ቴሌ/ቨርችዋል-ሜዲስን የዘመናዊ ሕክምና የተስፋ ጎህ

ሕክምናን ተደራሽ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ማድረግ አይደለም እንደኛ ላሉ ሀገራት ለበለጸጉ ሀገራትም ምን ያህል ፈተና እንደሆነ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ታዝበናል። ለነገሩ በድህረም ሆነ በቅድመ ወረርሽኝ ሕክምናን ተደራሽ የማድረግ ችግር የነበረ ዛሬም የቀጠለ ነው። የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ የባራክ ኦባማ ምርጫ ቅስቀሳ አካል ነበር። አሸንፈው ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ኦባማኬር የተባለ የጤና አገልግሎት ሥርዓት ተግባራዊ እስከ ማድረግ ደርሰዋል። ባይደን ለፕሬዚዳንትነት ሲወዳደሩ የምርጫ ቅስቀሳ አካል ሆኖ በመቀጠል ሥርዓቱ አንድ ጊዜ ሜዲኬር ሌላ ጊዜ ኦባማ ኬር እየተባለ ቀጥሏል።

በዓለማችን የተዋጣለት የጤና አገልግሎት ለዜጎቹ በማድረስ የሚታወቀው የብሪታንያ ወይም የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ወይም በምሕጻሩ ኤንኤችኤስ ለዜጎች ተደራሽ መሆን ባለመቻሉ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ሕክምና ለማግኘት ወረፋ እየጠበቁ ነው። ይህ የጤና አገልግሎት ቀውስ መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባበተ። በተያዘው ወር መጨረሻ አካባቢ በሚካሄደው ምርጫም ቅድሚያ ካገኙ አጀንዳዎች አንዱ ሆኗል። የሌበሩ መሪ ሰር ኪር ስታርመር ለዚህ ያበቃችሁ ሥልጣን ላይ ያለው የኮንሰርቫቲቭ ወይም የቶሪ ፓርቲ ነውና እኔን ብትመርጡ በአጭር ጊዜ የሕክምና አገልግሎቱን ተደራሽ አደርገዋለሁ እያሉ የመራጮችን ልብ እያሸፈቱ ነው።

ወረፋውን ከማቃለል ባሻገር ዘላቂ መፍትሔ አሠራር አበጃለሁ። የሕክምና ባለሙያዎችን በስፋት እቀጥራለሁ። ተቋማትንም አስፋፋለሁ እያሉ ነው። አቃልልና በሒደት አጠፋዋል እያለ እየቀሰቀሰ ይገኛል። የሪሺ ሱናክ ፓርቲን ለሽንፈት ከሚዳርጉ ችግሮች የጤና አገልግሎት ተደራሽ አለመሆን ግንባር ቀደም ነው። የኑሮ ውድነት፣ ታክስ፣ ሥራ አጥነትና የኢነርጂ ዋጋ አልቀመስ ማለት የምርጫውን ውጤት ከሚወስኑ አጀንዳዎች ውስጥ ተካተዋል።

እንግዲህ ለአሜሪካና ለታላቋ ብሪታኒያ የጤና አገልግሎትን በፍትሐዊነት በሰዓቱ ማድረስ እንዲህ ዳገት ከሆነ እንደኛ ላለ ሀገር ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆን አስቡት። ለዚህ ነው በመንግሥት ብቻ የሚደረጉ ጥረቶች ችግሩን መቅረፍ ስለማይችሉ የግሉ ዘርፍ እና ቴክኖሎጂ የማይተካ ሚና እንዲጫወቱ የሚፈለገው። የሐኪም፣ የነርስ፣ የጤና መኮንንና የሕዝቡ ጥምርታ፤ የጤና ተቋማትና የሕዝቡ ጥምርታ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቁ መሆን ቴሌ እና ቨርቹዋል ሜዲሲንን ወደፊት እንዲመጣ መግፍኤ ሆኗል።

ቴክኖሎጂ ዓለምን ወደ አንድ መንደር በማቀራረብ ሰዎች በብዙ ማይል ርቀት ላይ ሆነው ልክ አብረው በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚወያዩ፣ እንደሚሠሩና እርስ በርስ እየተያዩ ደስታም ሆነ ኅዘናቸውን እየተጋሩ እንዲኖሩ ማድረግ ከጀመረም ሰነባብቷል:: የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችም ኑሯችንን ከማቅለላቸው ባሻገር ርቀትንና ጊዜን ምንም እያደረጓቸው ነው። ምን አለፋችሁ ዓለምን ወደ ሰፈርነት እየቀየሩ ይገኛሉ::

ዓለማችን ለቴክኖሎጂ እጅን ሰጥታ ከየብስ እስከ ጠፈር ከባሕር እስከ ጨረቃ ጓዳ ጐድጓዳው በቴክኖሎጂ እየተሳሰረ እንደሆነ የመስኩ ተመራማሪዎች ይናገራሉ:: ምናልባትም አፍሪካውያን በተናጠል ወደ አውሮፓና አሜሪካ በመሄድና በቴክኖሎጂው መስክ በመሰማራት የራሳቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት ችለው ይሆናል እንጂ አሁን ላይ ግን እነዚህን እይታዎች ሊቀይሩ የሚችሉ ጅምሮች በየአቅጣጫው ይስተዋላሉ::

ለዚህ ደግሞ አንዱ ኢትዮ ቨርችዋል ሜዲስን ኬር በምሕጻሩ ኢቪኤምኬር በሕሙማንና በሕክምና ተቋማት ወይም በጤና እንክብካቤ አቅራቢዎች መካከል ርቀትና ሰዓት ሳይበግረው አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ራዕይ አንግቦ የተቋቋመ ድርጅት ወይም መድረክ አልያም ፕላት ፎርም ነው። ይህን ፕላት ፎርም በመጠቀም የሚመለከተውን ሐኪም ማማከር፣ ምርመራ ማድረግ፣ መድኃኒት ማሳዘዝ፣ ቀጠሮ ማስያዝ፣ የቤት ለቤት ክብካቤንና ክትትልን ማግኘት፤ የላብራቶሪ ምርመራ ማድረግ፣ የሕክምና ተቋማትን በቀላሉ ማግኘት ያስችላል።

ተልዕኮው በሕሙማን እና በሕክምና ወይም በጤና እንክብካቤ አቅራቢዎች መካከል ያለውን ክፍተት ቴክኖሎጂን እንደ ድልድይ ተጠቅሞ ማገናኘት ሲሆን፤ ሕሙማን የትም በማናቸውም ጊዜ የግድ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ሳያስፈልጋቸው በበይነ መረብ በመታገዝ በእጅ ስልካቸው፣ በታብሌት፣ በላፕቶፕ፣ በፒሲ፣ ወዘተረፈ ሕክምናን በቀላሉ ማግኘት ያስችላል። እንዲሁም ኢትዮ ቨርችዋል ሜዲሲንኬር ወይም ኢቪኤምኬር ለሕሙማን ግላዊነት ወይም ፕራይቬሲ ደኅንነት እና ምስጢራዊነት መጠበቅ ቅድሚያ እንደሚሰጥ፤ ፕላትፎርሙ የተገነባው ደኅንነቱ በተጠበቀ፣ HIPAA በሚያሟላ የደኅንነት መሠረተ ልማት ስለሆነ የግለሰቦች የጤና መረጃዎች የተጠበቁ መሆናቸውን ያረጋግጣል።

ኢትዮ ቨርቹዋል ሜዲስን ኬር እንደስሙ የጤና አጠባበቅ አገልግሎት አሰጣጥ ዘዴን እንደ አዲስ ለመበየን የሚሠራ ፋና ወጊ ተቋም ሲሆን፤ ፕላትፎርሙ ሕሙማንን ልምድ፣ ፈቃድና ብቃት ካላቸው እንዲሁም በሙያ ማኅበራቸው ከተመሰከረላቸው የሕክምና ባለሙያዎች እና ተቋማት ጋር ያገናኛል። በዚህም የጤና ባለሙያዎች ለአገልግሎታቸው ተጨማሪ ገቢ ያገኛሉ። ልምድ ያካብታሉ። ተቋማትም አገልግሎታቸውን በአነሰ ወጭ ተደራሽ ያደርጋሉ። የኢቪኤም ኬር በሌላ በኩል ቴሌ-ሜዲስን ማለት የጤና ጥበቃ አገልግሎቶችን ሐኪም እና ታካሚ በአካል ሳይገናኙ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶችን በመጠቀም የሚሰጥበት መንገድ ነው:: በሌላ አጠራሩ ቴሌ-ሄልዝ ወይም ኢ-ሄልዝ በመባልም ይታወቃል::

የቴሌ-ሜዲስን አገልግሎት የሚሰጠው ታካሚ ከሐኪሙ ጋር በስልክ ቀጥታ በመደዋወል አሊያም ለዚህ ዓላማ በተዘጋጀ መተግበሪያ በመታገዝ የሕክምና አገልግሎቱን የሚያገኝ ይሆናል:: በሂደቱ ታካሚው የነበረውን የኋላ ታሪክ እና ምልክቶቹን በመናገር በሰጠው መረጃ መሠረት ምርመራ ከተደረገ በኋላ መድኃኒት ሊታዘዝለት ወይም ተጨማሪ ክትትል እንዲያደርግ ሊታዘዝ ይችላል::

ቴሌ-ሜዲስን ከተዘረጋ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ጎን ለጎን በመተግበሪያም በመታገዝ በሽተኛው ከመተግበሪያው ጋር ብቻ በመገኛኘት የሕክምና ድጋፍ እና ክትትል ማግኘትም ያስችለዋል:: በዓለማችን የቴሌ-ሜዲስን አገልግሎት የሚሰጡ ብዙ ተቋማት አሉ:: ሲሳሜ፣ ኤምዲላይቭ፣ ቴሌዶክ፣ አምዌል እና ሌሎችም ይህን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ:: በሀገራችን ኢትዮጵያም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የቴሌ-ሜዲሲን አገልግሎት በተወሰነ ደረጃ ተጀምሮ እንደነበር የኢዜአ ዘገባ ያወሳል::

ቴሌ-ሜዲስን ለግንኙነት በሚጠቀማቸው መንገዶች በአራት ዓይነት መደብ ይከፈላል:: አንደኛው በግንኙነት ማዕከል የሚፈጸም የቴሌ-ሜዲስን ዓይነት ነው። የግንኙነት መሠረተ ልማት በተሟላለት ማዕከል ውስጥ በሕሙማን ከሐኪሞች ጋር ቪዲዮ ኮንፍረንስን ጨምሮ በግንኙነት አማራጮች የሚገናኙበት ነው::

የጤናችንን ሁኔታ በመቆጣጠር መረጃ የሚሰጡ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚተገበር የቴሌ-ሜዲስን ዓይነት ደግሞ ሌላው ነው:: የጤና ሁኔታችንን የተመለከተ መረጃ የሚሰጡ መሣሪያዎች በእጅ እንደ ሰዓት የሚታሠሩ ወይም የሚለጠፉ ሆነው የሙቀት መጠንን፣ የስኳር መጠን፣ የደም ግፊትን እና መሰል የጤና ሁኔታ ጠቋሚ ምልክቶችን የሚያሳውቁ ናቸው::

ከመሣሪያዎቹ የሚገኘውን መረጃ ከርቀት ሆኖ በመከታተል ድጋፍ የሚያደርግ ሐኪም ይኖራል:: ሌላው የግንኙነት መሠረተ ልማትን በመጠቀም ሁለት የሕክምና መስጫ ተቋማት ስለሕሙማኑ መረጃ የሚለዋወጡበት አማራጭ ያለው የቴሌ-ሜዲሲን ነው:: ታካሚው ክትትል ሲያደርግበት በነበረው ተቋም ርቆ በሚሄድበት ወቅት የታካሚውን የኋላ ታሪክ፣ የምርመራ ሁኔታ እና የላብራቶሪ ውጤት ካንዱ የጤና ተቋም ወደ ሌላ ከርቀት ሆኖ ማጋራት የሚቻልበት ዓይነት ነው::

አራተኛው ደግሞ ስልክን በመጠቀም ሐኪም ከታካሚ ቀጥታ ይገናኙበታል:: በዚህም ታካሚዎች ከርቀት ድጋፍ ለማግኘት ይችላሉ:: ሆኖም ቴሌ-ሄልዝ በርካታ ጥቅሞች እና የተወሰኑ እንደ ችግር የሚታዩ ውስንነቶችም አሉት:: ከሚሰጣቸው ጠቀሜታዎች ውስጥ በሕሙማን ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ሆነው የጤና ጥበቃ ድጋፍ ስለሚያገኙ በጉዞ የሚጠፋን ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጭ ይቀንሳል::

ከከተማ ርቀው የሚገኙ ሰዎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ይረዳል:: ለምሳሌ ቀዶ ጥገና ያደረጉ ታካሚዎች ባሉበት ክትትል ማድረግ የሚችሉበትን ዕድል ይሰጣል:: ተላላፊ በሽታዎች ሲሆኑ እንዳይዛመቱ ይከላከላል:: የግንኙነት ሥርዓቱ ላይ ሊደርስ የሚችል የሳይበር ጥቃት፣ የመስመር ላይ መድኃኒት ማዘዣን የሚከለክሉ ሀገራት መኖራቸው፣ የቴሌ-ሄልዝ ቴክኖሎጂዎች ሥልጠና የሚያስፈልጋቸው መሆኑ ደግሞ እንደ ውስንነት ይነሳበታል::

የቀድሞዋ ጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በአንድ መድረክ ከጤና ተደራሽነት አኳያና በአሁኑ ጊዜ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ኢንተርኔትን በእጃቸው ላይ የሚጠቀሙ እንደመሆናቸው መጠን የጤና አገልግሎት ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ፤ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመቀናጀት የኢንተርኔት ተደራሽነቱን ማስፋፋት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን፤ ሥራው ሰፊ ጉልበትና ገንዘብ እንደሚጠይቅ በማንሳትም የጤናውን ዘርፍ ለማዘመን እንደ አገር የአሥር ዓመት ስትራቴጂ ተቀርፆ እየተሠራ እንደሆነ እና የስፔሻሊቲ አገልግሎቶችን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ እንዳልተቻለ አንስተው፣ ለዚህም የቴሌሜዲስን ቴክኖሎጂን መጠቀም አገልግሎቱን ለሚሰጡ ዶክተሮች ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል ማለታቸው አይዘነጋም::

ሻሎም ! አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You