ባለፈው ረቡዕ ጠዋት ነው። በመንግሥት ሠራተኞች ማመላለሻ አገልግሎት (ሰርቪስ) ወደ ሥራ እየሄድኩ ነው። አንድ የንግድ (የግል) ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ተከፍቷል። ጋዜጠኛዋ ‹‹ከአዲስ አበባ ፖሊስ የደረሰን አንድ የወንጀል መረጃ አለ›› አለች። ምን ተፈጥሮ ይሆን ብዬ ጆሮዬን አቁሜ ሰፍ ብዬ ማዳመጥ ጀመርኩ። የተናገረችው መረጃ ግን ማክሰኞ አመሻሽ ጀምሮ በዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ሲዘዋወር ያመሸ የሆነች ወጣት ሴት የመኪና ስርቆት ዜና ነው። በተለይ በማኅበራዊ ገጾች በቀልድ ጭምር ‹‹እንዴት ይቺን የመሰለች ቆንጆ ትሰርቃለች?›› በሚል በሰፊው ተዘዋውሯል።
በመጀመሪያ ‹‹እዚህ ውስጥ ካሉት ሰዎች ይህን ዜና ያልሰማ ይኖር ይሆን?›› ብየ አሰብኩ። ቀጥሎ፤ በአዲስ አበባ ነባራዊ ሁኔታ ማኅበራዊ ሚዲያ የማይጠቀም ይኖር ይሆን? በማለት ዜናው እንደ አዲስ መቅረቡ አግባብ ነው፤ አግባብ አይደለም በሚለው ከራሴ ጋር ተከራከርኩ።
ዜናውን እንደ አዲስ የሚሰማ ሰው ይኖራል። ማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀም ሁሉ ሁሌም ይጠቀማል ማለት አይደለም። በተለይም የቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑ እናቶችና አባቶች ማታ ከቤተሰብ ጋር ሆነው ላይጠቀሙ ይችላሉ። የከፈቱትን ቴሌቪዥንም ልብ ላይሉት ይችላሉ፤ ምናልባትም የዜና ቻናል ላይ ላይሆን ይችላል። ስለዚህ ዜናው መቅረቡ ችግር የለውም። አቀራረቡ ግን ችግር ነበረበት፤ በአዲስ አበባ ነባራዊ ሁኔታ አብዛኛው ሰው የሰማው ዜና ነው። መቅረብ የነበረበት ልክ እንደ አዲስ አሁን የደረሰ መረጃ አስመስሎ ሳይሆን ከትናንት ጀምሮ የቀረበ መሆኑን በመግለጽ ነው። ምክንያቱም የብሮድካስት ሚዲያ ባሕሪ አዲስ ነገር መንገር ነው። አለበለዚያ የሰማውን ዜና እንደ አዲስ ሲያቀርቡለት ሬዲዮ የከፈተው ሰውዬ ጣቢያውን ይቀይረዋል።
ዘመኑ ፈጣን የመረጃ አማራጮች ያሉበት መሆኑ እንደ ምክንያት ቢቆጠርም፤ አሁን አሁን ግን የሬዲዮ ጣቢያ ላይ ያለው ጉጉት የቀዘቀዘ ይመስላል። የሬዲዮ ማድመጫ ፀጉር ቤት እና ታክሲ ብቻ ይመስል ሌላ ቦታ ብዙም አይሰማም። በተለይ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ሬዲዮ ማድመጥ ብዙም የሚስተዋል አይደለም፤ ልክ እንደ ህትመት ሚዲያው እየተዳከመ ይመስላል።
‹‹በእገሌ ሬዲዮ ጣቢያ የተላለፈ›› ተብሎ አጀንዳ የሆነ ትልቅ ጉዳይ እምብዛም አይሰማም። በቴሌቪዥን የተላለፉ ግን ብዙ ጉዳዮች አጀንዳ የመሆን ዕድል አግኝተዋል። ለምን ይሆን? ትልልቅ ፖለቲከኞች እና ባለሥልጣናት ቴሌቪዥን ላይ ሲቀርቡ የሚታየው? ትልልቅ ፖለቲከኞች የሚቀርቡበት የሬዲዮ ጣቢያ አንድ ወይም ሁለት መጥቀስ ቢቻል ነው። ከብዛታቸው አንፃር በጣም አነስተኛ ነው።
በሌላ በኩል ግን የሚዲያ ግንዛቤ (Media Literacy) ችግርም ጎልቶ ይታያል። ማኅበረሰቡም ሚዲያ የሚመስለው ቴሌቪዥን ብቻ ሆኗል። ልብ ብለው ቢያስተውሉት ግን ሬዲዮ አንድ ነገር ላይ በጥልቀት የማተኮር ልዩ ባሕሪ አለው። የሕክምና፣ የሕግ፣ የምሕንድስና፣ የአርክቴክት፣ የቱሪዝም፣ የትራፊክ፣ የተሽከርካሪ ባሕሪያት (ሳይንስ)፣ የአካል ጉዳተኛ፣…. በአጠቃላይ አንድ ጉዳይ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ፕሮግራሞች አሉ። እንዲህ አይነት ፕሮግራም የሚበረታታ ነው። አንድን ሙያ በጥልቀት እንዲታይና እንዲተነተን ያስደርጋል። በዚያ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ሰዎች እውቀት እንዲያገኙ ያደርጋል። ለምሳሌ ስለተሽከርካሪ ባሕሪያትና መገጣጠሚያዎች የሚሠራ ፕሮግራም ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ በዚያ ዘርፍ ለሚማሩ እና ለሚሠሩ ሁሉ ራሱን የቻለ ትምህርት ነው። ሕግ ላይ፣ ሕክምና ላይ፣ ቱሪዝም ላይ፣ ውበት ላይ . . በየዘርፉ ያሉ ሙያዎች የራሳቸው ታዳሚ አላቸው። በባለሙያ ሲብራሩና ሲተነተኑ ብዙ ዕውቀት ያስይዛሉ። የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥራቸውም አነስተኛ ስለሆነ ብዙም የዚህ አይነት ፕሮግራም የላቸውም፤ ያሉትም መዝናኛ እና የውጭ አገር ስልት ያለው ይዘት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። ሀገርኛ ፕሮግራሞችም እንዳሉ ሳንዘነጋ ማለት ነው።
የኤፍኤም ጣቢያዎችን በጣም የታዘብኳቸው ዜና ላይ ነው። የአንድ መገናኛ ብዙኃን ተቀዳሚ ሚናው ዜና ነው። ሬዲዮ ሲባል ለማንም ቀድሞ ትዝ ማለት ያለበት ዜናው ነው። ሬዲዮ ደግሞ በባሕሪው ከየትኛውም የመገናኛ ብዙኃን በተሻለ ቀዳሚ መሆን አለበት። እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው። በቴሌቪዥን (ይባስ ብሎም በጋዜጣ) እየተቀደሙ ነው። ሬዲዮ በባሕሪው በደቂቃ ልዩነት ውስጥ የተፈጠሩ ክስተቶችን ለመዘገብ ዕድል ያለው ነው። ቴሌቪዥን ይሄን ዕድል ማግኘት አይችልም። እርግጥ ነው ቀረፃ ባይኖረውም ጉዳዩን ብቻ ዜና አንባቢው ማሳወቅ ይችላል። በሬዲዮ ግን ሰበር ዜና መስማት ብዙም አያጋጥመንም። ውሎውን ሲራገብ የዋለ ክስተት ነው የምሽት 12፡00 ዜናቸው ላይ የሚያወሩት።
ሌላው ችግራቸው ምንጭ ሳይጠቅሱ (ሁሉንም ማለቴ አይደለም) ሌላ መገናኛ ብዙኃን የሠራውን ዜና ማንበብ ነው። በአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ላይ በተደጋጋሚ ሰምቻለሁ። ቃል በቃል ሙሉውን አንብበው የሪፖርተሩ ስም ላይ ሲደርሱ ‹‹ዘገባው የእገሌ›› ነው ብለው የራሳቸውን ሪፖርተር ስም በመጥቀስ ይደመድሙታል። እንግዲህ ያ ሪፖርተራቸው ዋሽቷቸዋል ማለት ነው፤ ወይም ራሳቸው ሆን ብለው አድርገውታል ማለት ነው። እንደ አርታኢ መገናኛ ብዙኃንን አለመዳሰሳቸውና አለማስተካከላቸውም ስህተት ነው። እርግጥ ነው አንድ አርታኢ የእያንዳንዱን መገናኛ ብዙኃን ዜና ሁሉ አያይም፤ ግን የዕቅድ ዜና ሲሆን በቤቱ ሪፖርተሮች የተሠራ መሆን አለመሆኑን ማወቅ ነበረበት። ደግሞ ለምን እንደሆነ አላውቅም፤ ብዙ ጊዜ ምንጭ የማይጠቅሱት ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሲወስዱ ነው። በዓይናቸው ካስተዋሉ ሰዎች እንደሰማሁት የሌላ መገናኛ ብዙኃን ድረ-ገጽ ከፍተው ቀጥታ ከዚያው ላይ የሚያነቡ የሬዲዮ ጋዜጠኞች አሉ። ይሄን ማድረጋቸው ጥሩ ነበር፤ ችግሩ ራሳቸው የሠሩት ዘገባ አድርገው ነው የሚያቀርቡት። የሰው ኃይል እጥረት እንዳለባቸው ግልጽ ነው፤ ቢሆንም ግን ምንጭ ላለመጥቀስ ምክንያት አይሆንም።
የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ ደግሞ ችግሩ የባሰ ነው። የሰው ኃይል እጥረት ብቻ ሳይሆን የሙያ ልምድ የለም፤ የሙያ ብቃትና ልምድ ሲኖራቸው ወደ ሀገር አቀፍ ጣቢያዎች ይሄዳሉ። የብሮድካስት ባለሥልጣን ለማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች በተደጋጋሚ ሥልጠና ይሰጣል፤ በየሥልጠናው የሚነሳው ግን ተመሳሳይ ችግር ነው።
እነዚህ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ብቃት ያለው በቂ ባለሙያ ቢኖራቸው ለሀገር አቀፍ ጣቢያዎች ትልቅ የመረጃ ምንጭ የሚሆኑ ናቸው። ዳሩ ግን ‹‹እገሌ የማኅበረሰብ ሬዲዮ እንደዘገበው›› ሲባል ሰምተን አናውቅም። ቢሠራባቸው ግን የአካባቢውን ሁኔታ በቅርበት የሚያውቁት እነርሱ ነበሩ። ለምሳሌ የጉራጌ ማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ አለ እንበል። አዲስ አበባ፣ መቀሌ ወይም ባሕር ዳር ሆኖ ስለጉራጌ በስልክ ከመጠየቅ ከዚህ ሬዲዮ ጣቢያ መረጃ መውሰድ የበለጠ ቅርብ ይሆን ነበር። እርግጥ ነው የማኅበረሰብ ሬዲዮ እነዚህ አካባቢዎች አይደርስም፤ ዳሩ ግን የቴክኖሎጂ ዘመን መሆኑን አንርሳ። የተደራጀ ድረ-ገጽ ካላቸው ከዚያ ላይ ይጫናል። ብዙ የወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤቶች እኮ የማኅበራዊ ገጾች አሏቸው። በነገራችን ላይ እነዚህ የወረዳ ኮሙዩኒኬሽን የማኅበራዊ ገጾች በተደጋጋሚ ስለሚሳሳቱ ከመረጃ ሰጪነታቸው ይልቅ አዝናኝነታቸው በልጧል።
የሬዲዮ ጣቢያዎች በበዙ ቁጥር ተጨማሪ አዳዲስ ሀሳቦችና ፈጠራዎችም አብረው ይብዙ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም