤቶችን በአግባቡ የማይጠቀምባቸውና በንጽህና የማይያዛቸው ከሆነ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ እንዳያመዝን ስጋት አለኝ።
ሁሉንም መሠረተ ልማቶች አካቶ የሚሰራው የኮሪደር ልማት ከዳር ደርሶ እያንዳንዱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ከተፈለገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋል። መንግሥት የሕዝብ ወኪል በመሆኑ ሕዝብን ወክሎ ሥራዎችን ይሠራል እንጂ ብቻውን የሚያደርገው አንዳችም ነገር አለመኖሩን ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሊገነዘብ ይገባል።
መንግሥት ሕዝብን ወክሎ የሚሠራውን ፕሮጀክቶች ሕዝብ ኃላፊነት ወስዶ ካልተንከባከበና በአግባቡ ካልተጠቀመ የአገልግሎት ጊዜያቸው ሊያጥር፤ አለያም ምንም አገልግሎት ሳይሰጡ ከጥቅም ውጭ ሊሆን ስለሚችል የሁሉንም ኅብረተሰብ ኃላፊነት ይጠይቃል። ለሕዝብ ጥቅም ተብለው ብዙ ሀብት የፈሰሰባቸው ፕሮጀክቶች አንዳንዴ በሕዝቡ የተሳሳተ ግንዛቤ፤ ሌላ ጊዜ በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የአፈጻጸም ችግር ሕዝቡን ሳይጠቅሙ መና የሚቀሩበት አጋጣሚዎች ብዙ ናቸውና ከፕሮጀክት ሥራዎች ጎን ለጎን በመገናኛ ብዙሃን በኩል ወይም በተቋማቱ የተግባቦት ክፍል የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት የልማቱን ትሩፋቶች መንከባከብ ያስፈልጋል።
ጋሹ ይግዛው (ከወሎ ሠፈር)
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም