አሁን ላይ ብዙ ነገሮች የተቀየሩ ይመስላል። ቀድሞ በኑሮ ልማድ ህግና መመሪያ የወጣላቸው ጥቂት እውነታዎች ዛሬ በነበር ተረስተዋል። በእርግጥ ጊዜ ጊዜን በተካው ቁጥር የምንጠብቃቸው ለውጦች አይጠፉም። በሂደት አሮጌው በአዲስ መተካቱ፣ የቀደመው በሚከተለው ታሪክ መቀየሩ ግድ ይላል። አንዳንዴ ግን ያልተገቡ ጉዳዮች እንደዋዛ ህግ ሆነው ሲጸኑ ለምን? ማለት ያስፈልጋል።
ጉዳዬን ‹‹ድሮ፣ ድሮ …›› እያልኩ ማስታወስ አልሻም። የማነሳው ርዕስ እምብዛም ዓመታት ባለመሻገሩ አባባሉን መጠቀም አያሻኝም። ከጥቂት ጊዜያት በፊት በተለይም ማህበራዊ ሚዲያ ይሉት ልምድ ከመስፋፋቱ አስቀድሞ ለህግና ልማድ ትኩረት ይሰጥ ነበር ብል እያጋነንኩ አይደለም። ማንም ያለወጉ አሰራርን ጥሶ ቢገኝ ለምን ይባላልና መስመሩን ለማለፍ አይዳፈርም።
ወደዘመናችን የየዕለት ልማድ ልመለስ። አሁን ላይ ማንም ተነስቶ የሰዎችን ስም ቢያጠፋ፣ እንዳሻው አስተያየት ቢጽፍ፣ ምስልና ፎቶግራፍ ለጥፎ መዛበቻ ቢያደርግ የሚገስፁ፣ የሚቃወሙት ምናልባትም በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው።
ይህን ከሚያደርጉት ባሻገር አብዛኞቹ እንደወደቀው ዛፍ ምሳር ለማንሳት የሚጣደፉ ይሆናሉ። እንደውም አንዱ በሰጠው ሃሳብ ተመርኩዘው የማይነቀል ስር የሚመዙት ይበረክታሉ። የአብዛኞቹ አስተያየት በክፉ ከተጀመረ ደግሞ ቀጣዩን ለመረዳት አይቸግርም። የእነሱን ፈለግ ተከታዩ በእጥፍ ይበረክታል።
ይህ አይነቱ አጋጣሚ ሲፈጠር አንዳንዶች ሆን ብለው የተዘጋጁ ይመስላል። ዞር ብሎ ከማስተዋል ይልቅ ‹‹በለው እንበለው››ን ይዘው መድረኩን የፍልሚያ ሜዳ ያደርጉታል። ተደገግሞ እንደሚስተዋለው አብዛኞቹ ጉዳዩ ስለተነሳ ብቻ የውስጣቸውን ለመዘርገፍ እንጂ ሃሳቡ ከመነሻው ገብቷቸው አልያም ተቆርቋሪ ሆነው አይደለም።
እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ምንጊዜም ለልማደኞቹ አእምሯዊ ባዶነታቸውን ያጋልጣል፣የወሬ ሱሰኝነታቸውንም ያሳያል። ከምንም በላይ ግን ለሚያልፍ ቀን፣ የማያልፍ ክፉ ታሪክ መከተባቸው የህይወታቸው ማፈሪያ ታሪክ ሆኖ በመዝገባቸው ይከተባል።
እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ማህበራዊ ሚዲያውን በጎ ባልሆነ መንገድ የሚጠቀሙ ሰዎችን ልምድ አመላካች ነው። የዚህ አይነቱ ልማድ መበራከት ደግሞ አስቀድሜ ተለምዷዊ ህጋችን እየተጣሰ ነው ላልኩበት ጉዳይ እንደማሳያ ሊሆን ይችላል።
በቅርቡ አንዲት ወጣት አንድ የቤት መኪናን ከቆመበት አስነስታ ዘርፋ ስለመውሰዷ ወሬው ሲመላለስ ቆይቷል። ጉዳዩ እንዲህ መሆኑ ብቻ አይደለም። መኪናውን ሰርቃለች የተባለችው ሴት ፊቷ ሳይሸፈን፣ ስሟ ሳይደበቅ በየሁሉም ገጽ ውርጅብኝ ስታስተናግድም ነበር።
አሁን ላይ ለምን እንደሚደጋገም ባላውቅም እንዲህ አይነት ታሪኮች በግልጽ እየተለጠፉ ነው። በህግ አግባብ እንደተጠቀሰው ግን ማንም ሰው ክስ ቀርቦበት፣ማስረጃ ተደራጅቶበት፣ ጥፋተኛነቱ ተረጋግጦ በፍረድ ቤት እስካልተወሰነበት ድረስ ወንጀለኛ ነው ሊባል አይችልም። በእርግጥ ይህችው ሴት ቆየት ብሎ ክስ እንደተመሰረተባት ተሰምቷል።
ይህ እንኳን ቀድሞ ቢታወቅ ማንነቷን እያነሱ ለመወቅስ በቂ አይሆንም። ውሎ አድሮ የሚገኘው ውጤት ምን እንደሆነ አይታወቅምና ተጣድፎ ስም ማንሳቱ ተገቢ አይሆንም።
አንድ ሰው በዚህ አይነቱ ድርጊት ተሳትፏል ተብሎ ቢያዝ ‹‹ተጠርጣሪው›› እየተባለ ይጠራል እንጂ እንደወንጀለኛ በአደባባይ ፊቱ ተጋልጦ ስም ከነአባቱ እየተጠራ ‹‹እዩት፣ ፍረዱበት›› አይባልም። አሁን ላይ ግን ይህ ይዘነው የቆየነው ተለምዷዊ ህጋችን ተጥሶ በሌላ ታሪክ ተተክቷል። ዛሬ አንድ ሰው ድርጊቱን ይፈጽም፣ አይፈጽም ሳይታወቅ በድንጋይ ሊወግሩት፣ የሚሰለፉ በርካቶች ናቸው። ታሪኩን ከስር ከማጥራትና ቆም ብሎ ከማሰብ ይልቅ ሞራል እየነኩ፣ጾታና ማንነትን እያንቋሸሹ፣ ሰድቦ ለሰዳቢ የሚሰጡ ብዙ ናቸው።
ወዳጆቼ! ይህን ሃሳብ ስሰነዝር ድርጊቱን በትክክል የፈጸሙትን ሰዎች ተግባር እያበረታታሁ አይደለም። እውነታው ቀድሞ አይታወቅም እንጂ በአስነዋሪ ታሪክ የሚያልፉ አጥፊዎች ሁሉ ማንነታቸው ቢጋለጥ በእጅጉ ደስ ይለኛል። እስከዛሬ በዚሁ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ብዙ ታሪኮችን አይተናል፣ሰምተናል።
ታሪኮቹ ለሌሎች እስካስተማሩ ድረስ መታየት መሰማታቸው ችግር የለውም። የእኔ ተቃውሞ ግን ጉዳዩ በህግ ሳይረጋገጥ አንዱ ሰው በግል ስልኩ አንስቶ ስለለጠፈው ብቻ ውርጅብኝና ኩነናው ለምን? የሚል ነው። በአንዳንዶች ዘንድ ጥንካሬው ስለሌለ እንጂ እንዳደጉት ሀገራት ተሞክሮ መፍትሄ ቢገኝ እሰዬው ነው።
ከደሙ ንጹህ ሆነው በአጉል ፍረጃ በአደባባይ ስማቸው የጠፋ፣ምስላቸው የተለጠፈ ተጎጂዎች መረጃ ቆጥረው ከሳሾቻቸውን በህግ ፊት ማቆም በቻሉ ነበር። ይህን የሚያደርጉ ጠንካሮች በተበራከቱ ቁጥር ብዙዎች ከተለምዷዊ ስህተታቸው ይመለሳሉ፣ ካልታረመ አንደበታቸውም ይቆጠባሉ። አሁን ላይ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለጠፉትን መረጃዎች አንዳንዴ ፖሊስ ጭምር ሲጋራው እያስተዋልን ነው።
አሁንም ድርጊቱን የፈጸሙት ተጠያቂነታቸው እንዳለ ሆኖ በጥድፊያ የሚወጡ መረጃዎች ሊታሰቡበት ይገባል። ባይ ነኝ። በተለይ ፖሊስ በራሱ አርማና ባለሙያዎች የተረጋገጡ መሰል መረጃዎችን ማውጣቱ አንባቢው ያለምንም እማኝነት ድርጊቱ ትክከል ነው ብሎ እንዲያምን ያስገድዳል።
እኔ እስከማውቀው በተለይ የፖሊስ መረጃዎች ምንጊዜም ተጠርጣሪነትን የሚያስቀድሙ ናቸው። ‹‹ተጠርጣሪ›› የተባለው አካል ውሎ አድሮ በህግ ፊት ወንጀለኛነቱ እስካልተረጋገጠ ምስሉም ሆነ ሙሉ ስሙ ገሀድ ሆኖ አይታይም። ቀደም ባሉ ዓመታት በነበሩ ተሞክሮዎች እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ሲከሰቱ የግለሰቦች ምስል ያለአንዳች መደባበቅ በአደባባይ እንዲታይ ይደረግ ነበር።
ተጠርጣሪ ሆነው የቆዩ ሰዎች ውሎ አድሮ ህግ ነጻ ሲያወጣቸው ግን መልሰው የሚመለከተውን አካል በስም ማጥፋት ወንጀል ለመክሰስ መንቀሳቀሳቸው አይቀርም። ግለሰቦቹ ፈጽመውታል ከተባለው ድርጊት ጀርባ የራሳቸው ህይወት አለ። ቤተሰብ፣ ማህበረሰብና ማህበራዊ ህይወት ይሏቸው እውነታዎችም ተጽዕኖ ደርበው መምጣታቸው ግድ ይላል።
ይህን ሀቅ ተሻግሮ ጸንቶ ለመቆም ታዲያ ‹‹ከአፍ ከወጣ አፋፍ›› ይባል ተለምዶን በቀላሉ መቀልበስ የዋዛ አይሆንም። ህግ ነጻ ቢያወጣቸውም ከሌሎች ጋር እንደትናንቱ ተቀላቅሎ ለመኖር ያለፉበት መንገድ ተጽዕኖው የጎላ ነው።
‹‹ተጠርጣሪ›› ሆነው መቆየት ሲገባቸው ማንነታቸው በወንጀለኛነት ተጋልጦ በየሚዲያ ታይቷልና የሞራል ስብራታቸው ይልቃል። እንዲህ አይነቶቹ አጋጣሚዎች ሲደጋገሙና ተጠያቂነቱ ሲበዛ ያለ ህግ ውሳኔ የማንም ሰው ፊት ተጋልጦ እንዳይታይ ሆኖ መተላለፍ ያለበት መረጃ ብቻ ተደራሽ ሲደረግ ቆይቷል።
ይህን እውነት ወደዘመናችን አምጥተን ስናየው ደግሞ ችግሩ በእጥፍ ገዝፎ ይታያል። ዓለም በአንድ መስኮት በሚተያይበት ቅርበት በቀላሉ የሰዎችን ስም በማንሳት፣በገሀድ ምስላቸውን ለጥፎ ያሻውን ለማለት መንገዱ አጭርና ቀላል ነው።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ አይነቱ ሀቅ በግልጽ እየተስተዋለ ነው። አንዳንድ ሰዎች ህይወት አጠፉ፣ ሰረቁ፣ አጭበረበሩ ከመባላቸው አፍታ ምስላቸው ከነሙሉ ስምና ታሪካቸው ገሀድ ይሆናል። አሁንም ድጋሚ እንደምለው የሰዎቹን ድርጊት እያበረታታሁ አይደለም። የእኔ ስጋት ከዚህ ጥድፊያ ጀርባ የሰዎቹ ታሪክ ሀሰትና ስህተት ሆኖ ቢገኝ ማካካሻው ምን ይሆናል እያልኩ ነው።
ለማንኛውም የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን የሰከነ ቢሆን እንማርበታለን እንጂ አንከስርበትም። በጥድፍያና በወሬ ወዳድነት፣ ቅድሚያውን ለመያዝ የምናደርገው ሩጫ ግን የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል ይሉትን ብሂል በራሳችን ላይ ከማስተረት ያለፈ የሚጠቅመን አይሆንም። ቆምብሎ ማሰብ ለራስም፣ ለሌላውም ይበጃልና።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም