የውሽሞቹ ሽኩቻ

ቅናት – የሰዎችን ውስጥ የሚበላ አሰቃቂ ስሜት ነው። ይህ አሰቃቂ ሰሜትም የሰዎች ንፁህ ህልሞች ይመርዛል። በዚህም ምክንያት ቅናት ሰዎችን ቅር የሚያሰኝና መራር ህመም ትቶ የሚያልፍ ጉዳይ ነው።

ቅናት ለአንዳንዶች በተለይ በወጣት ወንዶች እና ሴቶች መካከል ለፍቅር ወሳኝ እይታ ነው ብለው ያምናሉ። ቅናት የፍቅር ማጣፈጫ እንደሆነ የሚያምኑ ቢኖሩም በቅናት የተነሳ ቤት ንብረታቸውን ያጡ፤ ከንብረትም በላይ የቤተሰብ ፍቅር የተነጠቁትን ቤት ይቁጠራቸው።

የቅናት ስሜት ሚስት ወይም ባል ላይ እኩል ጥቃት የሚያደርስ ጉዳይ ነው። በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ብዙ ችግሮች ይፈጥራል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለ ነገር ፍቺን፤ አካላዊ ጥቃትን፤ የመንፈስ ጭንቀት የመሳሰሉ ሁኔታዎችን የሚያመጣ ነው።

ከላይ ያነሳነው የቅናት ጉዳይ ሳይሸነቁጠው ያለፈ ሰው ይኖራል ተብሎ ባይገመትም ለዛሬ የተዘጋ ዶሴ አምድ ይዘንላችሁ የመጣነው ጉዳይ እንዲህም ያለ ቅናት አለ እንዴ የሚያሰኝ ነው። ይህን መረጃ በዚህ መልኩ ለአንባቢ እንዲደርስ ለፈቀዱልን የአዲስ አበባ ፖሊስ መዝገብ ቤት ባልደረቦች አመስግነን ጽሑፉን እንድታነቡት ጋብዘናል።

ነገሩ እንዲህ ነው። አንድ ከትዳር አጋሩ ውጪ የፍቅር ጓደኛው የነበረችው ሰው ቤቷ በሄደበት አጋጣሚ እሷን ተከትሎ ከቤት በመውጣት በዱላ ሊመታኝ ነበር ካለው ግለሰብ ጋር ባደረጉት ፀብ ሕይወት ይጠፋል፡፡እነዚህ ሁለት ውሽሞች እስከመገዳደል ያደረሳቸውን ታሪክ እነሆ፡፡

ፍቅረኛሞቹ

መጀመሪያ የተዋወቁ ሰሞን በነፃነት የሚንቀሳቀስ ሰው ነበር። አብረው በእግር መጓዝ፤ ፍቅረኞች እንደሚያደርጉት በየካፌውና ሬስቶራንቱ አብረው መታየት ያዘወትሩ ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ሰውየው በድብቅ መገናኘትን ምርጫው ማድረግ ጀመረ። ብዙ ጊዜ ምሽት ላይ ስልኩን ማጥፋት ፣ መዋሸትና የተለያዩ ነገሮችን ማድረግ መገለጫው ሆነ።

ልጅቷ ከልቧ ብትወደውም በነፃነት አብረው ያለመሆናቸው ነገር ይከነክናት ጀመር። በየእለቱ የሚቀያየረው የሰውየው ባህሪ አንጀቷን ቢበላው በድብቅ ክትትል ታደርግበት ጀመር። ከእሷ ጋር ለመገናኘት እንዲመቸው ከመኖሪያ ሰፈሩ ራቅ ወዳለ ቦታ ቤት እንድትከራይ ካስገደዳት በኋላ ጥርጣሬዋ ወደ እርግጠኝነት ተጠጋ።

ይች ወጣት ባል አገኘሁ ብላ ፈጣሪዋን ባመሰገነች ማግስት ፍቅሬ ትዳሬ ይሆናል ያለችው ሰው የሌላ ሰው ባልና የሁለት ልጆች አባት መሆኑን ሰማች። የሰማችውን ነገር በተለያዩ ማስረጃዎች ካረጋገጠች በኋላ ለፍቅረኛዋ ነግራ ግንኙነቱ እንዲቋረጥ ለማድረግ ወሰነች።

ግንኙነቱ እንዲቆም የፈለገችው ሴት

ምንም ያህል ብትወደውም ነገ የኔ ይሆናል ብላ የማታስበው ሰው በህይወቷ ውስጥ እንዲቆይ መፍቀድ ከበዳት። ምንም እንኳን ግንኙነቱ እንዲቋረጥ ብትፈልግም የገንዘብ ምንጯ በእሱ ላይ የተመሰረተ ነበርና የራሴ የምትለውን ገቢ እስክታገኝ ድረስ ታግሳ በዘዴ መራቅን ምርጫዋ አደረገች።

በመጣ ቁጥር ስራ መጀመር እንደምትፈልግ ተናግራ ስራ ማፈላለግ ጀመረች። ስራ በምትፈልግበት አጋጣሚ ደግሞ ሌላ ሰው ተዋወቀች። ይህ የተዋወቀችው ሰው ስራ አግኝቶ እንደሚያስገባት ከመንገር በተጨማሪ ሊፈርስ ወደ ተቃረበው ግንኙነት ውስጥ ሶስተኛ ሰው ሆኖ ገባ።

ልጅትም ራሷን ለማኖር የሚያስችል ገቢ ልታገኝበት የምትችልበት ስራ ስታገኝና መደላደሏን ስታረጋግጥ ከባለትዳር ወንድ ጋር ግንኙነት መቀጠል እንደማትፈልግ ትናገራለች። የተለያዩ ምክንያቶች እየዘረዘረ ሊያስረዳት ቢሞክርም እስከመጨረኛው አብሯት ሊቆይ ከማይችል ሰው ጋር ግንኙነት እንዲኖራት እንደማትፈልግ ቁርጥ አድርጋ ነገረችው።

ምንም እንኳን ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላትና ከእሱ ጋር መቀጠል እንደማትፈለግ አስረግጣ ብትናገርም ሰውየው እየተመላለሰ ሲያባብላትና ሲለማመጣት ሰንብቷል። በዚህ መካከል ስራ ያስገባትን አዲሱን ፍቅረኛዋን ቤት ማምጣት የጀመረችው ሴት ባልትዳሩን ሰው ገሸሽ ማድረግ ትጀምራለች።

ሰውየው እግር ቢያበዛም ፊት እየነሳች እግሩ እንዲያጥር ለማድረግ ብትሞክርም ሰውየው በእልህ መመላለስ አበዛ። ቤት የለሁም ብትለውም ገፍቶ እየመጣ ከአዲሱ ፍቅረኛዋ ጋር ጥሩ ጊዜ እንዳታሳልፍ እንቅፋት ይሆንባት ጀመር። በዚህ መካከል ሴትየዋ ለአዲሱ ፍቅረኛዋ ከሰውየው ጋር የነበራትን ግንኙነትና ለምን እንዳቆመች ነግራው እንዲያባርረው ትጠይቀዋለች።

ወትሮም ፍቅረኛ እንዳላት እያወቀ በውሽምነት የገባው አዲስ ፍቅረኛ በአጭር ጊዜ የወደዳትን ሴት የግሉ ለማድረግ ፍቃድ ስለተሰጠው ሴት የላከው ሞት አይፈራም ብሎ በጀግንነት ከደጃፏ እንደሚያባርረው ዝቶ መጠባበቅ ጀመረ።

ሴትዮዋና አዲሱ ፍቅረኛዋ

ከአዲሱ ፍቅረኛዋ ጋር ልብ ለልብ መግባባት ላይ ደረሱ። አንድ ሆነው ለመኖር ቃል ተግባቡ። የህይወታቸው ሳንካ የሆነውን የቀድሞውን ሰው በምን መልኩ ከህይወታቸው ሊያስወጡት እንደሚችሉ ማሰብ ጀመሩ። እሱ የሰው ፍቅረኛ ላይ ተደርቦ የገባ ውሽማ መሆኑን ዘንግቶታል። ምንም እንኳን የቀድሞው ሰው ከትዳሩ በላይ ያስቀመጣት ውሽማ ብትሆንም የተጀመረ ግንኙነት ሳይቋረጥ ሌላ ህይወት ውስጥ በመግባቷ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊፈጠር እንደሚችል አስበው ተጨንቀዋል።

ምንም ይሁን ምን ግን ከፍቅራቸው የሚበልጥ ነገር አለመኖሩን ተረድተው ሰውየውን ከቤቷ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚቀርበትን አንድ ነገር ለማድረግ ተስማምተው ይጠባበቁ ጀመር። ባለትዳሩም ሰው ወጣቷን ውሽማውን ያፈቅር ስለነበር ግንኙነቱን ማቆም ቢያቅተውም የልጅቷን ፈቃደኝነት ለማግኘት በማሰብ ወደ ቤቷ መጣ። ቤት ሲመጣ ተዘጋጅተው የሚጠብቁት ፍቅረኛሞች ያቀዱትን ነገር ለማድረግ ተከታትለው ከቤት ወጡ።

የሁለቱ ውሽሞች መጨረሻ

ጫላ አስናቀ የተባለው የልጅቷ የቀድሞ ፍቅረኛ የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 4፡30 ሲሆን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አላንጉራ መንደር 3 እየተባለ በሚጠራው ሰፈር በሚገኘው የፍቅረኛው ቤት ሞቅ ብሎት ይደርሳል። ከትዳር አጋሩ ውጪ የፍቅር ጓደኛው የሆነችውን ሴት መኖሪያ ቤት ሳያንኳኳ በርግዶ ይገባል።

ሰአቱ መሽቶ ስለነበር ከዚህ በኋላ ማንም አይመጣም ብለው ተረጋግተው የተቀመጡት ፍቅረኛሞች የበሩ በኃይል መበርገድ አስደንግጧቸው ከመቀመጫቸው ብድግ አሉ። ከውጭ የሚሰማው ሰው ድምፅም የልጅቷ የቀድሞ ፍቅረኛ ጫላ መሆኑን ከተረዱ በኋላ ከበር ጀርባ የተቀመጠውን ዱላ ሳብ አድርገው በመያዝ ወደ ውጭ ተከታትለው ወጡ።

ከልጅቷ ኋላ ወንድ ተከትሎ መምጣቱን የተመለከተው ጫላ ከሞቅታው ጋር ተደምሮ ንዴቱን መቆጣጠር አቃተው። ልጅቷን ተከትሎ ከወጣው ወንድ ጋር የከፋ ፀብ ውስጥ ይገባሉ።

ሰውየው ቀድሞም ከቻለ በፀባይ ካልቻለም በማስገደድ ፍቅረኛውን ሊያሳምን ተዘጋጅቶ የመጣ ስለነበረ ፍቅረኛዋና ልጅቷ ያሰቡትን ሳይፈፅሙ ቀደማቸው። ሰውየው ከትዳር አጋሩ ውጪ የፍቅር ጓደኛው የነበረችውን እና እሷን ተከትሎ ከቤት በመውጣት በዱላ ሊመታኝ ብሎ ነበር ያለውን ግለሰብ በሕጋዊ መንገድ ይዞት በነበረው ሽጉጥ ተኩሶ ገደለው። ፍቅረኛሞቹ በዱላ አስፈራርተው ሊያባርሩት ቢያሰቡም እሱ ቀድሞ ሽጉጥ በመምዘዝ እስከወዲያኛው አለያያቸው።

የተኩስ ድምፅ እንደተሰማ በአካባቢው የተገኘው ፖሊስ አስክሬኑን በማንሳት ለምርመራ ከላከ በኋላ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይወስደዋል።

የፖሊስ ምርመራ

ተጠርጣሪው ግለሰብ በሕጋዊ መንገድ ይዞት በነበረው ሽጉጥ ተኩሶ በመግደሉ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ህጻናት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕ/አ 540 መሰረት በእያንዳንዱ የግል ተበዳዮች ሁለት ተደራራቢ ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ እንዲመሰረትበት መረጃውንና ማስረጃውን አጠናቅሮ ለአቃቤ ህግ ይልካል።

የአቃቤ ሕግ ክስ ዝርዝር

መረጃው የደረሰው በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕ/አ 540 መሰረት በእያንዳንዱ የግል ተበዳዮች ሁለት ተደራራቢ ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

የክስ ዝርዝሩ እንደሚያመለክተው ጫላ አሰፋ የተባለ ተከሳሽ የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 4፡30 ሲሆን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አላንጉራ መንደር 3 እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ከትዳር አጋሩ ውጪ የፍቅር ጓደኛው የሆነችውን የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት ሳያንኳኳ ከግል ተበዳይ ኋላ ወንድ የግል ተበዳይ ተከትሎ በመምጣት በዱላ ጭንቅላቴን ሊመታኝ ብሏል በሚል ምክንያት ከትዳር አጋሩ ውጪ የፍቅር ጓደኛው የነበረችውን እና እሷን ተከትሎ ከቤት በመውጣት በዱላ ሊመታኝ ብሎ ነበር ያለውን ግለሰብ በሕጋዊ መንገድ ይዞት በነበረው ሽጉጥ ተኩሶ በመግደሉ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶ መቅረቡን ያመለክታል።

በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕ/አ 540 መሰረት በእያንዳንዱ የግል ተበዳዮች ሁለት ተደራራቢ ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት የቀረበው ክስ ላይ ክርክር ሲደረግ ቆይቶ ለውሳኔ ቀነ ቀጠሮ ተሰጠ።

    ውሳኔ

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የተሰየመው ችሎት የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ የመከላከያ ምስክሮችን በማቅረብ ያሰማ ቢሆንም የቀረበበትን ክስ ሊከላከል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You