አዲስ አበባ፡- ሚዲያው በመዲናዋ እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን ልማት ለዜጎች በትክክለኛው መንገድ ተደራሽ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ተጨማሪ ሶስት የሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ “AMN plus” የተሰኘ አዲስ የቴሌቪዥን ቻናል ትናትና አስጀምሯል።
አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ያስጀመረውን ተጨማሪ ቻናል አስመልክቶ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ሚዲያዎች በመዲናዋ እየተሠሩ ስለሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ በማድረግ እድገቱን ማፋጠን ተገቢ ነው፡፡
ማህበረሰቡ ከሚዲያዎች ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ከተደረገ የከተማዋን ልማት ይበልጥ ይደግፋል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ለዚህም ሚዲያዎች ወቅታዊና ትከክለኛ መረጃ በማድረስ ሊሠሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የማህበረሰቡን ድምፅ ማንፀባረቅ የሕዝብ ሚዲያ ያደርጋል፤ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የተከፈተው ተጨማሪ ቻናል የማህበረሱ ድምፅ ሆኖ ሊያገልግል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ተጨማሪ ቻናሉ በቴክኖሎጂ የተደራጀና በሰው ሃይል የተጠናከረ በመሆኑ ትክክለኛ መረጃ ለማህበረሰቡና በከተማዋ ለሚኖሩ ዲፕሎማቶች ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ጣቢያው የዜጎች ደስታ፣ ኀዘኑ፣ ቅሬታው፣ ትችቱ የሚቀርብበት የማህበረሰብ ድምፅ ነው ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤ ማህበረሰቡ ተጨማሪ የቋንቋ ቻናሉን ሊጠቀምበት እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመዲናዋ እድገት፣ ልማት፣ ንፅህና በፍጥነት እያደገ ነው፤ የዜጎች ኑሮም እንዲሻሻል እየተደረገ ነው ያሉት ከንቲባ ሚዲያው እየተሠሩ ስላሉ ነገሮች ትክክለኛ ማህበረሰቡን የሚመጥን መረጃ ተደራሽ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ከተማዋንና ማህበረሰቡን የሚመጥን መረጃ ተደራሽ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
አዲስ የተከፈተው ኤኤምኤን ቻናል ማህበረሰቡን የሚመጥ መረጃ ተደራሽ እንዲያደርግ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ አመላክተዋል።
የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ሚዲያው በለውጥ ላይ ያለችውን ከተማና ማህበረሰብ የሚመጥን መረጃ ተደራሽ በማድረግ ተደማጭነቱን ለማሳደግ እየተሠራ ነው።
አዲሱ ቻናል የሕዝብ ፍላጎትን የሚያሟላ መረጃ በጥራትና በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ የተከፈተ ነው፤ ሚዲያው መረጃን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ የሌሎች የመረጃ ምንጭ እንዲሆን የሚያስችል ነው ብለዋል።
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም