አንድ ሰውዬ በድብድብ ወቅት የተጋጣ ሚውን ጣት በመንከሱ ተከሶ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ ዐቃቤ ህጉም ጉዳዩን ያስረዳልኛል ያለውን ምስክር እንዲቀርብ ያደርጋል፡፡ የተከሳሹ ጠበቃ ለምስክሩ እንዲህ የሚል ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ‹‹ደንበኛዬ የከሳሽን ጣት ሲነክስ ዓይተሀል›› ምስክር‹‹ አይ አላየሁም›› ብሎ ይመልሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ጠበቃው ‹‹ እና በምን እርግጠኛ ሆንክ እሱ መንከሱን›› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ምስክርም ‹‹ አይ ሲተፋው ተመልክቼ›› ብሎ መለሰ።
ከላይ የተቀመጠው ታሪክ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ባለስልጣናት የፍልስጤምን የሰላም ስምምነት እቅድ ከመተግበሩ በፊት ምንም ዓይነት አስተያየት እንደማይሰጡ የተናሩ ቢሆንም የሰላም ስምምነቱ ተግባር ላይ መዋል አለበት በማለታቸው የተሰጠ ነው፡፡ በፍልስጤምና እሥራኤል ጉዳይ ባለፉት ሁለት ዓመታት አሜሪካ የተለያዩ ፖሊሲዎችን ስታወጣ ቆይታለች፡፡ ፖሊሲዎቹ ፍልስጤም በአረብ አገራት ውይይት መድረክ ላይ ውድቀት እንዲገጥማት ያለመ ነበር፡፡ ኢየሩሳሌም የእሥራኤል ዋና ከተማ መሆኗን እውቅና በመስጠት፣ በዋሽንግተን የሚገኘውን የፍልስጤም ሊብሬሽን ድርጅት ፅሕፈት ቤትን በመዝጋት፣ ለፍልስጤም ስደተኞች ይሰጥ የነበረውን ዕርዳታ በማስቆም፣ የተለያዩ ማዕቀቦች ቢጣሉም እሥራኤልን ያስደሰተ ባለመሆኑና የእሥራኤል ፍላጎት በማደጉ የትራምፕ አስተዳደር አሥራኤል አጠቃላይ የፍልስጤምን ይዞታ መቆጣጠሯን ዓለም አቀፍ አገራት እንዲያውቁ ጥረት አድርጓል፡፡
በጉዳዮቹ ላይ ፍልስጤም እንደማትስማማ ተቃውሞዋን ያቀረበች ሲሆን ህጎቹ ለውይይት የቀረቡበት ስብሰባዎች ላይ ሳትገኝ ቀርታለች ነገር ግን የተለያዩ አረብ አገራት በተደጋጋሚ ፍልስጤም አገራዊ መብቷ መከበር አለበት ብለው ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ በተለይ በተያዘው ሳምንት በባህሬን የሚካሄደው ወርክ ሾፕ ላይ ድጋፋቸውን ለማሳየት ዝግጅት አድርገዋል፡፡ በወርክ ሾፑ የገንዘብና የእትማማች አገራት ስምምነት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አስርት ዓመታት የዘለቀው የአረብ አገራቱ ውድቀት
ከሰባ ዓመት በፊት አረብ አገራት ከእሥራኤል ጋር የጅዊሸ አገር እንዳይመሰረት ጦርነት ካደረጉ በኋላ ውድቀታቸው እየተፋጠነ መጥቷል፡፡ የእሥራኤል አገር መሰረት የሆነው ደግሞ የፍልስጤም ይዞታ ነበር፡ ፡ አረብ አገራት ጉዳዩን በኃይል ለመፍታት ተደጋጋሚ ጦርነት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ በሌላ በኩል ከእሥራኤል ጋር የፍልስጤምን ጥያቄ ይዘው በዲፕሎማሲ መንገድ ቢሞክሩም አልተሳካቸውም። ለግማሽ ምዕተ ዓመታት በአሜሪካና በእሥራኤል ትብብር የሰላም ድርድር ለማድረግ የሚቀርቡ ሃሳቦችን አረብ አገራት በጥርጣሬ እያዩት ይገኛል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት የእሥራኤልን ፍላጎት ለማስፈፀም የሚያደርገው ጥረት በሰላም ስምምነቱ ላይ ጥላ አጥልቷል፡፡
በአሁን ወቅት ደግሞ የፂዮኒስት ዋነኛ ደጋፊዎች በተለይ ጃሬድ ኩሽነር ፣ ጄሰን ግሪንብላት እና ዴቪድ ፍሪድማን የትራምፕ አስተዳደርን ዲፕሎማሲን በመዘወር እሥራኤል በፍልስጤም ላይ እየተከተከች ያለችው ፖሊሲ ትክክለኝነት እየሰበኩ ይገኛሉ፡፡
በሌላ አነጋር የፍልስጤም ጉዳይ እልባት የማግኘቱ ጉዳይ ያልተሳካ መሆኑ ሲሆን አብዛኛዎቹ አረብ አገራት የፍልስጤምን ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ እንዲያገኝ የመሥራት ፍላጎት አላቸው፡፡ ነገር ግን ለምን የፍልስጤምን ነፃ አገር የመሆን መብት ማክበር እንዳልፈለጉ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ለምሳሌነት ቢነሳ የሳውዲ፣ የአረብ ኢምሬት እና የባህሬን መሪዎች የአሜሪካንን ሰላም ስምምነት በመደገፍ በባህረሰላጤው አካባቢ ያላቸውን ኃያልነት ለማስጠበቅ እየጣሩ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም እሥራኤል በኢራን ላይ ያላትን ጥላቻም ደግፈው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ይታወቃል፡፡ ጆርዳንና ግብፅ ደግሞ የአሜሪካንን ጥሪ እንቢ ለማለት አቅም ያነሳቸው ሲሆን በተለይ የትራምፕ አስተዳደር ላደረጉት ትብብር የገንዘብ ድጋፍን ተስፋ አድርገው እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡
ነገር ግን ዴሞክራሲ ያልሰፈነባቸው የአረብ አገራት ቅድሚያ እየሰጡ የሚገኙት የእራሳቸው እንጂ በአካባቢው ስለሚኖረው አንድነትና መረጋጋት አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ በፍልስጤም ያለው ሁኔታ ለማሳያነት መቅረብ ይችላል፡፡ ሁሉንም አገራት ህዝባዊ ድጋፍ፣ ብሔራዊ ታማኝነት እና ክልላዊ አንድነት ያጡ በመሆናቸው እነዚህ አካላት ድጋፍ እና ጥበቃ ለማግኘት ወደ አሜሪካ ተመልሰዋል ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ የሚያስገርመው ነገር የአረቡ ዓለም ሰዎች ለአሜሪካ የተለያየ ስሜት እና ታማኝነት አላቸው፡፡
የፍልስጤም ትርጉም
ባለፈው ምዕተ-ዓመት በተካሄደው የአረብ እና የሙስሊም ዓለም ክፍሎች ቅኝ ግዛት፣ ፓንአረቢዝም፣ እስከ እስልምና ማስፋፋት እንዲሁም ከለውጥ አራማጅነት ወደ ለውጥ ቀልባሽነት መመለስ ሂደት ውስጥ ፍልስጤም ጭቆናን የማትቀበል አገር ተደርጋ እንደ ምልክት ትታያለች፡፡ የአረቦችና ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ መሪዎች የፍልስጤምን አለመረጋጋት ለራሳቸው ጥቅም እያዋሉት ይገኛሉ፡ ፡ በእርግጥ የፍልስጤምን እና የኢየሩሳሌም ጉዳይ በንግግር ለመፍታት የነበሩ ፍላጎቶች በተደጋጋሚ ቢገፋም ለረዥም ጊዜ በአገር ውስጥ እና ክልላዊ ህጎችን በጠበቀ መንገድ የተከናወነ አልነበረም፡፡
ለምሳሌነት ቢታይ የኢራን መሪዎች እና በሳውዲ የውሃቢይ መሪዎች በብዙ ነገር መስማማት ባይችሉም በፍልስጤምና በኢየሩሳሌም ጉዳይ ግን ድጋፋቸውን አሳይተዋል፡፡ እአአ 1979 ከነበረው የኢራን ለውጥ በኋላ የአያቶላህ መሪ ሮሃላህ ኮሜኒ የፍልስጤም ጉዳይ የሁሉም አረብ አገር ጉዳይ ነው በሚል አል ቁዱስ በሚል በየዓመቱ የሚከበር በዓል ሰይሟል፡፡
በተመሳሳይ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት የሳውዲ መሪዎች በፍልስጤም የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን ስፖንሰር ያደርጉ ነበር፡፡ እአአ 2018 የአረብ ሊግ ስብሰባ በሪያድ አል ቁዱስ በሚል ተከናውኗል። ስብሰባው ከተካሄደ ከወራቶች በኋላ ግን የተወሰኑ አረብ አገራት ኢየሩሳሌም የእሥራኤል ዋና ከተማ ናት ብለው እውቅና ሰጥተዋል፡፡ በተመሳሳይ በፍልስጤም ጉዳይ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ የነበሩ ሰዎች ደግሞ እስከ ህይወት መስዋትነት ከፍለዋል። ለአብነት የጆርዳኑ ንጉሥ አብደላ እአአ 1951፣ የግብፁ ፕሬዚዳንት አንዋር አል ሳዳት እአአ 1981 እና የሊባኖን ፕሬዚዳንት በሽር ገማይል እአአ 1982 መጥቀስ ይቻላል፡፡
የነፃነት ምልክት
አብዛኛው የአረብ አገራት መሪ በፍልስጤም ጉዳይ ተንኮል ወይም ዕድል አስበው የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ አረብ አገራት ያለ አንዳች እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለትራምፕ አስተዳደር እያሳዩት ባለው ትብብር ብዙ ነገር መማር አለባቸው፡፡ አብዛኛው አረብ አገራት ፍልስጤምን ጨምሮ በፍልስጤምና በኢየሩስሳሌም ጉዳይ አቋማቸውን በአግባቡ ባለማሳወቃቸው ምክንያት እሥራኤል አካባቢውን እንድትቆጣጠር ረድቷታል፡፡ የፍልስጤምና የኢየሩሳሌም ጉዳይ ከመጠን በላይ የሆነው በአቀማመጥና በፖለቲካል እንቅስቃሴ የተሳሰሩ በመሆናቸው ሲሆን በተጨማሪም ፍልስጤማውያን ኢየሩሳሌም የትውልድ ስፍራችን ነው ብለው የሚያምኑ በመሆናቸው ነው፡፡
ለአስርት ዓመታት ፍልስጤም ከውጭ ወራሪዎች ማለትም ከእንግሊዝ፣ ከፈረንሳይና ከአሜሪካ እራሷን ጠብቃ ስለኖረች የነፃነት ምልክት ተደርጋ ትወሰዳለች። ከመቶ ዓመታት በፊት እንግሊዝ ከፍልስጤም የጅዊሾችን መኖሪያ እንደምታስመልስ ቃል ገብታለች። በወቅቱ የጅዊሾች ቁጥር በኢየሩሳሌም አስር በመቶ ነበር፡፡ በአሁን ወቅት ደግሞ አሜሪካ ኢየሩሳሌም የጅዊሽ ዋና ከተማነቷን እውቅና ሰጥታለች፡፡ የአረብ አገራት እውቅናውን ከእሥራኤል መስፋፋት ጋር በማያያዝ ፍልስጤም በምዕራባዊያን እጅ ወድቃለች ብለው ያስባሉ፡፡ ይህ ሁልጊዜ በምዕራቡ ኃያላን እና በአንድነት ላይ የማያቋርጥ ጥላቻ ምንጭ እንዲኖር አድርጓል፡፡ የሳውዲዎች እና የኢራኖች፣ የአፍጋኒስታን እና የፓኪስታን አሊያም ሙስሊሞች በፖለቲካ ወይም በርዕዮተ ዓለም የማይስማሙ ቢሆኑም በፍልስጤም ጉዳይ አንድ በመሆን በአሜሪካንና በምዕራባዉያን ሊሰነዘርባቸው ለሚችሉ ጥቃቶች ቀድመው መከላከል ይችላሉ፡፡
የአረብና የፍልስጤም ጥምረት
እንደ ቀድሞ የፍልስጤም የለውጥ እንቅስቃሴ አሁን ያለው የፍልስጤም ህዝባዊ ተቃውሞ ለብዙ አረብ አገራት ህዝቦች የነፃነት ትግል ምክንያት ነበር፡ ፡ አብዛኛው የአረብ አገር ወጣት የተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎችን በመምራት ከአስር ዓመት በፊት የተጀመረውን የአረብ ፀደይ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ የአረብ ህዝቦች የመሪዎቻቸውን ጭካኔ ለመግለጽ የፍልስጤምን አካሄድ መርጠው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በፍልስጤም ብቻ የሚታወቀው የህዝብ ተቃውሞ ቀስ በቀስ ጊዜውን ጠብቆ በአብዛኛው አረብ አገር ላይ ተከስቷል፡፡
ዛሬ የአረብ አንድነትና አለመግባባት የሚታይበት እና የአረብ መንግሥታት እጅግ በጣም አስከፊ በሆነ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ ካሉበት ችግር ለመውጣት በቅድሚያ አሜሪካንን የማስደሰት ፍላጎታቸው ጨምሯል፡፡ በአረብ አገራት ብጥብጥ ውስጥ እጃቸው ያለበት ሰዎች ከእሥራኤል ጋር ሰላም ለማውረድ እየተጉ ይገኛሉ፡፡ የትራምፕ አስተዳደር በአረብ አገራ ዋና ከተማዎች ላይ የሚታዩትን ችግሮችና የፍልስጤምን ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት እየሠራ ይገኛል፡፡የትራምፕ አስተዳደር ከተሳካለት ፍልስጤም፣ አረብ አገራትና ሌሎች የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ አገራት አንድ ሆነው የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ፖለቲካን እንዲያስተካክሉ ይፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2011
መርድ ክፍሉ