ኦሮሚያ ክልል ምቹ የአየር ፀባይና የተፈጥሮ ፀጋ ካላቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ይህም ምቹ ሁኔታ ለተለያዩ እንስሳት ዝርያዎች እርባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ይታመናል፡፡ በክልሉ በአሁኑ ወቅት 25 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ የዳልጋ ከብቶች፣ 10 ሚሊዮን በጎች እና ስምንት ነጥብ ሁለት ፍየሎች ባለቤት መሆኑን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።እንዲሁም ሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጋ የንብ መንጋ ያለ ሲሆን የዓሳ ምርትም 38 ሺ 500 ቶን በየዓመቱ የሚመረቱበት ክልል ነው፡፡
ይህም እንደሀገር ላለው የእንስሳት ሀብት ድርሻ ከፍተኛ እንዲሆን ያደረገው መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቶሌራ ደበላ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በክልላችን ያለው የእንስሳት ሀብት ክምችት ለክልልም ሆነ ለሀገር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፤ የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው›› ይላሉ፡፡ በተጨማሪም የእንስሳት ዘርፉ ከስራ እድል ፈጠራ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡
ይህንን ሀብት በተጨባጭ ጥቅም ላይ ከማዋልና የእንስሳት ሀብቱን ምርታማነት ለማጎልበት ቢሮው ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ዋነኛው ስራ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ ክልሉ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት አንድ ሚሊዮን 500 እንስሳት ዝርያ ማሻሻል ስራ ለመስራት አቅዶ፤ እስካሁን በተሰራው ሥራ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን 637 ሺ የእንስሳት ዝርያዎችን በማሻሻል ከተያዘው እቅድ በላይ መከወን ችሏል፡፡ በተጨማሪም 250 ሺ 590 ጥጆች ይወለዳሉ ተብሎ በእቅዱ ተይዞ የነበረ ሲሆን እስካሁን ድረስ ወደ 300 ሺ ጥጆች መወለዳቸውን አቶ ቶሌራ ያስረዳሉ፡፡
‹‹ይህም ከእቅዳችን አንፃር 120 በመቶ ማሳካት መቻሉን ያሳያል፤ በሌላ በኩል የዝርያ ማሻሻል ስራው ክልሉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በሠራው ሥራ የተገኘ ውጤት ነው›› ይላሉ፡፡ ይህም ይሳካ ዘንድ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለባለሙያዎች መሰጠቱን ጠቅሰው፤ በዋናነትም ለእንስሳት አዳቃይ ቴክኒሻኖች ልዩ ትኩረት በመስጠት ስልጠና መሰጠቱን ነው የሚጠቁሙት፡፡ አርሶ አደሮችም በዚህ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል፡፡
‹‹ይህንን ስራ ስንሰራ ቶሎ ከብቶቹ ፍላጎት እንዲያሳዩ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ነው እንዲዳቀሉ የተደረገው›› የሚሉት ምክትል ኃላፊው፤ እንደክልል በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ʻአንድ አመት እንደ አምስት አመት አምስት እንደ 25 ዓመት’ በሚለው መርሀ ግብር አማካኝነት አሰራርን የማዘመንና ምርታማነትን ከጊዜው ቀድሞ የመከወን፤ የማሳካት ሂደት መከተሉን ያመለክታሉ፡፡ ይህም ሲባል በአምስት ዓመት የታቀደውን እቅድ በአንድ አመት ማከናወን የሚቻልበት ሂደት መኖሩን ነው ያስረዱት፡፡ በዚህም ክልሉ ካለው ስፋትና የህዝብ ቁጥር አንፃር እቅዱን ለማሳካት ርብርብ መደረጉንም ይጠቁማሉ፡፡
ለዚህም አብነት አድርገው ሲጠቅሱ ‹‹በአምስት ዓመት ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ከብቶች ላይ የዝርያ ማሻሻያ ስራ እንሰራለን ብለን አቅደን የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ እንደክልል በተቀመጣው አቅጣጫ መሰረት በአመት ውስጥ ብቻ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ከብቶች ላይ የዝርያ ማሻሻል ስራ ሰርተናል›› በማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል የክልሉ ሰፊ አካባቢ ቆላማና አርብቶ አደር የሚበዛበትና ድርቅ የሚያጠቃው እንደመሆኑ በተጨባጭ ምን ያህል ውጤት መጥቷል ማለት ይቻላል? ተብለው የተጠየቁት ምክትል ኃላፊው ተጠይቀው ‹‹ቆላማ የኦሮሚያ ክልል አካባቢ ድርቅ ያጠቃዋል፤ በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከፍተኛ ችግር ነበር፤ ይህንን ችግር ለመፍታት እንደክልል በተቀመጠ አቅጣጫ መሰረት ድርቅን የመከላከልና የመቋቋም አቅም ለማሳደግ ርብርብ ስናደርግ ቆይተናል›› ይላሉ፡፡
በተለይም የውሃ ማቆር ስራ ቆላም በመሆኑ አካባቢዎች በስፋት መሰራቱን ይጠቅሳሉ፡፡ በተመሳሳይ የውሃ ፕሮጀክቶችን በማቀናጀት ለሁሉም አርብቶ አደሮች ተደራሽ እንዲሆን ርብርብ መደረጉን ያስረዳሉ። ከዚሁ ጎን ለጎንም የመኖ ልማትን በማጠናከር በድርቅ የሚጎዱትን እንስሳቶች ቁጥር መቀነስ መቻሉንም ያመለክታሉ፡፡ በዝርያ ማሻሻል ረገድም ቆላማ አካባቢ በተለየ መልኩ ሲሰራ መቆየቱን አቶ ቶሌራ አስታውሰው፤ የተለያዩ ትላልቅ መጋዘኖችን በመስራትና የመኖ ክምችት እንዲኖር በማድረግ የነበረውን ችግር ለመፍታት ጥረት ተደርጓል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
‹‹ይህም አንደኛ በቆላማ አካባቢዎች ላይ የግጦሽ መሬት ማሻሻያ ሥራ የተሰራ ሲሆን በተለይ አላስፈላጊ የሆኑ እፅዋቶችን እያፀዱ የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን ለማስፋፋት ጥረት ተደርጓል›› ይላሉ አቶ ቶሌራ፤ ይህም ስራ በዘመቻ መልክ የተከናወነ በመሆኑ ከዚህ ቀደም በቆላማ አካባቢ የሚስተዋለውን የመኖ እጥረት ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ማሻሻል መቻሉን ነው የሚያመለክቱት። ‹‹ቦረና፣ ምሥራቅ ኦሮሚያ ላይ አላስፈላጊ እፅዋቶችን የማስወገዱ ሥራ በዘመቻ መልኩ በመሰራቱ ከፍተኛ ለውጥ አለ፤ የተለያዩ የመስኖ ዝርያዎችን በማሰራጨት ወደ ልማት የተገባ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ይገኛል›› ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሰፊ ጥረት እየተደረገ የመሆኑን ያህል ለአርሶና አርብቶ አደሩ የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ሰፊ ክፍተት መኖሩ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ክልል ተሞክሮ ምን ይመስላል? በተለይ የተመረቱ የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶችን በቀጥታ ወደ ተጠቃሚው ለማድረስና አምራቹ ኃይል የልፋቱን ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ ስለተደረገው ጥረት አቶ ቶሌራን ጠይቀናል። እንደእርሳቸው ማብራሪያ ከሆነ፤ በክልሉ ከመደበኛ የግብርና ስራ በተጨማሪ በሌማት ቱሩፋት መርሀ ግብርም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት ተደርጓል፡፡
ከእነዚህም መካከል የወተት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ሲሆን እንደ ክልል ሶስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ሊትር ወተት የማምረት አቅም መጎልበቱን ያብራራሉ፡፡ በመጠናቀቅ ላይ ባለው በጀት ዓመትም የሰኔ ወርን ሳይጨምር ሶስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ሊትር ወተት መመረቱን ጠቁመዋል፡፡ ይህም ከተያዘው እቅድ አንፃር 92 በመቶ ማሳካት መቻሉን ያመላክታል፡፡
በበጀት ዓመቱ በዶሮ እርባታ ረገድ እንደ ክልል 20 ሚሊዮን የዶሮ ጫጩት ለማሰራጨት ታቅዶ እንደነበር አቶ ቶሌራ አመልክተው፤ በተደረገው ቅስቀሳና ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በገጠር የክልሉ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን በከተሞችም ጭምር ያሉ ነዋሪዎች በዘርፉ በመሰማራታቸው 42 ሚሊዮን ዶሮ ማሰራጨት መቻሉን ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ምርት በመጨመሩ የእንቁላል ዋጋም ቀላል በማይባል ሁኔታ ቅናሽ ማሳየቱን ያብራራሉ፡፡ ይህም የክልሉን የግብርና ውጤቶች ላይ ይታይ የነበረውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት እንዳስቻለም ይጠቅሳሉ፡፡
እንደምክትል ኃላፊው ማብራሪያ፤ በበጀት ዓመቱ ክልሉ የማር ምርትን ለማሳደግም ሰፊ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በተለይም በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር አማካኝነት አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ዘመናዊ ቀፎ ለማሰራጨት ታቅዶ የነበረ ሲሆን እስካሁን ድረስ 971 ሺ ዘመናዊ ቀፎ ለአርሶ አደሮች እና ለአርብቶ አደሮች ተሰራጭቷል፡ ይህም የእቅዱን 97 በመቶ ያህሉን ማከናወን መቻሉን ያመላክታል፡፡ በዚህ መሰረት የማር ምርትም በዓመት 113ሺ221 ቶን ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ሲሆን 117 ሺ 800 ቶን ማር ማምረት ተችሏል፡፡
ከዚህ አንፃር ከእቅድ በላይ ማሳካት የተቻለው አመራሩና ባለሙያው በቅንጅትና በንቅናቄ በመስራታቸው እንደሆነ ምክትል ኃላፊው ያስረዳሉ። ‹‹ይህንን ስራ ስንሰራ በሞቢላይዜሽንና የንቅናቄ መድረኮችን አዘጋጅተን በየተዋረዱ ተናበን በመንቀሳቀሳችን ነው ማሳካት የቻልነው›› ይላሉ፡፡ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ በልዩ ትኩረት የዓሳ እርባታ መርሀ ግብር እንደክልል ተቀርፆ መሰራቱን አቶ ቶሌራ አመልክተው፤ በዋናነትም አርሶአደሩ በጓሮው ኩሬ ቆፍሮ ዓሳን የማርባት ባህል እንዲስፋፋ መደረጉን ይጠቅሳሉ። ከዚህ ቀደም ዓሳ በማይታወቅባቸው አካባቢዎች ላይ ባሉ በተለያዩ የውሃ አካላት ዓሳ እንዲራባ መደረጉን ነው ያብራሩት፡፡
በበጀት ዓመቱ በተለይም ከእንስሳት ሀብት ልማት ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮችንና የታዩ ክፍተቶችን በሚመለከት ‹‹በተለይም የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ስራ በበቂ ሁኔታ ያለመከናወኑ ተጠቃሽ ነው፡፡ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የእንስሳት መጠን አሁን ካለበት በላይ ማሳደግ ይጠበቅብን ነበር›› ሲሉ አቶ ቶሌራ ይናገራሉ። የመኖ ልማትም እንዲሁ በክልሉ ካሉ የእንስሳት ሀብት ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝ ያለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የመኖ አቅርቦቱን ለማሻሻልም የክልሉ መንግሥት በኢኒሼቲቭ መልክ እየሰራ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
የእንስሳት ጤና ሽፋን በበቂ ያለማዳረስም ጎልተው ከታዩ ችግሮች መካከል እንደሚጠቀስም ምክትል ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ ዘመናዊ የእንስሳት ቴክኖሎጂ ለአርብቶ አደሩና አርሶ አደሩ በጊዜውና በበቂ ሁኔታ ያለማሰራጨት ሁኔታ ሌላው እንደክፍተት የታየ ጉዳይ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የክልሉ መንግሥት የተለዩ ችግሮችን በቀጣይ በጀት ዓመትም ችግር ሆነው እንዳይቀጥሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ለአብነትም ‹‹ዝርያ ማሻሻል ላይ ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ወደ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ ታቅዷል›› በማለት ይጠቅሳሉ፡፡ የመኖ ልማትም አሁን ካለው መጠን በእጥፍ ለማሳደግ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ርብርብ የሚደረግ ስለመሆኑ ያስገነዝባሉ፡፡
የቴክኖሎጂ አቅርቦት ችግሩን ለመፍታትም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ለመነጋገር ለመፍታት መታቀዱን አቶ ቶሌራ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ መንግሥት ብቻውን እነዚህን ችግሮች መፍታት የማይችል በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለንን ግንኙነት በማጠናከር፤ በመናበብና በማሳተፍ የምንሰራ ይሆናል›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
እንደ ምክትል ኃላፊው ማብራሪያ፤ በኦሮሚያ ክልል በ2017 በጀት ዓመት በዘርፉ ለመከናወን ከታያዙ ዋና ዋና እቅዶች መካከል የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ሥራ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህንንም ሥራ በስፋት ለማከናወን ያስችል ዘንድ ከዞን ጀምሮ እስከ አርብቶ አደርና አርሶ አደር ድረስ እቅዱ ወርዶ መግባባት ተፈጥሮ የሚሰራ ይሆናል፡፡ ከእንስሳት ጤና አገልግሎት ሽፋን አኳያም በዋናነት ለሁሉም እንስሳት የክትባት አገልግሎት መስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ በጥቅሉ በክልሉ የእንስሳት ሀብት ልማትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም