ቀኑ አልፎ ምሽቱ ሲጀምር ጎኗ ከመኝታ ያርፋል:: ሰውነቷ እንደዛለ፤ ውስጧ ሃሳብ እንዳዘለ ሌቱን ታጋምሳለች:: የቀን ድካሟ፣ የውሎ ገጠመኟ ሁሌም ከእሷ ጋር ነው:: ሸለብ ሳያደርጋት በፊት ቀጥሎ ያለውን ቀን ታስበዋለች፣ በሃሳብ ስትወጣ ስትወርድ ጊዜው እንደዋዛ ይነጉዳል:: ጨለማ ከጋረጠው፣ ድቅድቅ ከዋጠው ውስጠቷ ጀርባ ወለል ያለው ስጋት ለእሷ ብቻ ይታያታል – ለእሷ ብቻ::
በመጪው ቀናት ሁሌም ትከሻዋ፣ እጅና እግሮቿ እረፍት አልባ ይሆናሉ:: በየቀኑ አንዳቸው ከአንዳቸው ተባብረው ቢታደጓትም አዝናላቸው አታውቅም:: ዘወትር ያለ ምህረት ታዛቸዋለች፣ በፍጥነት ታሰራቸዋለች:: እሷ እንዲህ ከመሆን ውጪ ምርጫ ኖሯት አያውቅም:: የአቅሟን ታግላ ኑሮን ማሸ ነፍ ህይወትን መምራት ግዴታዋ ነው::
ለዚህ እውነት ጉልበቷ ዋስትናዋ ሆኗል:: በጥረቷ ሠርታ ታገኝበታለች:: በድካሟ ጎርሳ፣ ታድርበታለች፣ ከፈጣሪዋ ቀጥላ አቅም የሆናት እርሱ ብቻ ነው:: ችግሯን ስትወጣበት፣ ሮጣ ስታድርበት መፍትሄዋ ነው:: እንዲህ ሲሆን ደስ ይላታል:: ያለዛ ትቸገራለች፣ ጦሟን ውላ ታድራለች:: ካጣች፣ ከነጣች ደግሞ ይከፋታል:: ለመከረኛ ዓይኖቿ ስቃይ አቀብላ በህመም ትከርማለች:: እናም መሮጥ፣ መፍጠን ግዴታዋ ነው:: በየቀኑ እንዲህ ይሆን ዘንድ አይቀርምና::
በሃሳብ …
ብዙነሽ ካልጋዋ ጋደም ብላ ንጋቷን ስታስብ አዋዋሏን አትዘነጋም፤ ውጣውረዷ፣ድካም ዝለቷ ሁሉ ውል ይላታል:: ዛሬ ነግቶ ነገ ሲተካ ህይወቷ በለመደችው መንገድ ይቀጥለል:: በየቀኑ ሩቅ መንገድ በእግሯ ትጓዛለች፣ ከመንገደኛው፣ከአህያ፣ከመኪናው መጋፋት ልማዷ ነው:: የውሎ እንቅፋቷም በዋዛ አይነገርም:: አንዳንዱ ሳታስበው ገፍትሯት ያልፋል:: ሌላው ሮጦ ይቀድማታል:: ገሚሱ ደግሞ ከታማኝነቱ አጉድሎ ሴትነቷን ይፈልጋል::
ይህ ከብዙ እውነቶች መሀል ተቆንጥሮ የሚገለጸው የብርቱዋ ብዙነሽ ታሪክ ነው:: ሁሌም ከውሎ መልስ እግሮቿ ቤቷን ሲረግጡ ዓይነ ህሊዋ ድካሟን የሚያስታውሳት፣ ስለ ነገው አብዝቶ የሚያሳስባት ባተሌዋ ሴት:: ለእሷ ይህ ትውስታ ማለት በይደር የሚያልፍ አይደለም፤ ወደአይቀሬው ነገ አሻግሮ ዳግም ከትካዜ ይጥላታል እንጂ::
ልጅነት…
ብዙነሽ አድማሱ ስለልጅነቷ የተነገራትን ይዛ አድጋለች:: ወላጅ እናቷን ያጣችው ገና በጠዋቱ ነበር:: ከፍ ስትል እንደ እኩዮቿ ‹‹እማዬ›› ብላ ለመጣራት አልታደለችም:: ከእሷ ሌላ ልጅ የለምና ብቸኝነትን መቀበል ግዷ ነበር:: እናቷ እንዳረፉ ግን ለጥቂት ጊዜያት ከዘመድ እጅ አርፋለች::
አባቷ ከሚስታቸው ሞት በኋላ በብቸኝነት የቆዩት ለጥቂት ጊዜ ነበር::የወዳጅ ዘመድ ግፊት፣የአካባቢው ሰው ምክር ፈጥኖ ከሌላ ትዳር አገናኛቸው:: አባወራው አዲስ ህይወትን ከአዲስ ሚስት ሲጀምሩ ትንሽዬዋ ብዙነሽ ትኩረት ታጣ ጀመር:: እንጀራ እናቷ ለባሏ እንጂ ለእሷ ግድ የምታጣ ሆነችባት::
ሴትዬዋ መጀመሪያ ሰሞን የነበራት ፈገግታ እያደር ከገጽታዋ ጠፋ:: ለህጻኗ ፍቅር ነፈገቻት፣ በአባወራዋ ፊት ሞገስ ለማግኘት ፣ ቤቷን ለመሙላት ብቻ የምትኖር ሆነች:: አባት የሚስታቸውን ሀዘን በአዲሷ ሙሽራ ለመርሳት አልዘገዩም:: ፈገግታዋ ፣ ‹‹አለሁልህ›› ማለቷ የልጃቸውን ፍቅር እስኪነጠቁ አዘናጋቸው:: ብዙነሽ ነፍስ ማወቅ ስትጀምር ተከታትለው የተወለዱ እህት ወንድሞቿን አገልጋይ ልትሆን ተፈረደባት:: እነሱን አቅፎ አዝሎ መዋል ግዴታዋ ሆነ::
የነብዙነሽ መንደር ከከተማ የራቀ ነው:: ገጠር በመሆኑ በቀላሉ የተፈለገው አይገኝም:: የበረቱ አንዳንድ የሰፈሩ ልጆች ለትምህርት ሲሉ ረጅም የእግር መንገድ ያቋርጣሉ:: ከነዚህ መሀል ከዓላማቸው ደርሰው ዓመቱን የሚጨርሱ ጥቂቶች ናቸው:: ጥር ሲደርስ አብዛኞቹ ለትዳር ይታጫሉ፤ ሌሎቹም ቢሆኑ ወላጆቻቸውን በእርሻ ለማገዝ ከትምህርት ያቋርጣሉ::
ይህ እውነት ባለበት ለብዙነሽ ዕውቀት አስቦ ትምህርት ቤት የሚልካት ፣ ቀለም የሚያስቆጥራት የለም:: ሆዷ ሞልቶ ካደረ ሁሌም መብቷ እንደተጠበቀ ይታሰባል:: ብዙነሽ ዕድሜዋ ቢደርስም ትምህርት ቤት አልገባችም:: የልጅነት ጫንቃዋ በሥራና ልጆች ማሳደግ እንደጎበጠ ጊዜ ገፋች:: ከዚህ ሌላ ህይወት አታውቅምና ኑሮዋን አምና ተቀብላለች::
አስታማሚ አልባ ሕመምተኛ
ትንሽዋ ልጅ አንዳንዴ ጤናዋ ይቃወሳል::ደርሶ ራሷን የሚይዛት ህመም በትኩሳት በጭንቀት ሲያንገላታት ይውላል:: እንዲያም ሆኖ ስለሷ ህመም ማንም ‹‹ነገሬ›› የሚል የለም::አንዳንዴ ሲብስባት ለመተኛት ታስባለች::ይህን ከመሞከሯ ግን የእንጀራ እናቷ ኃይለኛ ድምጽ እንደ መብረቅ ይጮህባታል:: ይህኔ ሁሉን ትታ ደንግጣ ትነሳለች::
አሁን የብዙነሽ እንግልት ጨምሯል:: ከራስ ምታቷ አልፎ ዓይኖቿ ክፉኛ እየታመሙ ነው::ጠዋት ከእንቅልፏ ስትነቃ ሁለቱም ዓይኖቿ ተደፍነው ያረፍዳሉ:: በወጉ እስኪገለጡ የሚያቆያት የለም:: እንደምንም እየተደናበረች ከዕለት ግዴታዋ ትገኛለች::
ሰአቱ ረፈድ ሲል የብዙነሽ ዓይኖች ከብርሀን ሊገናኙ ትግል ይይዛሉ::ጸሐይ ላይ ከሆነ ፈጽሞ ልትገልጣቸው ይቸግራታል::በቆሸሹ እጆቿ ደጋግማ እያሸች የተደፈነውን ልታስለቅቅ ትሞክራለች:: ለጊዜው ይህን ማድረጓ እፎይታ እየሰጠ ያውላታል:: ይህን ስታደርግ ቀርቦ ‹‹ተይ፣አትንኪው›› የሚላት የለም::
ቀኑን ሙሉ ዝንቦች ሲወሯት እያዩ ዝም ይሏታል:: ከውሃ ሳትገናኝ፣ፊቷ ሳይታጠብ ያለመፍትሔ መሽቶ ይነጋል:: አጋጣሚውን እንደ ልማድ የቆጠሩት ቤተሰቦች በማግስቱም ከግዴታዋ እንድትገኝ ስራዋን ይጠቁሟታል:: ከዝንቦች እየተጣላች፣ከህመሟ እየታገለች ልጅ አዝላ ትውላለች:: እንዲህ ማድረግ አይቀሬ ግዴታዋ ሆኗል::
አሁን የብዙነሽ ህመም እየባሰባት ነው::ሁኔታዋን ያስተዋሉ አንዳንዶች የዓይኖቿ ችግር ‹‹ምች›› እንደሆነ ገምተዋል:: ከዚህ በላይ አውቀናል ያሉት ደግሞ መፍትሔ ያሉትን ጠቁመው፤ የአበሻ መድኃኒት ተጀምሮላታል::ሁሌም ማለዳ ከዓይኖቿ የሚታሰረው ቅጠላቅጠል መሳይ ዕጽ ከስቃይ በቀር በጅቷት፣ጠቅሟት አያውቅም::
ብዙነሽ ዘወትር ራሷን ይዛ ልቧን ደግፋ ትውላለች::ስቃዩ ሲብስ ዕንባ የሚሞሉ ዓይኖቿ ከብርሃን ለመታገል ይቸግሯቸዋል:: እንቅልፍ አልባዋ ታዳጊ ህመም ስቃይዋ ቢበዛም ከዕለት ግዴታዋ አልራቀችም:: እጅ እግሯ ይሰራልና የሚያዝ የሚጠራት ፣ነይ፣ሂጂ የሚላት ብዙ ነው::
ውሎ አድሮ የብዙነሽ ዓይኖች ሰላም ያገኙ መሰሉ:: በየቀኑ መደፈናቸው ቀርቶ ነጻነታቸው ተስተዋለ:: እንደቀድሞ ብርሃን ለማየት የማትደፍረው ትንሽ ልጅ ጨለማና ደመና ምርጫዋ ሆነ:: አንዳንዴ ከእንጀራ እናቷ ጋር ገበያ ውላ ስትገባ በከባድ በራስ ም ታት ትሰቃያለች::
ቀናት የሚሻገረው ይህ ስሜት አሁንም ለቤተሰቡ የተለመደ ሆኖ ቀጥሏል::እንዲያም ሆኖ ብዙነሽ ዓይኖቿ እየደከሙ እይታቸው እየቀነሰ ነው:: የልጅነት ጫንቃዋን ብቻ የሚፈልጉት ወላጆቿ ስለእሷ ችግር ደንታ ካጡ ቆይተዋል:: አንዳንዴ ህመሟን ደፍራ መናገሯ ካለመታዘዝና ስንፍና ይቆጠርባታል:: ፍራቻዋ ዝምታን አስመርጦ በትካዜ ያውላታል::
ከቀናት በአንዱ …
ብዙነሽ ስለ ሟች እናቷ ያላት ትውስታ ደብዛዛ ነው:: አንዳንዴ ግን በወጉ የማታውቃቸው እናት በሃሳቧ ውል እያሉ ይፈትኗታል:: እንዲህ ሲሆን ተሰምቷት የማያውቅ ናፍቆት በውስጧ ውሎ ያድራል:: እናቷን አቅፋ መሳም ትሻለች:: በጉያቸው ተወሽቃ እንደ እህት ወንድሞቿ ጡት መጥባት ያምራታል::
ይህ ሁሉ ምኞት ግን ለእሷ መቼም የማይፈታ ህልም ነው:: ደጋግማ ብትመኝ አታገኘውም፣ ብትሮጥ አትደርስበትም:: መለስ ቀለስ የሚለው የብዙነሽ ህመም አንዳንዴ ጫን አድርጎ ይጎበኛታል:: ችግሩ አሁንም ችግሯ ለሌሎቹ እንደ ቀላል እየተቆጠረ ነው::
እንግዳዋ…
አንድ ቀን በድንገት ወደ እነ ብዙነሽ ቀዬ የአንዲት እንግዳ እግሮች ደረሱ:: ወይዘሮዋ ወደመንደሩ ከዘለቁ ዓመታት ተቆጥረዋል:: እንዲያም ሆኖ ማንነታቸው አልተረሳም:: እሳቸው በመጡ ጊዜ ያደጉበትን ቀዬ እየዞሩ ማየትን ለምደዋል። ቀናዋ ሴት ሁሌም እጃቸው ርጥብ ነው:: ለሰው ለመንደሩ የጎደለውን ያውቃሉ:: በየቤቱ እየዞሩ የአቅማቸውን ያደርጋሉ::
ቀናዋ ሴት አካባቢውን ጠያይቀው እንደጨረሱ ማምሻቸውን ወደ እነብዙነሽ ቤት ማምራት ፈልገዋል:: ጊዜው ሳብ ቢልም በቤቱ ከባድ ሀዘን ማለፉን ሰምተዋል:: ለቅሶ ቢቆይም ለቅሶ ነው:: ዓመታት ቢያልፍም ተጎጂውን ማጽናናት ‹‹አይዞህ›› ብሎ ማበርታት ግድ መሆኑን ያውቃሉ::
ቀናዋ ሴት ከቤቱ ሲዘልቁ ዓይናቸው ያረፈው በትንሽዋ ብዙነሽ ላይ ሆነ:: የሟቿ ወይዘሮ ብቸኛ ልጅ እንደሆነች ያውቃሉ:: ገና ሲያይዋት ውስጣቸው ተነካ፣እጅግ የተጎሳቆለችው ሕፃን ልባቸው ለመግባት አልዘገየችም:: ዓይኖቿ ታመዋል፤ አካሏ ከስቷል:: ልብሷ በላይዋ አልቆ እጅጉን ቆሽሿል:: ግራ ተጋብተው ምክንያቱን ጠየቁ:: ምላሹን ለማግኘት አልቸገራቸውም::
ማግስቱን እንግዳዋ ከአባወራው ቤት ዘልቀው ስለብዙነሽ ብዙ አወጓቸው:: በተለይ በዓይኖቿ ላይ ያዩት ጉዳት ከስጋት ጥሏቸዋል:: ጉዳዩን በግልጽ አነጋግረው ከአንድ ውሳኔ መድረሳቸውን ተናገሩ። ብዙነሽ ከእሳቸው ጋር አዲስአበባ ሄዳ ዓይኖቿን እንድትታከም ወስነዋል::
የብዙነሽ አባት የልጃቸው መራቅ ቢያስጨንቃቸውም መታከሟን መርጠውታል:: እስከዛሬ ያለመፍትሔ ለመቆየቷ ጥፋተኝነት እየተሰማቸው ነው:: አሁን ልጃቸውን በይሁንታ አስረክበው በሰላም ሸኝተዋታል:: የዘገየ ጸጸት ቢሆንም ውስጣቸው ሀዘን ሲመላለስ ከርሟል::
አዲስ አበባ…
ወይዘሮዋና ብዙነሽ የወሎ ምድርን ለቀው አዲስ አበባ ገብተዋል::ለእሷ ከምንም በላይ ከነበረችበት ህይወት መራቋ ያስደሰታት ይመስላል:: የወይዘሮዋ እውነት ግን ከዚህ የተለየ ነበር:: ዓይኖቿ ላይ ያስተዋሉት ችግር እንቅልፍ እየነሳቸው ነው::
ዋል አደር ብለው ወይዘሮዋ ብዙነሽን ከአንድ ሆስፒታል ይዘዋት ደረሱ:: አስቀድመው ለእሷ ህክምና የሚበጀውን ስፍራ ሲያማርጡ ቆይተዋል:: ሀኪሞች እጅ የገባችው ሕፃን በአስቸኳይ ህክምና ምርመራውን ቀጠለች::ለቀናት በምልልስ የዘለቀው ጊዜ መጨረሻው ከወይዘሮዋ ስጋት ላይ የሚያደርስ ሆነ::
ብዙነሽ የዓይኖቿ ውስጣዊ ክፍል ክፉኛ ተጎድቷል:: እስከዛሬ ያለአንዳች ህክምና መቆየቷም ችግሩን አባብሶታል:: ለጊዜው በመድኃኒትና በዓይን ጠብታ ጊዜውን ገፋች ::መነጽር ታዞላትም የምትፈራውን ብርሃን ስትከላከል ቆየች:: ጥቂት ቆይቶ ግን ሙከራው ሁሉ ተስፋ የሚያስቆርጡ ምልክቶች መታየት ያዙ:: ለዓመታት ጉዳት ሲያስተናግዱ የቆዩት ዓይኖቿ ብርሃናቸው ተፋዘዘ::
በተለይ የቀኝ ዓይኗ አስቀድሞ መጎዳቱ ቀጣዩን ጊዜ በእይታ ሊቆይ አልታደለም:: ቀስ እያለ ከብርሃን ጋር ተለያየ:: አሁን የብዙነሽ ቀሪ ተስፋ የግራ ዓይኗ ብቻ ነው:: እሱም ቢሆን የእይታው መጠን በከፊል ሆኗል:: በመነጽር እየታገዘች መንገድ የለመደችው ብዙነሽ ጊዜው ሲነጉድ ፣እድሜዋ ሲጨምር ያለፈውን ወደ ኋላ እያሰበች የሆነባትን በደል በትዝታ አመላለሰችው::
የዓይኗን ብርሃን አጥታ ለጉዳት መብቃቷ መነሻው የእናቷ በሞት መለየት ነው::አባቷ ልጅነቷን ጤንነቷን ነጥቃዋታል::እንደልጅ መብትና ፍቅር ሊኖራት ሲገባ በእንጀራ እናት ለበቅ ከዕድሜዋ ላይ ዕድሜን ቀንሰዋል::ከምንም በላይ ግን ሳታስበው የዓይኖቿን ብርሃን ማጣቷ ከልብ ያበግናታል::
ከዓመታት በኋላ…
እነሆ! ጊዜያቶች አልፈው ዓመታት ተተክተዋል:: ዛሬ ብዙነሽ ወጣትነቷን ተሻግራ ጥሩ ወይዘሮ ሆናለች:: በህይወቷ ብዙ ውጣውረዶች ተጋፍጣለች:: በገሚሶቹ ስትሸነፍ በሌሎቹ በድል እየቆመች አልፋዋለች:: ብዙ ጊዜ አልቅሳ ብዙ ጊዜ ቸግሯታል::
ሀዘንና መከራ ለእሷ ብርቅ ሆነው አያውቁም:: ከምንም በላይ ግን ለዛሬ መቆም ምክንያት የሆኗትን ወይዘሮ ሞት መቋቋም ተስኗት ጊዜያትን አንገቷን ደፍታለች:: ሀዘን የገባው ልቧ ስለሳቸው አንብቶ፣አልቅሶ አያባራም::
እሳቸው ለእሷ የህይወቷ ብርሃን የዓይኖቿ መብራት ነበሩ:: ከገጠሩ የስቃይ ቤቷ ነጥቀው ሰው እንድትሆን አግዘዋታል::ከችግር አውጥተው በመልካም ህይወት አኑረዋታል:: ቢዘገይም እሳቸው ከእሷ ጎን ቆመዋል:: በሰዎች ክፋትና ግዴለሽነት የተጎዱ ዓይኖቿ በነጭ በትር እንዲመሩ፣ እግሮቿ መንገድን እንዲለምዱ፣ተስፋ ሆነዋታል::ይህን ሁሉ የሆኑ እናት ዛሬ ከጎኗ የሉም::
ብዙነሽ ከእሳቸው ሞት በኋላ ከቤታቸው ለመውጣት ቀናት አልቆጠረችም:: ‹‹ይመለከተናል›› ያሉ ወራሾች ቤቱን ሲይዙት የእሷ ዕጣ ፋንታ ግልጽ ነበር:: ከነበረችበት የሞቀ ቤት ስትወጣ ከእጇ የቀረችው ነጯ በትሯ ነች:: ከዚህ በኋላ ከፊት ቀድማ የምትመራት ብቸኛ አጋር እሷ ብቻ ትሆናለች::
ብቸኝነትን በፈተና…
ብዙነሽ ግማሽ ዕድሜዋን ከገፋችበት ቤት ከወጣች ቆየት ብላለች::ዛሬም ቢሆን በወጉ ቀለም ያላየው ማንነቷ ለሥራ ውድድር አላበቃትም:: ቀድሞ በከፊል ሲያይ የቆየው ግራ ዓይኗ ሙሉ ለሙሉ ብርሃኑን ተነጥቋል:: የነጭ በትር ጉዞን በቀላሉ አለመደችም::
መንገዱ ለእሷ ምቹ ሆኖላት አያውቅም:: ሜዳ ያለችው ገደል እየሆነ የተቸገረችበት ጊዜ በርካታ ነው:: እንዲያም ሆኖ ራሷን ለማሸነፍ ብርቱ ናት:: ዓመታትን በቅጥር ከሠራችበት የአካል ጉዳተኞች ተቋም ብዙ ተምራለች:: ጥበበኛ እጆቿ ስጋጃውን፣ ቡርሽና መጥረጊያውን በጥራት ያመርታሉ:: ክፍያው ጥቂት ቢሆንም ራሷን አስችሎ ዓመታትን አሻግሯታል::
ዛሬን…
ብዙነሽ የተመላለሰችባቸው የህይወት መንገዶች ቢያደክሟትም እጅ ሰጥታ አታውቅም:: ሁልጊዜ ለመኖር ትታትራለች፣ ከጥቂት ጊዜያት በፊት ያቋረጠችው ሥራ ልምድ አዳብራ ኑሮዋን የገፋችበት ነው:: በበጀት ምክንያት ደመወዝ ተቋርጦ ገቢ ባጣች ጊዜ ከእጅ ወደ አፍ በሆነው ኑሮዋ ተፈትናለች::
በወጉ እግር ለማታዘረጋው ጠባብ ቤቷ ወር ላይ ኪራይ ይጠበቅባታል:: ለነገ ብላ ጥሪት የማታውቀው ብዙነሽ ዛሬ ለእኔ የምትለው ወዳጅ ዘመድ ጎኗ የለም:: አሁን ምርጫ የላትም፤ ‹‹ዓይን የለኝም›› ብላ ልመና መውጣት አትሻም::
ዛሬም ከጎድጓዳ ምቾት አልባ አልጋዋ ላይ ተኝታ ስለመንጋቱ የሚያበስሯትን የወፎች ድምጽ ትጠብቃለች:: ዛሬን ባለፈች ቁጥር ስለነገ ማሰቧ ግድ ሆኗል:: ነገ የትናንቱ ድካም አለበት:: ትናንት አልፏል፤ ነገ ደግሞ ገና ነው:: ብዙነሽ ዛሬን በወጉ ሳይነጋ ከቤት መውጣት አለባት::
ህይወት ሌላ ምርጫ ሰጥታ ጧፍ ነጋዴ ካደረገቻት ቀናት ተቆጥረዋል:: እሱን ለማድረስ ከቤተክርስቲያን ደጃፍ የምትደርሰው በማለዳው ከወፎች ጫጫታ ጋር ነው:: ለወጉ ካልጋው ታርፋለች እንጂ እንቅልፍ ከራቃት ቆይቷል:: በነጋ አልነጋ ጭንቀት ስትባንን ታድራለች:: ለእሷ ያልሆነን ብርሃን ለሌሎች ልታደርስ ትጣደፋለች::
ይህ ብርሃን ለእሷ መብራት ሆኖ አያውቅም:: ጨለማውን አይገፋላትም:: መንገዷን አያሳያትም:: ግን ስለሌሎች ስትል ይህን የጧፍ መብራት ትሸጣለች:: ለእሷ ውጤቱ ምንዳዋ ነው:: እንጀራ ይሆናታል:: እንደ ነጭ በትሯ ስለመኖር መንገዷን ይመራታል:: ብዙ ለሆነችው ብዙነሽ ጠንካራዋ፤ ልበ ብርሃኗ ሴት::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም