ለከተማዋ ፅዳት የነዋሪነት ግዴታችንን እንወጣ

መዲናችን ሀገር የሚያውቀው ፀሐይ የሞቀው የመጸዳጃ ቤት ችግር አለባት፡፡ ከዚህ የተነሳም በየቦታው ሰው አየን አላየን እያለ የሚሸና ፣ ሸሸግ ያለ ቦታ እየፈለገ ወገቡን የሚሞክር ጥቂት አይደለም። አሁን አሁን ደግሞ በሃይላንድ የውሃ መያዣ ላስቲክ ሽንቱን እየሸና እየከደነ አስፋልት ላይ የሚጥልም እየተበራከተ ነው፡፡

ችግሩ አሁን ላይ ለከተማዋ ጥልቅ ፈተና እየሆነ ነው። ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት በቅርቡ ‹‹ፅዱ ጎዳና ኑሮ በጤና›› የተባለ የዲጂታል ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ አሕመድ አማካይነት ይፋ ሆኗል፡፡ ቴሌቶኑ ችግሩን በመቅረፍ ሂደት ውስጥ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል።

ንቅናቄው በቀዳሚነት ሰዎች በመጸዳጃ ቤት መጠቀም የሚችሉበት እድል ያመቻቻል፤ በመጸዳጃ ቤቱ ተቀጥረው ለሚሠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ያስገኛል፣ የመዲናዋ ጎዳናዎች ጽዱ፣ ውብና መስህብ የተላበሱ እንዲሆኑ፤ ነዋሪውም ሆኑ ጎብኚዎች በከተማዋ ጉዳናዎች በተሻለ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ያስችላቸዋል።

እጃችንን አፋችን ላይ ጭነን የአዲስ አበባ ጎዳና እየተዘዋወርን መዲና እንደስምዋ ሆነች ማለት የሚያስችለንን እድል ይፈጥርልናል፤ ሸተተኝ ብለን እጃችንን አፍንጫችን ላይ ከመጫንም እንታቀባለን፡፡ በቆሻሻ ምክንያት ሊፈጠሩ ከሚችሉ የጤና ችግሮች እራሳችንን መታደግ እንችላለን፡፡

በአዲስ አበባ ከንጉሱ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ፤ በፒያሳ አራዳ ሕንፃ አካባቢ፣ በመርካቶ ሳጥን ተራ ማለትም ከአመዴ ገበያ ሕንፃ ጀርባ፣ በሸራ ተራ፣ በምናለሽ ተራ፣ ወደ መሳለሚያ መንገድ አካባቢ፣ በኳስ ሜዳ፣ በአራዳ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ነበሩ። መጸዳጃ ቤቶቹ በማዘጋጃ ቤት የተገነቡና ተቀጣሪ ሠራተኞች የነበራቸው፤ ለሕዝብ በነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡

አብዛኞቹ አሁን ላይ ተዘግተው ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል፡፡ ‹‹ፅዱ ጎዳና ኑሮ በጤና›› ንቅናቄ ሲተገበር የጠቀስኳቸውን የመሳሰሉ የተዘጉ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች በድጋሚ ታድሰው ለአገልግሎት ብቁ ቢሆኑ ሸጋ ነው፡፡

በተለይም በቅርብ ጊዜ የተገነቡ ለመንገደኞች ሦስት ብር ከፍለው አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አሁንም ያሉ መጸዳጃ ቤቶች አሉ፡፡ የአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ ያለው ችግር እንዳለ ሆኖ ፈረንጆቹ ‹‹አንድ ነገር ከኢምንት ነገር ይሻላል›› እንደሚሉት መኖራቸው በራሱ የሚበረታታ ነው፡፡

መጸዳጃ ቤቶቹ የሚጠይቁት የተጋነነ ክፍያ በራሱ የነዋሪውን የመክፈል አቅም ሆነ የአገልግሎቱን ጥራት ያገናዘበ ነው ወይ የሚለው በራሱ መልስ የሚፈልግ ቢሆንም የመጸዳጃ ቤት አጠቃቀማችን በራሱም ሌላ ምላሽ የሚሻ ነው፡፡ ችግሩ እንኳን በነዚህ መጸዳጃ ቤቶች በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም የሚስተዋል ነው፡፡ በጤና ጣቢያዎችና በሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች ያለውም ከዚህ በብዙ የተለየ አይደለም። ታካሚ ሊጠይቁ ሄደው ታማሚ ሆነው የሚመለሱ አይጠፉም፡፡

ችግሩ በሕዝብ ትራንስፖርት መናኸሪያዎችም በስፋት የሚስተዋል ነው። መናኸሪያዎቹ ብዙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘወትር የሚያስተናግዱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ግን አብዛኞቹ ለተሳፋሪዎች መጸዳጃ አልባ ናቸው፡፡

መቼም ስለመጸዳጃ ቤቶች ስንናገር በከተሞቻችን ያሉ ሻይ ቡና ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች ፣ ኬክ ቤቶች ፣ መጠጥ ቤቶችም ሆነ ሆቴሎችም ጭምር የመጸዳጃ ቤቶቻቸው ለደንበኞቻቸው በአግባቡ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉበት መንገድ መታየት አለበት። አምስት ስድስት ፎቅ ሆቴል ይዘው፤ መጸዳጃ ቤቶቻቸው እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ በየወረዳው ያሉ የሕዝብ መዝናኛ ክበቦችም ትኩረት ሊደረግባቸው ያስፈልጋል፡፡ አብዛኞቹ የሕዝብ መዝናኛ ክበቦች መናኛ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ ብዙ ሰው ቢራውን ድራፍቱን እየጠጣ ከአንድ የዘለለ መጸዳጃ ቤት የላቸውም፡፡ በዚያ ላይ በሁሉም መጸዳጃ ቤቶች የሚታየው ዝርክርክ አሠራር በመናኛ መዝናኛ ክበቦቹ ተባብሶ በስፋት ይታያል፡፡ ከፊሎቹ የሴቶች መጸዳጃ ቤትም የሌላቸው ናቸው፡፡

ችግሩ በመንግሥት ብቻ ሊፈታ የሚችል አይደለም ፤ከሁሉም በላይ አጠቃላይ በሆነው የከተማ ጽዳት ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። እያንዳንዱ የከተማዋ ነዋሪ ከተማዋ ንጹህ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ ሊያገኝ የሚችለውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በአግባቡ የሚያጤንበት ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል። ይህን ማድረግ ከተቻለ ችግሩ ከከተማዋ ነዋሪ አቅም በላይ ሊሆን የሚችል አይደለም።

እስካሁን ባለው ሁኔታ ‹‹ ፅዱ ጎዳና ኑሮ በጤና›› ንቅናቄው ብዙዎች እየተሳተፉበት ነው። በንቅናቄው ከፍተኛ ተሳትፎ ካሳዩ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች መካከል በአቡዳቢና በዱባይ የሚገኙ የዳያስፖራዎች እያንዳንዳቸው በየኮሚኒቲያቸው ስም አንድ አንድ መጸዳጃ ቤቶችን የሚያስገነባ ከ1.5 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ተስማምተዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በበኩላቸው 12 መጸዳጃ ቤቶችን ለማስገንባት ቃል በመግባት፣ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል። እኛም ለዚህ በጎ ዓላማ በመንቀሳቀስ ለከተማዋ ንጽህና የነዋሪነት ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ለዚህ ደግሞ ወቅቱ አሁን ነው።

ይቤ ከደጃች ውቤ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You