በኮሪደር ልማቱ የተመለከትነውን ትጋት ለማስቀጠል …

አዲስ አባባ ስሟን የሚዋጅ ደረጃ ላይ እንድትደርስ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል። ከጥረቶቹም መካከል ‹‹እውነት ይህ ሰፈር እንዲህ ያምር ነበር እንዴ ?›› በሚያሰብል ደረጃ የከተማዋ ታዋቂ ሰፈሮች ፒያሳና አራት ኪሎ በሚያሰደንቅ ሁኔታ ተቀይረው መመልከት ችለናል:: የኮርደር ልማት መላዋን አዲስ አበባ አዳርሶ አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብና አዲስ እንድትሆን ተመኝተናል::

እስካሁን ባለው የልማቱ ሂደት፤ ቀድሞ ሥርዓት ባጣ መልኩ ተጠባብቀውና ተቀጣጥለው የነበሩት ህንፃዎች ቅጥልጥላቸው ፈርሶ ታደሰው ሲታዩ አዳዲሶቹን የሚያስንቁ የከተማዋ ውበት መታያ መሆናቸውን ተመለክተናል። የኮሪደር ልማት ቀድሞ በተጀመረ የሚል ቁጭት ፈጥሮብናል።

ዘመን ዘመን ሲተካ ፍልውሃ አካባቢ የተቆረቆረችው አዲስ አበባ በተለያየ ጊዜ ማስተር ፕላን እየወጣላት ስታሸበርቅ በርካታ ዓመታትን አሳልፋለች:: በየጊዜው ከተማይቱን ይመጥናል የተባለ ማስተር ፕላን ሲወጣና ወደ ተግባር ሲገባ ተመለልክተናል። ከዚህ ቀደም በተለያየ መልኩ እና መንገድ ከተማዋን የማልማት ሥራዎች ቢካሄዱም፤ እንደ አሁኑ ግን በአንድ ጊዜ ውበትን፤ ጥራትን እና ፍጥነትን አጣምሮ የሚጓዝ አተገባበር አልታየም::

ማስተር ፕላን የመሬት አጠቃቀምን እና ልማትን፣ የህንፃ አሠራርንና መዋቅርን እና የገበያ ቦታዎችንና ከፍተኛ መንገዶችንና ንዑስ መንገዶች አረንጓዴ ሥፍራዎችን ክፍት ቦታዎችንና የህንፃ ዓይነቶች በዝርዝር ይይዛል:: ምንም ዓይነት ከፕላኑ ውጭ ያፈነገጠ ነገር እንዳይሠራ የሚገድብ፤ እስከ አስር ዓመት የአፈፃፀም ጣራ ያለው ዝርዝር ፕላን ነው:: በአጠቃላይ የአንድ ከተማ ቁልፍ የዲዛይን ሰነድ ነው ።

በከተማዋ በየወቅቱ የተተገበሩ ማስተር ፕላኖች የከተማዋን ታሪክ እና የአፍሪካ መዲናነቷን የማይመጥኑ እንደነበሩ ይታወሳል ፤ ነዋሪውን ከአካባቢው አፈናቅለው የትም የሚበትኑ ነበሩ:: አሁን ሁኔታዎች ተሻሽለዋል:: በየወቅቱ ይከናወን የነበረው ሕገወጥ የመሬት ወረራና የጨረቃ ቤቶች ግንባታ ቀርቶ የልማት ተነሺው የሚመጥነው ማረፊያ እያገኘ ከተማዋ የሚገባት ዋጋ እየተከፈላት እየለማች ነው። እውነታው እጅግ በጣም የሚያኮራ ነው።

ማህበረሰቡም ልማቱ የራሱ ልማት እንደሆነ አስቦ ተሳታፊ ከመሆንም በላይ ተጠቃሚ እንዲሆን በመንግሥት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። ነዋሪውም ከአዲስ አበባ ልማት የተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንደቻለ በተጨባጭ መስክሯል::

በቀጣይም ይህንን ጅማሮ በማስፋት ከአዲስ አበባ ልማት ነዋሪውም ሆነ ነጋዴው ማህበረሰብ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስልት መቀየስ ይገባል:: ይህ ማለትም ከመንገዱ በስተጀርባ የሚኖረውን ነዋሪ የሚመጥን አገልግሎት በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ፤ማህበረሰቡን እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁንታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል።

በተለይም በተለያዩ አነስተኛ ንግድ ላይ ተሠማርተው ይንቀሳቀሱ የነበሩና ለኮሪዶር ልማቱ ተብሎ ከአካባቢያቸው የተነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች በተሻለ ሁኔታ ሥራቸውን የሚሠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት የሚቻልበትን እድል በመፍጠር ዜጎች በተሠማሩበት የንግድ ዘርፍ ለከተማዋ ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል።

ሀገራችን ከዚህ ቀደም የቱሪዝም መዳረሻ ሆና የምትታወቀው በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ሀብቷ፣ በመልካምድሯ፣ በታሪኳ፣ በባህሏና ሌሎችም ነበር:: አሁን ደግሞ ለቱሪዝም ምቹ የሆነ የመንገድ መሠረተ ልማት እየተሟላላት ነው። ይህም በራሱ ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ ሊሆናት እንደሚችል ይታመናል።

ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ በተመረጡ ዋና ዋና ከተማ በመከናወን ላይ ያለው የኮሪዶር ልማት በተመሳሳይ መንገድ ለአካባቢው ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ መሆኑ አይቀርም:: የልማት ሥራዎቹ በከተሞቹና በሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ሚና እንደሚኖራቸውም ይታመናል። ለዚህ ደግሞ ልማቱ ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት ሲገባ በጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ መሥራት ያስፈልጋል። ነዋሪው የተሠራውን ልማት በባለቤትነት እንዲጠብቀው የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ይገባል።

አሁን ላይ የተመለከትነው ውበት ነባር ህንፃዎች ላይ የተደረገውንም እድሳትን ስለሚጨምር፤ በቀጣይነት ከተማዋ የጊዜ ገደብ ተቀመጦላት የምትታደስበት ሁኔታ ቢኖር ውቧ አዲስ ውበቷን እንደጠበቀች መቆየት ያስችላታል:: አሮጌ የነበሩ፤ እንኳን ሊገባባቸው ለዓይን የሚከብዱ የነበሩት ህንፃዎች የቀለምና ሌሎች አነስተኛ እድሳቶች የሚደረግበት መመሪያ ሊኖር ይገባል::

የተሠሩት ሥራዎች የተወሰነ ጉዳት ሲደርሰባቸው ጉዳቱ ሳይበባስና የከፋ ጉዳት ሳይደርስበት መልሶ የሚጠግን የሚያስተካክል ይህኑኑ በቅርበት የሚከታተል አካልም የግድ ያስፈለግናል። እስከ ዛሬ በተለያዩ ምክንያቶች ተደብቆ የቆየው የስራ ባህላችን መቀየሩን ያመላከተው ይህ የኮሪደር ልማት ለቀጣይ ስራዎቻችንም መለኪያ መስፈርት ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባ ነው::

ይህን የመሰለ ዘመናዊ አካባቢ በሶስት ወራት መጨረስ እንደሚቻል ኮሪደር ልማቱ አሳይቶናል:: ስለሆነም በተለመደው ሁኔታ ሶስት ዓመትና ከዚያ በላይ የሚጓተቱ ልማቶችን ሕዝብም ሆነ መንግስት መታገስ እንደማይችሉ ማሳያ ነው:: እንደምንታዘበው የኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ አዲስ ውበት እና ሞገስ እያጎናጸፋት ነው:: ከሁሉም በላይ የሚያስደስተው / አግራሞትን የሚፈጥረው ደግሞ ሥራውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ የሚደረገው ርብርብ ነው::

በአጠቃላይ በኮሊደር ልማቱ የታየው ሀገራዊ ንቅናቄ ውበትን፤ ጥራትንና ፍጥነትን በአንድ ጊዜ መመከልከት ያስቻለ ፤ መሽቶ በነጋ ቁጥርም አዲስ ነገር መፍጠር ያስቻለ ነው:: የተሽከርካሪ መሄጃ አስፋልቱን እና የእግረኛ መንገዱን ስፋት ለተመለከተውም ዓለም አቀፍ ደረጃን ባሟላ መልኩ እየተገነባ መሆኑን ማንም አይቶ የሚረዳው ነው:: ይህንን በልዩ ትጋት የተገኘን ስኬት ለማስቀጠል እራሳችንን የልማቱ አካል አድርገን መቆም ይጠበቅብናል።

ለብስራት

አዲስ ዘመን ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You