ለ33 ዓመታት 98 ጊዜ ደም የለገሱት በጎ ሰው

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ግዴታ ሰዎች ውስጣቸው ከሚሰማቸው ሰብዓዊነትና በጎ አመለካከት ተነስተው ለሚኖሩበት ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ የሆኑ አገልግሎቶችን በነፃ ለማቅረብ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውንና በጎ አመለካከታቸውን ሰውተው የሚሰጡት አገልግሎት ነው::

በዚህ ሂደት ሌሎችን ከመርዳት አኳያ በጎ ፈቃደኞቹ ከማኅበረሰባቸው የሚማሩበትና የሕይወት ክህሎት የሚቀስሙበት እንዲሁም ለተተኪው ትውልድ አርዓያ የሚሆኑበትና የእነሱን ልምድ የሚያስቀምጡበት የአገልግሎት ዘርፍ ነው::

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፅንሰ ሀሳብ እንደየኅብረተሰቡ የዕድገት ደረጃና አካባቢያዊ ሁኔታ የሚለያይ በመሆኑ አንድ ወጥ ትርጉም ባይኖረውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት” የሁሉም ሥልጣኔና ማኅበረሰብ አካልና ውጤት ነው” ይለዋል::

ፅንሰ ሀሳቡ ሲተነተንም የበጎ ፈቃድ አስተዋፅዖ በተለያዩ መስኮች እንያንዳንዱ ሰው ያለ ትርፍ ፍለጋ፣ ያለ ክፍያ፣ ሙያዊ አጽንዖት ባልተጫነው መልኩ ለማያውቋቸው ግለሰቦችና ለሚያውቋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ለማኅበረሰቡና በጠቅላላው ለሕዝብ የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ መሆኑን ያመላክታል:: የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕድሜና ፆታ፣ ማኅበራዊ ደረጃ፣ መልክዓ ምድራዊ ወሰን ሳይገድበው የሰብዓዊነት መርሕን ብቻ መሠረት በማድረግ የሚሰጥ ወይም የሚከናወን ተግባር ነው::

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስፈላጊ የሆነባቸው መሠረታዊ ነጥቦች በርከት ያሉ ቢሆኑም ዋና ዋናዎች ግን የማኅበረሰቡን መልካም ዕሴቶች ማስቀጠል፣ ማኅበራዊ ተሳትፎን ማበረታታትና ማሳደግ፣ ለሕፃናትና ለታዳጊ ወጣቶች አርዓያ (ሞዴል) የሚሆኑ ወጣቶችን ማፍራት፣ በመንግሥትና በኅብረተሰቡ ያልተሸፈኑ የልማትና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ማሟላት፣ ለኅብረተሰቡ ተቆርቋሪና የኃላፊነት ስሜት የሚሰማው ወጣት ትውልድ ማፍራት፣ ታዳጊዎች ከአልባሌ ቦታዎች ርቀው ኅብረተሰቡን ሊጠቅሙ በሚችሉ የሥራ መስኮች የሚሰማሩበትን ዕድል መፍጠር፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውስጥ በመሳተፍ የዜግነት ኃላፊነትን ወጣቶችና ታዳጊዎች እንዲገነዘቡ ማድረግ፣ ሀገራዊና ብሔራዊ ግዴታቸውን እንዲያውቁና በማኅበራዊ ሚናዎቻቸው ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የሀገርንና የወገንን ፍቅር የሚያዳብሩበት ሁኔታ ለመፍጠር ብሎም ችግሮችን ተቋቁመው ጠንካራ የሥራ ፍላጎት አዳብረው ራዕያቸውን ማሳካት እንዲችሉ ማድረግ ይጠቀሳሉ::

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች፣ የዕድሜ ባለፀጎች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ ቤተሰቦች እና ሌሎች ማኅበራዊ ቡድኖች በሀገራዊ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የፖለቲካዊ፣ የባሕልና የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችል ወሳኝ መሣሪያ መሆኑም ሊታወቅ የሚገባው ሐቅ ነው::

አገልግሎቱ እንደየሀገራቱ ታሪክና ፖለቲካዊ ሥርዓት የሚለያይ ሲሆን ማኅበረሰብንና ራስን የሚጠቅም የዕድገትና የብልጽግና ምንጭ መሆኑ በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ነው::

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቁርጠኝነት፣ ፈቃደኝነት፣ ነፃ አገልግሎት፣ ሰብዓዊነት ዓለም አቀፋዊነት የማኅበረሰቡን እሴቶች ማክበር ከሌሎች ለመማር ዝግጁ መሆንን የሚጠይቅ ሥራም ነው::

በተለይም እንደ ሀገር የምንፈተንበትና አንዳንድ ጊዜ አማራጮች እየጠፉ ሰዎች በዘመቻ ሥራ ወጥተው ደም የሚለግሱ አካላትን ሲያሰባስቡ የሚውሉበትን ሁኔታ መጠነኛ ፋታ ከመስጠት አንጻር ሚናው በቀላሉ የሚታይ አይደለም ::

በሀገራችን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተጀመረ ረዘም ያለ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በደም ልገሳና በሌሎች ነገሮች ላይ የሚሳተፉ ፈቃደኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተበራከቱ መጥተዋል::

በጎ ፈቃደኝነት ለሌሎች መትረፍ መትረፍረፍ ነው ሰው በሚችለው ሁሉ ተሳትፎን ካደረገ እንደ ማኅበረሰብ የማንሻገረው ችግር አይኖረም:: ያም ሆኖ ግን አሁንም በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ዙሪያ ያለን ግንዝቤ የዳበረ ነው ለማለት ያስቸግራል::

የዛሬ የሕይወት ገጽታ ዓምዳችን ከማንም ምንም ሳይጠብቁ የተፈጥሮ በጎ ምግባራቸውና ለሰዎች የመኖር ሕልማቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ በበጎ ፈቃድ ሥራ ውስጥ እንዲያልፉ ያደረጋቸው ሰው ናቸው::

አቶ ዳዊት ተስፋዬ ውልደታቸው አርባምንጭ ከተማ ነው:: ውልደታቸው አርባ ምንጭ ይሁን እንጂ እድሜያቸው ለትምህርት ደርሶ ትምህርት ቤት መግባት በሚኖርባቸው ጊዜ ግን አባታቸው ሥራ ቦታቸው ወደ ወላይታ በመቀየሩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት ወላይታ ነው:: እዛም እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ ያለውን የትምህርት ጊዜያቸውን በጥሩ ሁኔታ ያሳለፉ ሲሆን ከስምንተኛ ክፍል በኋላ ያለውን የትምህርት ጊዜያቸውን ያሳለፉት አዲስ አበባ ከተማ መሆኑን ይናገራሉ::

“……አባቴ የባንክ ባለሙያ ስለነበርና የሥራ ቦታውም አርባ ምንጭ ስለሆነ እኔም የተወለድኩት አርባምንጭ ነበር:: ከዛ ደግሞ በድጋሚ የሥራ ቦታ ሲቀየር የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን የጀመርኩት ወላይታ ነው:: እዛም እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ ያለውን የትምህርት እርከን ከተማርኩ በኋላ አሁንም አባቴ በሥራው ምክንያት አዲስ አበባ ስለገባ ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ ያለውን ትምህርቴን ንፋስ ስልክ አካባቢ ሰኔ 9 የሚባል ትምህርት ቤትና የቀድሞ ተፈሪ መኮንን የአሁኑ እንጦጦ አጠቃላይ ነው ያጠናቀቅሁት” ይላሉ::

አቶ ዳዊት የልጅነት ጊዜያቸውን በተለይም አርባምንጭና ወላይታ አካባቢ ያለውን ጊዜ ያሳለፉት እንደ እኩዮቻቸው ከመጫወት ትምህርታቸውን በአግባቡ ከመከታተልና ወላጆቻቸውን በሚፈለገው ሁሉ ከማገዝ ባለፈ ለሌሎች የሚተርፍ እውነት በእዛ በልጅነት እድሜ በማይታሰብ ሁኔታ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን በማከናወን ነው::

“……ወላይታ ሶዶ ከተማ ውስጥ በነበርንበት ወቅት እኔም የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ በትምህርት ቤት ውስጥ የቀይ መስቀል ወጣት ክበባት መሳተፍ የጀመርኩት፤ ይህም በ1978 ዓ.ም ነው” በማለት አጀማመራቸውን ያስታውሳሉ:: አቶ ዳዊት ቤተሰባቸው የአድራሻ ለውጥ አድርጎ አዲስ አበባ ሲገባም ይህ በተፈጥሮ ያገኙት የበጎነት መንፈስና ለሰዎች የመኖር እሳቤ አብሯቸው ነበር:: ከለመድኩበት አካባቢ ቀይሬአለሁና አያስፈልገኝም፤ ልተወውም አላሉም:: ይልቁንም አዲስ አበባ ከተማ ገብተው ትምህርታቸውን ለመከታተል በተመዘገቡባቸው ትምህርት ቤቶች ሁሉ ይህንን በጎ ተግባራቸውን ቀጠሉት::

“……. አዲስ አበባ ከተማም ትምህርት ለመከታተል በገባሁበት ትምህርት ቤት ውስጥ በነበረው የቀይ መስቀል ክበብ ለመቀላቀልና የምወደውን የሰብዓዊነት ሥራ ለመሥራት ጊዜያት አልፈጁብኝም” ይላሉ::

ወላይታ ሶዶ ተማሪ በነበሩበት ወቅት ምንም እንኳን ልጅ ቢሆኑም በአቅማቸው ሊረዷቸው ሊደግፏቸው የሚችሉ ብዙ ሰዎች ነበሩና እሳቸውና መሰሎቻቸው ሰዎቹን በበጎ ፈቃደኝነት ከመርዳት አላቋረጡም:: በዛም የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ በመሠልጠን የተጎዱ ሰዎችን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ደግፈዋል::

“……ልጅነት ብዙ ጊዜ በወላጅ ቁጥጥር ስር የሚኮንበት ጊዜ ነው፤ እኔ ውስጤ ሰዎችን መርዳትና መደገፍ ብፈልግም የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ሥልጠናን ብወስድም እንደ ልቤ ባስፈለገኝ ሰዓት ከቤት ወጥቼ ሥራውን መሥራት ላይ ገደቦች ነበሩብኝ፤ ያም ቢሆን ግን በተገኘው አጋጣሚ አቅሜ የሚችለውን ያሕል አግዣለሁ” በማለት ይናገራሉ::

አቶ ዳዊት አዲስ አበባ ሲገቡም ለሀገሩ እንግዳ ቢሆኑም ለትምህርት በገቡበት ተፈሪ መኮንን (እንጦጦ አጠቃላይ) ያንን ያደጉበትን የበጎ አድራጎት ሥራ ለመቀጠል አላመነቱም፤ በዚህም ወዲያውኑ ወደቀይ መስቀል ክበብ ወስጥ በመቀላቀል ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሥራቸውንም መሥራት ቀጠሉ::

“…..አዲስ አበባ ከገባሁ በኋላ በተቀላቀልኩት የቀይ መስቀል ማኅበር ውስጥ እሳተፋለሁ በተለያዩ ሕዝብ በሚበዛባቸው ሃይማኖታዊና ሌሎች ክብረ በዓላት ላይ የስፖርታዊ ውድድሮች አካባቢ የመኪና ውድድር ሲኖር የመጀመሪያ የሕክምና እርዳታን እየሰጠን ተሳትፎን አድርገናል” በማለት በማኅበሩ ውስጥ ስለነበራቸው ተሳትፎ ይናገራሉ::

ከዛም ባሻገር አቶ ዳዊትና ጓደኞቻቸው በትምህርት ቤታቸውና ከትምህርት ቤት ውጪ ለአቻዎቻቸው በኤች አይ ቪ፤ በሥነ ተዋልዶና ወጣትነትን ተከትለው ስለሚመጡ ለውጦች ለትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብና ለተለያዩ የኅብረተሰብ ከፍሎች በማስተማርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራት ይካፈሉ የነበረ ሲሆን ከዛም በላይ ደግሞ በ1983 ዓ.ም ሀገሪቱ ላይ አጋጥሞ የነበረውን የሥርዓት ለውጥ ተከትሎ የተፈጠሩ አንዳንድ ችግሮቸ ላይ በመገኘትና የመጀመሪያ የሕክምና እርዳታ እንዲሰጥ በማድረግ ከአምቡላንሶች ጋር አብሮ በመሄድ በርካታ ተግባራትን ስለማከናወናቸው ይናገራሉ::

በሌላ በኩልም በከተማዋ ባሉ እንደ የካቲት 12 ዳግማዊ ምኒሊክ ጥቁር አንበሳና ሌሎች ሆስፒታሎች ላይ እየተመደቡ በድንገተኛ የሕክምና መስጫ ክፍል ውስጥ ያለውን ሥራ እየሠሩ ባለሙያዎችንም በበጎ ፍቃድ እንዲያግዙ ይመደቡም እንደነበር ያስታውሳሉ::

በወቅቱ በመንግሥት ለውጥ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ባሉበት ጃንሜዳ አካባቢ ተመድበው ብዙ የመጀመሪያ ሕክምን እርዳታዎችን መስጠታቸውን የሚናገሩት አቶ ዳዊት በሥራውም ብዙዎች ሲጠቀሙ ያዩ ስለነበር እጅግ ይደሰቱ እንደነበር ያብራራሉ::

አቶ ዳዊት በቀይ መስቀል ውስጥ የነበራቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ኅብረተሰብን ከማገልገል ባሻገር ማኅበሩንም በመሪነት ያገለግሉ እንደነበር አስታውሰው ይህ ሁኔታ ደግሞ ኃላፊነታቸውን ከሌሎች ላቅ ሲያደርገው በትምህርታቸውም ላይ መጠነኛ ተፅዕኖን ማሳደሩ አልቀረም::

“…….በወቅቱ አባቴ የጤና ችግር የነበረበት በመሆኑ ወደ ተለያዩ የሕክምና ማዕከላት ለሕክምና ይመላለስ ነበር:: አልጋ ይዞም ይተኛ ነበር፤ እኔም የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ለመስጠት የሚያስችለውን ሥልጠና ወስጄ የተሰጠኝ መታወቂያ ስለነበር ሆስፒታሎች ውስጥ እንደልቤ ተንቀሳቅሼ አባቴን ለማስታመም አልቸገርም ነበር፤ አባቴንም የእውቀቴን ያህል እረዳው ስለነበር ቤተሰቦቼ ባይደግፉኝም እንኳን ተፅዕኖን ግን አላደረሱብኝም” ይላሉ::

በሌላ በኩል አቶ ዳዊት ዓመለ ሸጋና ለትምህርታቸው ታማኝ የነበሩ ስለሆኑ ቤተሰብ ያን ያህል በስጋት ዓይን አይመለከታቸውም ነበር፤ የት ሄዶ ይሆን ብለውም አይሰጉም፤ ምክንያቱም አቶ ዳዊት ትምህርት ቤት ከዛ በትርፍ ጊዜያቸው ደግሞ የበጎ ፈቃድ አገልግሎታቸው ላይ ስለሚሆኑ ነው:: ቤተሰቡ በዚህን ያህል የሚያምናቸው አቶ ዳዊት በአካባቢያቸው ነዋሪዎችም የተፈለጉ የተወደዱ እንዲሁም የተመረቁ ነበሩ፤ ምክንያቱ ደግሞ ሰፈር ውስጥ ሰዎች ሲታመሙ በመጀመሪያ የሕክምና እርዳታ ያግዙ ስለነበር ብሎም አምቡላንስ በሚያስፈልግበት ወቅት በቂ መረጃን ይዘው በፍጥነት አምቡላንስ ወደአካባቢው እንዲደርስ ያደርጉ ስለነበር ነው::

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ከአዋዋላቸውም ተነስተው ለሕክምና ሥራ ልዩ ፍቅር እንደነበራቸው የሚናገሩት አቶ ዳዊት ነገር ግን አጋጣሚው ስላልተመቻቸ እሳቸው ሐኪም መሆን አልቻሉም:: ነገር ግን ታላቅ ወንድማቸው የሕክምና ባለሙያ ሆነዋል:: እሳቸው ደግሞ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩት በኮንስትራከሸን ዘርፍ ኮንትራክተር ሆነው ስለመሆኑም ይናገራሉ::

ለ 98 ጊዜ ደም መለገስ

የሰው ልጅ በተለያየ ምክንያት ታሞ አልያም አደጋ አጋጥሞት እናት በወሊድ ላይ ሳለች ደሟ ፈሶ አልቆ ደም ሊያስፈልጋት ይችላል:: ይህ ደም ደግሞ የሚገኘው እንደነ አቶ ዳዊት ያሉ ለሌሎች መኖርን ካስቀደሙ ደጋጎች ነው:: ደም መለገስ ምናልባትም ለለጋሹ ምንም ላይሆን ቢችልም ያ ደም አስፈልጎት ለሚጠባበቀው ሕመምተኛና ቤተሰቡ ግን የከበረ ውድ ስጦታ ነው::

አቶ ዳዊትም ይህንን የከበረና ውድ የሕይወት ስጦታ ላለፉት 33 ዓመታት 98 ጊዜ ደማቸውን አስቀድተው በመለገስ መልካም ሥራን አቆይተዋል:: አዎ ይህ ሥራቸው ምንም እንኳን ለእሳቸው ተራና ቀላል ሊደረግ የሚችል ነገር ቢመስልም ይህንን ደም አግኝተው ለተፈወሱ ሰዎች ግን የሕይወት ዘመን ስጦታ ሆኖ በልባቸው ይቀመጣል::

“…….ደም መለገስ የጀመርኩት በ1983 ዓ.ም ነው:: በወቅቱ በቀይ መስቀል ማኅበር ታቅፌ በየሆስፒታሉ ስሄድ ደም አስፈልጓቸው በደም እጦት ምክንያት ብዙ ሰዎች በሞትና በሕይወት መካከል ሲገቡ ቤተሰብ ሲያዝን ሲጨነቅ ማየቴ ከምሰጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተጨማሪ ደም መለገስ ብጀምር የብዙዎችን ሕይወት ማትረፍ እችላለሁ ብዬ ነው እንግዲህ ወደ ደም ልገሳ የገባሁት” ይላሉ::

ከዛ ጊዜ ጀምሮ በቀጠለው ደም የመለገስ ሥራቸው 33 ዓመታትን ማስቆጠር ችለዋል:: በዚህም ለ 98 ጊዜ ደም መለገስ ችለዋል:: በዓመት ቢያንስ ሦስት ጊዜ ደም መለገስ የማይተውት የሕይወት ቃል ኪዳናቸው ስለመሆኑም ነው የሚናገሩት::

የበጎ ፈቃድ ሥራ በምድር የሚያስደስት በሰማይ ደግሞ ትልቅ ዋጋ የሚያሰጥ የበረከት ሥራ ነው:: ይህም ቢሆን ግን ማንም ተነስቼ በጎ ፈቃደኛ እሆናለሁ ቢል ላይሳካለት ይችላል:: አንዳንድ ጊዜ መሰጠትንም ጭምር የሚፈልግ ነው:: ነገር ግን ሰው አጠገቡ ላለው ለጎረቤቱ፤ ለእህት ለወንድሙ በጎ ከሆነ ያለውን ካካፈለ በኃዘን በደስታው ጊዜ አብሮ ከሆነ በጠቅላላው ለሰው ችግር ሳይሆን መፍትሔ መሆን ከተቻለ ያ ከምንም የላቀ በጎነት ነው ለእኔ ይላሉ::

“……የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ደም መለገስ ብቻ ላይሆን ይችላል ነገር ግን ሁሉም አቅሙ የሚችለውን በእውቀቱ በጊዜው በጉልበቱ መሳተፍ ይችላል:: እኔ ለምሳሌ ለረጅም ዓመታት ብዙ ጊዜ ደም በመለገሴ እታወቅ ይሆናል እንጂ ሌሎች በጎ ተግባራትን ግን አልፈጽምም ማለት አይደለም ለምሳሌ የተቸገሩ ሰዎችን በአቅሜ አግዛለሁ፤ አካባቢዬ ላይ ባሉ የልማት ሥራዎች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነኝ፤ ምክር ለሚያስፈልጋቸው በመምከርና በሌሎቹም በኩል በነቃ ሁኔታ እሳተፋለሁ ” በማለት አገልግሎታቸውን ይናገራሉ::

ለሌሎች መትረፍ በጣም ደስ ይላል እኔ ለምሳሌ ይህንን ሁሉ ዓመት ለዚህን ያህል ብዙ ጊዜ ደም ስለግስ በእኔ ላይ የሆነ ምንም ነገር የለም፤ ነገር ግን እኔ በለገስኩት ደም የሰዎች ሕይወት ሲተርፍ በዓይኔ አይቻለሁ:: ቤተሰብ አዝኖ የነበረ ፊቱ ሲፈካ ተመልክቻለሁ ካሉ በኋላ በአካባቢዬ ላይ በማደርጋቸው ተሳትፎዎች ላይም ውጤታቸው መልሶ ሲከፍለኝ አይቻለሁ በማለት ይናገራሉ::

እኛ ዛሬ ለይ የምንሠራት ትንሿ መልካም ሥራ ብዙዎችን የምታፈራ ናት የሚሉት አቶ ዳዊት እሳቸው የሚሠሩት የበጎነት ሥራም ዛሬ ላይ ልጆቻቸውና ባለቤታቸው ላይ ተጋብቶ የበጎ አድራጎት ሥራውን በደስተኝነት እየሠሩ ስለመሆኑም ነው የሚናገሩት::

የበጎ አድራጎት ሥራ ለሁሉም

እንደ ሀገር የበጎነት ሃሳቡ ቢኖረንም ያንን ሃሳብ ወደተግባር ቀይሮ ውጤታማ መሆን ላይ ግን ሰፊ ችግሮች የሚስተዋሉብን ነን፤ ሰዎች ወደ በጎ አድራጎት ሥራ ወስጥ እንዳይገቡም ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ እጥረት እንዳለባቸውም እረዳለሁ በማለት የሚናገሩት አቶ ዳዊት እንደውም አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለው ተሳትፎ አድጓል ለማለት የሚያስችል መሆኑንም ነው የሚያስረዱት ::

“……..አሁን ከላይ በበጎ ፈቃደኞች አማካይነት ብዙ ሰዎች ከድህነት እየወጡ ሕይወታቸው እየተለወጠ ይገኛል፤ ከዚህ አንጻር አሁን ሁሉንም ተደራሽ ለማድረግ ትንሽ የግንዛቤ ሥራ ብቻ ነው የሚጠይቀን” ይላሉ::

ወላጆች ልጆቻችንን በበጎ ሥነ ምግባር አንጸን ለማሳደግ ከምናደርገው ጥረት ጎን ለጎን ለሰው ማሰብን በጎ ሥራን ማስተማር በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለበጎ ፍቃድ ሥራ የነቁና የተጉ አድርጎ ማሳደግ ሊሰመርበት የሚገባ ነገር መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዳዊት የእምነት ተቋማትም ተከታዮቻቸውን በዚህ መልኩ እየቃኙ ቢያስተምሩ እውነት በሌላው ዓለም የምናየው የተቀናጀ የበጎ አድራጎት ሥራ ሀገራችን ላይም የማይሆንበት አንዳችም ምክንያት የለም በማለት ያስረዳሉ::

ገጠመኞች

በሕይወት ማዳን ሥራ ውስጥ ያለ ሰው ብዙ ነገሮች ይገጥሙታል እኔ ደግሞ ከልጅነት እስከእውቀት ያለፍኩበት ሂደት በመሆኑ ብዙ የሚያስተምሩ የሚያሳዝኑ ገጠመኞች አጋጥመውኝ ያውቃሉ:: ነገር ግን ከሁሉም በላይ የሚጎዳውና ልብ የሚሰብረው ገጠመኝ ሰዎች በአደጋ አልያም በሌላ ነገር ራሳቸውን ስተው አድናቸዋለሁ ብለን እየተሯሯጥን ከእጃችን ሲያመልጡ የሚሰማው ስሜት የማይረሳና ከፍተኛ ነው በማለት ይናገራሉ::

በአንጻሩ ደግሞ ምንም ረዳት የሌላቸውን ሰዎች በቤተሰብ አለመስማማት ምክንያት የተበተኑ ሕጻናትን ሰብስበን አግዘን በወቅቱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር አግዣቸው ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች መኖራቸው ደግሞ ያበረታኛል :: በተለይም መጀመሪያ ያሳደኩት ልጅ ተምሮ ተመርቆ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ እየሠራ ከፍ ብሎ ሳየው ደስታዬ ወደር ያጣል በማለት ይናገራሉ::

የወደፊት እቅድ

በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዙሪያ እግዚአብሔር በሰጠኝ ጉልበት የአገልግሎት ዘመን ሁሉ ለሌሎች በመትረፍ እንዲሁም ከታች ላሉት ወጣቶች ምሳሌ በመሆን ብዙ ደጋጎችን ለማፍራት ጥረት አደርጋለሁ ሕልሜም ነው:: ከተቻለ ደግሞ ልጆቼን ቤተሰቤን በዙሪያዬ ያሉትን በሙሉ አሰባስቤ ለሌሎች የምንደርስበትን መንገድ ባመቻች በጣም ደስ ይለኛል::

የቤተሰብ ሁኔታ

አቶ ዳዊት ባለትዳርና የልጆች አባት ናቸው:: ለዚህ የበጎ ተግባር ሥራቸው ደግሞ ባለቤታቸው ትልቅ ሚና እንዳላቸው ይናገራሉ :: ” …..እሷ በሥራዬ በጣም ደስተኛ ናት እኔንም ታነሳሳኛለች ትደግፈኛለች በሌላ በኩል ደግሞ እሷም በምትችለው መጠን ሁሉ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ብዙ ለውጥ አምጥታለች” በማለት ያብራራሉ::

መልዕክት

አንድ ሰው ወደበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወስጥ ሲመጣ አልጋ በአልጋ የሆነ ነገር መጠበቅ አይገባም:: ነገር ግን ያሉትን ችግሮች ተቋቁሞ ለሌሎች በጎ ነገርን አደርጋለሁ ብሎ መነሳቱ በራሱ ትልቅ እርምጃ ነው:: ስለሆነም በጎ ለማድረግ ዛሬውኑ መነሳትና ወደ ተግባር መግባት ይገባል በማለት መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ::

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You