መንግሥትና ሕዝብ የሚያከናውኗቸው ሥራዎች ተከትሎ እንደ ሀገር በምጣኔ ሀብትም ሆነ በማኅበራዊ ልማት በኩል ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ይታያል። በምጣኔ ሀብቱ በኩል ብዙ ለውጦች እየታዩ ናቸው። እነዚህ በግብርናው፣ በአንዱስትሪው፣ በቱሪዝም ዘርፉ፣ ወዘተ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ለውጥም የበለጠ ለውጥ ለማምጣትም ትልቅ አቅም ናቸው። በማኅበራዊው መስክም ስንመለከት በትምህርት፣ በጤናና በመሳሰሉት ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በአንጻሩ ሀገሪቱ ብዙ የመልማት ፍላጎትና አቅም ቢኖራትም በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ እና በአቅም ውስንነት ሳቢያ ልትፈታቸው ያልቻለቻቸው በርካታ ችግሮችም አሉባት። እነዚህን ችግሮችም አልገፋቻቸውም፤ ችግሮቹን ዜጎች በተለያየ አግባብ ለመፍታት እንዲንቀሳቀሱም ለማድረግም እየሠራች ትገኛለች።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ከእዚህ አኳያ ይጠቀሳል። ይህ የመደጋገፍ እሴት በተለይ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰፋ መጥቷል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአዲስ አበባ በመኖሪያ ቤት እድሳትና አዲስ መኖሪያ ቤት ግንባታ፣ በማዕድ ማጋራት፣ በደም ልገሳ የተከናወኑት ተግባሮች የኢትዮጵያውያንን የመደጋገፍ እሴት ፍንትው አርገው አሳይተዋል። በእዚህ ቅዱስ ተግባር የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት እየተሳፉበት ይገኛሉ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ባለሀብቶች እንዲሁም በርካታ ግለሰቦችንም እያሳተፈ ይበልጥ ውጤታማ እየሆነ የመጣው ይህ ተግባር በየጊዜው እያደገ እና እየሰፋ ሀገራዊ መልክ እየያዘም ይገኛል። በአገልግሎቱ እየተከናወነ ያለው ተግባር በገንዘብ ሲተመን በብዙ ቢሊዮኖች ብር እየተገመተ ይገኛል። ይህም ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ በውስብስብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት የመንግሥት እጅ ሳይጠበቅ መታደግ እንደሚችል ትልቅ ማሳያ ነው።
በተያዘው 2016 በክረምት ወራት በሚደረገው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብቻ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሥራ እንደሚሠራ ተጠቁሟል፤ በዚህ አገልግሎት ከ40 ሚሊዮን ሰዎች በላይ የሚሳተፉበት ሲሆን፤ በአገልግሎቱ ያላቸው በገንዘብ፣ የሌላቸው ደግሞ በጉልበታቸውና በእውቀታቸው ይሳተፉበታል። በዚህ አገልግሎት ከ50 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ መረጃዎች ጠቁመዋል።
መምህራን በማስተማር፣ የጤና ባለሙያውም የሕክምና አገልግሎት በመስጠት፣ የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎችም እንዲሁ መረጃ በማድረስና በመሳሰሉት ይሳተፉበታል። ተማሪዎች ባላቸው እውቀትና ጉልበት በአገልግሎቱ በስፋት ይሰማራሉ። ሕዝቡን በሚገባ ማነቃነቅ ከተቻለ ለእዚህ አገልግሎት፣ አገልግሎት መስጠት የማይችል አንድም ዜጋ አይኖርም ማለት ይቻላል።
ከዚህ ሁሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ምን ያህል ትልቅ አቅም እንዳለው መገንዘብ አያዳግትም። በአገልግሎቱ ብዙ ሚሊዮን ሰዎችን ከልጅ እስከ አዋቂ ማንቀሳቀስ፣ ብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመቱ አያሌ ሥራዎች የሚሠሩበት እንዲሁም ብዙ ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ በእርግጥም በሀገሪቱ መረዳዳት ከተቻለ አያሌ ዜጎችን መታደግ የሚያስችል አቅም እንዳለ ያመለክታል።
በእዚህ ታላቅ ሥራ ዜጎችን መርዳት ብቻ ሳይሆን የመንግሥትን ሸክም ማቃለል እንደሚቻልም ማየት ተችሏል። ሕዝብና ሀገር በእጅጉ የሚፈልጓቸው አያሌ ሥራዎች ላሉበት የኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝቡ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይህን ያህል ሥራ መሠራት መቻሉ ትልቅ አቅም መሆኑን ማየት ያስቻለም ነው።
በተለምዶ ሕዝብ የጎደለውን ሁሉ መንግሥት እንዲሞላ ሲጠበቅ ኖሯል። የሕዝቡን ጉድለት በራሱ በሕዝቡ መሙላት እንደሚቻል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማሳየት መቻል በራሱ ትልቅ ተግባር ነው። ለእዚህም በእዚህ ተግባር ዘለው የገቡትንም ሆነ በማስተባበሩ ሥራ ለተሠማሩትና ምቹ ሁኔታ ለፈጠረው መንግሥት ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል።
የኢትዮጵያውያን የመረዳዳት እሴት ይበልጥ እንዲጠናከር የተደረገበትም ነው፤ ከሀገራችን ሕዝብ 98 በመቶ ያህሉ ሃይማኖተኛ እንደሆነ ይገለጻል። የየእምነቱ ተከታይ ዜጎችም በእምነቱ እሴቶች የተገነባ ነው። ሕዝቡ በባሕልም በኩል ቢታይ እንዲሁ መረዳዳት ትልቅ እሴት አርጎ የኖረ ነው። በጎነት የኢትዮጵያዊነት መገለጫም ነው፤ አንድ ኢትዮጵያዊ ሌላውን ኢትዮጵያዊ በበጎነት ሲያስብ እምነቱን ተመልክቶ አይደለም፤ ኢትዮጵያዊነቱን፣ ወገኑ መሆኑን ተመልክቶ ነው። ይህ ሁሉ ኢትዮጵያ ያለውን የሚያካፍል፣ መረዳዳትን ባሕሉ ያደረገ ሕዝብ ሀገር መሆኗን ያስገነዝባል።
ይህ የኢትዮጵያውያን የመረዳዳትና መደጋገፍ ባሕል ግን በቀደመው ልክ አለ ብሎ መናገር የማያስችሉ ሁኔታዎች እየታዩ ናቸው። በዜጎች ርብርብ ከችግር ሊወጡ የሚችሉ አካል ጉዳተኞች፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የአዕምሮ ሕመሙን፣ .ወዘተ ቁጥር እየጨመረ መምጣት የመደጋገፍ እሴቱን በቀደመ ቁመናው ላይ ነው ለማለት የማያስችል ሆኖ ቆይቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመታደግ በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና በመሳሰሉት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ዜጎች በስፋት እየተሳፉ መሆናቸው፣ ኢትዮጵያውያን ዘመናትን በዘለቀው የመረዳዳት ባሕላቸው ላይ አርፎ የነበረውን ትቢያ በማራገፍ በተናጠል ከሚያደርጉት ዜጎችን የመታደግ ጥረት ወደ ተቀናጀ ርብርብ በመግባት ለውጥ ማሳየት መጀመራቸውን ያመለክታል።
የርብርቡ አንድ ማሳያም ሰሞኑን በይፋ የተጀመረው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው። እንደሚታወቀው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለይ በአዲስ አበባ በስፋት ሲካሄድ ቆይቷል፤ በዚህም ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል።
ዘንድሮም ይህን አገልግሎት ይበልጥ እንደ ሀገር ማስፋት የሚያስችል የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው በመላ ሀገሪቱ ማካሄድ ውስጥ የተገባው። ተማሪዎችን በማሳተፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ መሆን የጀመረው አገልግሎት በዘንድሮው ንቅናቄው ወጣቶች ብቻ አይደሉም የሚሳተፉበት። ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲሳተፍበት ይደረጋል። ይህም ሰፊ ሀገራዊ ፋይዳ ይኖረዋል።
የበጎነት ሥራ የአንድ ተቋም ወይም የብዙ ተቋማት ሥራ ሳይሆን ሁሉም የራሱን ድርሻ የሚወስድበት ነው። ለአንድ አቅመ ደካማ እናት የሚታደሰው ቤት የኢትዮጵያውያንን ቤት የመጠገን አንዱ አካል በማድረግ የሚከናወን ተደርጎ እየታየ ነው። ተቋማዊ በሆነ መንገድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን በመላ ሀገሪቷ ተደራሽ የሚደረግበት ሁኔታ እየታየ ነው። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ሀገራዊ ንቅናቄ ሀገርን የመገንባት አንዱ አካል እንጂ የአንድ፣ የሁለት፣ ወዘተ ጊዜ ወይም የዘመቻ ሥራ ብቻ እንደማይሆንም ብዙዎች ይስማሙበታል።
በአገልግሎቱ ዘንድሮ በተለይ በተማሪዎች የሚከናወኑ ተግባሮች ለዜጎችም ለሀገርም ወሳኝ ናቸው። የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት ማደስ ወይም በአዲስ መልክ መሠራት፣ ተማሪዎችን ለመጪው የትምህርት ዘመን ማዘጋጀት፣ ወዘተ ማከናወን ብቻ አይደለም ራሳቸውንም የሚገነቡበት ሁኔታ ይፈጠራል። ተማሪዎች በወሰን ተሸጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ20 ሺ በላይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለአንድ ወር ቆይታ ያደርጋሉ። በዚህም ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ራሳቸውም ከሚቆዩበት ማኅበረሰብ ብዙ የሚወስዱት ይኖራቸዋል ተብሎ ታሳቢ ተደርጓል።
ተማሪው ሀገር ውስጥ ያለውን እምቅ አቅም መረዳት ይችላል፤ የሌላውን ባሕል እና ቋንቋ፣ አኗኗር የሚያውቅበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠርለታል። የሀገሪቱን ችግሮች እና ፈተናዎች፣ መልካም ዕድሎች መመልከትም ይችላል። አገልግሎቱን አጠናቆ ሲመለስ ጥሩና ሥራ ፈጣሪ ዜጋ እንደሚመለስ ይጠበቃል። ከሌሎች የማኅበረሰቡ አካላት ጋር በመገናኘቱም የሰከነ፣ ያደገ፣ የሠለጠነ ግንኙነት ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል። ይህ ሁሉ ደግሞ ወጣቱን በተለያዩ መልኩ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም ሆኖ ያገለግላል።
ይህ አገልግሎት ነው እንግዲህ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተዘርቶ በክረምት ሰፋፊ ሥራዎች ከማከናወንም አልፎ ሥራው በበጋ ጭምር እንዲቀጥል እየተደረገ ያለው። ይህ ለአቅመ ደካሞች፣ የጤና መታወክ ለደረሰባቸው ወገኖች፣ ለጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለተማሪዎች፣ በአጠቃላይ ለዜጎችና ለሀገር መድኅን እየሆነ የመጣ አገልግሎት የበለጠ ስር እየሰደደ እንዲመጣና የሕዝብና የሀገር አለኝታነቱን እንዲወጣ ለማድረግ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል። ካለው ችግር ብዛት፣ ችግሩን ለመፍታት ካለው ሰፊ አቅም አኳያ ሲታይ አሁን እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ይበልጥ እንዲሰፋ መሥራት ያስፈልጋል፤ ለእዚህ ደግሞ በማስተባበሩ ሥራ ላይ የተሰማሩ ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ ወዘተ ሰፊ ሥራ ይጠብቃቸዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም